Wednesday, 29 September 2021 00:00

የኢንተርኔት አፈና በአለማቀፍ ደረጃ መባባሱ ተነግሯል

Written by 
Rate this item
(0 votes)

 የኢንተርኔት ነጻነትን የሚጻረሩ የተለያዩ አፈናዎችና ገደቦች ባለፈው የፈረንጆች አመት 2021 በአለማቀፍ ደረጃ ተባብሶ መቀጠሉንና በአመቱ በ41 አገራት ውስጥ የሚኖሩ ተጠቃሚዎች በኢንተርኔት ባስተላለፏቸው መልዕክቶች ሳቢያ አካላዊ ጉዳት እንደደረሰባቸው ከሰሞኑ የወጣ አንድ አለማቀፍ ጥናት አመለከተ፡፡
ፍሪደም ሃውስ የተባለው ተቋም ሰሞኑን ያወጣውን አለማቀፍ የኢንተርኔት ነጻነት ሁኔታ አመላካች ሪፖርት ጠቅሶ ዘ ጋርዲያን እንደዘገበው፣ መንግስታት በመብት ጥሰቶች መግፋታቸውንና ጥናት ከተደረገባቸው 70 የአለማችን አገራት መካከል በ56ቱ ከኢንተርኔት አጠቃቀም ጋር በተያያዘ ዜጎች መታሰራቸውንና መከሰሳቸውን ለማረጋገጥ ተችሏል፡፡
የኢንተርኔት መብቶች ጥሰት ዘንድሮም በአለማቀፍ ደረጃ ለ11ኛ ተከታታይ አመት ተባብሶ መቀጠሉን የጠቆመው ሪፖርቱ፣ ተጠቃሚዎችን በተለያዩ መንገዶች የሚያፍኑና ለእስር የሚዳርጉ መንግስታት ቁጥር መበራከታቸውንና በአንጻሩ ደግሞ በኢንተርኔት የሚሰራጩ የተሳሳቱ መረጃዎች መበራከታቸውንም አክሎ ገልጧል፡፡
በአመቱ 20 የተለያዩ የአለማችን አገራት የኢንተርኔት አገልግሎትን ማቋረጣቸውን የጠቆመው ሪፖርቱ፣ 20 ያህል መንግስታት ደግሞ የማህበራዊ ድረገጾችን መዝጋታቸውን አስታውሷል፡፡
በአመቱ ከአለማችን አገራት መካከል እጅግ የከፋ የኢንተርኔት አፈና የታየባት ቀዳሚዋ አገር ተብላ በሪፖርቱ የተጠቀሰችው ቻይና ስትሆን፣ የኢንተርኔት አፈና በከፍተኛ ሁኔታ የተባባሰባቸው ተብለው የተጠቀሱት ቀዳሚዎቹ ሶስት የአለማችን አገራት ደግሞ ማይንማር፣ ቤላሩስና ኡጋንዳ ናቸው፡፡


Read 970 times