Monday, 27 September 2021 12:56

ሮናልዶ የአመቱ ባለ ከፍተኛ ገቢ የእግር ኳስ ተጫዋች ሆነ

Written by 
Rate this item
(0 votes)

  ፖርቹጋላዊው የአለማችን የእግር ኳስ ኮከብ ክርስቲያኖ ሮናልዶ በፎርብስ መጽሄት የአመቱ የአለማችን ባለ ከፍተኛ ገቢ የእግር ኳስ ተጫዋቾች ዝርዝር ውስጥ የ1ኛ ደረጃን መያዙንና የዝውውር ክፍያን ሳይጨምር የተጫዋቹ አጠቃላይ ገቢ ከታክስ በፊት 125 ሚሊዮን ዶላር እንደሚደርስም ተዘግቧል፡፡
ከሰሞኑ ከጁቬንቱስ ወደ ማንችስተር ያቀናው የ36 አመቱ ሮናልዶ፤ ለዝውውሩ በቦነስ መልክ የተከፈለውንና ደመወዙን ጨምሮ በአመቱ 70 ሚሊዮን ዶላር ማግኘቱን የዘገበው ፎርብስ መጽሄት፣ የተቀረው ገቢ ደግሞ ናይኪን ከመሳሰሉ ታላላቅ የንግድ ኩባንያዎቹ ጋር ባለው የማስታወቂያና የንግድ ስምምነቶች የሚያገኘው መሆኑንም አስታውሷል፡፡
የሁልጊዜ ተቀናቃኙና አምና በአንደኛ ደረጃ ላይ የነበረው የ34 አመቱ አርጀንቲናዊ ኮከብ ሊዮኔል ሜሲ፣ ዘንድሮ በ110 ሚሊዮን አጠቃላይ ገቢ ወደ ሁለተኛ ደረጃ ዝቅ ማለቱንም መጽሄቱ ያወጣው መረጃ ያሳያል።
የ29 አመቱ ብራዚላዊ ኔይማር በ95 ሚሊዮን ዶላር፣ የ22 አመቱ ኪሊያን ማፔ በ43 ሚሊዮን ዶላር፣ የሊቨርፑሉ ሞሃመድ ሳላ በ41 ሚሊዮን ዶላር እስከ አምስተኛ ያለውን ደረጃ መያዛቸውንም ፎርብስ መጽሄት ባወጣው መረጃ አስታውቋል፡፡
የ2021 የፈረንጆች አመት 10 ባለ ከፍተኛ ገቢ የአለማችን የእግር ኳስ ተጫዋቾች እስከ አመቱ መጨረሻ በድምሩ ከታክስ በፊት 585 ሚሊዮን ዶላር ያህል ገቢ ያገኛሉ ተብሎ እንደሚጠበቅ የጠቆመው ፎርብስ፤ በተጨዋቾች ገቢ ስሌት ውስጥ የዝውውር ክፍያ አለመካተቱንም አመልክቷል፡፡
በሌላ በኩል ደግሞ፣ ተጫዋቹ ባለፈው ረቡዕ ፖርቹጋል ከአየርላንድ ጋር ባደረገችው ጨዋታ ባስቆጠራቸው 2 ጎሎች በአለማቀፍ ጨዋታዎች ለአገሩ ብሔራዊ ቡድን ያስቆጠራቸውን አጠቃላይ ጎሎች 111 በማድረስ አዲስ ክብረ ወሰን ማስመዝገቡ ተነግሯል፡፡
የአምስት ጊዜ የባሎንዶር የወርቅ ኳስ ተሸላሚውና በሻምፒዮንስ ሊግ የምንጊዜም ጎል አስቆጣሪ የሆነው የማንችስተር ዩናይትዱ አጥቂ ሮናልዶ በዕለቱ የሰበረው ክብረ ወሰን ከሌሎች ስኬቶች ሁሉ ልዩ ትርጉም የሚሰጠውና በእጅጉ ያስደሰተው እንደሆነ በኢንስታግራም ባሰራጨው መልዕክት ማስታወቁን አልጀዚራ ዘግቧል፡፡
በአለማቀፍ ጨዋታዎች 109 ጎሎችን በማስቆጠር ክብረ ወሰኑን ይዞት የቆየው ኢራናዊው ተጫዋች አሊ ዳይ እንደነበርም የአልጀዚራ ዘገባ አስታውሷል፡፡


Read 1150 times