Print this page
Monday, 20 September 2021 16:41

አዲሱ ዓመት እና አሮጌው ሀሳባችን

Written by  ሰዓሊ በቀለ መኰንን
Rate this item
(1 Vote)

የአዲስ አመት ፅንሰ-ሐሳብ መቸም ለሁላችንም ለየቅል ነው። በፆታ ፣ በእድሜ፣ በሐብት፣ በአካባቢ ወግና ልማድ መጠን ይለያያል። በልጅነት እድሜ ምናልባትም ከአዲስ ጥብቆ ጋር የተቆራኘ ይሆናል። ትንሽ ከፍ ሲባል ደግሞ ከትምህርት ቤት ዳግመኛ መከፈት፣ ከመስክ ልምላሜና ካደይ አበባ ድምቀት፣ ከችቦ ብርሃንና ከሞቀ ጭፈራ ጋር ይታወሳል። በጉልምስና ወራት ግን የትውስታው ጉዞ ሁሉ ወደ ሁዋላ መሆኑ ቀርቶ ወደፊት ብቻ ይሆናል። ምናልባትም ሕይወት በዚያን እድሜ  ከኃላፊነት ሸክም ጋር ስለምትቆራኝ፣ ካለፈው  ትዝታ ይልቅ ከመጪው አውዳመት አከባበር ጋር በሐሳብ መወዛወዝ የሚጐላበት ዘመን መሆኑ አይቀርም።
ስለ አዲስ አመት በሚፃፉ  ሐተታዎች ውስጥ ከላይ ከጠቀስኳቸውም የዘለሉ አያሌ  ያውዳመት ልምዶች፣ ትዝብቶች፣ ጨዋታዎችና ቁምነገሮች ተነግረዋል። ተፅፈዋል። በዚህች አጭር መጣጥፍ ደግሞ የተሻለ የማውቀውን  የራሴንና የሰፈሬን የአዲስ አመት መንፈስ ላውራ። ሁሌም እንደ ብዙ ኢትዮጵያዊ ሁሉ ስለ ራስ ማውራቱ ለኔም የሚደላ ነገር አይደለም ነበር። አስፈላጊ በሆነ ጊዜ ግን ወደ ሁዋላ አለማለት የጀመርኩት አንድ የሰለሞን ዴሬሳን አስተያየት ካነበብኩ እለት ጀምሮ ነው። ሰለሞን በዚያ ቃለምልልሱ ሰውን ማዳመጥ እንዲያውም ስለ ራሱ ሲያወራ ነው። ምክንያቱም በደምብ ስለሚያውቀው ነገር ሲያወራ ነው ማዳመጥ። ስለራሱ ከርሱ በላይ ማን ሊያውቅ ይችላል? ይላል። በጉራ ብዛት እጅ እጅ ካላለ  በስተቀር በርግጥም አንዳንዴ ችግር የለውም፤ ታግሶ ማዳመጡ።
ወደ ሰፈራችን ልመለስ። አዲስ አመት እንደ ማናቸውም ሰፈር የኛም እንዲሁ ማለዳ የእንኳን አደረሳችሁ አበባ በየቤቱ እያዞሩ፣ ፀሐይ ሳትበረታ፣ ከጃቸው ጨርሰው ወደ ቤት ለመመለስ ወዲያና ወዲህ በሚራወጡ ሕፃናት ትሞላለች። ጥቂት ረፈድ ሲል ጓዳ ባፈራት ቅባትም ትሁን ዘይት ታብሳ ወደ ሁዋላ የፊጥኝ የተቀፈደደች ቁርንጫጭ ጠጉር ወይም እስክትብለጨለጭ በወዛች ሉጫ ሶስትዮሽ ተሾርበው ያማሩ  ትናንሽ ልጃገረዶች ሰባት ስምንት  ሆነው በየደጃፉ አበባየሆይ ሲሉ ይሰማሉ። እንደኔ ላብ ላብ የማይላቸው ደፋር ታዳጊዎች፤  ፀሐዩ ከርሮ  ልጃገረዶቹ ከመበታተናቸው በፊት  ተንጠራርተውም ቢሆን የሚስሙት የከንፈር ወዳጅ አያጡም። ቀድሞ ተነቅቶባቸው ጥፊ እየላሱ የሚመለሱም አይጠፉም። አበባው ታድሎ አበባየሆይም ተጨፍሮ፣ የተገኘውን ሳንቲም እየቆጣጠሩ የተለበሰችውን አዲስ ጨርቅ አስሬ እያጐነበሱ ማየት የተለመደ ነው። ያን እለት ሰፈሩ በሙሉ በፊሽካና በፊኛ ይጥለቀለቃል። ያኔ ባለቀለም ላባ አናቷ ላይ የታሰረ አጭር ቀሰም ጫፏ ላይ በታሰረላት ተርገብጋቢ ወረቀት አዝናኝ ድምፅ ስለምታወጣ ሁሉም ገዝቶ ሲያስለቅሳት ይውላል። የጥቂቶች ምርጫ የነበረው የእጅ ሰዓት  ለአላፊ አግዳሚው አይን ፈጥኖ ስለማይታይ በብዙ ልጆች ተመራጭ አልነበረም። የከሰዓት በሁዋላው የገበያ ዳር ጭፈራ ከመድረሱ በፊት ባዶ ሆድ እንዳይኮን ወደ ቤት ተመልሶ ከቤተሰብ ጋር ምሳ መብላት ግድ ነው። በዚህ መሐል  ጐረቤቱ ሁሉ  ባንድ ጊዜ ጠበል ጣዲቅ ቅመሱ ማለቱ ስለማይቀር ከምሳ በፊት እያንዳንዱ ቤት በመዞር ሆድ እንደ ከበሮ እስኪነረት የተገኘውን  ቀማምሶ፣ የተረፈውን በልብስ ቋጥሮ መመለስ ተለምዷል። በስልሳዎቹና በሰባዎቹ እንዲህ እንደ ዛሬው ሸቀጥ የተትረፈረፈበት ወቅት አልነበረም። ለብዙ ወላጅ ልብስ ከመግዛት ይልቅ ማሰፋት ወጪው የቀለለና ክብሩም የተሻለ ነበር።
ለዚህ ይመስለኛል  ከ“ልብስ እገዛልሐለሁ” ይልቅ “ልብስ አስቀድድልሐለሁ” ዝነኛ የዘመኑ ቃል የነበረችው። ከጫማም አይነቶች አሁን በፋኖዎች ሐብትነት  የምትታወቀው አንዳንዴ አሽሟጣጮች “ሰቭን ዶርስ” የሚሏት ባለመስኮትዋ ፕላስቲክ “ኮንጐ” ጫማ  ሲበዛ ተወዳጅ ነበረች። ሸራ ጫማ በገቢ መጠናቸው ሻል ባሉ ቤተሰቦች ዘንድ የምትመረጥ ወይም የጉልበት  ሥራ ሰርቶ መጠነኛ ሳንቲም ማግኘት በሚችሉ ጎረምሶች እግር የማትጠፋ ነበረች። በሙቀት የተነሳ ለክፉ ጠረን ስለምታጋልጥ ገንዘብ እንኳ ቢገኝ  በእንደኔ አይነቱ ሰነፍ ዘንድ ተመራጭ አልነበረችም። የኮንጎ ነገር ከተነሳ የባለ ብሯ የላስቲክ ኳስ ነገርም በቀላሉ የሚዘነጋ አይደለም። ባለ ብሯ የላስቲክ ኳስ “ሜድ ኢን ቼኮዝሎቫኪያ“ የሚል ፅሑፍ የታተመባት በዘመኑ ታዳጊዎች እንደ ብርቅ የተወደደች የእግር ኳስ መጫወቻችን ነበረች። የብር ኳስ አዲስ አመትን በመሰለ በተለይ በቅዱስ ዮሐንስ አይነቱ ገንዘብ የሚገኝበት አመት በዓል ሰሞን በመናጢዎች ሰፈር ሳይቀር በብዛት የምትሸመትበት ወቅት ነው። በግልም ተገዛች በቡድን ሹል ጫማና ጥፍር ከግሩ ላይ ያለው ሁሉ እንዲጫወትባት አይፈቀድም። ምናልባትም አንዳች ችግር አጋጥሟት በጨዋታ መሐል ተበስታ ስትተነፍስ ወዲያው በጋለ ሚስማር ቀዳዳዋን በመተኮስ ከተጨማሪ መተርተር ማዳን በየሰፈሩ የተለመደ፣ ሁሉ ታዳጊ የሚያውቀው ዘዴ ነው። የከሰአቱ የገበያ ዳር ጨዋታ ማንም ሳይጠራው በተሰበሰበ በሺህ የሚቆጠር ተመልካችና  ጨፋሪ መድመቅ ይጀምራል። ጭፈራው ዳንስ፣ እስክስታና ረገዳ ይበዛዋል። የጉራጊኛ ጭፈራ በየጣልቃው የማጣፈጫ ያህል አይታጣም። ለምን እንደሆን በማላውቀው ምክንያት የትግሪኛ ጨዋታ ላይን ሲይዝ በከተማው ውስጥ በታወቁ  ሁለት ሶስት ጥጎች ብቻ ተለይቶ እንደሚጨፈር አስታውሳለሁ። ከበሮው ከጀመረ በቀላሉ እንደሌሎቹ ጨዋታዎች ከምሽቱ ጋር በዋዛ የሚፋታ አልነበረም። አልፎ አልፎ ጥቂት ተቀባይ ከተገኘ በሌሎችም ቋንቋዎች የሚያስነካው አይጠፋም ነበር። እንዳሁኑ ቋንቋ ፖለቲካ ሳይሆን። የየሰፈሩ ሐርሞኒካ ነፊዎች የሸሚዞቻቸውን ኮሌታ ሽቅብ ገትረው  በቄንጥ እየተዘዋወሩ ደናሽ ደናሾችን በዜማ ያጅባሉ። ከተመልካቾች መሐል እየተፈናጠሩ የሚጨፍሩ ብዙ ሁለገብ ጨዋታ አድማቂዎችም ነበሩ። በስም የሚታወቁ።
ከማዶ ከገበያው ዙሪያ ጥግ ጥጉን ከወደ እህል በረንዳዎቹ በሩቅ የሚታዩ የባለረዣዥም ዱላ ኦሮምኛ  ጨፋሪዎች መሰባሰብ ይጀምራሉ። በዝንጀሮ ፀጉር በተለበጠ ኮፍያ በሐገር ባሕል ነጭ ልብስ አምሮ የጠገበ የሽመል ዱላ በሚያወዛውዝ ሸበላ  ጎልማሳ የሚመራ ሰልፍ “ሆ” እያለ እንደ ዘንዶ በጭፋሮ እየተምዘገዘገ ገበያውን እያጋመሰ፣ በተመልካች ፊት ማለፍ ይጀምራል። ሽቅብ ከእህል በረንዳዎቹ በላይ ትንሹ ኮረብታ ገበያውን በስተምስራቅ ጫፍ አቅፎታል። ከኮረብታዋ አናት ሲኞር ደበሌሪ ሰርቶታል የሚባለው የቅዱስ ሩፋኤል ቤተክርስቲያን፤ በደማቅ አረንጓዴ ዛፎቹ ታቅፎ፣ በአዲሱ የመስከረም ሰማይ ላይ አምሮ ተሰይሟል። የዛሬን አያድርገውና እነዚያ ዛፎች አሁን በቁማቸው የቀብር ቤት በመሻማት ላይ ባሉ ባለገንዘቦችና በአለም ጉዳይ በተጠመዱ ካሕናት ስምምነት የሸቀጥ ቡቲክ በመሰሉ ጉሮኖ ቤቶች ተተክተዋል። የኦሮምኛ ጨፋሪዎቹ ሰልፈኛቸውን እየመሩ ጥግጥጉን መዞር፣ እየጋለ በሚሄድ ዜማ ወደ ገበያው መዝለቅ ይጀምራሉ። እሱም የራሱ ስነ-ስርዓትና አጨፋፈር አለው። በየተወሰኑ አመታት የዚሕ ጭፈራ መሪዎች ይለዋወጡ ነበር። “አለ ከረሜላ መስቲካ“ እያሉ በአል አክባሪውን ሁሉ መስቲካ አላማጭ የሚያደርጉ ሱቅ በደረቴዎች፣ በየጨፋሪው እግር ስር እየተሽሎከሎኩ ይነግዳሉ። ሲመቻቸው ወይ ሲነሽጣቸው እቃቸውን አስይዘው አንዳፍታ ዳንሱንም ጭፈራውንም ያስነኩታል። ጭፈራ አንዳንዴ በብዙ ሰዎች ዘንድ እንደ ስለት የሚወጡት ግዴታም አይነት ነበር። የየመንደሩ አዶ ከበሬዎችም የየራሳቸው ተመልካችና የጭፈራ ስልቶች ነበሯቸው። የገበያ ዳር ጭፈራ ሲከለከል የአዶ ከበሬዎች ቁጥርም አብሮ እየተመናመነ ሔዶ ሁዋላ ከናካቴው ጠፍተዋል። እያደርም ከጭፈራው አልፎ ሙሾም ተከለክለና አረፈው።
ነውረኛ የሌሊት መማገጫዎች በሕጋዊነት ካመት አመት በሚነግዱበት አገር፣ያገር ባሕል፣ ያደባባይ ወግና ማዕረግ ባመት አንድ ቀን እንኳ መከልከሉ  እስከ ዛሬ ሳይገባኝ አለሁ። በዜማ መደሰትና እና በዜማ ማልቀስ በሚከለከልበት ምድር፣ ሰው ከሰውነቱ የሚቀረው ወግ ቢኖር ቀን እየሰራ ሌቱን ሲበላ ማደር ብቻ መሆኑ ነው። ሰው መሆን አዲዮስ!
ወደ ራሴ ልመለስ፣ እንግዲህ ይሄ በነበረበት ወቅት፣ በመጪው አዲስ አመት ምን ልታደርግ አቅደሀል በሚል ጥያቄም ሆነ  እንዲህ ላደርግ አቅጃለሁ በሚል መልስ  ሬዲዮም ቴሌቪዥንም ተመልካችና አድማጩን ሲነተርኩ መስማቴን እጠራጠራለሁ። ወይ የልጅነት እድሜ በመሆኑ ሳላስተውል ቀርቼ ይሆናል።
 በነገራችን ላይ እውነት እውነቱን ለመነጋገር በበኩሌ በራሴ ጀምሬ በራሴ ብቻ  የምጨርሰው  ከማንም የማያነካካኝ የግል ጉዳይ  ካልሆነ በስተቀር አልሜና ተመኝቼ እንደሆን እንጂ አቅጄ ያደረግሁት ነገር የለም። መቸም አንድን ነገር ለማግኘት ቢያንስ መፈለግ ወይም መመኘት ያስፈልጋል። ለማግኘት መጀመሪያ መፈለግ ግድ ነው። በርግጥ ያገኙት ነገር በሙሉ የፈለጉትና የተመኙት ነው ባይባልም። እናም በመመኘትና  በመፈለግ በኩል እኔም እንደ ብዙ ሰው ገደብ የለሽ ነው ሕልሜ። የሚሆነው ይሆናል የማይሆነው ይቀራል።  የተመኘሁትን የማገኘው በትጋትና በጥረት መሆኑን ለራሴ ስለማምን በፅናት እደክምለታለሁ። በርግጥም ብዙውን አግኝቼዋለሁ። ያጣሁት ጥቂቱንም ቢሆን  ዘግይቼም ቢሆን ለመጣር አልቦዝንም። የግድ ባጣሁት ግን ተቃጥዬ አላውቅም። ምናልባትም ተመኝቼው እንጂ አቅጄው ስለማላውቅ ይሆን እላለሁ። ለኔ ማቀድ በውስጡ አስገዳጅ ድምፀት ያለበት ሆኖ ይታየኛል። ሳይሆን በቀረ ጊዜ ቁጭትና መቃጠል፣ የሚቆጠር ኪሳራም ያለበት መስሎ ይታሰበኛል። ይሔ አጠቃላይ መንፈሱ ነው ለኔ። በሌላ ቋንቋ  እንደኔ ግምት እቅድ ከአቃጁ በተጨማሪ ለስኬቱ የሌሎችንም በጎ ፈቃድና ቅንጅትን የሚጠይቅ በጋራ ልፋት ላይ የተመሰረተ ክንዋኔ ነው። ሁሉም በጋራ በብቃት ከልብ ካልተሳተፈ በግማሽ አንካሳ ቡድን ማቀድና  ለመፈፀም መባዘን፣ ለኔ ቀድሞ የለየለት ኪሳራ ይመስለኛል። በሌላ በኩል ግን ያንድ ሰው የማሰብና የመፈፀም ጉዳይ ሲሆን “one man mission" የሚሉት አይነት ማቀድ የተሻለ የሚያዋጣ ይመውስኛል። ቢያንስ እዚህ አገር ማለቴ ነው። ለምሳሌ ሲጃራ ጠጪ ሰው ሲጃራ አይረባኝም በአዲሱ አመት ላቆም አስቤያለሁ” ቢል ሐሳቡም አፈፃፀሙም ጥቅሙም ያንድ ሰው ጉዳይና ያንድ ሰው  ተልዕኮ በመሆኑ፣ አቅጃለሁ  ብሎ ቢጠራው ተስማሚ የድርጊቱ ወካይ ቃል ሊሆን ይችላል። ችግሬ ከቃሉ ሳይሆን ቃሉ ሊመነዝር ከተፈጠረለት ፅንሰ-ሐሳብ ጋር ነው። ባንድ ሰው ታስቦ በሌሎች ተሳትፎ ሊሳካ ይችላል ተብሎ በሚታሰብ ጉዳይ  ላይ ግን አቅም የሌለው የኔ ብጤ ዝም ብሎ ቢያልም ወይ ቢመኝ ያዋጣዋል። ታክሲና አምቡላንስ  በታሰበ ሰዓት በማይደርስበት፣ ኮረንቲ ባልተጠበቀ ተደጋጋሚ  ቅፅበት በሚቋረጥበት፣ የቋመጥክለትን ዕቃ ለመግዛት ገንዘብ አግኝተህ ተንደርድረህ ስትደርስ ቆጠራ ላይ ነን በምትባልበት፣ መሰረታዊ ጥቅሞች ሁሉ በሻሞ እድል ላይ በወደቁበት አገርና ዘመን ባንድ ሰው ቢታቀድ እንኳ ባንድ ሰው የማያልቅ ሐሳብ ሲመጣ፣ ከማቀድ ይልቅ አልሞ መልፋት ለኔ አደጋ -አልባ፣  ፀፀት-አልባ ፣ ጉራ-አልባ ትሁት ዘዴ ሆኖ አግኝቼዋለሁ። ሆኖም ምንም ቢሆን ማቀድ ይሻለኛል ለሚሉ ምናልባት አንድ ከበላይ ልንማረው የምንችለው መንሸራተቻ አለ። “ከእቅዴ ይሔን ያህሉን አሳክቼ ይሔን ያህል ረክሶብኛል“ የምትል። ለሁሉም ግን “የሚጥመውን ባለቤቱ ያውቃል” አለ በግ ነጋዴው! መልካም አዲስ አመት!!
ከአዘጋጁ፡- የዛሬ ስድስት ዓመት አዲስ ዓመትን አስመልክቶ ያወጣነውን ጽሁፍ ከአዲስ አድማስ ድረገጽ ላይ በድጋሚ አትመነዋል፤ 11 ሰፕቴምበር 2015
 አድማስ ትውስታ

Read 967 times