Sunday, 26 September 2021 00:00

ኢትዮጵያን በፍቅር የሚያስተዋውቀው ታንዛንያዊ

Written by  ትዕግስቱ በለጠ
Rate this item
(0 votes)

”የጠ/ሚ ዐቢይ ደብዳቤ የሚያወራው ስለ ኢትዮጵያ ብቻ አይደለም”
                         
            ስዋሂሊ ኔሽን የተባለውን ቻናል ከሰሞኑ ማየት የጀመርኩት በቅርብ ወዳጄ ጥቆማ ነው፡፡ የቻናሉ ባለቤት ወይም አዘጋጅ ሚካ ቻቫላ ይባላል። ታንዛኒያዊ ወጣት ነው። አፍሪካዊ ወጣት ቢባል የሚመርጥ ይመስለኛል፡፡ ለአፍሪካ አንድነት፣ ፍቅርና ሰላም እንደሚሰራ ይናገራል፡፡ መናገርም ብቻ ሳይሆን በዩቲዩቡ ቻናሉ ላይ በተግባር የሚሰራው ይሄንኑ ነው፡፡ ቻናሉን አይታችሁ መፍረድ ትችላላችሁ፡፡ አፍሪካውያን እርስ በርስ በጥላቻ ከመተያየትና ከመገዳደል ይልቅ ለጋራ ጥቅም ሃብትና ዕውቀታቸውን በጋራ አስተባብረው መሥራት እንዳለባቸው ይሰብካል፡፡ አልተሳሳተም፡፡ አፍሪካውያን በብልሃትና በትጋት ራሳቸውን ከድህነትና ከእርዳታ ጠባቂነት ካላወጡ በቀር ፈተናቸው እየከበደ እንደሚመጣ እያየነው ነው፡፡ የገዛ አገራችንን በመረጥነው መንገድ ማስተዳደርና መምራት እንደማንችል ሁሉ እያስጠነቀቁን ነው፤ በማዕቀብና በብድር እያስፈራሩን፡፡ አሁንማ እነ አሜሪካ እንኳንስ መንግስትን የአገሩን ብቸኛ ባለቤት ህዝቡንም ጭምር ከምንም የቆጠሩት አይመስሉም፡፡ ወይም መሬት ላይ ያለውን እውነታ አልተረዱትማ ማለት ነው፤ አሊያም የሚደርሳቸው መረጃ የተሳሳተና የተዛባ ነው ማለት ነው፡፡ እውነቱን ቢያውቁት ኖሮ፣ ኢትዮጵያ ላይ ማዕቀብ ስለመጣል ከማሰባቸው በፊት በሁለቴ ያስቡበት ነበር፡፡ በፓርላማ በአሸባሪነት የተፈረጀና አጥፊ ቡድንን፣. በህዝብ ከተመረጠ ህጋዊ መንግስት ጋር እኩል አይመለከቱም ነበር፡፡
 ወደ ስዋሂሊ ኔሽን ልመልሳችሁ፡፡ ሚካ ቻቫላ፤ ለኢትዮጵያ ከፍተኛ ፍቅርና ክብር አለው። ኢትዮጵያን ከልቡ ይወዳታል ብዬ አምናለሁ፡፡ የአፍሪካ መሰረት መሆኗን ደጋግሞ ይናገራል፡፡ ኢትዮጵያ ሰላም ስትሆን አፍሪካም ሰላም ትሆናለች ይላል፤ ቃል በቃል፡፡ የነጻነት ቀንዲልነቷን ደጋግሞ ያነሳል። ኢትዮጵያውያን፤ ለሌሎች አገራት ሰላምና ነጻነት የተዋደቁ፣ መስዋዕትነት የከፈሉ፣ ነጻነት ወዳድ ጀግና  ህዝቦች ናቸው ብሎ ያምናል፡፡ አልተሳሳተም፡፡
የኢትዮጵያን መልካም ነገሮች ሁሉ ለዓለም ከማስተዋወቅ ወደ ኋላ አይልም። በቻናሉ ላይ አዳዲስ የወጡ የኢትዮጵያ ዜማዎችን ይለቃል፤ ቋንቋው በደንብ ባይገባውም አንድነትን የሚያቀነቅኑ አዳዲስ ዜማዎችን ያስተዋውቃል፤ስሜቱን ያንፀባርቃል። በቻናሉ ካቀረባቸው ዜማዎች መካከል  የእጅጋየሁ ሽባባው (ጂጂ)፣ የቴዲ አፍሮ፣ የራሄል ጌቱ፣ የሮፍናን፣ ዲሽታጊና ወዘተ ይጠቀሳሉ፡፡
ባለፉት ሁለት ዓመታት፣ በኮቪድ ሳቢያ፣ ብዙዎቹ የአፍሪካ አየር መንገዶች፣ በኪሳራ ሰራተኞቻቸውን መቀነሳቸውን በመግለጽ፣ የኢትዮጵያ አየር መንገድ ግን በተቃራኒው፣ በስኬት መዝለቁን የሚያስተዋውቅ ግሩም  ዘገባ ማቅረቡን አስተውያለሁ - በስዋሂሊ ኔሽን ቻናሉ። በቅርቡ ደግሞ በጋና ቴሌቪዥን ጣቢያ የቁንጅና ውድድር ላይ፣ ኢትዮጵያን ወክላ ያሸነፈችው ጋናዊት ተወዳዳሪን የተመለከተ ፕሮግራም ሰርቷል።
“ኮሪያውያን የኢትዮጵያውያንን መስዋዕትነት እንዲህ ነው የሚያስታውሱት” በሚል ርዕስ ከሥፍራው -ከደቡብ ኮሪያ የሰራው ቪዲዮ አስደማሚ ነው። ጠ/ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ ባለፈው ሳምንት ለአሜሪካው ፕሬዚዳንት ጆ ባይደን የፃፉት ግልፅ ደብዳቤም አላመለጠውም፡፡ ሃሳቡን በስፋት አንጸባርቆበታል፡፡ በመጠነኛ ቅኝቴ ሚካ ቻቫላ፤ ከየትኛውም የአፍሪካ አገራት በላይ በኢትዮጵያ ላይ የሚያጠነጥኑ፣ ኢትዮጵያን ለዓለም የሚያስተዋውቁ አያሌ ፕሮግራሞችን መስራቱን ታዝቤአለሁ፤  ብዙዎቹ ደግሞ ከአፍሪካ አንድነት፣ ፍቅርና  ሰላም አንጻር የተቃኙ ናቸው።
ኢትዮጵያ በሰሜኑ የአገሪቱ ክፍል  ከተከሰተው ጦርነት ጋር ተያይዞ፣ ዓለማቀፍ ሚዲያ ስለ አገሪቱ የተዛባ ፕሮፓጋንዳ፣ ገፅታዋን የሚያጠለሽ መረጃ በማሰራጨት ተጠምዶ ባለበት ወቅት፣ ኢትዮጵያን በበጎ እያነሰ በአፍሪካ ያላትን ታሪካዊ ቦታ የሚያጎላ፣ የሚያስተዋውቅ ቻናል ማግኘት እንደ ብርቅ የሚታይ ነው፡፡ ትውውቁ በእንግሊዝኛ ቋንቋ መቅረቡ ደግሞ ዓለማቀፉ ማህበረሰብ ጋር እንዲደርስ የላቀ አስተዋጽኦ ያበረክታል፡፡ ሌላ ጊዜ ቢሆን ምናልባት ለራሴ ብቻ አይቼ የማልፈው ቻናል ይሆን ነበር፡፡ ዛሬ ግን በጥቂቱም ቢሆን ልዳስሰው ላስተዋውቀው ወደድኩ፡፡ በእጅጉ ያስፈልገናል፡፡ በመጀመሪያ ከ10 ቀን በፊት የለቀቀውንና  “ኮሪያውያን የህይወት መስዋዕትነት የከፈሉ ኢትዮጵያውያን ወታደሮች እንዴት እንደሚያስታውሱ ተመልከቱ” በሚል የሰራውን ቪዲዮ በአጭሩ ላስቃኛችሁ፡፡ “Welcome to Chuncheon” (እንኳን ወደ ቹንቾን በደህና መጣችሁ) ሲል ይጀምራል- በቪዲዮ ቻናሉ። ሚካ፤ ከ145 ሺ በላይ ለሚሆኑ የቻናሉ ተከታዮች የሚያስተዋውቀው፣ በኮሪያ ጦርነት ወቅት፣ ዘምተው መስዋዕትነት ለከፈሉ የኢትዮጵያ ጀግና ወታደሮች በቹንቾን ከተማ የቆመላቸውን ድንቅ የመታሰቢያ ሃውልት ነው። ጊዜው እንደሚታወቀው፣ በንጉሱ የቀዳማዊ ኃይለስላሴ ዘመን ሲሆን  በተባበሩት መንግስታት የሰላም አስከባሪ ቡድን በኩል ነው ወደ ኮሪያ የዘመቱት። የሰላም አስከባሪው ቡድን ቃኘው በሚል ይታወቃል፡፡
 በአማርኛ፣ እንግሊዝኛና ኮርያ ቋንቋ “ኢትዮጵያ” የሚል ፅሁፍ የተቀረፀበት ረዥም አስደማሚ ሃውልት ፊት ለፊት ቆሞ ሚካ እንዲህ ይናገራል፡- “በእንዲህ ያለ አጋጣሚ አፍሪካዊ መሆን ያኮራል።  በእጅጉ ያኮራል። … ኢትዮጵያዊ ብሆንማ ምን ሊሰማኝ እንደሚችል አላውቅም---አስቡት  የአገሬ ስም እንዲህ ተፅፎ ስመለከት … ኢትዮጵያዊ ብሆን … ከፍተኛ ኩራት ነበር የሚሰማኝ፡፡ አሁንም ግን …  አፍሪካዊ ነኝ… ኢትዮጵያ ደግሞ አፍሪካዊ ናት። እንደዚህ ያለው አጋጣሚ በምንም ሊተመን የማይችል ነው፡፡ --- አንዳንዴ ከማድነቅ ይልቅ ማማረር ይቀላል። እዚህ የምታዩት ነገር… ኢትዮጵያ- (አፍሪካ-) ለሰራችው ነገር የቆመላትን መታሰቢያ ነው…”
ሚካ ቅኝቱን ቀጥሏል። በኮሪያኛ፣ አማርኛና እንግሊዝኛ ቋንቋዎች፣ በእምነበረድ ላይ የተቀረፀ  ፅሁፍ እያሳየ ነው። “መታሰቢያ- በኮሪያ ጦርነት ጊዜ ለነጻነትና ለዓለም ሰላም በዚህ ስፍራ በጀግንነት ለተዋጉ የኢትዮጵያ ወታደሮች የቆመ” ይላል ጽሁፉ።
ሚካ የእንግሊዝኛውን ጽሁፍ ካነበበልን በኋላ `peace` የሚለው ቃል ላይ በማተኮር ስለ ኢትዮጵያና ኢትዮጵያውያን ሃሳቡን ያንፀባርቃል፡- “ወገኖቼ… ሰላም ሁልጊዜ  በቻናላችን የምናወራው ጉዳይ ነው። ይሄ… ኢትዮጵያውያን ሌሎች አገራት ሰላምና ነፃነታቸውን እንዲቀዳጁ ምን ያህል መስዋዕትነት እንደከፈሉ የሚያሳይ ነው (ሀውልቱን ማለቱ ነው)። አሁን ልናደርገው የምንችለው ትልቁ ነገር፣ ለኢትዮጵያ  ሰላም መጸለይ ነው፤ ምክንያቱም ኢትዮጵያውያን በአፍሪካ የቅኝት ግዛት ዘመንም ሆነ በተለያዩ ጦርነቶች ለበርካታ አገራት ብዙ አስተዋፅኦና ድጋፍ አድርገዋል። አሁን አፍሪካውያን ልናደርገው የምንችለው ነገር ቢኖር፣ ለሰላም መፀለይ ነው…” ይላል፤ መላ አፍሪካውያን፣ ለኢትዮጵያም ሆነ ለቀረው አፍሪካ  የሰላም ጉዳይ፣ ትኩረት መስጠት እንዳለባቸው ሲያሳስብ፡፡
ሚካ ቻቫላ ፤የኢትዮጵያና የደቡብ ኮሪያ ባንዲራዎች እጅግ ረዥም ዘንግ ላይ በኩራት ተሰቅለው ወደ ሚውለበለቡበት ስፍራ በማምራት ሃሳቡን ያንጸባርቃል፤ በስሜትና መነቃቃት ተሞልቶ።
“ብዙ ኢትዮጵያውያን ወደዚህ ሥፍራ መምጣት እንደምትሹ አውቃለሁ… ምናልባት አትችሉም ይሆናል… ግን እኔ እናንተን ወክዬ እዚህ ተገኝቼአለሁ… እናም ልትኮሩ ይገባል…ምንም እንኳን በተለያዩ ምክንያቶች መምጣት ባትችሉም…  አሁን ይህን ቪዲዮ ማየትና  ያለውን እውነታ መረዳት ችላችኋል። በአንድ መልኩ በዚህ ቅጽበት፣ እዚህ እኔ ያለሁበት ስፍራ እንዳላችሁ ልትቆጥሩት ትችላላችሁ፡፡ ዛሬ አዲሱን ዓመት 2014 እያከበራችሁ ባላችሁበት  ዕለት፣ መልካም አዲስ ዓመት ይሆንላችሁ ዘንድ ምኞቴን እገልጻለሁ፡፡ ለሌሎች አገራት ሰላም፣ ፍቅርና ነጻነት እንደተዋደቃችሁት ሁሉ፣ እናንተም  ይሄንኑ እንድትቀዳጁ እፀልይላችኋለሁ- ለአገራችሁም ለአፍሪካም!!”
ታንዛንያዊው የፓን አፍሪካኒዝም አቀንቃኝ፣ አሁንም ጉብኝቱን አልጨረሰም። በነገራችን ላይ የኮሪያ ቅኝቱን ያደረገው የአዲስ ዓመት ዕለት ነበር- መስከረም 1 ቀን 2014 ዓ.ም።
በመቀጠል በኢትዮጵያ ስም የተሰየመውን ጎዳና ያሳየናል- “የኢትዮጵያ ጎዳና” ይላል። ከዚያም ወደ “ኢትዮጵያ ቤት” (Ethiopian House) ይወስደናል። ተዓምር ነው። ከውጭ ትልቅ የአንበሳ ምስል ይታያል፡፡ ብሄራዊ ቴአትር ጋ ያለውን አንበሳ ይመስላል። መግቢያው በር ላይ “ከ1968 አንስቶ” ይላል። ወደ ውስጥ ስትዘልቁ ፊት ለፊት የምትፋጠጡት  ከቀዳማዊ ኃይለስላሴ ግዙፍ ምስል ጋር ነው፤ ከእነ ግርማ ሞገሱ፡፡ በዚህ ቤት ውስጥ የኢትዮጵያውያን የተባለ ነገር ሁሉ የሚታይበት ነው፡፡ የባህል ሙዚየም በሉት፡፡ ሚካ ቻቫ፤ ከኢትዮጵያን ቤት ሃላፊ ጋር ጥቂት ቆይታ አድርጓል። በዚህ ቃለ-መጠይቅ፤ ሃላፊው በመጪው የመስቀል በዓል፣ በዚህ ቤት ውስጥ ልዩ የመስቀል ዝግጅት እንደሚኖራቸው ገልፆለታል። ከሁሉም በላይ ስሜት የሚነካው ግን ሃላፊው ከ50 ዓመት በፊት በኮሪያ ጦርነት ለተዋደቁ የኢትዮጵያ ጀግና ወታደሮች፣ በጥልቅ ስሜት ውስጥ ሆኖ ያቀረበው ምስጋና ነው። “በኮሪያ ጦርነት ወቅት ጦራችሁን (ወንድማችሁን፣ አባታችሁን፣ አያቶቻችሁን”) ልካችሁ ዋጋ ከፍላችሁልናል። እናመሰግናለን! ውለታውን መቼም አንረሳውም! አመሰግናለሁ!” ይላል፤ ኮሪያዊው  ሲቃ እየተናነቀው። በእርግጥም ከዚህች አገር መፈጠር ያኮራል፡፡ አፍሪካዊነትም  በእጅጉ ያኮራል- ሚካ ቻቫላ ደጋግሞ እንደሚለው።
ታንዛንያው የፓን አፍሪካኒዝም አቀንቃኝ፤ ከጥቂት ቀናት በፊት ደግሞ ጠ/ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ፣ ለአሜሪካው ፕሬዚዳንት ጆ ባይደን በጻፉት ግልጽ ደብዳቤ ላይ ሃሳቡን በስፋት አንፀባርቋል- በስዋሂሊ ኔሽን ቻናሉ። እንደተለመደው በደብዳቤው ላይ ሃሳቡን  ለማንጸባረቅ የተነሳበትን ምክንያት ሲገልጽ፤ ስለ አፍሪካ ብዙ ስለሚያወራ ነው ይላል፡፡ በመግቢያ ንግግሩ ላይ እንደሚያሳስበው፤ ለማንም ለመወገን አይደለም…. ይህን ፕሮግራም የሰራው። “…የኢትዮጵያ ጠ/ሚኒስትር ቀንደኛ ደጋፊ ልትሆኑም ላትሆኑም ትችላላችሁ፤ የእኔ ትኩረት ግን እሱ አይደለም፤ የእኔ ትኩረት  አፍሪካ ናት” ይላል።
በዚህ ቪዲዮ ጠ/ሚኒስትር ዐቢይ አህመድን የማሞገስ ወይም የማወደስ ፍላጎት ወይም ዓላማ እንደሌለው በግልጽ ይናገራል - ሚካ ቻቫላ። ይህንንም እያለ ግን ጠ/ሚኒስትሩን ወይም ደብዳቤያቸውን አለማድነቅና አለማወደስ ግን አልተቻለውም፤ ይረታል።
ደብዳቤውን ከአምስት ጊዜ በላይ እንዳነበበው የሚናገረው ሚካ፤ በርካታ መረጃዎችን የያዘ በመሆኑ ጊዜያችሁን ወስዳችሁ በተደጋጋሚ ልታነቡት የሚገባ ደብዳቤ ነው ይላል። “የኢትዮጵያን ሙሉ ታሪክ በደብዳቤ መልክ” እንደ ማለት ነው ሲል ይገልፀዋል።
በጠ/ሚኒስትሩ ደብዳቤ ላይ አፍሪካ በተደጋጋሚ መጠቀሱም ትኩረቱን የሳበው ይመስላል። ለዚህም ነው የወደድኩት ያለውን፣ የመጨረሻውን የደብዳቤውን፣ ለቻናሉ ተከታዮቹ ደጋግሞ በአጽንኦት የሚያነበው።
“… ከብዙኃን ደህንነት ይልቅ ስልጣንን ያስቀደሙ ግለሰቦች ባቀናበሩት ሴራ ለመጣው የውጭ ግፊት ኢትዮጵያ አትንበረከክም፤ ኢትዮጵያዊ ማንነታችንና አፍሪካዊ ማንነታችን ይህ እንዲሆን አይፈቅድም። ቀደምት የአፍሪካ መንግስታት ላይ የደረሰው በደልና ግፍ በአሁኑ ወቅት በዚህች ምድር ላይ ሊደገም አይችልም። የአረንጓዴ ቢጫና ቀይ ቀለም ምድር የሆነች ነፃ አገር፣ ሌሎች በርካቶች በትግላቸው ነፃነታቸውን እንዲቀዳጁ ተምሳሌት የሆነች አገር ናት።
 አዲሱ የአሜሪካ መንግስት ወደ ስልጣን መምጣቱን ተከትሎ፣ እንደ ኢትዮጵያ ያሉ በማደግ ላይ የሚገኙ በተለይ የአፍሪካ አገሮች፣ የአሜሪካ መንግስት ከቀደመው በግለሰብ ተፅዕኖ ስር ከወደቀ የውጭ ግንኙነት ፖሊሲው ይላቀቃል የሚል ተስፋ ነበረን፡፡ ነገር ግን በተቃራኒው የአሜሪካ የውጭ ግንኙነት ፖሊሲ፣ እንደ ህውኃት ባሉ አሸባሪ ቡድኖች ጭምር ተፅዕኖ የሚያርፍበት ሆኗል።…
“የተለያዩ የአሜሪካ መንግስታት ያልተጠኑ ቅጽበታዊ ውሳኔዎችን በማሳለፍ በሌሎች አገሮች የውስጥ ጉዳይ ላይ ያደረጉት ጣልቃ ገብነት፣ መፍትሄ ከማምጣት ይልቅ ህዝቦችን ለባሰ ቀውስ ሲዳርግ ቆይቷል። ኢትዮጵያ ግን ለመሰል የውጭ ተጽዕኖ አትንበረከክም…”
ሚካ ቻቫላ ስለ ጠ/ሚኒስትሩ ግልጽ ደብዳቤ በሰጠው አስተያየት፤”ይሄ ደብዳቤ የሚያወራው ስለ ኢትዮጵያ ብቻ አይደለም፤ የሚያወራው ስለ አፍሪካም ጭምር  ነው፤ ስለዚህች አህጉር” ይላል፡፡ በጠቅላይ ሚኒስትሩ ደብዳቤ ላይ ሃሳቡን ለማንጸባረቅ በቁርጠኝነት ያነሳሳውም ስለ አፍሪካና አፍሪካውያን የሚያነሳ ስለሆነ ነው ብሏል- በትንታኔው። አሜሪካንን በመሰሉ ሃያላን መንግስታት ላይ አቋሙንና እውነቱን በድፍረት የሚናገር ማንም የለም፡፡ ለአፍሪካ ሰላምና ነጻነት ሽንጡን ገትሮ የሚቆምና  የሚከራከርም አይገኝም፡፡ የተገኘ ጊዜ ግን እሱ መከበር አለበት- ይላል ታንዛናዊው የፓን-አፍሪካኒዝም አቀንቃኝ።
በቅርቡ ህይወታቸው ያለፈውን የአገሩን የታንዛንያ የቀድሞ ፕሬዚዳንት በቁጭት ያስታውሳል፡፡ ለአፍሪካ ነጻነት ሽንጣቸውን ገትረው ሲከራከሩ፣ አፍሪካውያን ለማንም እጅ እንዳይሰጡና በራሳቸው እንዲቆሙ ሲያስተምሩና ሲተጉ ነው የኖሩት፡፡ ችግሩ ግን ማንም የተረዳቸው አልነበረም፡፡ አሁን ከሞቱ በኋላ ነው ሁሉም የተቆጨው ይላል፤ ደረቱን እየደቃ፡፡ ሚካ፤ቃል በቃል ባይናገረውም አሁንም፣ ኢትዮጵያውያንም ሆኑ አፍሪካውያን፣ ጠ/ሚኒስትሩ የያዙትን አቋም መደገፍና ከጎናቸው መቆም እንዳለባቸው ማሳሰቡ ነው - ከቁጭት ለመዳን፡፡
የምዕራብ መንግስታት በታዳጊ አገራት የውስጥ ጉዳይ ጣልቃ-መግባት ጥፋት እንጂ መፍትሄ አምጥቶ አያውቅም የሚለው ሚካ፤ የኦባማ አስተዳደር በሊቢያ ላይ ያደረሰውን መጠነ ሰፊ ምስቅልቅ  ይጠቅሳል። የኮንጎ ጦርነትም ቢሆን የእነሱ ሥራ ነው ይላል። “…በኮንጎ በርካታ ዓለማቀፍ ድርጅቶች አሉ። ግን ምንድነው የሚሰሩት? እርቅና ሰላም ያመጣሉ? ምንም ካልሰሩ ደግሞ ለምን  ከአገሪቱ አይወጡም” ሲል አበክሮ  ይጠይቃል። አሜሪካ አሁን በኢትዮጵያ ላይ የጣለችው ማዕቀብም ሆነ የሌሎች ምዕራባውያን ጫናን በቀላሉ ለመቋቋም መፍትሄው፣ የአፍሪካውያን መተባበርና በአንድነት መቆም ነው ይላል- ሚካ ቻቫላ። መቶ ፐርሰንት ትክክል ነው፡፡
በጣም የሚገርመው ነገር፣ ባለፉት ጥቂት ወራት፣ የኢትዮጵያ መንግስት፣ ታጣቂው የህወሃት ቡድን፣ ህፃናትንና እናቶችን በጦርነት እያሰለፈ እንደሆነ በመግለጽ ዓለማቀፉ ማህበረሰብ ድርጊቱን እንዲያወግዝ በተደጋጋሚ ቢወተውትም፣ ሰሚ ጆሮ ሳያገኝ ነው የቀረው፡፡ ሌላው ቀርቶ በአሁኑ የፕሬዚዳንት ባይደን የማዕቀብ ማስፈራሪያ ላይ እንኳን የአጥፊውን ቡድን የጅምላ ጭፍጨፋና የሰብአዊ ውድመት ሳያወግዝ ነው፣ እንደ ሰፈር ልጆች ጠብ፣ አንተም ተው፣ አንተም ተው ዓይነት  ትዕዛዝ ሊሰጥ የዳዳው፡፡
ሚካ ቻቫላ ስለ ጠ/ሚኒስትሩ ግልጽ ደብዳቤ ባንጸባረቀው ሃሳብ ላይ ግን “በጦርነቱ እየተሳተፉ ነው ስለተባሉት የትግራይ ህጻናትና እናቶች እንዲሰማኝ የግድ ኢትዮጵያዊ መሆን የለብኝም፤ ሰው መሆን ብቻ በቂ ነው” ሲል የተሰማውን ጥልቅ ሃዘን ይገልጻል፡፡ በመጨረሻም፤ አፍሪካውያን መንቃትና ለሰላም ለፍቅርና ለነፃነት  በጋራ መቆም እንዳለባቸው ያሳስባል፤ ”Africa must wake up” ይላል፡፡
ቀደም ብዬ እንደገለጽኩት፣ በዚህ ፈታኝ ወቅት፣ ኢትዮጵያን የሚያስተዋውቅና ከጎኗ የሚቆምላት፣ እውነቷንም የሚያስተጋባላት ትፈልጋለች፡፡ በተለይ ደግሞ  ከ145 ሺ ገደማ በላይ ተከታይ - subscriber  ያለው፣ ኢትዮጵያን የሚወድ፣ ለአንድ አፍሪካ የሚቆም --- እንደ ሚካ ቻቫላ ያለ አፍሪካዊ ሲገገኝ ዕድሉን መጠቀም ተገቢ ይመስለኛል። በዚህ ጦርነት ዋናው ድክመታችን ምን እንደሆነ አውቀነዋል፤ በዲፕሎማሲ ወይም ብዙ ሺ ዶላር በሚከፈልበት የህዝብ ግንኙነት ሥራ አጥፊውን ቡድን አልቻልነውም፡፡  
ከኢትዮጵያ ላይ በደህና ጊዜ የዘረፉትን ሃብት ለሎቢስቶችና ለፈረንጅ አክቲቪስቶች እየከፈሉ ሃሰተኛ መረጃና ትርክት ማሰራጨታቸውን ቀጥለውበታል፡፡
ኢትዮጵያ ደግሞ የዘረፈችው ሃብት ወይም ዶላር የላትም፡፡ ስለዚህ ለጊዜው ለሎቢስቶች የምትከፍለው ገንዘብ ላይኖራት ይችላል፡፡ ነገር ግን ሥራው መሰራት አለበት፡፡ እውነቱ ለዓለም መነገር ይገባዋል፡፡ ለዚህም ነው የተገኙ አጋጣሚዎችን በሙሉ መጠቀም ያለብን፡፡
ኢትዮጵያውያን ወገኖቼ፤ የማካ ቻቫላን ስዋሂሊ ኔሽን ቻናል ሰብስክራይብ በማድረግ ድጋፋችንን እንግለጽለት፡፡ አፍሪካዊ ወንድማማችነትን እናሳይ፡፡ መጪው ዘመን የአፍሪካውያን ነው!!

Read 8232 times