Print this page
Monday, 27 September 2021 14:18

ሌላው ሁሉ ትርፍ ነው

Written by  ኤፍሬም እንዳለ
Rate this item
(3 votes)

 እንኳን ለብርሀነ መስቀሉ አደረሳችሁ!
አንዴት ሰነበታችሁሳ!
‘ኒው ይር’ እንዴት ይዟችኋል? በነገራችን ላይ ከተማችን ቦግ ቦግ እያለች ነው መሰለኝ! ብቻ አንዳንድ ቦታ ላይ በነጭ ሱሪ ላይ ቀይ ጨርቅ እንደ መጣፍ እንዳይሆን በብስለት ይሠራ! በቀደም በበርካታ ባለሙያዎች እንደተተቸው እንደ ኪዳኔ ህንጻ አይነት ነገሮች እንዳይፈጠሩ ለማለት ያህል ነው፡፡ የምር ግን… አለ አይደል…እንዲህ በአንድ ሺህ አንድ ችግሮች በተከበብንበት ጊዜ፣ መልካም ነገሮች በማየት ለአፍታም ዘና ማለቱ ቀለል አይደለም፡፡  
ምስኪን ሀበሻ፡– አንድዬ
አንድዬ፡– ምስኪኑ ሀበሻ፣ እንዴት ከረምክ?
ምስኪን ሀበሻ፡– አንድዬ ዛሬ በጣም፣ በጣም ነው ያስደሰትከኝ፡፡ በዚች ሰዓት አንዴት ሁለመናዬን ደስ እንዳለኝ አልነግርህም፡፡
አንድዬ፡– እንኳን ነገርከኝ፣ አላወቅሁም ነበር እኮ! ለካስ ሌላ ጊዜ እኔ ዘንድ ስትመጣ ደስ እያለህ አልነበረም!
ምስኪን ሀበሻ፡– አንድዬ፣ ኸረ እንደሱ ማለቴ አይደለም፡፡ ለማለት የፈለግሁት በአንድ ጊዜ ስታውቀኝ ደስታ ሰውነቴን ውርር ነው ያደረገኝ፡፡
አንድዬ፡– ስማ ምስኪኑ ሀበሻ፣ አይደለም እዚህ ድረስ እስከትመጣ ገና ለመምጣት ስታስብ ነው የማውቅብህ፡፡ ችግራችሁ ምን እንደሆነ ልንገርህ?
ምስኪን ሀበሻ፡– ንገረኝ፣ አንድዬ፡፡
አንድዬ፡– እኔን ተወኝ፣  ብዙ ጊዜ አጠገባችሁ ያለው ሰው ሁሉ ምንም የማያውቅ እየመሰላችሁ ሳይ ይገርመኛል። ስማ፣ ሰው እኮ አፍ አውጥቶ ስላልተናገረ እንጂ ብዙ ነገር ያውቃል፡፡
ምስኪን ሀበሻ፡– አንድዬ፣ ምን እናድርግ! ትንሹንም ትልቁንም ምስጢር የማድረግ ጋኔን ሰፍሮብን ምን እናድርግ፡፡
አንድዬ፡– አንተ! አንተ! ብለህ፣ ብለህ ከእነ ጋኔንህ ነው እንዴ እኔ ዘንድ የመጣኸው!
ምስኪን ሀበሻ፡– ኸረ በጭራሽ አንድዬ! ኸረ በጭራሽ!
አንድዬ፡– እና ስንት ጊዜ ስትመላለስ ኖረህ!…እስከ ዛሬ አላውቅህም ነበር ማለት ነው? ነው ወይስ ከሌላ ሰው ጋር ነው ስነታረክ የከረምኩት!
ምስኪን ሀበሻ፡– አንድዬ! ኸረ እንደእሱ ማለቴ አይደለም! ምን ለማለት ፈልጌ መሰለህ…
አንድዬ፡– እየው እንግዲህ...አንተ ሰው ግን አንድ ነገር በተናገርኩ ቁጥር በድንጋጤ መርበትብት አትተውም ማለት ነው?
ምስኪን ሀበሻ፡– የተቆጣህ እየመሰለኝ ነው እኮ አንድዬ፡፡ አንተ ተቆጥተኸን የት አባታችን እንገባለን!
አንድዬ፡– እየው እንግዲህ በትንሽ ትልቁ ማማረርህን ልትጀምረኝ ነው፡፡ ይልቅ መጀመሪያ የጠየቅሁህን አልመለስክልኝም። ምስኪን ሀበሻ፡– አንድዬ፣ ም..ምን ጠየቅኸኝ?
አንድዬ፡– ደህና ከረምክ ወይ ብዬህ ነበር።
ምስኪን ሀበሻ፡– ደህና ነኝ አንድዬ፣ ደህና ነኝ፡፡ አንተ እያለኸኝ ምንስ እሆናለሁ ብለህ ነው፡፡
አንድዬ፡– ጎሽ፣ ምስኪኑ ሀበሻ፣ በአዲሱ ዓመት አዲስ ዘዴ ይዘህልኝ መጣህ!
ምስኪን ሀበሻ፡– አንድዬ… አጠፋሁ እንዴ!
አንድዬ፡– ይሄን ነገራችሁን መቼ እንደምትተዉ ነው ግራ የሚገባኝ! ለምንድነው ሁሉን ነገር ዙሪያውን የምትጠመጥሙት! አሁን አጠፋህ የሚል ቃል ከአንደበቴ ወጣ?
ምስኪን ሀበሻ፡– ይቅርታ አንድዬ፣ ይቅርታ፡፡
አንድዬ፡– አንተ እያለኸኝ ምንስ እሆናለሁ ብለህ ነው አይደል ያልከኝ?
ምስኪን ሀበሻ፡– አዎ አንድዬ፣ ሁሉንም ነገራችንን በአንተ ላይ እኮ ነው የጣልነው፡፡
 አንድዬ፡– ስማኝ እንጂ ምስኪኑ ሀበሻ…እኔ የእናንተ ሁሉንም ነገር መጣያ ነኝ እንዴ!
ምስኪን ሀበሻ፡– አንድዬ፣ እንደሱ ለማለት ፈልጌ እኮ አይደለም!… አንተ እንደሱ ስትለኝ  እኮ ሁለመናዬ ነው የሚረበሸው፡፡
አንድዬ፡– እሺ በቃ ተውኩት፣ ወይስ ሂሴን ተቀብያለሁ ልበል?
ምስኪን ሀበሻ፡– አንድዬ!
አንድዬ፡– ይልቅ ስማኝ… በፊት እኮ ሂሴን ውጫለሁ የምትሏት ነገር ነበረቻችሁ፡፡ አሁን፣ አሁን ግን ስትሏት አልሰማችሁም። ሆዳችሁ ሞልቶ ነው ወይስ የሚዋጥ ሂስ አልቆባችሁ ነው?
ምስኪን ሀበሻ፡– አንድዬ ምን ያልቅብናል!  መጀመሪያ ነገር የተሳሳተነውን ነገር ስናምን አይደል! ደግሞ ብናምንም እንኳን የዘንድሮው ሂስ  በእኛ አቅም የሚዋጥ አይደለም፡፡
አንድዬ፡– ቆይ ሌላ ነገር ውስጥ ሳንገባ አዲሱን ዓመት እንዴት ተቀበልከው? ብቻ በጉ፣ ዶሮው ዋጋው ናላችንን አዞረው፣ ጨጓራችንን አበገነው ምናምን እንዳትለኝ! መስማት የሰለቸኝ ነገር ቢኖር፣ የእናንተን የኑሮ ተወደደ አቤቱታችሁን  ነው፡፡ ነው ምድር ወርጄ መጋዘኑን ሁሉ እያስከፈትኩ ልፈትሽ?
ምስኪን ሀበሻ፡– አንድዬ፣ እኛም እኮ አንተን የምንጨቀጭቀው የምድር መፍትሄ ስላጣን ነው፡፡
አንድዬ፡– መፍትሄውን እስክታገኙ ሞክሩ፡፡ ይልቅ ዓመቱን እንዴት ተቀበልከው?
ምስኪን ሀበሻ፡– አንድዬ እንደ ጊዜው ለመቀበል ሞክሪያለሁ፡፡ ብቻ አልዋሽህም ሙሉ ለሙሉ ዘና ብያለሁ አልልም፡፡
አንድዬ፡– እንዴት ዘና ትላለህ! እንዴት ዘና ትላላችሁ! ስለ በግና ዶሮ ስታማርሩ ምኑን ዘና አላችሁት! እናንተ እኮ ከዘመን ዘመን በመሸጋገራችሁ ብቻ ደስ ሊላችሁ ሲገባ፣ ዱለት ስለቀረባችሁ የምታማርሩ ናችሁ፡፡
ምስኪን  ሀበሻ፡– አንድዬ፣ አንድዬ…
አንድዬ፡– ምስኪን ሀበሻ፣ እያሳቅህብኝ ነው እንዴ?
ምስኪን ሀበሻ፡– ኸረ አንድዬ፣ በጭራሽ! ምን..
አንድዬ፡– ስቀልድ ነው፤ እኔ መቀለድ አይፈቀድልኝም እንዴ! እንደው ቀንም ሌትም ኮስተር ብዬ የማሳልፍ ይመስላችኋል!
ምስኪን ሀበሻ፡– እንደሱ ሳይሆን..
አንድዬ፡– ስማ ምስኪን ሀበሻ፣ አንዳንዴ ሳስበው የአንድ ሰሞን ነገራችሁን አሁንም የተዋችሁ አይመስለኝም፡፡
ምስኪን ሀበሻ፡– ምን አንድዬ?
አንድዬ፡– እኔን እኮ ከጨዋታ ውጪ አድርጋችሁኝ ነበር፡፡
ምስኪን ሀበሻ፡– አንድ…
አንድዬ፡– ቆይ፣ አስጨርሰኝ፡፡ ሰው “እንኳን አደረሰህ!” ሲላችሁ... “የምን እንኳን አደረሰህ ነው፡፡ የደረስከው አንተ በራስህ ስለሆነ “እንኳን ደረስህ ነው የሚባለው...” ስትባባሉ አልነበር!
ምስኪን ሀበሻ፡– አንድዬ፣ እሱን እኮ እኛ አይደለንም…
አንድዬ፡– እናንተ ካልሆናችሁ ታዲያ ማን ነው?
ምስኪን ሀበሻ፡– እንደእሱ ይሉ የነበሩት እኮ ኮሚኒስቶቹ ነበሩ፡፡ እኛ የለንበትም፡፡
አንድዬ፡– ጎሽ ምስኪን ሀበሻ በአዲስ ዓመት አዲስ ጨዋታ ይዘህልኝ መጣህ፡፡ ኮሚኒስቶቹ ከሌላ ዓለም የመጡ ፍጡራን ናቸው እንዴ!
ምስኪን ሀበሻ፡– እንደሱ ሳይሆን…
አንድዬ፡– ምስኪን ሀበሻ፣ ኮሚኒስቶቹም፣ ምኖቹም እኮ እናንተው ናችሁ፡፡ እንደው ብቻ በሌላ ላይ ማላከክ ደስ ይላችኋል። ቆይ ከአንተ ቤተሰብ ውስጥ ኮሚኒስት ከምትላቸው ውስጥ የነበረ አልነበረም?
ምስኪን ሀበሻ፡– እሱማ አንድዬ ታላቅ ወንድሜ የለየለት ኮሚኒስት ነበር፡፡
አንድዬ፡– የለየለትና ያልለየለት ኮሚኒስት አለ እንዴ!
ምስኪን ሀበሻ፡– አንድዬ፣ የለየለት ማለት ወንበር እንኳን ቀይ ካልሆነ አይቀመጥም፡፡
አንድዬ፡– ምስኪን ሀበሻ፤ ዛሬ ገና ከልቤ አሳቅኸኝ! ግን እስካሁን ስናወራ ቆይተን ምን እንደታየኝ ልንገርህ?
ምስኪን ሀበሻ፡– ንገረኝ አንድዬ፡፡
አንድዬ፡– አንድም ቁም ነገር ሳናወራ እንዲሁ ስታስቀባጥረኝ ነው ጊዜውን የጨረስነው፡፡
ምስኪን ሀበሻ፡– አንድዬ፣ ያው የበዓል ሰሞን አይደል...
አንድዬ፡– እውነት ብለሀል፡፡ በነገራችን ላይ እዚህ በመድረሳችሁ ብቻ ደስ ሊላችሁ ይገባል፡፡ ሌላው ሁሉ ትርፍ ነው፡፡ በል መልካም በዓል፡፡ በሰላም ግባ፡፡
ምስኪን ሀበሻ፡– አሜን አንድዬ፣ አሜን!
ደህና ሰንብቱልኝማ!

Read 1837 times