Tuesday, 28 September 2021 18:47

ምናባዊ ፍቅር

Written by  ህላዊ ተስፋዬ
Rate this item
(7 votes)

  ..ሦስት ቀን ሲቀረው....
በከፊል ሰመመንና በከፊል ንቃት ውስጥ ባለች መስመር ላይ ሰውነቴ ተንጠልጥላ ባፍንጫዬ የምትገባውን የትራስና ብርድልብስ መአዛ በማለዳ አጣጥማለሁ።
እንዲሁ በእንዲሁ ሰአት ሁሌም እንደማደርገው፣ አሁንም  አሁንም አስባለሁ። ከአልጋው ላይ የሚመጣው የሚሸተኝ ጠረን የፀጉሯ ቅባት ይሆን? ወይስ ሰውነቷን የምትቀባው ሽቶ? ወይስ.... ሌላ ሀሳብ ይከተላል... እዚህ አልጋ ላይ ስትተኛ እንዴት ሆና ነው? እንደዚህ በደረትዋ? ወይስ በጀርባዋ? ወይስ?..እገላበጣለሁ...እዚህ መሀል ላይ ይሆን የምተኛው? ወይስ ዳር ላይ? እንፏቀቃለሁ... ስንት ሰአት ትነቃ ነበር? እንደነቃች ምን ታደርግ ነበር? ማሰብ መዟዟር፣ እንደገና መገላበጥ፣ እንደገና ማሰብ።
ጊዜው የዛሬ ሁለት አመት ነበር፡፡ አክስቴ የምታሳድጋት የጓደኛዋ ልጅ መቅደስ፣ ክረምቱን ዘመዶችዋ ጋ ስለምትሄድ አክስቴ ብቻዋን እንዳትሆን በሚል ምክንያት ነው፣ እዚህ እሷ ዘንድ ክረምቱን ለማሳለፍ በእናቴ ተማፅኖ የመጣሁት።
በቀዝቃዛው ክረምት ከለመድኩት ግርግር ያለበት ሞቅ ያለ አካባቢ በተቃራኒው ሹክሹክታ እንኳን የሚጎላበት…፣ ፀጥ ያለ በዛፎች የተከበበ ፣ጠፈጠፉ የማያቋርጥበት፣ ከፊል ጭቃማ ሳር የወረረው፣ ኡኡኡ  ቢባል እንኳን ሰሚ ጎረቤት የራቀበት ሁሉ ነገሩ ያረጀ፣ ገና ሲያዩት ብርድ ብርድ የሚል ጨለማ፣ ድባቴያም ቦታ ላይ እንዴት ነው ሁለት ወር የሚያልፈው ነበር ጭንቀቴ። ከባድ ወንጀል እንደፈፀመ ፍርደኛ በግዞት ወደዚህ የተላኩ ነበር የመሰለኝ።
ወደ ውስጥ ስንገባ “መቅደስ ክረምቱን እዚህ ስለሌለች እሷ ክፍል ነው የምትቆየው” ተባልኩኝ። ከውጪው የቤቱ ገፅታ ጋር የማይገናኘው የውስጥ ክፍሏ ንፅህና እና ጠረን፣ የእቃዎቹ አቀማመጥ፣ የቀለም  ምርጫ መጀመሪያም ስቦኝ ነበር።
ውዬ ሳድር የተኛችበት ስተኛ፣በጠጣችበት ስጠጣ፣ የነካችውን ስነካ፣ የምታዳምጠውን ሳደምጥ፣ ሀሳቧን የምጋራት የመንፈስ ቅርቤ ሆነችና ሀሳቤ እሷና እሷ ብቻ ሆኖ፣ ይኸው ሶስተኛ ክረምት መጣ። ታዲያ አንዳንዴ ሳስበው የሚገርመኝ፣ ሰው በፎቶግራፍ መልኳን አይቶት እንኳን  ከማያውቀው ሰው እንዴት ፍቅር ይይዘዋል?
 ....ሁለት  ቀን ሲቀረው...
መፅሐፍ መደርደሪያዋ ላይ ካለው  ወረቀት ከተቀመጠበት፣ የውጪው ገፁ የለቀቀ መፅሐፍ መሀል ገልጬ ያሰመረችበትን “የአዳምን ፅሁፍ  አየሁት”
 ... ልብ አድርግ፤ ይህቺን ሳንቲም ምልክት አድርጌባት፣ ጭሬአት፣ አጣምሜአት ዱቤ ገዛሁባት፡፡ ከስድስት ወር በሁዋላ መልሳ እጄ ገባች። ሳንቲሟ ከኔ ተነስታ ወደ እኔ መጣች። ይህችን ሳንቲም ከእጄ ስትወጣ ያገኛት ሰው ሁሉ ወዜን ነክቷል፡፡ ስለጠየኩት ፊት ለፊት ቢያየኝ ይንቀኛል፡፡ ቢሸሸኝም ግን በመኖር ኪነ ጥበብ ተነካክተናል፤ አያመልጥም፡፡ .......
ከሰጪ ወደ ቻሪ ይሄዳል፡፡
ዞር እንላለን እንጂ አንሸሽም” ይላል
መቼም ሰዎች የምንሰበስባቸው ነገሮች  ሁሉ ያየነውንና የሰማነውን ነገር ሁሉ ወደ ራሳችን  ስለምንወስድ፣ እኔም እቺን ወስጄ አንዷ ቃል ውስጤ ቀረች፡-
“ሁላችንም ፊት ለፊት ባንተዋወቅም በመኖር ኪነጥበብ ተነካክተናል”..
እዚህ ቤት ትታው በሄደችው ወዝ አልተነካካሁም?
....አንድ ቀን ሲቀረው....
እነሆ እዚህኛው ክረምት ላይ በአካል ላያት ወስኜ ከምሄድበት ቀን ሶስት ቀን ጨምሬ ቀኗን ስጠብቅ፣ ረጅሙ ጊዜ ቀኑ ቀኑን ቆጥሮ ደረሰ። በተደበላለቀ ስሜት ውስጥ ሆኜ፣ ያን ቀርፋፋ ሰአት እቆጥራለሁ። ማጫወቻ ውስጥ አንዱን ሲዲ አንስቼ ከተትኩት፡፡
Imaginary lovers
Never turn you down
When all the others turn you away
They’re around
It’s my private pleasure
Midnight fantasy
Someone to share my
Wildest dreams with me
Imaginary lover you’re mine anytime
Imaginary lovers, oh yeah
When ordinary lovers
Don’t feel what you feel
And real-life situations lose their thrill
Imagination’s unreal
Imaginary lover, imaginary lover
You’re mine anytime
Imaginary lovers never disagree
They always care
They’re always there when
You need satisfaction guaranteed
Imaginary lover, imaginary lover
You’re mine all the time
My imaginary lover
You’re mine anytime..
...
Imaginary lover
ይሄንንም ወደ ራሴ እወስደዋለሁ.....
የዛን ዕለት እንደከዚህ ቀደሞቹ ሌሊቶች ሁሉ ሳይሆን እንቅልፍ እንቢ ብሎኝ  የተለያየ ሀሳብ እያነሳሁ፣ እያወረድኩ በሙዚቃው ድግግሞሽ ታጅቤ አመሸሁ።.. “ሳገኛት ምንድነው የምላት? ምን ትመስል ይሆን? ስሜት ባልሰጣትስ? ከዛ በኋላስ ምን ይፈጠራል?” ብዙ ብዙ ጥያቄዎችን ሳነሳ ስመልስ ....
ሌላው ያስጨነቀኝ ግን ሳላውቃት መንፈሴ የሰራት የማስባትን የወደድኳትን እሷን ሴት ባትሆንስ ? እኔ የማስባት ልጅ  ጋር ባይገናኙስ? ጊዜዬን ያስተካከለችልኝ፣ እዚህ ጨለማ ግቢ ላይ ብርሀን የሆነችኝ፣ እሷነቷ  ከውስጤ ቢወጣ እዚህ ድባቴያም ቦታ አንድ ቀንስ ውዬ አድራለሁ? ምን ሳስብ ማንን በመንፈስ ሳወራ? ይሄን ሸሽቼ ደግሞ ከአካባቢው ብርቅስ እንደዚህ ደስተኛ የሆነችብኝ እቺ ምስኪን አዛውንትስ ከልቧ አታዝንብኝም? መለስ ብዬ  ደግሞ  ከዚህ ተቃራኒው ተከስቶ እኔም ደስታዬን ባጣጥምስ?
...ዕለቱን...
ሰዓቱ እየደረሰ ሲመጣ ጭንቀቴ እየጨመረ፣ ብዙ ብዙ ከራስ ጋር ሙግት አደረግሁኝ። በመጨረሻም ገና ጠዋት ማለዳ ላይ ማንም ከእንቅልፉ ሳይነሳ አክስቴን እንኳን ሳልሰናበት ሻንጣዬን እየጎተትኩ የሚቀጥለውን ክረምት እየናፈቅሁኝ ረጅሙ ጉዞዬን ጀመርኩ ........

Read 1822 times