Monday, 27 September 2021 12:37

የአሜሪካን ጫና እንዴት እንቋቋመው?

Written by  ደረጀ ይመር
Rate this item
(3 votes)

የሎቢስት ሚና
ቫን ባተን የተባለው የሕወሓት ተከፋይ ጉዳይ አስፈጻሚ ወይም ሎቢስት ድርጅት፣ ኢትዮጵያን አገዋ ከተባለው የነጻ ንግድ ተጠቃሚ ማእቀፍ ለማሰረዝ ከፍተኛ እንቅስቃሴ እያደረገ እንደሆነ መረጃዎች ይጠቁማሉ፡፡
ታዛቢዎች እንደሚናገሩት፤ የአሜሪካን ፖሊሲ አውጪዎች ያለ ተከፋይ ጉዳይ አስፈጻሚ፣ ተጽእኖ ማሳደር የሚታሰብ አይደለም፡፡ ከዚሁ ጋር በተያያዘ፤ የቀድሞ የአለም ባንክ ከፍተኛ አማካሪ ዶ/ር ዮናስ ብሩ፣ ”ቦርከና” በተባለ ድረገጽ ላይ ባሰፈሩት ጽሑፍ ይህንኑ  ነጥብ ያጠናክራሉ፡፡
የአሜሪካንን ፖሊሲ አውጪዎች አቋም፣ ያለ ሕዝብ ግንኙነት ሥራና የፖሊሲ አግባቢ ድርጅት መቀየር የሚሞከር አይደለም፡፡ የአሜሪካ የቅርብ ወዳጆች ሳይቀሩ፤ የፖሊሲ አግባቢ ድርጅቶችን ወይም ሎቢስቶችን ይቀጥራሉ፡፡
ጃፓን ባለፉት አምስት ዓመታት፣ለእነዚህ መሰል ድርጅቶች ወደ 200 ሚሊዮን ዶላር የሚጠጋ ገንዘብ አውጥታለች፡፡ደቡብ ኮሪያ 172 ሚሊዮን ዶላር፤ እስራኤል 143 ሚሊዮን ዶላር፤ሳውዲ አሬቢያ 112 ሚሊዮን ዶላር አውጥተዋል፡፡ 13 ቢሊዮን ዶላር ጥቅል ዓመታዊ ምርት ያላት ደቡብ ሱዳን፣በዓመት 1.83 ሚሊዮን ዶላር ስታወጣ፣ 279 ቢሊዮን ዶላር ጥቅል ዓመታዊ ምርት ያላት ኢትዮጵያ ግን ለሎቢስቶች ቤሳ ቤስቲን አላወጣችም ተብሏል!
ሕወሓት በተንቤን የቀበሮ ጉዳጓድ ውስጥ በነበረበት ወቅት እንኳን፣ በዲፕሎማሲው መስክ መንግሥትን ያስከነዳው ሎቢስቶች በተጫወቱት ሚና ነው፡ የሽብር ቡድኑ ከሎቢስቶች በተጨማሪ በታላላቅ መገናኛ ብዙኅን ብቅ  እያሉ የሚሟገቱለት  ነጭ ጀሌዎች አሉት፡፡ እነዚህ ጀሌዎች ከቡድኑ ጋር ለሦስት አሥርተ ዓመታት በማፊያ የትስስር መረብ ማእድ ሲቆርሱ ነው  የኖሩት፡፡ ይኽ እውነታ እንዳለ ሆኖ፤ አሜሪካ ከማእከላዊው መንግሥት ይልቅ፤ ታዛዡን ሕወሓት በቀንዱ ላላት ተጽዕኖ ተመራጭ ማድረጓ ጉዳዩን የበለጠ አወሳስቦታል፡፡ ለዚህም ነው፤ ድርጅቱ ሰብዓዊ ፍጡር ሊሸከመው የማይችል ዘግናኝ ወንጀል እየፈጸመም አሜሪካ ዝምታን የምትመርጠው፡፡
ጭራሽ ባሳለፍነው ሳምንት፣ የባይደን አስተዳደር፣ የሽብር ቡድኑን  ከመንግሥት ጋር በእኩል የሞራል ደረጃ ላይ በማስቀመጥ ማእቀብ ለመጣል ቅድመ ሁኔታዎችን መደርደሩ አስገራሚ መሆኑን  የፖለቲካ  ተንታኞች እየገለጹ ነው፡፡     
ከዚሁ ጋር በተያያዘ፤ አንጋፋው ዲፕሎማት ካሜሮን ሀድሰን፣ አሜሪካ እጥለዋለሁ ያለችውን ማእቀብ አስመልክተው አትላንቲክ ካውንስል በተባለው ድረገጽ ላይ አስተያየታቸውን አጋርተዋል፡፡ እንደ ዲፕሎማቱ ገለጻ ከሆነ፣ የባይደን አስተዳደር  በመስከረም መጨረሻ ላይ አዲስ መንግሥት ከመመመስረቱ በፊት ማእቀብ ለመጣል ከወሰነ  አስተዳደሩ ከዚህ ቀደም፣ በኢትዮጵያ የመንግሥት ለውጥ ለማምጣት ውጥን እንዳለው ሲሰነዘርበት የነበረውን ትችት እውነትነት የሚያረጋግጥ ይሆናል ብለዋል፡፡
በሎቢስት አማካኝነት ብሔራዊ ጥቅምን
ማስጠበቅ አመክንዮዋዊ ነው?
የፖለቲካ ተንታኞች፤ የፖሊሲ አግባቢ ድርጅትን (ሎቢስትን) ሚና በተለያየ ማዕቀፍ ነው የሚገመግሙት፡፡ ብሔራዊ ጥቅምን በፖሊሲ አግባቢ ድርጅት ለማስጠበቅ ታሳቢ ያደረገ፤ የውጭ ጉዳይ ፖሊሲ ስልት፣ ዘላቂነት የለውም ብለው የሚያምኑ ልሂቃን በርካቶች ናቸው፡፡
አሜሪካም ሆነች ምዕራባዊያን እየተከተሉ ያሉትን የተሳሳተ ፖሊሲን ወደ ትክክለኛ መስመር ለማምጣት ማንኛውም የሀገሪቱ ዜጋ በዲፕሎማሲው ረገድ ንቁ ተሳታፊ የሚሆንበትን አሠራር መንግሥት መዘርጋት ካልቻለ ፈተናውን ከባድ እንደሚያደርገው እነዚሁ ተንታኞች አጽንኦት ሰጥተው ይገልጻሉ፡፡
የዲፕሎሚሲና አለም አቀፍ መምህሩ አቶ እንዳለ ንጉሤ፤ በዚህ ሐሳብ ሙሉ ለሙሉ ነው የሚስማሙት፡፡ ከተከፋይ ጉዳይ አስፈጻሚ ወይም ሎቢስት ይልቅ በሀገር ወዳድ ዜጎች አማካኝነት ቢከናወን የተሻለ ይሆናል፡፡ የመንግሥት ዋነኛ ትኩረት መሆን ያለበት ዜጋ ተኮር ዲፕሎማሲ ነው፡፡ ማንኛውም የሀገራችን ዜጎች ባለቡት የዓለም ክፍል፣ የዲፕሎማሲው ደጀን በማድረግ፤ የሀገር ገጽታን መከላከል የበለጸጉት ሀገሮች ተሞክሮ ነው፡፡ ኢትዮጵያም ይኽንን ልምድ ብትወስድ የተሻለ እንደሆነ ይጠቁማሉ፡፡
የሥነመንግሥት ባለሙያዎች፣ የዲፕሎማሲ ሥራ በኤምባሲ ብቻ እንዲሠራ መጠበቅ የዋህነት ነው ይላሉ፡፡ የዲፕሎማሲውን መስክ በአግባቡ መከወን የሚችል ጠንካራ ተቋማዊ አደረጃጀት በአገር ውስጥ ካልተፈጠረ፣የአሜሪካንንም ሆነ የምዕራባዊያንን ያልተገባ ጫና መቋቋም የሚታሰብ አይደለም፡፡ ይኽን ደግሞ ገቢራዊ ለማድረግ  የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ውቅርን መቀየር፤ ከጥያቄ ላይ የሚወድቅ አይደለም። የዘውግ ፖለቲካ ሰለባ የሆነው ይኽው ተቋም፣ እስካሁን ብቃትን ሳይሆን የዘውግ ውክልናን ታሳቢ አድርጎ መዋቀሩ  እንደ ሀገር ብዙ ጎድቶናል፡፡
በሌላ በኩል፤ መንግሥት ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በዲፕሎማሲው ረገድ የተስተዋለውን ክፍተት ከግምት ውስጥ በማስገባት፤ አንዳንድ የማሻሻያ ሥራዎች በመሥራት ላይ እንደሆነ እያስተዋልን ነው፡፡ ለአብነት ባሳለፍነው ሳምንት፣ የውጭ ጉዳይ ሚነስቴር፣ የአጋር አካላትን ምክረ ሐሳብ ከግምት ውስጥ በማስገባት፣ ሚሲዮኖቹን በአዲስ መልክ የማዋቀር ሥራን ለማከናወን ሥልጠና መጀመሩ ይታወቃል፡፡
ሰልጣኞቹ በኢትዮጵያ ላይ በውጭ ኀይሎች እየደረሰ ያለውን ጫና ለመቋቋም የሚያስችል ጠንካራ የዲፕሎማሲ ሥራ ማከናወን እንዳለባቸው የተገለጸ ሲሆን ሥልጠናው አህጉራዊና ዓለም አቀፋዊ ለውጦችን ከግምት የጣፈ፣ የዲፕሎማሲ ሥራ ማከናወን የሚያስችሉ ክህሎቶችን ለማጎልበት ትኩረት እንደሚያደርግ ተጠቁሟል፡፡
ማሰሪያ ነጥብ
በአጠቃላይ አሜሪካ በማእቀብ በኢትዮጵያ ላይ ጫና ለማሳደር የማትፈነቅለው ድንጋይ አይኖርም፡፡ ልዕለ ኃያሏ ሀገር፣ሰብዓዊ ቀውስ የሚለውን አጀንዳ ይዛ ብቅ የምትለው ድብቅ ተልዕኮዋን ታሳቢ አድርጋ ነው፡፡ ለዚህም አላማ፣ የሀገሪቱ ፖሊሲ አውጪዎች ከመገናኛ ብዙኃን ጋር በቅንጅት ይሠራሉ። ለአብነት፣በቅርቡ በሱዳናዊቷ  የሲኤንኤን ጋዜጠኛ አማካኝነት የተቀነባበረው  የተከዜ የአስክሬን ድራማን ማንሳት ይቻላል። ፖለቲከኞቹ አቅጣጫ ያስቀምጣሉ፤ ሚዲያው ያስፈጽማል፡፡ ምዕራባዊያን የመገናኛ ብዙኃን ነጻና ገለልተኛ እንዲሆኑ የሚጨነቁት በመካነ አእምሮ ውስጥ በሚሰጡት ኮርስ ላይ ብቻ ነው፡፡ ስለዚህ የዓለም አቀፉ መገናኛ ብዙኃን በሚጥልልን አጀንዳ በመወሰድ ፈንታ የራሳችንን የቤት ሥራ መሥራት ይኖርብናል፡፡
የባይደን አስተዳደርን ቅጣ ያጣ ጣልቃ ገብነት አደብ ለማስገዛት፤በአማጺው ሕወሓት ላይ የማያዳግም ወታደራዊው ድል ማስመዝገብ የሚያነጋግር አይደለም፡፡ እንደ ሀገር ከዚህ በላይ ምርጫ የለንም፡፡ በዚህ ሂደት ውስጥ የምዕራባዊያን መንጫጫት የሚጠበቅ  ነው፡፡ በአውደ ውጊያው እንደ ዐይን ብሌን የሚሳሱለት የጥፋት ቡድን ሽንፈት ሲገጥመው፣ “ሰብዓዊ ቀውስ” የሚሉ አጀንዳዎችን በመምዘዝ መረባረባቸው አይቀርም፡፡ ይህን ለመቋቋም፤ መንግሥት ከራሺያና ከቻይና ጋር ያለውን ግንኙነት የበለጠ ማጠናከር ይጠበቅበታል፡፡
የባይደን አስተዳደር፣ ነጩን ቤተ መንግሥት ከረገጠ ወዲህ፣ በየጊዜው በአፍሪቃ ቀንድ እየጣለ ያለው ነጥብ፣ ለራሺያ ጥሩ ሲሳይ ፈጥሮላታል፡፡ በዚህም ምክንያት፤ የቀጠናውን እጅግ ወሳኝ ሀገር ኢትዮጵያን አጥብቃ እየያዘች ነው፡፡ ኢትዮጵያ ይኽንን የኃይል እሽቅድምድም፣ እንደ ከለላ ተጠቅማ፤ ጦርነቱን በአፋጣኝ በአሸናፊነት ማጠናቀቅ ይኖርበታል፡፡ ወታደራዊ ድሉ ብዙ ቋጠሮዎችን ይፈታል። ያልተገቡ መፋጠጦችን ያስወግዳል፡፡ ከምዕራባውያን መንግስታት ጋር ንትርክን ያስወግዳል፡፡

Read 2347 times