Saturday, 02 October 2021 00:00

አሜሪካ በኢትዮጵያ መንግስት ላይ ተጨማሪ ማዕቀብ ለመጣል ዝታለች

Written by 
Rate this item
(5 votes)

የኢትዮጵያ መንግስት ከትናንት በስቲያ በተባበሩት መንግስታት ድርጅት የተለያዩ ተቋማት ውስጥ በከፍተኛ ሃላፊነት ላይ የሚሰሩ ሰባት ሰራተኞች በአገሪቱ የውስጥ ጉዳይ ጣልቃ ገብተዋል በማለት በ72 ሰዓታት ውስጥ አገሪቱን ለቀው እንዲወጡ ማዘዙን ተከትሎ፣ አሜሪካ ውሳኔውን “ፈጽሞ ተቀባይነት የሌለው ነው”  ስትል አውግዛለች።
የዋይት ሃውስ ፕሬስ ሴክሬተሪ ጄን ሳኪ ትላንት በሰጡት መግለጫ፤ “ያልተጠበቀውን የኢትዮጵያ ውሳኔ የአሜሪካ መንግስት አጥብቆ ይቃወማል” ብለዋል።
በተመሳሳይ፤ በአዲስ አበባ የሚገኙት የእንግሊዝና የጀርመን ኤምባሲዎች፤ ኢትዮጵያ፣ የመንግሥታቱ ድርጅት ሠራተኞች ግዛቱን ለቀው እንዲወጡ ማዘዟ እንዳሳሰባቸው አስታውቀዋል፡፡
ፕሬስ ሴክሬታሪዋ፣ ኢትዮጵያ የተመድ ሠራተኞችን ከአገር ለማስወጣት የወሰነችው፤ በሰሜኑ የአገሪቱ ክፍል በሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎች በረሃብ ምክንያት እየሞቱ ነው የሚል የማስጠንቀቂያ ሪፖርት ከወጣ በኋላ ነው ሲሉ ከሰዋል፡፡ ቃል አቀባይዋ፤ የኢትዮጵያ መንግሥት፣ የምግብ፣ መድኃኒትና ሌሎች ሕይወት አድን የሰብዓዊ አቅርቦቶች ለሚያስፈልጋቸው ወገኖች እንዳይደርሱ እንቅፋት መሆኑ እጅጉን አሳስቦናል ብለዋል።
“ሰብዓዊ እርዳታ አቅርቦትን ማደናቀፍ እና የራስን ዜጋ መሠረታዊ አማራጭን ማሳጣት ተቀባይነት እንደሌለው የተባበሩት መንግሥታት የጸጥታው  አባላትና ዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ለኢትዮጵያ መንግሥት ግልጽ እንዲያደርጉ ጥሪ እናቀርባለን” ብለዋል።
ፕሬስ ሴክሬታሪዋ ጨምረውም፤ ፕሬዝደንት ጆ ባይደን፣ በሰሜን ኢትዮጵያ የተከሰተው ጦርነት እንዲራዘም ምክንያት በሆኑ ግለሰቦች ላይ የፋይናንስ ማዕቀብ መጣል የሚያስችል ትዕዛዝ መፈረማቸውን አስታውሰዋል።
የሰብዓዊ ድጋፍ ሥራዎችን በሚያደናቅፉ አካላት ላይ ፕሬዚዳንቱ ያስተላለፉትን ውሳኔንም ሆነ “በእጃችን ያለ የትኛውንም አማራጭ ከመጠቀም ወደ ኋላ አንልም” ሲሉ አስጠንቅቀዋል፤ የዋይት ሃውስ ፕሬስ ሴክሬተሪ፡፡
የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ዋና ፀሐፊ፣ ኢትዮጵያ የተቋማቸው ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎችን ከአገር እንዲወጡ መወሰኗ “አስደንግጦኛል” ሲሉ ከትላንት በስቲያ መግለጻቸው አይዘነጋም፡፡
ዋና ፀሐፊው በመግለጫቸው፤ ሁሉም የተባበሩት መንግሥታት ሰብዓዊ ተግባራት የሚመሩት በሰብዓዊነት፣ከአድልዎ ነጻ በሆነ መንገድ፣በገለልተኛነትና በነጻነት መሆኑን አስታውሰው፤ በዚህም ድርጅታቸው በኢትዮጵያ በችግር ላይ ላሉ ሰዎች ምግብ፣መድኃኒት፣ ውሃና ንጽሕና መጠበቂያ የመሳሰሉ ሕይወት አድን እርዳታዎችን እያቀረበ ይገኛል ብለዋል።
“የሚመለከታቸው የመንግሥታቱ ድርጅት ሠራተኞች አስፈላጊ ሥራቸውን እንዲቀጥሉ ከኢትዮጵያ መንግሥት ጋር እየተነጋገርን ነው” ብለው ነበር።
የኢትዮጵያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር እርምጃውን በተመለከተ ለመንግሥታቱ ድርጅት በጻፈው ደብዳቤ፤ ግለሰቦቹ በአገሪቱ የውስጥ ጉዳይ ጣልቃ በመግባታቸው፣ በ72 ሰዓታት ውስጥ ኢትዮጵያን ለቀው እንዲወጡ መታዘዙን አስታውቋል፡፡
ከኢትዮጵያ በ72 ሰዓታት ውስጥ ከአገር እንዲወጡ የታዘዙት ተከታዮቹ የመንግስታቱ ድርጅት ከፍተኛ የሥራ ሃላፊዎች መሆናቸው ታውቋል፡፡
የተባበሩት መንግሥታት የሕጻናት አድን የኢትዮጵያ ተወካይ አደልኾደር
የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የሰብአዊ እርዳታ ማስተባበሪያ ጽህፈት ቤት ኃላፊ ማርሲ ቪጎዳ
የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የሰብአዊ እርዳታ መስተባበሪያ   የጽህፈት ቤቱ የሰላምና ልማት አማካሪ ክሰዌሲ ሳንስኩሎቴ
የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የሰብአዊ እርዳታ መስተባበሪያ ጽህፈት ቤት ምክትል ኃላፊ ሳኢድ ሞሐመድ ሄርሲ
የተባበሩት መንግሥታት የሰብአዊ መብት ድርጅት የክትትል፣ የሪፖርት እና አድቮኬሲ ቡድን መሪ ሶኒ ኦንዬግቡላ
የተባበሩት መንግሥታ ትድርጅት በኢትዮጵያ ምክትል የሰብዓዊ እርዳታ አስተባባሪ ግራንት ሌኢተይ እና
የተባበሩት መንግሥታት ተጠባባቂ የሰብአዊ እርዳታ አስተባባሪ ጋዳ ኤልታሂር ሙዳዊ
ፕሬስ ሴክረተሬዋ “ኢትዮጵያ የመንግስታቱ ድርጅት ሰራተኞችን ከአገር ለማስወጣት የወሰነችው በሰሜኑ የአገሪቱ ክፍል በሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎች በረሃብ ሳቢያ እየሞቱ ነው የሚል ሪፖርት ከወጣ በኋላ  ነው  ሲሉ ከሰዋል።
በአዲስ አበባ የሚገኙት የእንግሊዝና የጀርመን ኤምባሲዎችም፤ በተመሳሳይ የኢትዮጵያ መንግስት የመንግስታቱ ድርጅት ሠራተኞች ግዛቱን ለቀው እንዲወጡ ማዘዙ እንዳሳሰባቸው በመግለጽ፣ መንግስት እርምጃውን ዳግም እንዲያጤነው ጠይቀዋል።

Read 21325 times