Monday, 10 September 2012 13:52

የአቶ ኃይለማርያም አዲሱ አስተዳደርና ተግዳሮቶቹ

Written by  አልአዛር ኬ
Rate this item
(0 votes)

አዲሱ ጠ/ሚኒስትር ራሳቸውን እንጂ መለስን እንዲሆኑ አይጠበቅባቸውም

ዛሬ ቀኑ ሰኞ ጳጉሜ 5 ቀን 2004 ዓ.ም ነው፡፡ ሟቹ ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ አፈር ከቀመሱ ልክ ዘጠነኛ ቀናቸው፡፡ መቃብር መቸም ቢሆን ቀዝቃዛ ነው፡፡ ክረምት በጋ ብሎ ወቅት አይመርጥም፡፡ እሳቸውን ግን ጨርሶ ሊቀዘቅዛቸው አይችልም፡፡ ለምን ቢባል እንባ ትኩስ ነው፡፡ ይሞቃል፡፡ እናም ድፍን ሀበሻ ከዳር እስከዳር ተጠራርቶ ለአስራ ሁለት ቀናት ሙሉ ያነባላቸው እንባ ያሞቃቸዋል፡፡ አሊያም ደግሞ ያ በርካቶችን ያስደመመ አስገራሚ ጽናታቸው በመቃብር ውስጥም ቢሆን አንድ መላ ማበጀቱ አይቀርም፡፡

ቀጣዩ ጉዳይ የአገሪቱ መፃኢ እጣ ፈንታ ምን ይሆናል የሚለው ነው፡፡ አገሪቱን በመምራት ረገድ የሁሉም ቀልብ ያረፈው የአቶ መለስን እግር ተከትለው በምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርነት በስልጣን ወንበሩ ላይ በተተኩት በአቶ ሃይለማርያም ደሳለኝ ላይ ነው፡ የወቅቱ ዋነኛ የትኩረት አቅጣጫና የመነጋገሪያ አጀንዳም የድህረ መለስ ኢትዮጵያና የአቶ ሀይለማርያም አዲሱ አስተዳደር የወደፊት ሁኔታ ተግዳሮቶቹ ምን ሊሆን ይችላል የሚለው ነው፡፡ ይህንኑ መሠረታዊ ጉዳይ ዋነኛ የመወያያ አጀንዳ በማድረግ ባለፈው ሳምንት በተለይ የጠቅላይ ሚኒስትር መለስን ሞት ተከትሎ በሀገሪቱ ምን አይነት ሁኔታ ሊፈጠር ይችላል? ሀገሪቱ በውጪ ታከናውናቸው የነበሩ የተለያዩ ስራዎች እጣ ፈንታ ጉዳይና ስለ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ ሃይለማርያም ደሳለኝ ነገር አንስተን ነበር፡፡ የዛሬው ጽሑፌ የባለፈው ሳምንት ቅጣይ ነው፡፡

ስለ ድህረ - መለስ ኢትዮጵያ መወያየት ከተፈለገ፣ በዚያም ቢባል በዚህ የውይይታችን መነሻ የሚሆነው ገዥው ፓርቲ ኢህአዴግ ነው፡፡ ከሁለት አስርት አመታት በላይ የመሩትን ዋነኛ መሪውን ያጣው ኢህአዴግ፤ በፖለቲካ፣ ኢኮኖሚና ማህበራዊ ጉዳዮች ላይ ያለው አቋም በግልጽ የታወቀ ነው፡፡ የድርጅቱ ሊቀመንበር በነበሩት በአቶ መለስ እግር የሚተካው መሪ ማንም ይሁን ማን በዋናነነት የሚጠበቅበት እነዚህን የታወቁ የድርጅቱን አቋሞች በትጋት ማስፈፀም ነው፡፡ ድርጅቱ በአቋሞቹ ላይ ለውጥ ካላደረገ በስተቀር ከዚህ ውጪ ለመንቀሳቀስ ምንም አይነት እድል የለም፡፡

የጠቅላይ ሚኒስትር መለስ በድንገት ከዚህ አለም በሞት መለየት፣ ከማንም በላይ ታላቅ ፈተና ውስጥ የከተተው ኢህአዴግን ነው፡፡

ለኢህአዴግ የ”ሰውየው” ሞት ለረጅም አመታት ከ”ህዝቡ ጋር እየወደቁ እየተነሱ” ጠንካራና ብቁ የፖለቲካ ድርጅት እንዲሆን ያበቁትን አንድ አሪፍ መሪ በማጣት ብቻ የሚገለጽ አይደለም፡፡ የመለስ ሞት ለኢህአዴግ ከሞትም በላይ ነው፡፡

ለገዥው ፓርቲ ኢህአዴግ የጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ያልታሰበ ሞት፣ የፈተናዎች ሁሉ ፈተና የሚሆንበት ከፍተኛ የአመራር ክህሎት ባለቤት፣ ባለ ብሩህ ራዕይ፣ ታላላቅ ህልሞችን አላሚ፣ የድርጅቱ ዋነኛ ስትራተጂ፣ ቀያሽና ግንባር ቀደም አንቀሳቃሽ ሞተር የነበሩትን መሪ በማጣቱ ብቻ አይደለም፡፡

የድርጅቱን የአመራርና ተጨባጭ ውጤት የማስገኘት ዙሪያ መለስ ደረጃውን እጅግ ከፍ አድርገው መስቀላቸውና ህዝቡ በሳቸው ጊዜ ከነበረው አመራርና ውጤት የበለጠ እንጂ ያነሰ እንዳይቀበል ወይም እንዳይጠብቅ ስላደረጉት ነው፡፡ የእሳቸውን ሞት ተከትሎ ህዝቡ ለኢህአዴግ ያስተላለፈው ግልጽ መልዕክት የሚያረጋግጠውም ይህንኑ ጉዳይ ነው፡፡

ህዝቡ በተለያየ ቋንቋ ነገር ግን በአንድ አይነት መልዕክት ለኢህአዴግ በጥሞና ማስገንዘብ የቻለው የተጀመረው ልማት ሳይቋረጥ ሳይሆን ይልቁንም ፍጥነቱን ጨምሮ እንዲካሄድ፣ ሀገሪቱ በአለም አቀፉ መድረክ የተጐናፀፈችውን ከበሬታና አመኔታ በማስጠበቅ ይበልጥ እንዲጐለብት እንዲያደርግ ነው፡፡ የድህረ መለስ ኢትዮጵያ ጥያቄ ይህ ነው፡፡

እንግዲህ ዋነኛው ጥያቄ የሚመጣው ይህን ተከትሎ ነው፡ የድህረ መለስ ኢህአዴግ ከላይ የተገለፁትን የድህረ መለስ ኢትዮጵያንና ህዝቦቿን ጥያቄዎች መመለስ ይችላል ወይ? እንደ እውነቱ ከሆነ ለድርጅቱ የፈተናዎች ሁሉ ፈተና ይህ ነው፡፡ በእርግጥ የድርጅቱ ስራ አስፈፃሚ ኮሚቴ በያዝነው ሳምንት መግቢያ ላይ ባካሄደው ስብሰባ የቀረቡለትን ህዝባዊ ጥያቄዎች ለመመለስ እንደሚጥር ቃል ገብቷል፡፡ ይሁን እንጂ ቃል ብቻውን ባዶ ነው፡፡ ዋናውና በሁሉም ዘንድ በጉጉት የሚጠበቀው የድርጅቱ ተግባራዊ ምላሽ ነው፡፡ እናም ኢህአዴግ ይህን የፈተናዎች ሁሉ ፈተና መወጣት መቻልና አለመቻሉን የምናየው ወደፊት ባሉት ጊዜያት በሚያከናውናቸው ተግባራት ብቻ ነው፡፡

ሟቹ ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ፤ ትተውት የሄዱት ፈተና ለድርጅታቸው ለኢህአዴግ ብቻ ሳይሆን በግለሰብ ደረጃም ለእያንዳንዱ የድርጅቱ ከፍተኛ አመራርም ጭምር ነው፡፡ የኢህአዴግ አመራር የቡድን አመራር ነው የሚለውን የድርጅቱን የተለመደ ምህላ ዝም ብለን እንደወረደ ብንቀበለው እንኳ፣ ከቡድኑ መሃል በመለስ እግር በሚተካው የድርጅቱ ሊቀመንበር ላይ ጫናው በተለየ ሁኔታ የበረታ እንደሚሆን ለመገመት ነቢይ አሊያም ወልይ መሆንን አይጠይቅም፡፡

አሁን ባለው ሁኔታ በኢህአዴግ ምክትል ሊቀመንበርነታቸው የዚህ ጫና ባለሳምንት ተረኛ ተሸካሚው አቶ ሀይለማርያም ደሳለኝ ናቸው፡፡

የእኒህን የድህረ መለስ የአዲሱ ዘመን የኢህአዴግ መሪ፤ የቅድመና ድህረ ፖለቲከኛነት ህይወት ባለፈው ሳምንት በመጠኑ ለመዳሰስ ሞክሬአለሁ፡፡ የድህረ መለስ ኢትዮጵያን በተመለከተ በሀገር ውስጥም ሆነ በውጪ ዋነኛ የትኩረት አቅጣጫና የመነጋገሪያ አጀንዳ ከሆኑት ጉዳዮች ውስጥ በዋነኛነት የሚጠቀሰው የእርሳቸውና የአዲሱ አስተዳደራቸው ነገር ነው፡፡ የዚህ ነገር ዋነኛ ማጠንጠኛ የሆነው ጥያቄ ደግሞ አንድ ነው፡፡ ምክትል ሚኒስትር አቶ ሃይለማርያም ደሳለኝ በሟቹ ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ ጫማ ልክ መሆን ይችላሉን? እንደ ድርጅቱ ኢህአዴግ ሁሉ በግለሰብ ደረጃም ለእርሳቸው ከፍተኛ ጫናና ፈተና ሊሆንባቸው ይችላል የተባለው ከባድ ጥያቄም ይህ ነው፡፡

ጥያቄውን ማብራራት ከመጀመራችን በፊት ግን መመለስ ያለበት አንድ ሌላ መሠረታዊ ጥያቄ አለ፡፡ ለመሆኑ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር በመሆን እያገለገሉ ያሉት አቶ ሃይለማርያም ደሳለኝ የድህረ መለስ ኢትዮጵያ የመጀመሪያው ሙሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ሆኖ የመመረጥ እድላቸው ምን ያህል ነው? ለዚህ መሠረታዊና ቁልፍ ጥያቄ በህዝቡና በድርጅቱ በኢህአዴግ መካከል ያለው የሃሳብ ወይም የግምት ልዩነት ከፍተኛ ነው፡፡ በሀገሪቱ አብዛኛው ህዝብ ዘንድ ያለው ግምትና ምናልባትም ወደ እርግጠኝነት በቀረበ ስሜት የሚጠብቀው የሰውየውን ቀጣይ አዲሱ የኢህአዴግ ሊቀመንበርና የሀገሪቱ አዲስ ጠቅላይ ሚኒስትር ሆነው መመረጥን ነው፡፡

ለኢህአዴግ ግን በቅርቡ በሚደረገው የድርጅቱ ካውንስል ስብሠባ በሚከናወን ምርጫ የኢህአዴግ ሊቀመንበር ሆነው መመረጥ መቻላቸው እስካልተረጋገጠ ድረስ የሚቆዩት በምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርነት ብቻ ነው፡፡ በዚያ ምርጫ ላይ የኢህአዴግ ሊቀመንበር ሆነው ለመመረጥ ያላቸው እድልስ ምን ያህል ነው ተብሎ ከተጠየቀ ግን በግሌ የማቀርበው መልስ፤ ከዘጠና በመቶ በላይ እድል አላቸው የሚል ነው፡፡

የዚህ ግምቴ ዋና ዋና ምክንያቶች የሚከተሉት ናቸው፡፡ አንደኛ ሟቹ ጠቅላይ ሚኒስትር በቀየሱትና ላለፉት ሁለት አመታት በከፍተኛ ሁኔታ ሲያስፈጽሙት በነበረው የኢህአዴግ የአመራር መተካካት ስትራተጂ ውስጥ ለድርጅቱ ከፍተኛ አመራርነት የታጩና በራሳቸው በመለስ የቅርብ ክትትል ሲኮተኮቱ የነበሩ በመሆናቸው፣ ሁለተኛ ለድርጅቱ ከፍተኛ አመራርነት ከሌሎች እጩዎች በተሻለ ሁኔታ የድርጅቱ በርካታ የስራ አስፈፃሚ አባላት ይሁንታና ድጋፍ ያላቸው በመሆኑ (ይህን በ2002 ዓ.ም ለኢህአዴግ ምክትል ሊቀመንበርነት በተደረገው ምርጫ ወቅትም በብአዴን የቀረቡትን እጩ በከፍተኛ ድምጽ በማሸነፍ አሳይተዋል) ሶስተኛ ደግሞ የአመራር መተካካቱ “ከህወሀት ወደ ህወሀት” ሊሆን ይችላል የሚለውን የበርካቶች ግምት ለማስቀረትና ኢህአዴግ “የአንድ ህዝብ የበላይነት የሚንፀባረቅበት” ድርጅት አለመሆኑን ለማሳየት የተሻሉ እጩ በመሆናቸው ሲሆን አራተኛ እርሳቸውን ሊፎካከር ይችላል ተብሎ ከአራቱም የኢህአዴግ አባል ድርጅቶች ወይም በወሬ በአሉባልታም ሆነ በፌስቡክም እንኳ ቢሆን የቀረበ አንድም እጩ አለመኖሩ ነው፡፡ ቀጣዮቹ ቀናትም የዚህን ግምት ትክክለኛነት ሊያረጋግጡልን ይችላሉ፡፡

እንግዲህ አቶ ሀይለማርያም ደሳለኝ አቶ መለስ ትተውት በሄዱት ጫማ ልክ መሆን ይችላሉ ወይ ለሚለው ወሳኝና የብዙዎች ወቅታዊ ጥያቄ የሚቀርበው ማብራሪያ፣ ቀጣዩ አዲስ ጠቅላይ ሚኒስትር ይሆናሉ ከሚለው ግምቴ በመነሳት ነው፡፡

አቶ ሀይለማርያም ደሳለኝ ተመርጠው፣ በአዲስ ጠቅላይ ሚኒስትርነት “በእሳቱ ወንበር” ላይ በተለይ ደግሞ እንደ ኢትዮጵያ ያለን ሀገርና እንደ ኢትዮጵያውያን ያሉ ህዝቦችን ለመምራት ከተቀመጡ፣ እንደማንኛውም ሰው ከተለያዩ ተግዳሮቶች ጋር ፊት ለፊት መጋፈጣቸው ተአምር ቢሠራላቸውም እንኳ ፈጽሞ የማይቀርላቸው ነገር ነው፡፡ ከተግዳሮቶቹ መካከል በውስጥም ሆነ በውጭ በበርካቶች ዘንድ የሚጠቀሰው፣ ያላቸው የአመራር ልምዳቸው ጉዳይ ነው፡፡ ለድርጅቱ ከፍተኛ አመራር ከፍ ያለ ቀረቤታ ያላቸው ሰዎች በተደጋጋሚ ሲናገሩ እንደሚደመጠው ከሆነ፤ የሰውየውን ልዩ ልዩ የአመራር ክህሎትና የእውቀት ችሎታ ቀድመው የተገነዘቡላቸው ሟቹ ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ነበሩ፡፡ የደቡብ ክልል ፕሬዚዳንት ስልጣናቸውን በፈቃዳቸው ለመልቀቅ ሲጠይቁ የተለያዩ ከፍተኛ ሀላፊነቶችን በመስጠት አጠገባቸው ሆነው እንዲሰሩ በማድረግ የተለያየ የስራ ልምዶችን እንዲቀስሙ ያደረጓቸው ሲሆን በድርጅቱ የአመራር መተካካት ስትራተጂ መሠረት ለድርጅቱ ከፍተኛ አመራርነት በግንባር ቀደምትነት በማጨት በተገቢው ሁኔታ እንዲበቁም ከፍተኛ እገዛና የቅርብ ክትትል ሲያደርጉላቸው የነበረውም ለዚህ እንደነበር በሰፊው ይነገራል፡፡

በዚህ መሠረትም አቶ ሀይለማርያም ደሳለኝ የፓርቲ ከፍተኛ አመራርን የደህዴንና የኢህአዴግ ከፍተኛ አመራር በመሆን፤ ድርጅታዊ የህዝብ ንቅናቄና አደረጃጀትን የጠቅላይ ሚኒስትሩ ልዩ አማካሪ በመሆን፤ የህዝብ አስተዳደርን የደቡብ ክልል ምክትልና ቀጥሎም ፕሬዚዳት በመሆን፤ የፓርላማ አሠራርን የኢህአዴግ ተጠሪ በመሆን፤ የውጪ አለምአቀፍ ዲፕሎማሲን ደግሞ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሆነው ላለፉት ሁለት አመታት በመስራት ያውቁታል፡፡ እናም በስራ ልምድ ማነስ አሁን እየታሙ ያሉትን ያህል ማማት አያስኬድም፡፡ የአቶ ሀይለማርያም ደሳለኝ ከፍተኛ ፈተና ይሆናል የሚባለው ሌላኛው ጉዳይ የፌደራሊዝምን እውነተኛ እሴቶች በተግባር የመተርጐም ጉዳይ ነው፡፡ የደቡብ ክልል ምክትልና ፕሬዚዳንት ሆነው ያገለግሉ በነበረበት ጊዜ በርካታ ብሔር ብሔረሠቦችና ህዝቦችን የማስተዳደር ችሎታቸውን በእጅጉ ይፈታተነው የነበረው ይህን ጉዳይ በተመለከተ ሲነሱ የነበሩ የተለያዩ ጥያቄዎች ስለነበሩ ለጉዳዩ እንግዳ አይደሉም፡፡ አሁን ተመሳሳይ ጥያቄዎች ቢነሱባቸው መፍትሄ መስጠት የሚያስችል ልዩ ክህሎት ማዳበራቸውን ማንም በእርግጠኝነት መናገር አይችልም፡፡ ነገር ግን ካለፉ ስህተቶቻቸው መልካምና ገንቢ ትምህርት ቀስመው ይሆናል ብሎ መገመት ግን ይቻላል፡፡ የሆኖ ሆኖ ጉዳዩ ከፈተናዎቻቸው አንዱ ሆኖ መዝለቁ አይቀሬ ነው፡፡ እጅግ በርካታ የሀገር ውስጥና የውጭ ታዛቢዎች፤ ለአቶ ሃይለማርያም ከሁሉም ይልቅ ታላቅ ፈተና ይሆንባቸዋል የሚሉት የጦር ሀይሉ ጉዳይ ነው፡፡ እነዚህ ታዛቢዎች፤ አቶ ሃይለማርያም የቱንም ያህል የመሪነት ችሎታ ቢኖራቸው፣ የህወሓት የበላይነትና ቁጥጥር ያየለበት ነው እየተባለ የሚታማውን የጦር ሀይሉን ልክ እንደ አቶ መለስ በሚገባ መቆጣጠርና ማዘዝ አይችሉም በሚል ይከራከራሉ፡፡

እንደ እውነቱ ከሆነ ሟቹ ጠቅላይ ሚኒስትር የህወሓትና የኢህአዴግ ሊቀመንበርነታቸውና ታጋይነታቸው ከህወሓትና ኢህአዴግ ታጋይነት ወደ ጦሩ ከተቀላቀሉት ተራ ወታደሮችና ከፍተኛ አመራሮች ጋር ለበርካታ ዘመናት የዘለቀ ጥብቅ ግንኙነት ለመመስረት አስችሏቸዋል፡፡

በጦር ሀይሉ ዋና አዛዥነታቸው ወቅትም የቀጠለው የበፊቱ ግንኙነት እንጂ ምንም አዲስ ነገር አልነበረም፡፡

የቀድሞ የህወሓትና የኢህአዴግ ታጋይ ለነበሩት ወታደሮችና ከፍተኛ መኮንኖች የጦር ሃይሎች ጠቅላይ አዛዥ የሆኑት ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ፤ ያው ድሮም በደንብ ያውቋቸውና ይመሯቸው የነበሩት የትግል ጓዳቸው መለስ ናቸው፡፡

ይሁን እንጂ ይህ ልዩና ታሪካዊ ግንኙነታቸው በጦር ሀይሉ ጠቅላይ አዛዥነታቸው በህግ ተገድቦ ከተሠጣቸው ስልጣንና ሃላፊነት በላይ የሆነ ድርጊት እንዲፈጽሙ የሚያስችላቸው መቼም ጊዜ የማይጠፋ አረንጔዴ መብራት አልነበረም፡፡

አቶ ሀይለማርያም ደሳለኝ፤ በፀረ ደርግ የትጥቅ ትግል ያልተካፈሉ የመጀመሪያው የኢህአዴግ ምክትል ሊቀመንበር ናቸው፡፡ እናም ድሮ ታጋይ ከነበሩት ወታደሮችና ከፍተኛ መኮንኖች ጋር መለስ እንደነበራቸው አይነት በልዩ የበረሃ ጓዳዊነትና የስነልቡና ገመድ የተቆራኘ ግንኙነት ሊኖራቸው ይገባል ብሎ መከራከር ጨርሶ የሚያዋጣ ሙግት አይደለም፡፡ ምክንያቱም በቃ አይችሉማ፡፡

የሆኖ ሆኖ የሀገሪቱን የጦር ሃይልና የዋና አዛዡን የጠቅላይ ሚኒስትሩን ግንኙነት ካነሳን የምናወራው፣ ስለ ህገመንግስታዊው ስርአት መሆኑን መዘንጋት አይገባም፡፡ እናም አዲሱ ጠቅላይ ሚኒስትር ሆነው ከተመረጡ፣ በአቶ ሃይለማርያም ደሳለኝና በዋና አዛዥነት በሚመሩት የሀገሪቱ ጦር ሃይል መካከል ያለው ግንኙነት የመጀመሪያም ሆነ የመጨረሻ መሠረቱ ህገመንግስቱ ብቻ ነው፡፡

በሀገሪቱ ህገመንግስት በተደነገገው መሠረት፤ የጦር ሀይሉ ታማኝነቱ ለህገመንግስታዊው ስርአት ብቻ ስለሆነ ጠቅላይ አዛዡ የሆኑትን የጠቅላይ ሚኒስትሩን ህጋዊ አመራር የማይቀበልበት ምክንያትም አይኖርም፡፡

ይልቁንስ ከዚህ ይልቅ ሊያከራክር የሚችለው አቶ ኃይለማርያም ደሳለኝ አዲሱ ጠቅላይ ሚኒስትር ሆነው ከተመረጡ ለክፉም ሆነ ለበጐ ቀን ብርሃን የሚሆን የጦር ሀይል አመራር ብቃት አላቸው ወይ የሚለው ነው፡፡ ልብ አድርጉ፡፡ አሁን ለአዲሶቹ የኢህአዴግ አመራሮች የመሪነትና የአመራር ችሎታ ዋናው መስፈሪያ አቶ መለስ ዜናዊ ናቸው፡፡ አቶ መለስ ትተውት በሄዱት ጫማ ልክ መሆን አለመሆናቸውን የሚያረጋግጥልን መጪው ጊዜ ብቻ ነው፡፡ ነገርዬው ዋነኛ መፈተኛቸው መሆኑ ግን እርግጥ ነው፡፡

ሌላ አንድ ትልቅ ተግዳሮት ደግሞ አለ፡፡ እርሱም ፍትሐዊ እድገትን ማስቀጠልና ሙስናን መዋጋት ነው፡፡ አቶ ሃይለማርያም ደሳለኝ እንደ ኢህአዴግ ከፍተኛ አመራርነታቸው ያለባቸው አንድ ችግር “የማይሰርቁ” መሆናቸው እንደሆን ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ በአንድ ወቅት ለየት ባለ አገላለጽ መስክረውላቸዋል፡፡

ከአርባ ምንጭ ውሃ ቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት እስከ ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ድረስ በቅርብ የሚያውቋቸው በርካታ ሰዎች አስረግጠው የሚናገሩላቸውም አቶ ሃይለማርያም በፈሪሃ እግዚአብሔር ግብረገብ የታነፁና ከሙስና የፀዱ ምግባረ መልካም ፖለቲከኛ መሆናቸውን ነው፡፡ ይህ እጅግ መልካም ነገር ነው፡፡ ይሁን እንጂ ይህ የእርሳቸው ብቻ የሆነ ነገር ነው፡፡ ዋነኛው ጥያቄ ድርጅታቸውንና አስተዳደራቸውን በድርጅታቸው ቋንቋ “ሙስናን የሚጠየፍ” ማድረግና በሀገሪቱ ውስጥ ፍትሐዊ እድገትን ማስቀጠል ይችላሉ ወይ የሚለው ነው፡፡ ለዚህም ጥያቄ ትክክለኛውን መልስ የሚሠጡን ቀጣዮቹ ጊዜያቶች ብቻ ናቸው፡፡

በዚህ ሁሉ መሀል ጨርሶ ልንዘነጋው የማይገባን አንድ እውነታ ግን አለ፡፡ ሟቹ ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ራሳቸውን መለስ ብቻ ናቸው፡፡ አዲሱ ጠቅላይ ሚኒስትር ሆነው ከተመረጡ አቶ ሃይለማርያም ደሳለኝም ራሳቸውን እንጂ አቶ መለስን አይደሉም፡፡ አይሆኑምም፡፡ ራሳቸውን እንጂ መለስን እንዲሆኑም አይጠበቅባቸውም፡፡ መለስን እንዲሆኑ መጠበቅ ተገቢም ጤነኛም አይደለም፡፡ ይህ ተገቢ ያልሆነ ግፊት ሰውየው መለስንም ራሳቸውንም ሳይሆኑ ኢትዮጵያውያኖች አዘውትረው እንደሚሉት “ከሁለት ያጣ ጐመን” ሆነው እንዲቀሩ ሊያደርጋቸው ይችላል፡፡ እንዲህ ከሆኑ ደግሞ የሀገርና የህዝብ መሪ ናቸውና ዳፋው የጋራችን ስለሆነ ከፍ ያለ ጉዳት ሊያስከትልብን ይችላል፡፡

በመጨረሻ ልናነሳው የሚገባን አንድ ጉዳይ የአለምአቀፉ ማህበረሰብ ጉዳይ ነው፡፡ ሟቹ ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ ለአለም አቀፉ ማህበረሰብ “መለስ ዜናዊ” ነበሩ፡፡ መለስ ድህነታችንና የአለም አቀፉን ማህበረሰብ እርዳታ ጠባቂነታችን የሚፈጥረውን ብሔራዊ ውርደትና ከፍተኛ ግፊት፣ በከፍተኛ ብልጠትና ሆደ ሰፊነት ተሸክመው በመታገል የሀገራችን ስም እንዲልቅና እንዲከበር ለማድረግ ችለዋል፡፡ መለስ የነበራቸው ከፍተኛ የእውቀትና የአመራር ብቃት ሀገሪቱ የአለም አቀፉን ማህበረሰብ ከፍተኛ ተጽእኖ እንድትቋቋም በእጅጉ ረድቷታል፡፡

ከፍተኛ ችሎታቸውንና ብቃታቸውን የአለም አቀፉ ማህበረሰብ በገዛ አንደበቱ ተራ በተራ የመሠከረላቸው መለስ፤ አሁን በመድረኩ የሉም፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትር ሆነው መመረጥ ከቻሉ አሁን ጊዜው የአዲሱ ተተኪ የአቶ ሃይለማርያም ነው፡፡ የአለም አቀፉ ማህበረሰብም ከአሁን በኋላ የሚቆመው በአዲስ የኢትዮጵያ መሪ ፊት ነው፡፡

አቶ ኃይለማርያም የዚህን ሃይል ተጽእኖና ግፊት መቋቋም መቻልና አለመቻላቸውን አሁን ላይ ሆኖ ማንም እርግጠኛ መልስ መስጠት አይችልም፡፡

እንደ ሌሎቹ ተግዳሮቶቻቸው ሁሉ ለዚህም ጥያቄ እርግጠኛውን መልስ መስጠት የሚችለው ጊዜ ብቻ ነው፡፡ ጉዳዩ ከዋና ዋና መፈተኛዎቻቸው አንዱ ለመሆኑ ግን አሌ የሚባል አይደለም፡፡ አዲሱ ዓመት የሰላም፣ የጤናና የብልፅግና ይሁንልን፡፡ ብሩህ ዘመን ለኢትዮጵያና ለህዝቦቿ!!

 

 

 

Read 44710 times Last modified on Monday, 10 September 2012 13:56