Sunday, 26 September 2021 00:00

አዲሱ የአሜሪካ ማዕቀብና ከኢትዮጵያ የገጠመው ተቃውሞ

Written by  መታሰቢያ ካሳዬ
Rate this item
(5 votes)


      • አሜሪካ ከተሳሳተ መረጃ ላይ ተነስታ በምትፈጥረው ጫና አንንበረከክም ጠ/ሚ ዐቢይ አህመድ
      • ማእቀቡ ከማስፈራሪያነት የዘለለ አቅም አይኖረውም- ፕ/ሮ በየነ ጴጥሮስ
      • አሜሪካ በኢትዮጵያ ላይ ልትጥል ያሰበችውን አዲስ ማዕቀብ ቻይና ትቃወማለች- የቻይና የውጭ ጉዳይ ሚ//ር
                   በአሜሪካው ፕሬዚዳንት ጆ ባይደን በቅርቡ የተፈረመውና ኢትዮጵያ ውስጥ የተቀሰቀሰው ግጭት እንዲራዘም ሰበብ በሚሆኑ ተጠያቂዎችና ተባባሪዎቻቸው ላይ አዲስ ማዕቀብ ለመጣል ያስችላል የተባለው ትዕዛዝ፣ ከኢትዮጵያ ከፍተኛ ተቃውሞ ገጥሞታል።
ጠቅላይ ሚኒስቴር ዶ/ር ዐቢይ አህመድ፤ ፕሬዚዳንት ጆ ባይደን ትዕዛዙን ከፈረሙ ከጥቂት ሰዓታት በኋላ ለፕሬዚዳንቱ በጻፉት ግልፅ ደብዳቤ፤ “ተስፋ በቆረጡና ከሚሊዮኖች ደህንነት ይልቅ የእነሱ ስልጣን በሚያስጨንቃቸው ግለሰቦች የተሳሳተ መረጃ  የተነሳ በሚፈጠር ጫና አንበረከክም”  ብለዋል። ቻይና በበኩሏ፤ አሜሪካ በኢትዮጵያ ላይ ልትጥል ያሰበችውን አዲስ ማዕቀብ እንደምትቃወም አስታውቃለች፡፡ የቻይና የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ ሊጂያን ዥዋ፤ “አሜሪካ በኢትዮጵያ ላይ ልትጥል ያሰበችው አዲስ ማዕቀብ ቻይና ትቃወማለች” ሲሉ በትዊተር ገፃቸው አስፍረዋል፡፡
ኢትዮጵያ ልዩነቶችን ለመፍታትና ሀገራዊ መግባባትን ለመፍጠር፣ ሰላምና ፀጥታን ለማረጋገጥ አቅሙም ጥበቡም  እንዳላት  እናምናለን ያሉት ቃል አቀባዩ፤ አሜሪካ በጥንቃቄ ገንቢ ሚናዋን ትወጣለች ብለን እናምናለን ብለዋል፡፡
ጠ/ሚኒስተር ዐቢይ በፃፉት ግልጽ ደብዳቤ፤ ህወኃት በኢትዮጵያ ላይ በፈፀማቸው ግፎችና በደሎች በርካታ ንፁሀን እየተገደሉ፣ ከቤት ንብረታቸው እየተፈናቀሉና ኑሮቸአው የተመሰቃቀለ እንዲሆን ሲደረግ እያየ የጆ ባይደን አስተዳደር፣ ጠንከር ያለ አቋም ሳይወስድ መቆየቱ መልስ ያጣ ጥያቄ ሆኗል ብለዋል።
አሸበሪው የህወኃት ቡድን በትግራይ ክልል የሚገኙ ህፃናትን እንደ ከለላ አግቶ ይዞ እያሰቃያቸው መሆኑን ለፕሬዚዳንቱ የገለፁት ጠ/ሚኒስትሩ፤ የክልሉን ህፃናት እያስገደዷቸው ወደ ጦርነት እየማገዳቸው እንደሆነና ይህም ድርጊት ቡድኑን በዓለም አቀፍ ህግ የሚያስጠይቀው ወንጀል ነው ብለዋል፡፡
እውነታው ይህ ሆኖ እያለ አለም አቀፉ ማህበረሰብ አይቶ እንዳላየ በመሆንና በተሳሳተ መረጃ ምክንያት ፊቱን ኢትዮጵያ ላይ አዙሯል ያሉት ጠ/ሚኒስትሩ፤ የዚህ ሁሉ ምክንያት የሆነውን አሸባሪ ድርጅት ግን በተገቢው መንገድ መግሰፅና ማውገዝ አልተቻለም ብለዋል፡፡ “ተስፋ በቆረጡና ከሚሊዮኖች ደህንነት ይልቅ የእነሱ ስልጣን በሚያስጨንቃቸው ግለሰቦች የተሳሳተ መረጃ የተነሳ በሚፈጠር ጫና አንበረከክም፤ ኢትዮጵያዊነታችንና አፍሪካዊነታችን ይህ እንዲሆን አይፈቅድም” ሲሉ ጠ/ሚኒስትሩ ፈርጠም ያለ አቋማቸውን አንፀባርቀዋል።
አሜሪካ በኢትዮጵያ ላይ ልትጥል ያሰበችው አዲሱ ማዕቀብ ምን እንደሆነ በዝርዝር ባይገልፁትም ማዕቀቡ ቢጣልም በአገሪቱ ላይ የሚያስከትለው ጫና እዚህ ግባ የሚባል አይደለም ያሉት ፕሮፌሰር በየነ ጴጥሮስ፤ ማዕቀቡ ከማስፈራሪያነት የዘለለ ነገር አይኖረውም ሲሉም አጣጥለውታል፡፡ “አሜሪካ  ማእቀቡን እጥላለሁ ማለቷ የተለመደ ዛቻና ማስፈራሪያዋ ነው፡፡ እኛ የምንላችሁን ካልተቀበላችሁ፣  እንደምንላችሁ ካልሆናችሁ እንዲህ እናደርጋለን በማለት ጫና ለመፍጠር አስባ የምታደርገው ነው፡፡ ማእቀቡ ቢደረግም እንኳን ጉዳቱ የከፋ ነው የሚል እምነት የለኝም፣ እንደተነገረው ማእቀቡ በባለስልጣናቱ ላይ የቪዛ፣ በአሜሪካ አገር የሚገኝ የባለስልጣናት የሃብት መንቀሳቀስ ክልከላና የንብረት እገዳ ናቸው፡፡ ይህ እገዳ የሚያስከትለው ጉዳት ብዙ አይመስለኝም፡፡ ቀደም ባለው መንግስት በርካታ ባለስልጣናት በውጭ አገራት ገንዘብና ንብረት ያላቸው ስለነበሩ ይህንን ለማገድ ይጠቅም ይሆናል፡፡ ከለውጡ ወዲህ ግን ይህን አይነት ነገር እምብዛም የሚያሳስበን አይደለም እናም ማዕቀቡ ከማስፈራራት ያለፈ ብዙም  ጫና አለው ብዬ አላስብም፤ ይልቅ የአሜሪካንን ከእኛ በላይነትን የሚያሳይ ነው፡፡ ሲሉ ትዝብታቸውን ገልጸዋል። በመቀጠልም “አሜሪካኖች ካለነሱ ኢትዮጵያ ቆማ አትሄድም ልዕልናዋም ጥያቄ ውስጥ ይገባል ብለው ካሰቡ በጣም ተሳስተዋል፡፡ አሁን የዓለም ሁኔታ ተቀይሯል፤ እንደ ድሮው እዚህም እዚያም ጫና እያሳረፈን እንቀጥላለን ብለው ካሰቡ አይሰራም” ሲሉ ፕሮፌሰሩ። አስረድተዋል። አክለውም፤ ማዕቀቡን እንዴት መቋቋም እንደሚቻል ሲገልፁም፤ “አሁን አሜሪካ ባትደግፈን፣ ሌላ የሚደግፍ አገር ሞልቷል፤ እኛ ብቻ በአግባቡ ፖለቲካችንን መጫወት ብቻ ነው የሚጠበቅብን፡፡ የውስጥ ሁኔታዎችን ማስተካከል፣ ያሉብንን አለመረጋጋቶች መፍታት፣ የህግ የበላይነት እንዲስፍን ለማድረግ የተጀመረውን ህግ የማስከበር እንቅስቃሴ አጠናክሮ መቀጠልና አገራችንን በሰላማዊ ሁኔታ ውስጥ ማስቀመጥ፣ ሁሉም ሃይሎች ወደ ማምረት እንቅስቃሴ ውስጥ እንዲገቡ ሁኔታዎችን ማመቻቸት ይገባል ብለዋል” ፕሮፌሰር በየነ ጴጥሮስ፡፡
የሳይበር ሴክሩቲ ስፔሻሊስትና የቀድሞው የአሜሪካ መከላከያ ሚ/ር አባል የነበሩት ኦሊቨር ቶማስ፣ አሜሪካ በቅርቡ በኢትዮጵያ ላይ የወሰደችውን በተሳሳተ እሳቤ ላይ የተመሰረተ የማዕቀብ እርምጃ ተቃውመዋል። “ፍላጎትን በድሃ አገራት ላይ ለመጫን ማዕቀብ፣ ፕሮፓጋንዳና ማስፈራርያ መጠቀም ከሰብአዊነት ያፈነገጠ ነው” ሲሉ ተችተዋል- ኦሊቨር ቶማስ።
የአሜሪካው ፕሬዚዳንት ጆ/ባይደን የሰብአዊ መብት ጥሰቶች እንዲፈፀሙ አድርገዋል ባሏቸው የኢትዮጵያና የኤርትራ መንግስታትና በአማራ ክልል ባለስልጣናት እንዲሁም በህወኃት አመራሮች ላይ ማዕቀብ ለማስጣል ያስችላል የተባለውን የውሳኔ ሃሳብ መስከረም 7ቀን 2014 ዓ.ም በፊርማቸው ማፅደቃቸው ይታወሳል፡፡


Read 10461 times