Print this page
Sunday, 26 September 2021 00:00

ሳምንታዊ ዜናዎች

Written by 
Rate this item
(1 Vote)

    በቆቦ ከተማና ዙሪያው የሲቪል ሰዎች ጭፍጨፋ ተፈጽሟል ተባለ
                      
               ላለፉት ሁለት ወራት ተኩል ገደማ በህወሃት ቁጥጥር ስር በቆየው የራያ ቆቦ አካባቢ በተለይ በቆቦ ከተማና ዙሪያው ቁጥራቸውን በውል ለማወቅ አዳጋች የሆነ የሲቪል ሰዎች ጅምላ ግድያ መፈጸሙን በአካባቢው ላይ ጥናት ያደረገው የወሎ ህብረት ለአዲስ አድማስ የገለጸ ሲሆን የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን በበኩሉ፤ ስለ ኢ-ሰብአዊ ድርጊቱ ተመሳሳይ መረጃዎች ማግኘቱን አመልክቷል። የኢትዮጵያ ሠብአዊ መብቶች ጉባኤ (ኢሠመጉ) በበኩሉ ከ5 መቶ በላይ ሰዎች ስለመገደላቸው አስታውቋል።
የህወሃት ሃይሎች በተለይ ጳጉሜ 4 እና 5 ቀን 2013 ዓ.ም  በቆቦ ከተማ ህፃናትን፣ ሴቶችንና አዛውንቶችን በአጠቃላይ በከተማዋ ጎዳናዎች ላይ ሲንቀሳቀስ ያገኙትን ሁሉ በመግደል፣  አስክሬኖችን ጭምር የመሰወር ዘግናኝ ኢ-ሰብአዊ ድርጊት መፈጸማቸውን የወሎ ህብረት በጎ አድራጎት ድርጅት ሊቀ መንበር አቶ ያሲን መሃመድ ለአዲስ አድማስ አመልክተዋል።
“አንዳንዶች የሟቾችን ቁጥር 800 ሲሉ ይገልጻሉ፤ ይህ ግን የሟቾችን ቁጥር ያሳነሰ ነው፤ ከዚህ በላይ የሆነ ህዝብ ነው የተጨፈጨፈው “ያሉት አቶ ያሲን፤ ገለልተኛ ተቋማት በጉዳዩ ላይ አስፈላጊውን ማጣራት እድርገው ለህዝብ እውነታውን ሊያሳውቁ ይገባል ብለዋል።
የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን በበኩሉ በቆቦ ከተማና ዙሪያው ባሉ የገጠር ከተሞች፣ በሲቪል ሰዎች ላይ በህወሃት ሃይል እየተፈጸመ ያለው ግድያ በእጅጉ አሳሳቢ መሆኑን አመልክቷል። የሲቪል ሰዎች መኖሪያ አካባቢዎችን፣ የቤት ለቤት ሃሰሳ ግድያ፣ ዝርፊያና የሲቪል መሰረተ ልማቶች ጥቃት ጭምር መፈጸሙን ኮሚሽኑ ሪፖርቶች እንደደረሱት አስታውቋል።
ኢሰመኮ በጉዳዩ ላይም ተጨማሪ ምርመራ እንደሚደርግ አስታውቋል።
የኢትዮጵያ ሠብአዊ መብቶች ጉባኤ (ኢሠመጉ) በበኩሉ በደረሰው መረጃ መሰረት ጳጉሜ 5 ቀን 2013 ዓ.ም በህወኃት ሃይሎች በቆቦ ከተማ በተፈፀመ ጥቃት ከ5 መቶ በላይ ንፁሀን በአንድ ጀምበር ተጨፍጭፈዋል፣ የገበሬው የእርሻ ሠብሎች በሙሉ እንዲወድሙ ተደርገዋል፡፡ ነዋሪዎች በገፍ ወደ ደሴ እና ኮምቦልቻ ከተሞች ተፈናቅለዋል፡፡

_______________________________________


                    “የሸቀጦች ዋጋ ንረት የዜጎችን በቂ ምግብ የማግኘት መብት እየተጻረረ ነው”
                      
            በኢትዮጵያ የሸቀጦች ዋጋ ንረት በእጅጉ እንዳሳሰበው ያመለከተው የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን፤ የዋጋ ንረቱ ዝቅተኛ ገቢ ያላቸው የህብረተሰብ ክፍሎች በቂ ምግብ የማግኘት መብታቸው ላይ አሉታዊ ተፅዕኖ እያሳደረ ነው ብሏል።
ኮሚሽኑ በሃገሪቱ የተከሰተውን የሸቀጦች ዋጋ ንረት አስመልክቶ ባወጣው አስቸኳይ መግለጫው የዋጋ ንረቱ  የሌሎችን በቂ ምግብ የማግኘት መብት የሚገድብ ከመሆኑም በላይ በሌሎች ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ መብቶች ላይ አሉታዊ ተጽዕኖ እያሳደረ ነው ብሏል።
ችግሩን ለማቃለል መንግስት የወሰዳቸው አንዳንድ እርምጃዎች በተለይም የተወሰኑ ከሃገር ውጪ የሚሸመቱ የምግብ ሸቀጦች ከቁርጥና ከግብር ነጻ እንዲገቡና በሃገር ውስጥ በሚገበዩ ምርቶች ላይ የተጨማሪ እሴት ግብር እንዲነሳ መደረጉ፣ አበረታች እርምጃ ነው ብሏል- ኮሚሽኑ በመግለጫው።
የዋጋ ንረትን ለማቃለል በመንግስት የሚወሰዱ እርምጃዎች የተቀናጁ እንዲሆኑና በእርግጥም ለጉዳት የተጋለጡ የህብረተሰብ ክፍሎችን ተጠቃሚ እያደረጉ ስመሆኑ በየጊዜው ክትትል እንዲደረግ ኮሚሽኑ ምክረ ሃሳብ አቅርቧል።


________________________________________________


                     “ኢዜማ” እና “ነዕፓ” ከሶማሌ ክልል= ምርጫ ራሳቸውን አገለሉ
                              
            የኢትዮጵያ ዜጎች ለማህበራዊ ፍትህ (ኢዜማ) እና ነፃነት እና እኩልነት ፓርቲ(ነእፓ) መስከረም 20 ቀን 2014 በሶማሌ ክልል ከሚካሄደው ምርጫ ራሳቸውን ማግለላቸውን አስታወቁ፡፡
ፓርቲዎቹ በጋራ በሰጡት መግለጫ፤ ከዚህ ቀደም በተካሄደው ሃገር አቀፍ ምርጫ የተስተዋሉ ስህተቶች በሶማሌ ክልል በሚካሄደው ምርጫ እንዳይደገሙ በተደጋጋሚ ችግሮችን ያመለከቱ ቢሆንም፣ ምንም አይነት የማስተካከያ እርምጃ ባለመወሰዱ ራሳቸውን ከምርጫው እንዲያገሉ መገደዳቸውን አስታውቀዋል።
በሶማሌ ክልል በሚካሄደው ምርጫ የመራጮች አመዘጋገብ ህግን ያልተከተለ ለአንድ ወገን ያደላ፣ የምርጫ ቅስቀሳውም በተመሳሳይ ለሁሉም እኩል በተከፈተው ሜዳ ሳይሆን ለአንድ ወገን ያደላ በመሆኑ ፓርቲዎቹ በዚህ ምርጫ ውስጥ መቆየት ለሚፈለገው የዲሞክራሲ ስርዓት ግንባታ አስተዋፅኦ አያበረክትም የሚል እምነት ስላደረባቸው ከምርጫው ራሳቸውን ማግለላቸውን ለአዲስ አድማስ ባደረሱት የጋራ መግለጫቸው ጠቁመዋል።
በተጨማሪም ወደ ክልሉ የተጓጓዘው የምርጫ ቁሳቁስ ዘረፋ የተፈፀመበት መሆኑን በማስረጃ በማስደገፍ የምርጫ ቁሳቁሶች በሙሉ በአዲስ እንዲቀየሩ ለምርጫ ቦርድ  የቀረበው አቤቱታም ምላሽ አለማግኘቱን የጠቆሙት ፓርቲዎቹ፤ በዚሁ ሁኔታ የሚካሄድ ምርጫም ተአማኒነት የጎደለው ነው የሚሆነው ብለዋል። ተጨማሪ የምርጫ ጣቢያዎች እንዲቋቋሙ የቀረበው ጥያቄ ምላሽ አለማግኘቱን መግለጫው ያትታል፡፡
በየደረጃው መዋቀር የነበረበት የብሔራዊ ምርጫ ቦርድ መዋቅር፣ ከመንግስት ጋር የተዋሃደ መሆኑን፤ የብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ባለሙያዎች ሳያውቁ የምርጫ ቁሳቁሶችና ሰነድ በወረዳና ቀበሌ የመንግስት መዋቅር ሠራተኞች እጅ እንዲቀመጥ ማድረጉ፤ እንዲሁም ስለ አጠቃላይ የምርጫው ሂደት ለተፎካካሪዎች ግልጽ መረጃ ያለመስጠቱ ምርጫውን ተአማኒ አያደርገውም ብለዋል-ፓርቲዎቹ፡፡
በተለያዩ ምክንያቶች ወደ ኋላ በቀሩት በሶማሌ ክልል፣ ሃረሪ ክልልና በደቡብ አጠቃላይ ምርጫ የሚደረግ ሲሆን በዚሁ ምርጫ በአጠቃላይ ከሰባት ሚሊዮን በላይ መራጮች ይሳተፋሉ፡፡

Read 12558 times
Administrator

Latest from Administrator