Saturday, 25 September 2021 00:00

የፀጥታ ስጋት ያጠላበት ቀጣይ ምርጫ

Written by 
Rate this item
(0 votes)

• በፀጥታ ስጋት ሳቢያ የመስከረም 20 ምርጫ፣ በ3 ክልሎች ውስጥ በሚገኙ 32 ምርጫ ክልሎች አይካሄድም
       • በሱማሌ ክልል ለምርጫ ከሚወዳደሩ 4 ፓርቲዎች 3ቱ ራሳቸውን አግልለዋል
                          በፀጥታ ችግር፣ በመራጮች ምዝገባ ወቅት በታዩ ግድፈቶችና በቀረቡ አቤቱታዎች ምክንያት  ሰኔ 14 ቀን 2013 ዓ.ም 6ኛው አገር አቀፍ ምርጫ ባልተካሄደባቸው  አካባቢዎች፣ መስከረም 20 ቀን 2014 ዓ.ም ሊካሄድ የታቀደው  ቀጣይ ምርጫ፤ በፀጥታ ስጋት ሳቢያ በ3 ክልሎች ውስጥ በሚገኙ 32 የምርጫ ክልሎች ውስጥ አይካሄዱም፡፡
ከኢትዮጵያ ምርጫ ቦርድ የተገኘ መረጃ እንደሚያመለክተው፤ የመስከረም 20 ምርጫ በአማራ ክልል፣በኦሮሚያ ክልልና በቤኒሻንጉል ጉምዝ ክልል ውስጥ በሚገኙ 32 ከተሞች ውስጥ አይደረግም፣፡፡ እንደ ቦርዱ መረጃ ምርጫ በአማራ ክልል በማጀቴ፣በአርጎባ፣ሸዋሮቢት፣ ኤፌሲዮን፣በጭልጋ አንድና ጭልጋ ሁለት  በአንኮበርና በበላይ አርማጭሆ ምርጫ ክልሎች በፀጥታ ስጋት ሳቢያ የመስከረም 20 ቀን  አገር አቀፍ ምርጫ  አይከናወንም፡፡ ለዚህም በአካባቢው በተከሰተው የፀጥታ ችግር ሳቢያ የመራጮች ምዝገባ ለማካሄድ ባለማቻሉም እንደሆነ ተጠቅሷል፡፡ በኦሮሚያ ክልል ቤጊ፣ ሰኞ ገበያ፣አያና፣ገሊላ፣አሊቦ፣ጊዳሚና ኮምቦልቻ ምርጫ ክልሎች  ምርጫው አይከናውንም፡፡ በቤኒሻንጉል ጉምዝ ክልል በመተከል፣ሺናሻ ልዩና ካማሺ ምርጫ ክልሎች መስከረም 20 ቀን 2014 ዓ.ም ለህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ምርጫ ድምጽ የመስጠት ሂደት አይከናወንባቸውም፡፡
በመስከረም ምርጫ የማይካሄድባቸው አካባቢዎች ቀጣይ እጣ ፈንታ አለመወሰኑንም  የኢትዮጵያ ምርጫ ቦርድ የኮሚሽን አማካሪ ሶሊያና ሽመልስ ተናግረዋል፡፡
መስከረም 20ቀን 2014 ዓ.ም በሱማሌ፣በደቡብና በሐረሪ ክልሎች እንደሚከናወን የገለፁት አማካሪዋ፤ ከስድስተኛው አገራዊ ምርጫ በተጨማሪ በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ የሚካሄደው ህዝበ ውሳኔም በዚሁ ቀን እንደሚከናወን ተናግረዋል፡፡ በ965 ምርጫ ጣቢያዎች ለሚከናወነው ህዝበ ውሳኔም 890 ሺ750 መራጮች ተመዝግበዋል ብለዋል፡፡ በሦስቱ ክልሎች ለሚካሄደው ምርጫም በአጠቃላይ ከ7.6 ሚሊዮን በላይ ህዝብ ተመዝግቧል ሲሉም ተናግረዋል፡፡
የሀረሪ ምርጫ ክልልን አስመልክቶ የክልሉ ተወላጆች በስፋት በሚኖሩባቸው አካባቢዎች ልዩ የምርጫ ጣቢያዎች እንዲቋቋሙ  በተጠየቀው መሰረት በአዲስ አበባ፣በድሬደዋና በኦሮሚያ 17 ልዩ የምርጫ ጣቢያዎች ተቋቁመዋል ብለዋል፡፡ በደቡብ ክልል ቁጫ ወረዳ ላይ ባለው የፀጥታ ችግር ሳቢያ ምርጫው መስከረም 20 እንደማይከናውን ተናግረዋል፡፡
በሱማሌ ክልል በሚካሄደው ምርጫ ተሳታፊ ከነበሩ አራት የፖለቲካ ፓርቲዎች መካከል  ሶስቱ ኢዜማ፣ የኦጋዴን ነፃነት ግንባር (አብንግ) እና የነፃነትና እኩልነት ፓርቲ ራሳቸውን ከምርጫው ማግለላቸውን አስታውቀዋል፡፡ ምርጫ ቦርድ  በበኩሉ፤ ከምርጫው ራሳችንን አግልለናል ካሉት ፓርቲዎች መካከል ስለ ጉዳዩ ለቦርዱ ያላሳወቁ መኖራቸውን ተልጿል፡፡
በክልሉ የሚወዳደሩት ሶስቱ ተፎካካሪ ፓርቲዎች፣ “የቦርዱ ምርጫ አስፈፃሚዎች በክልሉ አስተዳደር ጫና ስር ወድቀዋል፤ አጠቃላይ የምርጫው ሂደት ነፃና ፍትሃዊ አይደለም” በሚል ምክንያት ከምርጫው ራሳቸውን ያገለሉ መሆናቸውንም ገልፀዋል፡፡ በክልሉ የሱማሌ ክልል ብልፅና ፓርቲ ለምርጫ መቅረቡም ታውቋል፡፡
የምርጫ አስፈፃሚዎች የገለልተኝነት ችግር አለባቸው የሚል ቅሬታ ከሁሉም ተፎካካሪ ፓርቲዎች ሲነሳ መቆየቱን የገለፁት የምርጫ ቦርድ የኮሚኒኬሽን አማካሪዋ፤ ቦርዱ ሁሉም ተፎካካሪ ፓርቲዎች ተነጋግረውና ተስማምተው የሚያቀርቧቸውን ምርጫ አስፈፃሚዎች ለመቀበል ዝግጁ ቢሆኑም ፓርቲሪዎች ግን ይህንን ማድረግ አልቻሉም ብለዋል፡፡ ይህ ባልሆነበት ሁኔታ ቦርዱ የሚመድባቸው ምርጫ አስፈፃሚዎች የገለልተኝነት ችግር አለባቸው የሚል ጥያቄ ማንሳት ተገቢነት የለውም ሲሉም ተናግረዋል፡፡
መስከረም 20 ቀን 2014 ዓ.ም በሱማሌ በደቡብና በሀረሪ ክልሎች ለተወካዮች ምክር ቤት በ47 ለክልል ምክር ቤት፣ በ105 ምርጫ ክልሎች ምርጫው ይካሄዳል ተብሎ ይጠበቃል፡፡

Read 1217 times