Monday, 20 September 2021 17:02

አኮቴት

Written by  አብዲ መሐመድ
Rate this item
(1 Vote)

  ይድረስ ለ“ፖለቲካ በፈገግታ” አምደኛ
                     
               ገና ያኔ! ጊዜውን በውል አላስታውሰውም። ብቻ የዜጎች እልቂትና ሰቆቃ በየጋዜጣው እንደ-ጉድ ይዘገባል፡፡ በተለይ አብዛኞቹ የፖለቲካ ጋዜጦች አብይ ርእሰ-ጉዳይ አድርገው ዜናውን ማስጮህ፣ ትኩሳቱን ማጋጋል፤ የዘወትር ዋነኛ ተግባሮቻቸው ነበር፡፡ ይሄ በራሱ ታድያ… ከሰሀራ በታች በችግር ለምንጠበስ “ደሃ ህዝቦች” ምናችን ነው? ገጣሚ ታገል ሰይፉ በአንድ ቃለ-ምልልሱ እንዲህ ብሎ ነበር፡… የሃገራችን ምስኪን ህዝብ ስለ ሞት ስታነሳበት አይወድም፣ ሲበዛ ይፈራል … ጠጋ-ብለህ ህይወቱን ብትሾፈው ግን ኑሮው ከሞት የከፋ ነው፡፡ አዎ ታገል አልሣተም… ከዚህ የኑሮ ዚቅ ውስጥ አውጥቶ፤ ከደረቅ የፖለቲካ ዘገባ፣ በሀዘንና ሙሾ የተለወሰ ትንታኔ ይልቅ እኛ የሚያስፈልገን ችግራችንን የሚያለዝብልን፣ ከእንባ ይልቅ ፈገግታን የሚቸረን፣ ከፖለቲካዊ አዙሪታም ኑረታችን ውስጥ ሳቅን ፈልቅቆ እየጠቀለለ ለኛው መልሶ የሚያጎርሰን ፀሃፊ! አዎ አንድ ፀሀፊ ያስፈልገን ነበር፡፡ ከማስፈለግም በላይ ይናፍቀን ነበር፡፡ በእርግጥ የኛ መለያና ምልክት ሀዘን ብቻ ሆኖ እኮ አይደለም፡፡ ነገር ግን ጋዜጣ በገለጥን ቁጥር ይሄን ውስጣችን ያለን የሳቅ ተፈጥሮ የሚቆሰቁስ ፀሀፊ  አጥተን ከተቸገርን ባያሌው ባጀን፡፡ ፖለቲካ ሸፍኖት እንጂ የኑሮ ምሬትና የህይወት የረጋ ሀዘናችን ሲፋቅ ብቅ የሚለው ከንጹህ ጥርሳችን የሚቀዳው ያልቆሸሸ ሳቃችን ነበር፡፡ ከያኒው ድምፃዊ ንዋይ ደበበ አንድ ዘፈኑ ውስጥ የገለጻት እንስት የኛው ተምሳሌት ሣትሆን ትቀራለች… ጥርሶችሽ ደስታን ሲረጩ… ፍቅርን እየቀዱ ከምንጩ.. ሲል! ይሁንና ባጅተንም ሆነ ባዝነን ፣ ናፍቀን አልቀረንም። እግዜሩ የፖለቲካውን ትኩሳት በፈገግታ ጸዳል የሚተካልን ከዚሁ ጋዜጣ አስነሳልን። “ፖለቲካ በፈገግታ” በሚል ንዑስ ርእስ፣ ኤልያስ በሚል ስም በየሳምንቱ ፖለቲካን በጥበብ ለውሶ በሳቅ አሽሞንሙኖ ብቅ የሚል ዘጋቢ ተከሰተ፡፡
“ፖለቲካ በፈገግታ”
ነፍሱን ይማረውና ጋሽ ስብሀት ለአብ … “እንደ ማህበረሰብ እኮ ሀብታም የለም” ይል  ነበር፡፡ ሀሳቡን ዘርዘር አድርጎ ሲያብራራ… ከእያንዳንዱ ትንሽ ከምንለው ማህበረሰብ ውስጥ ቢያንስ አንድ ታላቅ “ሳይንቲስት”፣ አንድ ታላቅ “ደራሲ” ፣አንድ “ኮሜዲያን”፣ አንድ “ድምጻዊ” ሌላም-ሌላም ይወለዳል፡፡ አለማችንን የለወጡ ታላላቅ ሰዎች የተገኙት ከትንንሽ መንደሮች ነው የሚባለው ለዚህ ነው ይለናል፡፡ እኔም “አዲስ አድማስ” የተባለ የጋዜጣ ማህበረሰብ ውስጥ!… በፖለቲካ የሚኮምክ፣ በፈገግታ ጅምናስቲክ የሚያሰራ፣ የሳቅ ጀብደኛ ተደንቄ ጽሁፎቹን መኮምኮም የጀመርኩት ገና በአፍላነት በተማሪነቴ ጊዜ ነበር፡፡ በዚያን ወቅት ክፍለ-ሀገር ላይ ምንም በሚባል ደረጃ የቴክኖሎጂ አማራጭ ስለሌለ “ጋዜጣና መጽሄቶች” ሙሉ ለሙሉ ባይባልም በስፋት የመነበብ እድል ነበራቸው፡፡ (ከኢትዮጵያ ሬዲዮ ውጪ/እርሱም በረጅም አንቴና) ምንም አይነት የኤፍኤም ጣቢያዎች አይስቡም፣ ቪድዮ-ጌም ወይም ፕሌይ-ስቴሽን የለንም፣ ማህበራዊ ሚዲያ ገና አልተዳረሰም) ዘወትር ቅዳሜ ማለዳ ከወጣቶች ጋር ተንጋግተን  ለንባብ መሰለፍ የሰርክ ተግባራችን ነበር፡፡ በተለይ የአድማስ ”ጥበብ አምድ” በቂ ሽፋን ካልተሰጠው፤ ፖለቲካዊ ጉዳዮች ጠቅላላ አምዱን ሲያጥለቀልቁት እንጨነቃለን፣ እንደበራለን፡፡ የኛ ፀሀይ ሳትወጣ መጥለቋ እውን ይሆናል፡፡ በዚህ ጊዜ ነው ፖለቲካ በፈገግታን ፍለጋ የምንኳትነው፤ በአይናችን   የምናስሰው፡፡ እንዳሳደገን ድፎ በማሻመድ የንባብ ጥማችንን የምንቆርጠው፡፡ ሣይበሉት የሚያጠግብ ፈገግታዊ ምግብ! እንዳለው የሃገሬ አዝማሪ፡ የኛም የንባብ ከርስ ገና ሳንበላው የምንጠግበው በኤልያስ ፖለቲካ በፈገግታ ነበር፡፡
በኔ ትውስታና ንባብ በወቅቱ ጋዜጣዋ ላይ ከ“ትራጄዲ” ባሻገር “ኮሜዲ” ላይ ተንተርሰው ከኤልያስ በአቻነት የራሳቸው አምድ የነበራቸው ጸሃፍት በአድማስ ታሪክ ውስጥ ተከስተው አልፈዋል፡፡ ቢንያም ጀቤሳ “ወጋ ወጋ በፈገግታ፣ ተስፋዬ አለነ (የ”መንጌ ውሽሚት”እና እንክልካይ መጽሃፍ አዘጋጅ) ለናሙናነት መጥቀስ በቂ ነው፡፡ ይሁንና ለኤልያስ  በዚህ ልክ መሳባችን ለዚያውም ፖለቲካን ተገን አድርጎ ለሚያጫውት ልባችንን ከፍተን መመሰጣችን ሁሌም ጥያቄ ይሆንብናል፡፡ ለዚህ ሳይሆን ይቀራል እንስቷ ገጣሚ ትእግስት ማሞ… “ፍቅር እኮ ምክንያት የለውም” የምትለው! በርግጥ በኛም ቢሆን አይፈረድብንም! የጦቢያን ተጨባጭም ሆነ ነባራዊ ፖለቲካን መረዳት እንፈልጋለን፣ ነገር ግን ይከርብናል፣ ይጦዝብናል፡፡ ጡዘቱ በጨዋታና በጥበብ መለወስ ነበረበት፣ መለዘብ ነበረበት፡፡ ወጣቶች ስንባል ነፍሳችን ለሳቅ፣ ለቧልት፣ ለፌዝ ሲበዛ ቅርብ ናት፡፡ በሳቅና ጨዋታ እየተዋዛ ለሚነገረን ቁም-ነገር ልባችን ክፍት ነው፤ የመቀበል አቅማችንም ቢሆን የዚያኑ ያህል የሰፋ ነው፡፡ እንደ-ወገዝ በሬ በአሞሌ እያላወሰ ፖለቲካን የሚያላምድ ሲገኝ (እንደ ኤልያስ) እኛም እንደ ያ ትውልድ እንኳን ለመረዳት ለክፉ አላማውም ቢሆን ከመማገድ ወደ  ኋላ የማንል ነበርን፤ ወጣት የነብር ጣት! መሆናችን ቀረ፡፡ እርግጥ ነው ይሄ ትውልድ፣ ከ ያ ትውልድ ጋር ከፖለቲካዊ-ጀብድ አንጻር ሲታይ እንኳን ሊነጻጸር አብሮ ሊስተካከል የሚችል ቁመና አለው ብዬ አላምንም፡፡ እነርሱ እኮ ለውጥ ፈላጊ ትውልዶች ብቻ አይደሉም፡፡ ግርማ ሞገስ የታደሉ፣ ሃሳባቸው የማይነጥፍ፣ ከጊዜው የቀደሙ አብዮተኞች፣ በየድርጅቶቻቸው በማደራጀት በመታገል ውድ ጊዜያቸውን፣ ምትክ የሌለው ህይወታቸውን የሰዉ፤ እድሜያቸው ገና አርባ እንኳን ያልሞላ .. (አንዳርጋቸው ጽጌ “በትውልድ አይደናገር” እንደ ተረከልን ተስፋየ ደበሳይና መሰሎቹ አይነት ወኔ፣ መላኩ ተገኝ በ”ሰንጋ ተራ” ውስጥ እንዳሳየን ዘሩ ክህሽን እና መሰል ተራማጅ አንባቢ ጂንየስ ወጣቶች፣ ህይወት ተፈራ  በ”ማማ በሰማይ” ድርሳኗ እንዳስቃኘችን ፍቅረኛዋ ጌታቸው ማሩና የጓዶቹ የሞራልና የእምነት ትጋትና ወኔ፣ ታደለች ኀ/ሚካኤል በ”ዳኛው ማነው?” ወስጥ እንደሳለችው ባለቤቷ ብርሃነ መስቀል ረዳና የሌሎችም ብሄራዊ (አውሮፕላን ጠለፋ ድረስ) ሃገራዊ ገድል መሰል ዜና-መዋእላቸው ውስጥ እንዳወቅናቸውና እንዳሳወቁን አይነት “እኛ የዛሬዎቹ” አይደለንም፡፡ ግፋ ቢል መንግስትን አሽሟጦና ተርቦ እንጂ መጽሃፍትን አንግቦ መንግስትን በጥያቄ አፋጦ ጎዳናውን በመፈክር ማጥለቅለቅ ለኛ ሱሚ ነው፡፡ ለዚህም ይመስላል በትውልዳችን ተስፋ የቆረጡት አዱኛ ሂርጳ የተባሉ ጸሃፊ፣ ወጣቱ እንዲሆንላቸው የሚመኙትን በ“የለምን አሻራ” በተሰኘ መጽሃፋቸው ውስጥ አስፍረው ነበር፡፡ …ዛሬ ላይ ሃገራችን ለምን እንዲህ ይሆናል፤ ለምን እንዲያ አይሆንም የሚል ጠያቂ ወጣት ትውልድ ትፈልጋለች፡፡ ያለንበት የኢኮኖሚ የማህበራዊና  ፖለቲካዊ ቀውስ በቅን ልቦና በመነጋገር፣ በመተባበር የማይፈቱ አይደለም፡፡ ችግሩ ለምን ባይ ጠፍቶ ጊዜውን ጠብቆ የሚፈነዳ ቦንብ በእጃችን ይዘን መምሸቱ እና መንጋቱ ነው፡፡ ካሁን በኋላ ግን አያለሁ፤ ምኞቴም ነው ይህ ሲቀየር አያለሁ፤ ለምን ባይ ሰራዊት ሲነሳ አያለሁ፤ በእኔ ዘመን ይቺ ሃገር ይለፍላት የሚሉ እራሳቸውን የካዱ ወጣቶች ከራሳቸው ጥቅም ይልቅ የሃገር ጥቅም የሚያስቀድሙ ትውልዶች ለሃገር እድገት ሲንቀሳቀሱ አያለሁ፤ ስኬት ለብቻ መበልጸግ እንዳልሆነ የገባቸው ወጣቶች የወደቀውን ሲያነሱ፣ የተራበውን ሲያበሉ፣ የታረዘውን ሲያለብሱ አያለሁ! (ገጽ 284)
ሃገር  በተደጋጋሚ ትታመማለች። የህመምዋ መንስኤ ደግሞ ድንገተኛ መድሃኒት የሚሻ የመፍትሄ ሃሳብ ነው። በዚህ ጊዜ ለተያዘችበት ለአጣዳፊ ችግሯ የሚሆኑ አማራጭ እንክብሎችን በፕሮፖዛል ተረቅቆ በኤልያስ ይሰጣታል፡፡ በዚህም እፎይታን ታገኛለች፡፡ አምደኛው ለአመታት ለሃገርና ህዝብ ይበጃሉ እያለ የሚያዘጋጃቸው ፕሮፖዛሎች ግፋ-ቢል ጥቂቶቹ እንኳን ያኔ ቢሰራባቸውና ቢተገበሩ ዛሬ የተጋረጡብንን አያሌ ማጦችን ሊቀርፉና ሊለውጡ የሚችሉ፣ መፍትሄም የሚያመጡ እንደነበሩ እኔ ህያው ምስክር ነኝ፡፡ ብቅት ያለ ፕሮፖዛል፣ በጥልቅ ጥናት የተደገፈ፣ ወጪ የማይጠይቅ ንፁህ  ሃሳብ “እንካችሁ ተጠቀሙበት” ሲለን ኖሯል፡፡ በዚህም እናመሰግነዋለን፡፡  
የአምደኛው ሌላው ትሩፋቶች
ገንዘብ የሀጥያት ስር ነው እያለ ከሚተርት ማህበረሰብ ነው የተገኘሁት። ሃብታም መሆን በሚያሸማቅቅበት፣ መበልጸግ በሚያስኮንንበት፤ ብዙ ህዝቦቿ ሀይማኖተኛ በሆነባት ሃገር ድህነት ከፍ ከፍ ተደርጎ መታየቱ የሚጠበቅ  ነው። በርግጥ ይህ ሀይማኖት ተኮር ኋላ ቀር አስተሳሰብ በሉላዊነት ወይም በዲጂታል ግሎባላይዜሽን ዘመን እየወደቀ የመጣበት ዘመን ላይ ደርሰናል፡፡ ዞሮ ዞሮ የሰው ልጅ በአእምሮም ሆነ በመንፈሳዊ ህይወቱ የሚዳብረው ቁሳዊ ነገሮችን በመጠቀም ላይ ተንተርሶ እንደሆነ እሙን ነው፡፡ ቁሳዊ ነገሮች ከሰማይ እንደማይዘንብልን ኤልያስ ቀድሞ ተረድቶታል፡፡ ለዚህም ነው ቁሳዊ ነገሮችን የምትገዙበት ገንዘብ ያስፈልጋችኋል የሚለን፤ ለዚህም ነው በሳይንሳዊ መንገድ መበልጸግ አለባችሁ የሚለን፡፡ በዚህ መርህ መነሻነት በስኬት፣ በሀብት መበልጸግ ላይ ትኩረታቸውን ያደረጉ መጽሃፍቶችን እንካችሁ ብሎናል፡፡ እኔም በኋለኛው ዘመኔ! በእድሜም፣ በህይወት ልምድም፣ በንባብም ከጎለመስኩ በኋላ በአፍላነት የፖለቲካውን አለም በጨዋታ ያለማመደኝ ፀሀፊ እነሆ አድጌ ደግሞ የተረጎማቸውን መጽሃፍት ለማጣጣም በቃሁ፡፡ ታላላቅ ህልሞች፣ የርሆንዳ ባይርኔ ተአምራዊ ሚስጥር፣ የብልጽግና ሳይንሳዊ ሚስጥሮች …. ሌላም-ሌላም፡፡
በዚህ-ዘውግ የሚተረጎሙልን መጽሀፍት በገንዘብ ለመበልጸግ የሚያነሳሱ፣ መዋለ-ንዋይ የማግኛ የቤት ስራችንን የሚያቀሉ ብቻ ሳይሆኑ ሀገራችን ላለችበት ድህነትና ባህላዊ ኢኮኖሚያዊ አመለካከት ነጻ ለማውጣት የሚጫወቱት ሚና በቀላል የሚገመት አይደለም፡፡ ከዚህም በላቀ ሁኔታ ያነቁናል፣ ያነቃቁናል፡፡ ዋላስ ዲ ዋትልስ  የተባሉ የስነ-ስኬት ሊቅ! ….ድሆች የሚፈልጉት ችሮታ ወይም እርዳታ ሳይሆን መነቃቃት ነው ይላሉ፡፡ …ዋላስ አያይዘው ...ከችሮታ የሚያገኙት ነገር ቢኖር መከራቸውን የሚያስረዝምላቸው ቁራሽ-ዳቦ ብቻ ነው፡፡ ለአንድ ወይም ለሁለት ሰአት መከራቸውን የሚያስረሳ ነገር ሊያገኙ ይችሉ ይሆናል፡፡ የችሮታ ፋይዳው ይሄ ብቻ ነው፡፡ በውስጣቸው መነቃቃት ከተፈጠረ ግን ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ ከመከራቸው ፈንቅሎ የሚያወጣቸው መግነጢሳዊ-ሀይል ይቀዳጃሉ… ሲሉ ጽፈዋል፡፡ ስለዚህ ኤልያስ በተዋበና ጥንቅቅ ባለ አማርኛው በመተርጎም መበልጸግ የምንችልበትን መንገድ አመላክቶናል፡፡ ከድህነት መውጫ አቅጣጫውን ጠቁሞናል፡፡ በዚህም እናመሰግነዋለን፡፡
ማረፍያ
ፍጹም ጥበበ የተባለ ተዋናይና የፊልም ባለ-ሙያ! በአንድ-ወቅት ፋና ላይ ዘወትር  ቅዳሜ የሚያቀርበው “ቅን-ልቦች” የተሰኘ ፕሮግራም ነበረው፡፡ ዝግጅቱ ዛሬ ላይ ይኑር-አይኑር አላውቅም፡፡ አላማው ግን እንዲህ ነበር፡፡ በአንድ በማይወጡት የህይወት ዚቅ ውስጥ ተዘፍቀው በነበሩበት ወቅት ድንገት ደርሰው ህይወትን የሚቀይር መልካም ነገር የዋሉላቸውን፤ ነገር ግን የማያውቋቸውን ሰዎች ካሉበት በማፈላለግ በስልክ በመደወል ማወደስና ማመስገን ነው፡፡ አልዋሽም ከአንድም ሁለት ሶስቴ እነዚህ በጎ-ሰዎች ሲመሰገኑ እያዳመጥኩ በመልካምነታቸው ሳላውቀው እራሴን መቆጣጠር ተስኖኝ እንባዬ አምልጦኝ አልቅሻለሁ፡፡ እኔም ቀደም-ሲል ደረጄ በላይነህን አሁን ደግሞ ኤልያስን ለማወደስና ለማመስገን ምክንያት የሆነኝ ምናልባት ይሄ ፕሮግራም ሳይሆን ይቀራል?
እርሱን ማወቅም ሆነ መገመት አልችልም ነገር ግን በአንድ ወቅት በበጎ የምናውቃቸውም ሆነ የማናውቃቸው ሰዎች በህይወታችን ተከስተው አልፈዋል። እነዚህን ሰዎች ላደረጉልን ቅንጣት ማወደስም ሆነ ማመስገን እንደ ኑሮ-ዘይቤ ልንይዘው የሚገባ እሴታችን ቢሆን ብዙ እናተርፍበታለን ብዬ አስባለሁ፡፡ ሁላችንም ሰርክ አመስጋኞች እንድንሆን የኤፍሬም እንዳለ “አንድዬ” ይርዳን፡፡


Read 10965 times