Tuesday, 28 September 2021 18:53

“ፌሚኒስቱ” ጸጋዬ ገብረ መድኅን

Written by  ደሳለኝ ሥዩም
Rate this item
(0 votes)

በ1966 ዓ.ም በታተመው ‹እሳት ወይ አበባ› የግጥም ስብስብ ውስጥ የሚገኝ የገጣሚው ሥራ ነው፡፡ በአንዲት ሴተኛ አዳሪ ሕይወት ውስጥ ያለውን እውነታ ገጣሚው ይተርካል፤ በሴተኛ አዳሪዋ ጫማ ውስጠ ገብቶ፣ የእሷን ሥሜቶች ያነበንባል። የውስጧን ብሶት ይዘከዝካል፡፡ ሴቷ ራሷን፣ ቤተሰቧን፣ ዓለምንና ሰዎችን እንዴት እንደምታይ፣ በግልባጩ እነሱም እንዴት እንደሚያዩዋት እያየች እንደሆነ ገጣሚው በግጥሙ ይናገራል፡፡ አሥራ ሁለት ገጽ ያህልም ይሸፍናል- ‹‹ማነው ምንትስ?›› የሚለው ግጥም፡፡ ዛሬ ይሄንን ግጥም በፌሚኒዝም የንባብ እይታ ለመተንተን እሞክራለሁ፡፡ አስቀድሜ ግን ስለ ፌሚኒዝም ጥቂት ልበል፡፡
ከ18ኛው መቶ ክፍለ ዘመን ማጠቃለያ አንስቶ ነው፣ ‹ፌሚኒዝም› የሚለው ቃል አገልግሎት ላይ የዋለው፡፡ የፌሚኒስቶቹ ዓላማዎች የተለያዩ ደረጃ ያሏቸው ናቸው። ሴቶች ከወንዶች እኩል ማኅበራዊ፣ ፖለቲካዊና ኢኮኖሚያዊ እድልን ማግኘት አለባቸው ከሚለው ለዘብተኛ የመብት ጥያቄ እስከ ‹ሴቶች ከወንዶች ኅብረት የለንም፣ በወንድ የሚጠራ አምላክ አናመልክም፣ ከወንድ ጋር አንጋባም› እስከሚለው አክራሪ አቋም ያሉትን ያጠቃልላል፡፡
ፌሚኒዝም ሶስት ንቅናቄዎችን አድርጓል። የመጀመሪያው ንቅናቄ በ1800ዎቹ ተጀምሮ በ1930ዎቹ የተገባደደ ነው፡፡ የዚህኛው ንቅናቄ መሪ ጥያቄም፤ ሴቶች ከወንዶች እኩል መብት ያላቸው ፍጡራን መሆናቸው ይረጋገጥልን የሚል ነበር፡፡ በህግ፣ በፖለቲካና በትምህርታዊ ጉዳዮች ላይ ሴቶች እኩል እድል ይሰጣቸው የሚል ዘመቻ የተደረገበት ነው፡፡
ሁለተኛው ንቅናቄ ደግሞ በ1960ዎቹ የተጀመረ ነው፤ ይሄኛውም ንቅናቄ የሴቶችን እኩልነት የሚጠይቅ ይሁን እንጂ ከቀደመው ዘመቻ ይልቅ ጠንከር ያለ ጥያቄን ይዞ የተነሣ ሆኗል፡፡ ከዚያ ወዲህ በመላው ዓለም ለሴቶች መብት የሚቋቋሙ ኅብረቶች፣ የሚበለጽጉ አሠራሮችና ንድፈ ሐሳቦች፣ በተለይ በሥነ-ጽሑፍ  በፍልስፍና  ብሎም በማኅበራዊ ሳይንስ ትምህርቶች ውስጥ ቦታ እየያዙ መጥተዋል፡፡ የዚህኛው ንቅናቄ መገለጫ አክራሪነት ነው፡፡ “ጾታ እና ሥርዓተ ጾታ ይለይ” በሚል የተነሣው ጥያቄ፤ ከርሮ ከርሮ ”የጭቆና ሀሁ ከወንድ አካል (ብልት) ይጀምራል፤ ስለዚህም የወንድን አካል አንፈልግም” እስከሚል የደረሰ ነው፡፡  
ሦስተኛው ንቅናቄ  በ1992 (እኤአ) እንደተጀመረ ይገመታል፡፡ መነሻውም የርብቃ ወከር ‘Becoming the third wave’ የተባለ መጣጥፍ ነው፡፡ በዚህኛው ዙር ንቅናቄ የተንጸባረቁ ሀሳቦች፣ ድኅረ ቅኝ ግዛትና ድኅረ ዘመናዊ ሒሶች ላይ የሚነሡ ነጥቦች ናቸው፡፡ ማጠንጠኛውም በዓለም ሁሉ ይሠራል የሚባል የሕይወት ደረጃ መለኪያ መስፈርት (Standard) የለም፤ ሁሉም በዘመኑ፣ በጊዜውና በቦታው በመሠለው መንገድ መኖሩ ልክ ነው የሚል ነው፡፡
በሴቶች ላይ ለዘመናት ሲደርሱ የነበሩ ጭቆናዎችን፣ ግፎችን ለመቋቋም ፌሚኒስቶች ሁለት ዓይነት መንገዶች ይዘው ነው የመጡት፡፡ ለዘብተኝነትና አክራሪነት። ለዘብተኛ ወይም የተሀድሶ ዕይታን ከሚመርጡ ጸሐፊያን መካከል ጆን ስቱዋርት ሚል እና ሜሪ ዊልስቶን ክራፍት ይጠቀሳሉ። እነዚህ አሳቢያን ‹ለሴቶችም ልክ እንደ ወንዶች ሁሉ ዕድልን መስጠት ያስፈልጋል። ሴቶቹ አይችሉም ብሎ ከመከልከል ይልቅ ወንዶች በሚሰለፉበት ፖለቲካዊና ማኅበራዊ፣ እንዲሁም ሃይማኖታዊ ተቋም ውስጥ ሴቶችም ተመሳሳይ ዕድል እንዲያገኙ ማድረግ የሴቶችን የጭቆና ችግር ይፈታዋል የሚሉ ናቸው፡፡  
ሚል እና ዊልስቶን ክራፍት ይሄንን ለማለት ያስቻላቸው፣ ”ሴቶች የበታች ናቸው የሚለው አመለካከት ተፈጥሯዊ ሳይሆን ሰው ሠራሽ፣ በመፈጠር የመጣ ሳይሆን በመፍጠር የመጣ ነው” ከሚል መነሻ ነው፡፡ ዊልስቶን ክራፍት ‘Vindication of the Rights for Women’ በሚለው ዝነኛ መጸሐፏ እንዲህ ትላለች፡- “ሴቶች በተፈጥሯቸው ሆደ ቡቡ ደካማ፣ አልቃሻ፣ ስሜታዊና ስሱ ሆነው አልተፈጠሩም፡፡ ይልቁንም በማኅበረሰቡ እንዲህ እንዲሆኑ ተደርገው ይሠራሉ እንጂ።”
በዊልስቶን ክራፍት ዕሳቤ፤ “መፈጠር (Nature) አይደለም ሴቶችን ልፍስፍስ፣ አልቃሻና ጥገኛ አድርጎ የሠራቸው፤ ማኅበረሰቡ (Nurture) ነው እንዲያ እንዲሆኑ የሠራቸው፡፡ የዚህ ሁሉ መሠረት ደግሞ አሁን ያለው የትምህርት ሥርዓት ነው” ትላለች፡፡ በየሀገሩ ያለውን የተንሸዋረረ የትምህርት ሥርዓት ስትተችም እንዲህ ትላለች፤ …. “Like the flowers which are planted in too rich a soil, strength and usefulness are sacrificed to beauty” (1792:7)
በሌላ በኩል፤ ስቱዋርት ሚል ተፈጥሮ (Nature) የሚለውን እሳቤ አምርሮ ይቃወማል፡፡ “The Subjection of Women” በሚለው ሥራው ውስጥ የትኛዋም ሴት ብትሆን ስለ ተፈጥሮ አንደኛዋ ከሌላኛዋ ያላቸውን ልዩነት ልናውቅ አንችልም፡፡ በሚኖረን የዕለት ተዕለት ግብብነትና ቅርርብ እየተገነዘብናት እንሄዳለን አንጂ፡፡ በመሆኑም በተለምዶ ወይም ቀድሞ ባለው ፍልስፍና ውስጥ የሴቶች ተፈጥሮ እየተባለ የሚወራ ነገር ውሀ የማይቋጥር ተልካሻ ሙግት ነው ይላል፡፡
ፈረንሳዊቷ ኢግዚስቴንሻሊስት ሲሞን ዲቦቨር ደግሞ የቀደመውን ፍልስፍና ከመሠረቱ ትንደዋለች፡፡ ፕሌቶና አርስቶትል “ነገሮችን ነገር የሚያደርግ የራሳቸው የሆነ የማይለወጥ የማይናወጥ ማንነት (Essence) ሥሪት ናቸው” በማለት የሞገቱበትን ፍልስፍና ውድቅ ታደርጋለች - ኢሰንስ የሚባል ነገር፣ ኢሴንሻሊዝም የሚባል ፍልስፍና አይረባም በማለት፡፡
የዲቦቨር መከራከሪያ የነገሩ መገለጫ ከሆነው ኢሰንስ ይልቅ የነገሩ ኅልውና (Existence) ይቀድማል፡፡ የአንድ ነገር እጣ ፈንታውን ለመወሰን መገለጫው ምንነቱ ላይ ሳይሆን መኖር አለመኖር (ኃልዮው) ላይ ነው ማነጣጠር ያለብን ትላለች፡፡ የዲቦቮር ፍልስፍና (Existentialism) በዚህ የተነሣ ሁነት ላይ ሳይሆን ነፃነት ላይ ያተኩራል። ስለሆነም መገለጫዎችን እያነሱ ”የሴቶች እጣፈንታ” ከማለት ይልቅ ሴቶች በራሳቸው ኀልዮአዊ መሆናቸውን ተቀብሉ ፈቃድ አንዳለቸው ማመኑ ነው ትክክለኛ መንድ ትላለች፤ ዲቦቮር፡፡  
‘The second sex’ በተሰኘው ዝነኛ መጽሐፏ፤ የትኛውም አካላዊ፣ ሥነ - ልቦናዊ ወይም ኢኮኖሚያዊ ዕውነታ ሴቶች በተፈጥሮ ያላቸውን ምንነት ሊወስን አይችልም ትላለች፡፡ ”one is not born, but rather, become a woman, ” (1976፡267) ሴታዊነት ወይም የሴት ተብለው የተለዩ ኹሉ ለሴቶች እየተሰጡ ያሉ መገለጫዎች ናቸው፡፡
ይሄ የሴት እየተባለ የሚሰጥ መገለጫ ደግሞ ሴቶችን ሌሎች እንዲሰኙ አድርጓቸዋል፡፡ በመሆኑም ወንድነት እንደ አንደኛ ደረጃ ፆታ፣ ሴትነት እንደ ሁለተኛ ደረጃ ፆታ ተቆጠረ፡፡ ወንዶች ሴቶች እነሱ ሲሉ ዝቅ የሚያደርጓቸውን ያህል፣ ሴቶችም ወንዶችን እነሱ እያሉ ሌላ ከፍተኛ ደረጃ ላይ ያሉ አድርገው እንዲቀበሉ ተገደዱ፡፡
“ወንዶች እኔ ሲሉ፣ ሴቶችንም እሷ ሲሉ፣ ራሳቸውን ባለቤት አዛዥ የበላይ፤ ሴቶች ደግሞ የበታች መገልገያ ቁስ ያደርጓቸዋል። ከልጅነት ጀምሮ ወንዱ ወንድነት፤ ሴት ሴትነት እየተላበሱ እንዲያድጉ ይደረጋል። ለወንዱ ጎረድራዳነት፣ ድምቡጭነት፣ ውፍረት ወይም ክሳት መሥፈርት አይሆንም። የወንድ መልክ ለውድድር አይቀርብምና፡፡  ወንድ አያለቅስም፤ ወንድ ደረቱን ነፋ ማድረግ አለበት፡፡  ባንጻሩ ሴት መኳኳል አለባት፤ አካሏን ካልጠበቀች የሚነካት (የሚመኛት) እንደሌለ ይነገራታል።  ረጅም ሰዓቷን መስታውት ፊት እንድትቆም ትደረጋለች፡፡” ትላለች ዲቦቮር፡፡  
ሚሸል ፉኮ ደግሞ ”Genealogies of Power/Knowledge” በሚሉ ሥራዎቹ፤ ሴቶችን አስመልከቶ የጻፋቸው ሐሳቦች ጠቀሜታ ከፍ ያለ ነው፡፡ የፉኮ ዕይታ ያተኮረው በስልጣን (Power) ላይ የነበረውን ዘልማዳዊ አተያይ መቀየር እንደሚገባ ነው፡፡ ሴቶች በማኅበረሰባቸው ውስጥ ተገልለው ኖረዋል፤ ተጨቁነዋል ከሚለው ለቅሷዊ ምልከታ ወጣ ያለና መፍትሔ አዘል ምልከታን ለማምጣት የሚሸል ፉኮ ዕይታ ፌሚኒስቶችን  ያነቃቃ ይመስላል፡፡ ስለዚህም ፌሚኒዝም በሥነ ጽሑፍ ውስጥ አንድ ሁነኛ ንድፈ ሐሳብ ሆኖ የሥነ ጽሑፍ መፈክሪያ ሆኖ እያገለገለ ይገኛል፡፡ እንግዲህ በዚህ ጽንሰ ሐሳብ ውስጥ የጸጋዬ ገብረ መድኅንን ‹‹ማነው ምንትስ?›› የተሰኘ ግጥም፣ በሚቀጥለው ሳምንት ለማየት እሞክራለሁ፡፡
 የሣምንት ሰው ይበለን!

Read 1407 times