Monday, 20 September 2021 17:04

የደራሲ ቤት፤ ገነት ቅብ ሲኦል ነው!

Written by  ዓለማየሁ ገላጋይ
Rate this item
(4 votes)

ጆርጅ በርናርድ ሾ ቤት የሄደ አንድ ወዳጅ ተዘዋውሮ ቢመለከት አይኑን ቀለለው አሉ፤ ልብ ብሎ ሲያጤን ለካ በዘመኑ እንደ ዋነኛ ቤት ማሳመሪያ ይወሰድ የነበረው የአበባ ዝንጣፊ ሾ ክፍል ውስጥ አልነበረም፡፡ ስለዚህ አንድ ጥያቄ ጣል አደረገ፤ “ሚስትር ሾ፤ አበባ የምትወድ ይመስለኝ ነበር”
ሾ መለሰ፤ “ልጆችም እወዳለሁ፤ ነገር ግን ስለወደድኳቸው አንገታቸውን ቆርጬ አላስቀምጥም” ኦ! መውደድ በስምሽ ስንት ግፍ ተሰራ ማለት ይሄኔ ነው፡፡ የሚወዱትን ነገር ህይወት አሳጥቶ ማጌጥ “በአበባ ይብቃ” አላልንምና በሌሎችም ነገሮች ቀጥሎ ይስተዋላል፡፡ ወፍ እንወዳለን፤ የኛ ለማድረግ በፍርግርግ እናስራለን፣ ቢራቢሮ እንወዳለን ሰብስበን እናደርቃለን፣ ሴት እንወዳለን አንቀን እንገድላለን …
… ከዚህ ጋር ተነፃፃሪው የዘመኑ “መውደድ” ደግሞ በመፃህፍት ላይ ተከናውኖ አጋጥሞኛል። የተወደዱ የአማርኛ መፅሐፍት በሚል መነሻ የተለያዩ ሥራዎችን የኮምፒዩተር ውልድ በማድረግ መቀባበልና በ“ዌብሳይት” መልቀቅ ምን ይሉት “መውደድ” ይሆን? የዚህ ሰለባ ከሆኑ ስራዎች ውስጥ ጥቂቶቹን አይቻለሁ። የፀጋዬ ገብረመድህን “እሣት ወይ አበባ”፣ የስብሃት ገብረእግዚአብሔር “አምስት ስድስት ሰባት”፣ የደበበ ሰይፉ “የብርሃን ፍቅር”፣ የከበደ ሚካኤል “የትንቢት ቀጠሮ”፣ የብርሃኑ ዘሪሁን “የታንጉት ሚስጢር”፣ የዳኛቸው ወርቁ “አደፍርስ”፣ የበውቀቱ ስዩም “በራሪ ቅጠሎች” …
… ካየኋቸው ባሻገር ከሰው የሰማኋቸው ደግሞ እጅግ ብዙ ናቸው፡፡ ይሄ ዘመን አመጣሽ ወረርሽኝ ከህግ በላይ በመንሰራፋቱ ከሕሊና ውጭ የሚዳኘው እንደሌለ ግልፅ ነው፡፡ ድርጊቱ ከሕሊና በላይ የሚሆነው እራሱ ሕሊና ሳይኖር ሲቀር ብቻ ይመስለኛል፡፡ “ሙጥኝ” የሚባለው የሰው ልጅ አስተውሎት ከሌለ ደራሲውን እንደ አበባ ዘንጥፎ የጥቂት ቀን መድመቂያ ከማድረግ በማይተናነሰው “መውደድ” መቀጠል ይቻላል፡፡
ባለፈው ሳምንት አንድ ወዳጄ ደውሎ የእኔም መፅሐፍ የኮምፒዩተር ውልድ ተደርጎ ዌብሳይት ላይ መለቀቁን ነገረኝ፡፡
 “የቱ መፅሐፍ?” ስል ጠየኩት
 “አጥቢያ” አለኝ
ግራ ተጋሁ፤ “አጥቢያ” ሦስት ሺህ  ኮፒ የታተመው ከስምንት ዓመታት በፊት ነበር። ተሸጦ ያለቀው በሰባት አመታት “ምጥ በመሆኑ ለዚህ መፅሐፍ መጥፎ ትዝታ አለኝ፤ አሳታሚው ሱቅ ውስጥ ተደርድሮ ስመለከተው እንደ ደም ማነስ ያለ ተስፋ መቁረጥ ዥው አድርጎ ይወስደኝ ነበር፡፡ የህትመቱ ወጪ የተሸፈነው በአሳታሚውና በአንድ ጓደኛዬ መዋጮ ሲሆን መፅሐፉ በሰባተኛ ዓመቱ ሲያልቅ ያተረፍኩት ትልቅ እፎይታ ብቻ ነበር፡፡ አሁን ከአራት ወር በፊት ደግሞ ለሁለተኛ ዕትም የሚያነሳሱ መረጃዎች በመብዛታቸው ከአንድ አሳታሚ ጋር ተዋውዬ ሦስት ሺህ ቅጂ ታተመ። “ውረድ እንውረድ” ያሉት የ“አጥቢያ” ጠያቂዎች፤ “አፋፍ ቆመው ስላስደበሰቡ” የታተመው እንዳለ ተቀምጧል የሚል መረጃ ሰሞኑን ደርሶኛል፡፡ ለሁለተኛው ዕትም ሁለተኛ ዙር ተስፋ መቁረጥ እየዳዳኝ ሳለ ነው በዌብ ሳይት መለቀቁን የሰማሁት። የሚገርመው ደግሞ ኮፒ ያደረጉት ሁለተኛውን እትም ከእነ ሽፋኑ ነው፡፡ ለምን? ዋጋው በዛ? ከገበያ ጠፋ? ያን ያህል ተፈለገ? …. ይሄ ሁሉ ምክንያት አይሆንም መንስኤው፡፡ ያው አበባን ወድዶ በመዘንጠፍ የመርካት አባዜ የተጠናወተው ይመስላል፡፡
ጥሩ ደራሲ ሆኖ ግሩም መፅሐፍ ፅፎ የመክበር ባህልም ሎተሪ ቆርጦ ዕድለኛ ከመሆን ጋር ተነፃፃሪ ነው፡፡ መክበር ቀርቶ መኖር አይቻልም፡፡ ይሄንን በሌሎቹ ደራሲዎች ህይወት ሳይሆን ከእኔ ኑሮ አረጋግጫለሁ፡፡ እንዲህ ይከፋል ብዬ ባልጠብቅም ከመጀመሪያው ደራሲነት መሻቴ ጋር ድሎትን አዳብዬ አላሰብኩም። አዘቅቱ ግን እገምተው ከነበረው በታች፣ ጨርሶ የማይታይ እሩቅ ነው። ለተረት የቀረቡ የህይወት ቅንጣቶች የበዙበት ዝንጉርጉር። ይሄም ሆኖ፤ ያንን ሁሉ መከራ ለማካካስ የማይገድደው የሰው መውደድ አለበት፡፡ ያለ መዋሸት የደራሲ ቤት ገነት ቅብ ሲኦል መሆኑ እሙን ነው። በእጥረት የተወጠረ የመከራ ዳስ ሆኖ ሳለ ሌሎች ነፍሶች እንዲጠለሉት ግድ ያለ ግዜ፣ ያኔ መከራው ይከፋል፡፡ ሚስትና ልጆች ካሉ ማለቴ ነው። ለዚህ ማሳያ የበአሉ ግርማን “ደራሲው” የተሰኘ ልቦለድ ማንበብ በቂ ነው፡፡ ደራሲው ሲራክ በመፃህፍቶቹ የገባውን ኪሳራ ሚስቱና ልጁ ሲገፈግፉ በጉልህ ይታያል። በእጥረት የመወጠሩ ችግር በኑሮ ጉድለት ብቻ የሚተረጎም አይደለም፡፡ የፍቅርና የእንክብካቤ ማጣት የተጠናወተውም ነው። ለዚህ ደግሞ የበአሉ ግርማን ልቦለድ ሳይሆን ህይወቱን እንጥቀስ፡፡ የ“ከአድማስ ባሻገር”ን መታሰቢያነት ለባለቤቱና ለልጆቹ ሰጥቷል፡፡
የመታሰቢያነቱን ምክንያት ደግሞ ምስጋናው ላይ እንዲህ ሲል ገልፆታል፡-
“ለውጥና ሽርሽር እያማራቸው ቤት ውስጥ ከወር ወር ተዘግተው በመክረም ፍላጎታቸውን መስዋዕት ላደረጉት ለባለቤቴ ለአልማዝ፣ ለልጆቼ ለመስከረምና ለዘለአለም ምስጋና ይገባቸዋል፡፡ እነዚህ ነፍሶች መስዋዕት ያደረጉት ፍላጎታቸውን ብቻ ሳይሆን ባለቤት ባሏን፣ ልጆች አባታቸውን ጭምር ነው፡፡ ደራሲው ዓመቱን ሙሉ ከድርሰት ጋር ነውና ቤት ውስጥ ቢሆንም ከእነርሱ ጋር እንዳይደለ እሙን ነው፡፡ እናስ? ባልንና አባትን ያህል እጥረት እንኳንስ በጎዳደለ ኑሮ፣ ድሎት በበዛበት ህይወት ይካካሳል?
እንግዲህ መፅሐፍትን የኮምፒዩተር ውልድ አድርጎ ያለ ዋጋ ማስቀረት ከህግም በላይ የህሊና ጥያቄ የሚኖርበት እዚህ ላይ ነው። ሰው ስንቴ ይቀጣ? በኑሮ እጥረት፣ በባል ፍቅር እጦት፣ በአባት እንክብካቤ ጉድለት … ከዚህ ሁሉ በኋላ ደግሞ በውርስ መፃህፍት መና መቅረት፤ ከዚህ ውስጥ እጅን ማስገባት ንፁሃንን ሰለባ የማድረግ ግፍ አለበት፡፡
እደግመዋለሁ!!
… ይሄ ዘመን አመጣሽ ወረርሽኝ ከህግ በላይ የተንሰራፋ ነውና ከህሊና ውጭ የሚዳኘው እንደሌለ እሙን ነው፡፡ ድርጊቱ ከሕሊና በላይ የሚሆነው እራሱ ሕሊና ሳይኖር ሲቀር ብቻ ይመስለኛል። “ሙጥኝ” የሚባለው የሰው ልጅ አስተውሎት ከሌለ፣ ደራሲውን ቤተሰቡን እንደ አበባ ዘንጥፎ የጥቂት ቀን መድመቂያ ከማድረግ በማይተናነሰው “መውደድ” መቀጠል ይቻላል፡፡
ከአዘጋጁ፡- ከላይ የቀረበው ጽሁፍ ከጥቂት ዓመታት በፊት ለንባብ የበቃ ቢሆንም፣ አሁንም እውነታው አልተቀየረምና ለትውስታ አምድ በድጋሚ መርጠነዋል፡፡

Read 837 times