Print this page
Tuesday, 28 September 2021 19:01

በራስ ቀብር ላይ መደነስ

Written by  ያዕቆብ ብርሃኑ
Rate this item
(3 votes)

 ያ በ‹Midnight in paris› እና ‹Irrational man› በተሰኙ ፊልሞቹ ያስደነቀኝ ውዲ አለን እንዲህ ይላል፤ ‹‹What if nothing Exists and we all are in somebody’s dream?›› እውነትስ የከበበን ግሳንግስ ንቅሳታም ሕዋ ሁሉ ህልም ስላለመሆኑና እኛም የሆነ ከሰዋዊነት ከፍ ያለ ኃይል ያለው ገልጃጃ አካል፣ ጋደም ብሎ የሚቃዠን ህልሞች ስለአለመሆናችንን በምን እናውቃለን? በምንም! ተፋጠጥ እንግዲህ… መፋጠጥ እንጂ እንቅብ እንደተደፋባቸው ጫጩቶች ሰፊ በሚመስል መውጫ የሌለው ኩርማን ኦና ውስጥ ለተጣልን ለእኛ መሸሻማ ከየት ተገኝቶ?! ሌላም ማኮብኮቢያችንን የምታጎላ፣ የማናውቀው የማያውቀን ወዳጃችን (Michael Lebron [Lionel]) የተናገራት ግሩም ነገረ ሰበዝ ላክልላችሁ፡፡ ለአንድ መጽሐፉ አርዕስትነትም ተጠቅሞባት አይቻለሁ፡፡ ጥቅሷ ይቻትላችሁ፡- ‹‹ከእኔና አንተ ውጭ ሁሉም ሰው አብዷል፤ ተሳክሯል፡፡… አሁን እንዲያውም አንተንም መጠርጠር ጀምሬያለሁ፡፡››
የዓለማየሁ ገላጋይ አዲሱን መጽሐፍ ‹ሐሰተኛው - በእምነት ሥም› ማንበብ እንዲህ ዓይነት የሚያጠናግር ግራ መጋባት ውስጥ ይከትሃል፡፡ አንብበህ ስትጨርስ ሁሉንም ነገር መካድ ይዳዳሃል፡፡ የምታውቀው፣ የገነነ እውነት ያልከው እሱ ተሸርሽሯል። በእነዚህ ገጾች መሀል ከአያት ቅድመ አያት የተረከብነው፣ የማይሻር ያልነው ሀቅ ተገርስሷል፡፡ ትረካው ለመቃወም የሚበቃ የቅጽበት ፋታ እንኳን አይሰጥህም፡፡ አንድ ወጥ መልክ የሌለው እንዲያው በየፈተታው እየሰገረ የሚከስም ሽሽት አበዛዙ ለጉድ ነው፡፡ ከአማልክት ጋር አጉል የመጋፋት፣ እንደገና የመናፍስትን ከበባ ሽሽት በተፈጥሮ ጸዳል ስር ቀልብን ለመሰብሰብ፣ አምላክን ለመለማመን መፍገምገም… ሰው ከአማልክት ጋር በጀብድ ሲጋፋ መናፍስት ይሰለጥኑበት ዘንድ ተቅበዘበዙ፡፡ በእነዚህ ገጾች መሀል በአምሳሉ ተፈጠርኩ እያልክ የምትዘባነንበት አምላክ እንኳን ለቀብር ይታጫል፡፡ እናስ ከዚያ ወዲያ በአምሳሉ ተፈጠርኩ ይሉት መረግረግስ ከወዴት ሊገኝ?
የዚህ መጽሐፍ ቀዳሚ መቼት ቅንብቢት፣ በየካ ተራራ ወገብ ላይ እንደ ባለጌ የዝንጀሮ ልጅ አጉል ቂብ ብላ በዳበሳ ብቻ የምትገኝ አሳቻ ሰፈር ነች፡፡ እዚህ ሰው ከውሻ ጋር ይማከራል፤ ሰው ከአውራ ዶሮ ጋር ይፎካከራል፤ ሰው ለራሱ ድንጉጥ፣ መጠጊያ አልባ፣ ብኩን ለሆነው ነፋስ ብሶቱን አቤት ይላል፡፡ ኑረት ቅኝቱ ተዛብቷል፡፡ ከየጥጋጥጉ ያደፈጠ ረሀብ ፍጥረትን በሙሉ ሊውጥ ያዛጋል፡፡ ረሃብ ለውሻው ጃክ እንኳን የሚራራ አልሆነም፡፡ የውሻው ጃክ በሰከነ ታዛዥነት በጸጥታ ለተፈጥሮ ቁጣ መገዛት ሰውን ያሸብራል፡፡
የጋዜጠኝነትን ደመወዝ ሲያጡ መራር ረሀብን ሽሽት፣ ሩህን ለማሰንበት ወፍጮ ቤት በር ላይ ከእብቅ ጋር መንደፋደፍ… እንደገና የደስታየቭስኪን ‹ግራንድ ኢንኩዚተር› የሚመስለውን አለቃን ትዕዛዝ ተከትሎ ለወፍጮ ቤት ዱቄት መሰለፍ… ይህችን ጎምዛዛ ሀቲት እያባበሉ ቢከተሏት የምር የተኖረ የሕይወት ገጽ ላይ አታደርስም ይሆን? እዚህ ውስጥ የምንዘገበው እኛ ነና! ከቅንብቢት ለሰሚው ጆሮን ጭው የሚያደርግ ንፍገትና ከዓይነምሣ ክርስቶስን በአካል የመጨበጥ ያህል የሚያነሆልል ደግነት ጀርባ በምልዓት የምንዘገበው እኛ ነን፡፡
ታሪኩ ገና ሲጀምር ከቀብር መልስ የሚመስል በአርምሞ የተሸበበ ጠጣር የሀዘን ስሜት ይቀበለናል፡፡ የሆነ ለዘመናት የተዘጋ ቤትን ከፍቶ እንደ መግባት ያለ መደነጋገር አለው፡፡ በዚህ መጽሐፍ ውስጥ ሰው ከአውራ ዶሮ ተናንሷል፡፡ የሰው ልጅ ቀበናን ያህል ወንዝ እንደ እባብ ቀጥቅጦ ገድሏል። ወንዝ የሰውን ልጅ ነውር ቢጸየፍ ፈራሽ ገላ ለብሶ ሽታው ከሩቅ ይጋረፋል፡፡ የወንዝ ሞቱም ሆነ መበስበሱ እንደ ሰው በአንድ ሰሞን ብቻ የሚቀነበብ ትርክት አይምሰልህ።
እንደገና ሌላ መደነጋገር… የዚህ መጽሐፍ ደራሲ ዓለማየሁ ገላጋይ ሞቶ በልብወለዱ መግቢያ ላይ የመታሰቢያ ገጽ ተበረከተለት። ደራሲው እስከተሳለች ብዕሩ በሕልውና ሲቀዝፍ እያየነው ህልፈቱ ተሰበከልን፤ ለሙሾ ተጋበዝን፡፡ ያኔ ነው እንግዲህ ከከድር ሰተቴ በተዋስናት ውብ ቃል ‹ከዜሮ መቀነስ በራስ ቀብር ላይ መደነስ› ለማለት የከጀለን። ድርሰቱ ልብወለድነቱን ደጋግሞ እየካደ ራሱ በሚዋኝበት የተቀዣበረ የምናብ ዓለም ውስጥ ስቦ አስገብቶ፣ እንደ ጨው ሊያሟሟን አደፋፈረን፡፡ እናስ ከዚህ ሁሉ በኋላ በቆመበት ጸንቶ የሚቀጥል እውነት የቱ ነው? እናትነት እንኳን ይደነቃቀፋል፡፡
በዓለማየሁ ብዕር ሲገለጹ ዘመናት እንደ ቅጽበት ቀላል ናቸው፡፡ ሸክሙን ግሳንግስ ትዕይንት እንደ አንዳች ተራምዶ ከአስር ዓመታት በኋላ ስለሆኑት ነገሮች ሲተርክ ለምናብ አይጎረብጥም፡፡ በሦስቱ መጻሕፍቱ (በፍቅር ሥም፣ ታለ እና ሀሰተኛው) የብዕር ሹረት የተመዘገበው እርምጃ ፈጣን፣ ሽግግሩም ብዙውን ጥሎ ጥቂቱን አንጠልጥሎ የተከናወነ ነው፡፡ እንደ ሰርጥ መንገድ በየፈተታው እየከሰሙ የሚቀሩት፣ የሚያራግፋቸው ታሪኮች፣ ገጸባህሪያት ጥቂቶች አይደሉም፡፡ ሁሉም ነገር እንደ እንቅልፍ ባለ ሌላ ሰመመናዊ ድንግዝግዝ ሁነት የተከበበ ነው፡፡ ስሪቱ የሆነ ህልምና እውን የሚሳከሩበት፣ የሚወዳደሩበት፣ የሚሳሳሙበት፣ የሚተላለፉበት (dream realism- drealism) ነገር አለው፡፡ እናም ‹ሀሰተኛው›ን እንደ ሀዲስ፣ ዳኛቸው፣ በዓሉ ተለምዷዊ በሆነው የጽሕፈት ቅኝት ጠምዝዘን ለመረዳት መሞከር ስህተት ላይ ሊጥለን ይችላል፡፡
ዓለማየሁ ገላጋይ እንደ ራምብራንት (Rembrandt)
ራምብራንት እ.ኤ.አ ከ1606-1669 የኖረ እጅጉን የተወደሰ የደች ተወላጅ ሰዓሊ ነበር፡፡ ይበልጡኑ የሚደነቀው ጥቀርሻ የወረሳቸውን የመዳብ ሰሌዳዎችን በመርፌ ጫፍ እየጫረ ከጨለማ ውስጥ ተፍጨርጭሮ፣ ጨለማን ቧጭሮ፤ ጽልመቱን ገፍትሮ በሚወጣ ብርሃን በሚፈጥራቸው ምስሎች ነበር፡፡ የባህር ማዶ ሰዎች ይህንን ክህሎት በፈረንጅ አፍ- Chiaroscuro ይሉታል፡፡ የጽልመትን ጥልቅ ሰብረው ብቅ እንደሚሉ (light emerge out of the dark) የራምብራንት ምስሎች፣ የታለ አፈጣጠርም እንደዚያ ዓይነት ቀለም አለው፡፡
‹‹ስድስት ዓመት ሳይሆነኝ አይቀርም። አንድ ቀን የማላውቀው ጨለማ ውስጥ እንደቆየሁ ሁሉ ድንገት ተግ ያለ ብርሃን ታየኝ፡፡ ጸጥታ ውስጥ እንደቆየሁ ሁሉ ድንገት በድምጽ ተጥለቀለቅሁ፡፡ ቀለሙ ሁሉ ደማቅ ሆነብኝ፡፡ ከቤት መሰስ ብዬ ወጥቼ የሰንሰሉን አረንጓዴነት፣ የሰማዩን ድምቀት በእንግዳ ስሜት አጤንኩ፡፡ ቀን ታውሬ ዓይኔ እንደበራልኝ፣ ደንቁሬ እንደተከፈተ ሆንኩ።…›› በፍቅር ስም፤ ገጽ 36
ሆኖም በቀጠሉት የመጽሐፉ ገጾች ላይ ከአምስት ለማያንስ ጊዜያት ያህል ታለ በጨለማው ዓለም ውስጥ መቀጠሉን ይናዘዛል፡፡ ‹በፍቅር ሥም›ን ተከትሎ በመጣው ‹ታለ በእውነት ስምም› የሆነው የባሰ ነው፡፡ ታሪኩ ሲጀምር ታለ ከ11ኛ ክፍል ትምህርቱን አቋርጦ፣ ለሁለት ዓመታት እላዩ ላይ ከዘጋት ቤቱ ገና መውጣቱ ነበር። ‹‹እንደ በኣት የምትቆጠር ቤቴን ከፍቼ የገባሁት የ11ኛ ክፍል ትምህርቴን አቋርጬ ነበር፡፡ የዘጋሁትን ቤቴን ከፍቼ ስወጣ አንዲት ጀምበር በሚመስል እድሜ ሁለት ዓመታት ተራርቀው ነበር፡፡… እራሴን ፍርግርግ ጎጆ ውስጥ ተዘግቶባት እንደኖረች ወፍ ቆጠርኩት፡፡ ለሁለት ዓመታት አልፎ አልፎ የጡረታ ድልድይን ሰፈር ገርመም ከማድረግ ውጭ ራቅ ብዬ የሄድኩበት ቀን ትዝ አይለኝም፡፡››
ለመሆኑ በኑባሬ የስሪት ገጽ ላይ ከብርሃንና ከጨለማ የትኛው አስቀድሞ የተፈጠረ ይመስላቸኋል? መጽሐፍ ቅዱስ ኦሪት ዘፍጥረት ምዕራፍ አንድ ላይ፣ ከብርሃን በፊት ጨለማ መቅደሙን ምስክርነቱን ይሰጣል፡፡ በውሆች ላይ የተንሰራፋው ጨለማ ብርሃን ከመሆኑ በፊት የእግዚአብሔር መንፈስ ማደሪያ የነበረ ይመስላል፡፡ ሳይንስም የሚለው እንደዚያ ነው፡፡ ብርሃንን ልትፈጥር ትችላለህ፤ ጥላንም እንደዚሁ፡፡ ጨለማን መፍጠር ግን የሚቻል አይመስልም፡፡ ጨለማ በጠፈር ውስጥ በፍጥነት በመምዘግዘግ ጥበብ፣ ብርሃንን ሳያስከነዳው ይቀራል?
እናም በበልግ ወራት የአዛባውን ቅርፊት ሰብረው እንደሚወጡ እንጉዳዮች እንዲሁ የታለም አፈጣጠር ከጨለማ ጋር ይህን መሰል ፍልሚያ አለበት፡፡ ከልውውጡ ጊዜ ጀምሮ የታለ ግብግብ ከሚያሳድደው የጽልመት ቀለበት የመውጣት መፍጨርጨር ነበር፡፡ ዘወትር ሽሽት ላይ ነው፡፡ ጡረታ ድልድይ፣ ሰባራ ባቡር፣ ቅንብቢት፣ ዓይነምሣ… የረገጠው አበዛዙ! በዚህ መጽሐፍ ‹ሀሰተኛው- በእምነት ስም› በእነ ቢራራ ያለሰለሰ ማትጋት፣ ማባበል ታለ የጨለማውን ዓለም የመድፈር፣ የመሻገር፣ የመጋፈጥ ድፍረት ሲላበስ እናያለን፡፡ ጨለማው እዚያም (ቅንብቢት)፣ እዚህም (ዓይነምሣ) የትም አለ፡፡ እዚያ ጨለማው በጽልመትነት ይኮነናል፤ እዚህ ጨለማው ለግርማሞገሱ ይወደሳል፡፡ እዚያ ውሽንፍርን ደርቦ የለበሰው የጨለማው ዓለም ጥልቅ፣ በኤላዛቤላዊያን በፍርሃት ይረገድለታል፡፡ በጨለማ የማስፈራራት፣ የማባባት እንደገና በጨለማ የማጀገን፣ የማትጋት፣ የማወደስ መጣረሱ ለጉድ ነው፡፡ ሕብሩ፣ ዓይነቱ፣ ገጹ እንዲሁ የተሳከረ ነው፡፡
ታለ ለብቻው ከገጠመው የጨለማውን ዓለም ሰንጥቆ የመውጣት ትንቅንቅ ጋር ሲላጋ መለመላውን እስኪቀር ሁሉንም አራገፈ፡፡ እህቶቹ፣ ሲፈን፣ ሊሊ፣ ነጸብራቅ፣ ናትራን ሁሉም ሲክለፈለፉ መጥተው ለታለ ውሉ ያልለየ ጥሪ ጭዳነት ተረግጠው የታለፉ ናቸው፡፡ ጨለማው አንድ ወጥ መልክ የለውም፡፡ እንደ ሰባራ ጋን የቸለስክበትን ሁሉ ይውጣል፡፡ እንደ ሰደድ እሳት በቃኝን አያውቅም፡፡ ስንፈጠር ጀምሮ ጉዞአችን ከጨለማ ወደ ጨለማ ይመስላል፡፡ መወለድ እንደ ህልም ያለ አጥበርባሪ (illusionistic) ገጽ አለው፡፡ መሞትም እንደዚያ ነው፡፡ ከጨለማው ጋር ግብግብ ስትገጥም ነፋስ የተመቸው ሰደድ እሳት እንደሚያኳትነው አውሬ፣ ነፍስህን ብቻ አንጠልጥለህ በእልህ መሸሽ ግዴታህ ይሆናል፡፡ በኑረት ሰሌዳ ላይ አንበሳውን ወይም ሚዳቋዋን መሆንህ ልዩነት አያመጣም፡፡ ለመብላትም ላለመበላትም የግድ ከትናንቱ የበለጠ መሮጥ ይኖርብሃል፡፡
በመጨረሻ ታለ የሆነች የብርሃን ስንጥቅ መመልከት ችሏል፡፡ ሆኖም ታለ ሙሉ ለሙሉ ጨለማውን አላሸነፈውም፡፡ የራምብራንት በመርፌ ጫፍ መፍጨርጨርም ቢሆን ጨለማውን የሚሰብሩ ሽርፍራፊ የብርሃን ቅንጣቶችን ፈነጠቀ እንጂ ጨለማውን አልዋጠውም፡፡ ሙሉ ለሙሉ ጨለማን ማሸነፍ ብሎ ነገርስ አለ እንዴ? እንደዛ ብሎ ነገር የለም፡፡ ወዴት ወዴት…
እግዜር እንደ አጥቢያ ዳኛ (Deconstructing God)
‹‹እኛ እሱን በመፍጠራችን ልንፀፀት ይገባል፡፡ ከዚህ የተሻለ ያስቀመጥንበትን ቦታ የሚመጥን እግዚአብሔር ልንፈጥር ይገባ ነበር፡፡ የአጥቢያ ዳኛ ይምስል የሐጥያት መዝገብ አገላብጦ ‹አንተ ለእሳት›፣ ‹አንተኛው ለገነት› ብሎ መፍረድ እንኳን ታላቁን ፈጣሪ እኔንስ ይመጥናል? ይህንን ታላቅነት እኔስ እፈልገዋለሁ?... እንደተባለው እግዚአብሔር የለም! ወይንም እግዚአብሔር ሞቷል፡፡›› ሀሰተኛው በእምነት ሥም፤ ገፅ 84
ይህ ሀተታ ከንባብ በኋላ የሚሰጥ ግለ ዕይታ (reflection) እንደመሆኑ በታለ እና በከበበው የሕይወት ስሪት አፈጣጠር በዓለማየሁ የብዕር ሹረት ስለተሞገተው የሻገተ እግዜራዊ አረዳዳችን እንድናወራም ምኞቴ ነው፡፡ በተለይ በመጨረሻዎቹ ሁለቱ መጻሕፍት ‹ታለ› እና ‹ሀሰተኛው› የምናቡ ዓለም እግዜር ‹ዓለማየሁ ገላጋይ› ከገጸባህሪያቱ ሲተናነስ፣ ከደራሲነት ወርዶ በአርታኢነት ብቻ እውቅና ሲሰጠው፣ እንዲያውም ሕልውናው ተክዶ ለሕልፈቱ ሙሾ ስንጋበዝ፣ በገደምዳሜ የእኛውስ እግዜር መነካቱ አልነበረምን?
ዓለማየሁ ገላጋይ በተለይ ከ‹የብርሃን ፈለጎች› ጀምሮ በተከታታይ በጻፋቸው አራት ልብወለዶች የሻገተ፣ መታደስ ያቃተው እግዜራዊ አረዳዳችን ላይ ድርብርብ ጭብጦችን መዟል፡፡ በእነዚህ ጥበባዊ እርምጃዎቹ የቀሰቀሳቸው ጥያቄዎች ለዘመናት የሰለጠኑትን ዘልማዳዊ አስተሳሰቦች እንደ መነቅነቃቸው፣ እልፍ ብዕሮችን ለሂስ አለመጋበዙ ያለንበትን ምሁራዊ ማንቀላፋት የሚያሳይ ይመስለኛል።
በእርግጥ እግዚአብሔር ሸሽቷል፡፡ ይህችን ምድር ለሰው ልጅ ሲሰጥ አደራ ያለው ግን ለምኑ ነበር? ለሆዱ? ለሕሊናው? ለስሜቱ? ለእብደቱ? ምናልባት ለሌላ? ምናልባት ለሰይጣን? … እግዚአብሔር ሞቷል ወይም ሸሽቷል ብሎ ነገርስ ምን ማለት ነው? ያ የመከራ ቋት ኒቼ እንደ እብድ እግዚአብሔር ሞቷል እያለ ሲለፍፍ፣ ሬሳውን ተመልክቶ አይመስለኝም፡፡ የአሜን ዘመን አብቅቶ ሁሉም ነገር በምክንያታዊነት (reasoning) የሚበየንበት የአብርሆት ዘመን መጀመሩን ሲያበስር እንጂ…
የአዲሱን ዘመን ሰው የመሆን ጥያቄዎች በአሮጌው ዘመን ሀይማኖታዊ አስተሳሰብ መመለስ እንደማይቻል ግልፅ ነው፡፡ እግዚአብሔራዊነት የሕልውናን ምንጭ መሰረታዊ ጥያቄ የተሸከመ ሐቲት እንደመሆኑ፣ እንደ ጣዖታቱ ዘመን ለሁሉም ትውልዶች በሚስማማ መልኩ፣ በአንድ ወጥ ምስል ብቻ መቀንበብ አይቻልም፡፡ ለእኛ ለድህረ ዘመናዊያን ትውልዶች ትርጉም (እግዜርን ጨምሮ የነገሮች ግላዊ አረዳድ) በነጻ ፈቃድ የሚዳኝ እንጂ በወዮላችሁ የሚጫን ሊሆን አይችልም፡፡ እግዜርን በሰይፍ ከተሰበከልን ውጭ እንደ ኑረታችን፣ እንደ ንቃታችን፣ እንደ ጉስቁልናችን ልክ፣ በገባን መጠን ልንረዳው ይገባል፡፡ እግዜርን መሆን ሊመረመር፣ እንደገና ሊፈተሽ፣ ሊተነተን፤ ሁሉም እንደ ኑረቱና ብስለቱ ሊያመሰጥረው ግድ ነው፡፡
እንደኛ ዓይነት ለሺህ ዓመታት ዝግ የሆነ ማኅበረሰብ ውስጥ ለሚኖሩ ትውልዶች፣ በእርግጥም እግዜርን የመሳሰሉ ጭብጦች አይነኬ ነበሩ፡፡ ዛሬ እነዚህን የሻገቱ ሀሳቦች የሚያፍታቱ ጥያቄዎች መሰንዘር ስንጀምር፣ የማይገባው ድግምት ሲነበነብ አሜን እንዲል ያቀናነው ትውልድ ሊወግረን ኮብልድንጋይ ይዞ ቢሰለፍ የሚገርም አይሆንም። ፈለግነውም አልፈለግነውም በዚህ የዘመን ቅኝት ውስጥ ራሳችንን አግኝተነዋል፡፡ በድህረ ዘመናዊያን ትውልዶች ዓይን ሁሉም ነገር፣ ለራስ ትርጉም፣ ለራስ ተምሰልስሎት፣ ለራስ ፍካሬ የተተወ ነው፡፡ ምንም ነገር ዝግ አይደለም፡፡ ከእግዜር ጋር መሟገት፣ ከእግዜር ጋር መደነስ፣ ሲያስፈልግ ፈገግታውን መልበስ… ይቻላል፡፡
ዓለማየሁ ገላጋይ በተለይ ከብርሃን ፈለጎች ጀምሮ በወጡ አራቱም ልብወለዶቹ፣ ይሄን ነውርን የተሻገረ አይነኬ ‹እንትን› ደጋግሞ ነቅንቆታል፡፡ የሆነ ጊዜ ላይ እግዜርን በሊሊ ጀርባ ታዝሎ አየነው፡፡ ለዚያውም ከግንችሬ ወንድሟ ጋር ተዳብሎ እኮ ነው፡፡ በአንዲት የዓለም ሁሉ መከራ የተደራረበባት ምስኪን ታዳጊ ጀርባ ላይ ሲወጣ የማይቀፈው ምን ዓይነት አምላክ ቢሆን ነው? ሌላ ጊዜ እንደ እድር ዳኛ ቡትቷም ካፖርቱን ለብሶ አሮጌ ዶሴውን ታቅፎ በመካከላችን ቆሞም ነበር፡፡ እንደገና ሌላ ጊዜ በሰው ትከሻ እንደሚንቀሳቀስ ፊውዳል መከዳው ላይ አረፍ ብሎ በፈጠራት ዓለም ላይ ለሚደርሰው ጥፋት ሁሉ ግድየለሽ መስሎ ቀረበ፡፡ አሁንም የሆነ ጊዜ ላይ እግዚአብሔር እንደ ልጅ እያሱ፣ በውርስ የተሾመብንና በሚደርስብን በደል የሚሳለቅ ጅላጅል ሸክላ ሰሪ እንደሆነ እንድናስብ ተገፋፋን፡፡
‹‹በእኔ መጨነቅ እግዚአብሔር እየሳቀ ነው፡፡ እንዴት ከእኔ ከፍጡሩ ያንሳል? እንደ ልጅ ኢያሱ በልጅነቱ በውርስ የተሾመብን ሌላ አምላክ ይኖር ይሆን? የፈጠረን የሚያውቀንስ በዚህ ድክመታችን አይሳለቅም፡፡ እኔን ይተው ሊሊን አያይም? አሁን የእርሷ ኑሮ ፍቅር የሚያሻው ነው? እኔ ያየሁትን እንዴት እግዚአብሔር ሳያይ ቀረ? … አከራዬ እግዜርን መሰሉኝ። ይወተውታሉ፡፡ እግዜርን እንዲህ መራቅ ቢቻል፡፡… ከእሳቸው የተሻለ ያስብ ይሄን? ዓለም ሰብሳቢ እንዳጣ ጉባኤ የፍጡራን ኑሮ እንዲህ የተቀየጠው እሱ እያለ ነው? ወይስ ኒቼ እንዳለው እግዚአብሔር ሞቶ ይሆን?›› ታለ በእውነት ሥም
በዓለማየሁ ገላጋይ የትረካ ቀለማት እግዜር እልፍ ጊዜ አንሶ፣ ከተሰቀለበት ሰባተኛ ሰማይ ወርዶ በሁለት እግሮቹ የተለያየ ጫማ የተጫማውን የሰፈራችንን የእድር ጡሩምባ ነፊ መስሎ ለምናቤ ቀረበ። ቁምነገሩ ይህ ነው፡፡ እግዜር ሕልውናም ሆነ ማንነት የለውም፡፡ (God has neither existence nor essence.) ከፈለክ እግዜር የትም አለ፡፡ ከፈለክ እግዜር የትም የለም፡፡ እግዜርን ማየት ስትሻ ምኩራብና መቅደስ መኳተኑን ተውና መስታውት ፊት ቅረብ። ያኔ እግዚአብሔርን በዓይንህ በብሌኑ ትመለከተዋለህ፡፡ እሱ በልብህ መሻት የሆንከውን ይሆንልሃል፡፡ አየህ እግዜርን የምትፈጥረው አንተ ነህ፡፡ ጭብጡ ግን ሲበዛ ኮስታራ ነው፡፡
አፈክሮቱ በዚህች ቁንጽል ሀተታ ብቻ የሚቀነበብ አይደለም፡፡ ማን ያውቃል ንሸጣችንን መጠበቅ ከቻልን፣ ለዛሬ ሆነ ብለን ከዘለልናቸው ለዓለማየሁ ገላጋይ የሚላኩ ወቀሳዎች ጋር እንመለስበት ይሆናል፡፡ አንተ ግን አበጀህ!



Read 1385 times