Saturday, 25 September 2021 00:00

4ኛው “አግሮ ፉድ እና ፕላስት ፕሪንት ፓክ” ዓለም አቀፍ ኤክስፖ ይካሄዳል

Written by 
Rate this item
(0 votes)

  አራተኛው “አግሮ ፉድ እና ፕላስት ፕሪንት ፓክ”  ዓለም አቀፍ የንግድ ትርኢት ከጥቅምት 4-6 ቀን 2014 ዓ.ም በስካይ ላይት ሆቴል ይካሄዳል። የንግድ ትርኢቱ ኮቪድ 19 ከተከሰተ በኋላ  የሚደረግ የመጀመሪያው አለም አቀፍ የንግድ ትርኢት እንደሆነም ተገልጿል።
የንግድ ትርኢቱ በታዋቂው የጀርመኑ “ትሬድ ፌር” እና በኢትዮጵያ የኤግዚቢሽን ዘርፍ ከሚታወቁት አንዱ በሆነው  “ፕራና ኢቨንትስ” የጋራ ትብብር የሚዘጋጅ ሲሆን አዘጋጆቹ ባለፈው ረቡዕ በስካይ ላይት ሆቴል  መግለጫ፣ የንግድ ትርኢቱ በተለይም በኮቪድ 19 ምክንያት ተቀዛቅዞ የነበረውን የንግድ ልውውጥና ግንኙነት የማነቃቃት ፋይዳ እንዳለው ተናግረዋል።
በጋዜጣዊ መግለጫው ላይ የፕራና ኢቨንትስ ዋና ስራ አስፈጻሚ አቶ ነብዩ ለማ፣ የትሬድ ፌር መስራችና ማኔጅንግ ፓርትነር ማርቲን ማርዝ፣ በጀርመን ኤምባሲ የባህልና የኢኮኖሚክስ ዘርፍ ሃላፊና ተቀዳሚ ፀሀፊ የሆኑት ዶ/ር ካሌብ ሆልዝፉስና በቱርክ ኤምባሲ የንግድ አማካሪ የሆኑት  ሰዓት ኤርዶጉ፣ የጣሊያን ንግድ ኤጀንሲ (ITA) ዳሬክተር ሪካርዶ ዙኮኒ፣ በፈረንሳይ ኤምባሲ የንግድ አማካሪና የአገር ውስጥ ተጠሪ ማክሲም ባይለፍና ሌሎችም ተገኝተዋል።
የፕራና ኢቨንትስ የስራ ባልደረቦች፤ ባለፉት ወራት ይህ አለምአቀፍ የንግድ ትርኢት በተሳካ መልኩ እንዲከናወን በትጋትና በቁርጠኝነት ሲሰሩ ቆይተው ለዚህ ውጤት መብቃታቸውን የፕራና ኢቨንትስ ማኔጅንግ ዳይሬክተር አቶ ነብዩ ለማ ገልጸው፤ ይህ ዓለማቀፍ የንግድ ትርኢት በኢትዮጵያ መካሄዱ ያለውን ዘርፈ ብዙ ጥቅም ከኢኮኖሚ መነቃቃት፣ ከአገር ተጠቃሚነት፣ ከኢንዱስትሪ ፓርኮች መስፋፋትና ከስራ እድል ፈጠራ አንጻር አብራርተዋል።
ባለፉት ሶስት ዓመታት ፕራና ኢቨንትስ፣ ይህንኑ አግሮፉድና ፕላስት ፕሪንፕ ፓክ የንግድ ትርኢት፣ ፕራና ኢቨንትስ ከጀርመኑ አጋሩ “ትሬድ  ፉርመሴ” ጋር በተሳካ ሁኔታ ማካሄዱን የገለጹት አቶ ነቢዩ፤ የዘንድሮው ከቦታ ጥበት አንጻር የንግድ ትርኢቱ በቁጥር የሚለካ ሳይሆን በራሱ  መካሄዱ ብቻ በሚፈጥረው መነቃቃት ለሌሎቹ ዓለምአቀፍ የንገድ ትርኢቶች መካሄድ በር ከፋች ነው ብለዋል።
በንገድ ትርኢቱ ላይ ከ11 አገራት ማለትም ከፈረንሳይ፣ ከኢትዮጵያ፣ ከጀርመን፣ ከህንድ፣ ከጣሊያን፣ ከኩዌት፣ ከናይጀሪያ፣ ከሩሲያ፣ ከደቡብ አፍርካ፣ ከቱርክና ከአሜሪካ የተውጣጡ ተሳታፊ ድርጅቶች ከመላው ኢትዮጵያና ከጎረቤት ሀገራት ከሚመጡ የንግድ ትርኢቱ ጎብኚዎች ጋር ለመነጋገር፣ ፕሮጀክት ለመቅረጽና በጋራ ለመስራት ዝግጁ ሆነው የንገድ ትርኢቱን መከፈት እንደሚጠብቁ በመግለጫው ተብራርቷል። በንግድ ትርኢቱ ላይ ለኢትዮጵያ ፍላጎት የተዘጋጁ የግብርና፣ የምግብና የመጠጥ ማቀነባበሪያ ቴክኖሎጂዎች፣ ግብአቶች የፕላስቲክ፣ የህትመትና ማሸጊያ ቴክኖሎጂዎችና ለእይታ የሚቀርቡ ሲሆን ለሶስት ቀናት በሚዘልቀው የንግድ ትርኢት ከ2ሺህ በላይ ሰዎች ይጎበኙታል ተብሎም ይጠበቃል።
አራተኛው አግሮ ፉድ ፕላስት ፕሪንትፓክ አለም አቀፍ የንገድ ትርኢት፣ በኢትዮጵያ በኩል ከግብርና ሚኒስቴር ፣ ከኢትዮጵያ ምግብ መጠጥና መድኃኒት ኢንዱስትሪ ልማት ኢንስቲትዩት፣  የኬሚካልና ኮንስትራክሽን ግብአቶች ኢንዱስትሪ ልማት ኢኒስትትዩት፣ ከዓለም አቀፍ ደግሞ ከጀርመን ግብርና ማህበረሰብ፣ ከጀርመን መንግስት ምግብና  ግብርና ሚኒስቴር፣ ከጀርመን ዓለምአቀፍ ትብብር ማዕከል እንዲሁም፣ ከጀርመን፣ ፈረንሳይ፣ ጣሊያና ቱርክ ኤምባሲዎች፣ ከሌሎችም በተጨማሪም ከዓለምአቀፍ ተቋማት እውቅና ድጋፍ ተችሮት የሚዘጋጅ የንግድ ትርኢት እንደሆነ ከዘጋጆቹ ለመረዳት ተችሏል።

Read 1402 times