Print this page
Friday, 01 October 2021 00:00

አንጋፋው ጋዜጠኛ ከበደ አኒሳ አረፉ

Written by 
Rate this item
(1 Vote)

በኢትዮጵያ የጋዜጠኝነት ታሪክ ፈር ቀዳጅ ከሆኑት መካከል አንዱ የነበሩት አንጋፋው ጋዜጠኛ ከበደ አኒሳ ከዚህ ዓለም በሞት ተለዩ፡፡
በአሜሪካ ማካልስተር ኮሌጅ ጋዜጠኝነት የተማሩት አቶ ከበደ፤ ‹‹የኢትዮጵያ ድምፅ›› እና ‹‹የዛሬይቱ ኢትዮጵያ›› ጋዜጦች ዋና አዘጋጅ እንዲሁም የአሜሪካ ድምፅ (VOA) ሪፖርተር ሆነው ሰርተዋል፡፡ ‹‹The Ethiopian Herald›› ጋዜጣ ላይም ሰርተዋል።
አቶ ከበደ ደርግ ከመመስረቱ ዘጠኝ ዓመታት በፊት፣ በ1957 ዓ.ም፣ “ኢትዮጵያ ትቅደም” የሚለውን  ቃል  በ‹‹የኢትዮጵያ ድምፅ›› ጋዜጣ ላይ መሪ መፈክር አድርገው ያሳተሙ ሰው ነበሩ፡፡   እርሳቸውም ‹‹በጋዜጠኝነቴ  ዘመን የላቀ ደስታ የሰጠኝ ነገር ቢኖር ‹የኢትዮጵያ ድምፅ› ጋዜጣ ላይ መሪ መፈክር አድርጌ ያስቀመጥኩት ‹ኢትዮጵያ ትቅደም› የሚለው ቃል ነው›› ብለው ተናግረው ነበር።
የአቶ ከበደ የሙያ አጋራቸውና ከ35 ዓመታት በላይ የቅርብ ወዳጃቸው የሆኑት አንጋፋው የሮይተርስ (Reuters) ጋዜጠኛ አቶ ፀጋዬ ታደሰ ስለዚህ ጉዳይ በሰጡት ምስክርነት ‹‹በወቅቱ ቀዳማዊ አፄ ኃ/ሥላሴ ‹ኢትዮጵያ ትቅደም ስትል ምን ማለትህ ነው?› ብለው ጠይቀውት ነበር። እሱም ‹ኢትዮጵያን ስለምወድ፣ ሕዝቡንም ስለማከብር ሃገሬ በሁሉ ነገር ቀድማ ማየት ስለምፈልግ ነው› ብሎ መልሷል›› በማለት ተናግረዋል።
አንጋፋው ጋዜጠኛ አቶ ከበደ በዘውዳዊው አገዛዝ ዘመን ማብቂያ ላይ በወሎ ተከስቶ የነበረውን ረሃብ ለእንግሊዛዊው የBBC ጋዜጠኛ ጆናታን ድምቢልቢ በማሳየት ረሀቡ ለዓለም ይፋ እንዲሆን ያደረጉ፤ ሙሉጌታ ሉሌን፣ ብዙ ወንድማገኘሁንና ሌሎች ጋዜጠኞችን ወደ ሙያው እንዲገቡና አርዓያ የሆኑና ለታላቅነት ያበቁ፤ ገብረክርስቶስ ደስታንና ሌሎች ገጣሚያንን እያበረታቱ ለክብርና ለዝና ያደረሱ  እንደሆኑም ይነገርላቸዋል፡፡ የመጀመሪያው የኢትዮጵያ ጋዜጠኞች ማኅበር ፕሬዝደንትም ነበሩ፡፡
ከጋዜጠኝነት በተጨማሪ በቆጵሮስ እና በእስራኤል የማኅበራዊ ሳይንስ ጥናቶችን ያጠኑት አቶ ከበደ፣ በመምህርነት፣ በትምህርት ቤት ሥራ መሪነት፣ በአገር አስተዳደር ሚኒስቴር እንዲሁም በሕዝባዊ ኑሮ እድገትና ዘመቻ መምሪያ  ለበርካታ ዓመታት አገራቸውን አገልግለዋል።
አቶ ከበደ አኒሳ የተወለዱት ታህሳስ 19 ቀን 1924 ዓ.ም በወለጋ ጠቅላይ ግዛት፣ ነቀምት ከተማ ሲሆን የአንደኛ ደረጃ ትምህርታቸውን በነቀምት ቀዳማዊ ኃ/ሥላሴ ትምህርት ቤት ካጠናቀቁ በኋላ የሁለተኛ ደረጃ ትምህርታቸውን ደግሞ በአዲስ አበባ መምህራን ማሰልጠኛ ኮሌጅ ተከታትለዋል።
አቶ ከበደ አኒሳ የዘጠኝ ልጆች አባት ሲሆኑ ስምንት የልጅ ልጆችንም ዐይተዋል።


Read 5425 times
Administrator

Latest from Administrator