Sunday, 03 October 2021 18:06

ጥናትና ፅናት የእድገት እርሾ ነው!

Written by 
Rate this item
(3 votes)

ከዕለታት አንድ ቀን፣ አንድ ለምድር ለሰማይ የከበደ የንጉሥ ልጅ፣ ያማረ ሠረገላውን አሳጥቦ፣ አስወልውሎ  ታጭታልሃለች የተባለችውን ቆንጆ ልጅ ለመጀመሪያ ጊዜ ሊያይ፤ አሽከር አስከትሎ ወደ ሩቅ  አገር ሊሄድ ተነሳ።
አባቱ የተከበሩ አንቱ የተባሉ ስመ-ጥር ጀግና፣ ከትውልድ ትውልድ ከሚከታተለው ሥርወ-መንግስት የመነጩ፣ የተከበሩ ሰው ናቸው። ልዑሉም ሊሰናበታቸው ወደ ዙፋናቸው ቀረበና፤
ልዑሉ- “ንጉሥ ሆይ! እንግዲህ ወደ ሩቅ አገር መጓዜ ነውና ፈቃድ ይሰጠኝ?”
ንጉሡም- “ወደ የት ልትሄድ ተነሳህ?”
ልዑል- “ወደ ሩቅ አገር ነው የምሄደው።”
ንጉሥ- “እሺ መሄዱንስ ሄድክ፣ ምን ልታደርግ ነው የምትሄደው?”
ልዑሉ “ንጉሥ ሆይ! ታጭታልሃለች የተባልኳትን ቆንጆ ልዕልት፣ ቁንጅናዋንና ሰብዕናዋን ሳላይና ሳላውቅ ላገባ አልሻምና ሄጄ ማረጋገጥ ይኖርብኛል”።
ንጉሥ- “እኛ ለልጃችን ክፉና የማይሆን ነገር እንመኛለን?”
ልዑል- “አይደለም ንጉሥ ሆይ! የእናንተን ደግነት ከቶም ተጠራጥሬ አላውቅም። ሆኖም በእናንተ ውሳኔ ላይ የእኔም አስተያየት ቢታከልበት፣ ነገሩን ያጠነክረዋል እንጂ አያላላውም! ዞሮ ዞሮ ከእናንተ ፍቃድ አልወጣም።”
ንጉሥ- “ደህና፣ ሂድ። ለማንኛውም አንድ አሽከር በቅሎ ይዞ ይከተልህ። ደህና ግባ።”
ልዑሉ ምስጋና አቅርቦ የተመደበለትን አሽከር ይዞ መንገዱን ቀጠለ።
ከከተማው ወጣ እንዳሉ አንድ መንገደኛ ያገኛሉ፤
 መንገደኛውም - “እባክህ ጌታዬ አፈናጠኝና ጥቂት መንገድ አብረን እንግፋ” አለው።
ልዑሉም ደግ ሰው ነበርና፤
“ና ውጣ” አለው።
አሽከርየው ግን፣
“እኔ ይህ ሰው ከእርስዎ ጋር መሄዱ ቅር ብሎኛል። ደረጃው አይፈቅድም “ አለው።
ልዑሉም- “ግዴለም። ይሄ ሰውና እኔ በሰውነታችን አንድ ነን። ምናልባትም የጊዜና የቦታ ጉዳይ ሆኖ እንጂ የተሻለ እጣ-ፈንታ ያለው ሰው ይሆናል። ስለዚህ ይውጣና አብሮን ይሂድ” ሦስቱም አብረው ተያይዘው መንገድ ቀጠሉ።
ጥቂት እንደተጓዙ ተፈናጣጩ ሰው ልዑሉን እንዲህ ሲል ጠየቀው፡
 “እንዴት ያለህ ደግ ሰው ነህ? ምንም የማታውቀኝን ሰው መጫንህ አስገርሞኛል። አንተ ማን ነህ?” ሲል ጠየቀው።
ልዑሉም- “እኔ ልዑል ነኝ” አለው።
 ተፈናጣጩ ሰውም- “ልዑል ማለት ምን ማለት ነው?” ሲል ጠየቀው።
ልዑል- “ልዑል ማለት በየመንገዱ ሰዎች ቆመው የሚያሳልፉት እጅ የሚነሱት ነው፤ አሁን መንገድ ላይ የሚሆነውን ተከታተል” ሲል መለሰለት።
ጥቂት እንደሄዱ እውነትም ሰው ሁሉ ቆሞ፣ እጅ እየነሳ ያሳልፋቸው ጀመር።
ልዑሉ ወደ ተፈናጣጩ ዞሮ፤
“አሁንስ ልዑል ማን እንደሆነ አወቅህ?”
ተፈናጣጭ- “አዎን”
ልዑል- “ማን ነው?”
ተፈናጣጭ- “እንግዲህ ወይ እኔ ወይ አንተ ነሃ” አለው።
*   *   *
የአንድን አገር ልዑል አገሬው ሳያውቅ ከቀረ ትልቅ እርግማን ነው። ተገዥው ገዥው ማን እንደሆነ ሳያውቅ የሚኖርበት ሁኔታ አለ እንደ ማለት ነው። አሳሳቢ ሁኔታ አለ እንደ ማለትም ነው። በዚህ ዓይነት መንፈስ፣ መሪው ተመሪውን  ህዝብ  እንደምን ሊያውቀው ይችላል?  ስለዚህ፤ ምንም እንኳን የሥራ ድርብርብና ጫና ሰንጎ ሊይዛቸው ቢችልም፤ የአገራቸውን ፖለቲካዊ ችግር ብቻ ሳይሆን፣ የኢኮኖሚ ነገረ-ሥራውን ሁሉ በሚገባ ማጤን ይገባቸዋል፡ ለዚህም ዋናና ቁልፍ ናቸው ከሚባሉት ጉዳዮች አንዱ ከሙያው ጋር አግባብ አላቸው የሚባሉ ሁነኛ ምሁራንን አሰባስቦ መምከር ነው። የሚቀጥለው ዋና ነገር የምሁራኑን አስተያየት በቅጡ ማዳመጥና ስራዬ ብሎ ለሥራ መዘጋጀት ነው። ከዚህ በኋላ እንግዲህ አስፈላጊውን ግብረ-ሃይል በተጠናከረ ሁኔታ አደራጅቶ ማሰማራት  ነው። የዚህ  ሁሉ ጉዳይ መጠቅለያው ቆራጥ አቋም ነው። ቆራጥነትም ቢሉ ዘላቂና የተቀናጀ መሆን ይኖርበታል “Sustainable and Integrated” እንዲሉ”፡፡
ይህ በፈንታው አንድ ፈታኝ ጥያቄ ላይ ያነጠጥራል። ይኸውም ቁጥጥር ማድረግና የስራ ግምገማን ማካሄድ ነው። (Monitoring and Evaluation እንዲሉ)  ቀጥሎ ደግሞ ሳይታክቱ “የሰራነው ሁሉ የት ደረሰ?” ማለት ያሻል። ችግኝ ተክሎ ማደግ አለማደጉን አለመከታተል፣ ካለመትከል እኩል ነው፡፡ ቸልተኝነትም አንድ የልማድ ዘርፍ ነው። ሎሬት ፀጋዬ ገ/መድህን፤
“ዛሬ ለወግ ያደረግኸው፣ ወይ ለነገ ይለምድብሃል
ልማድ ፊት እንዳሳዩት ነው፣ ወይ ይጠፋል ወይ  ያጠፋል
ከርሞም የሰለጠነ እንደሁ፣ ተፈጥሮ ይሆናል ይባላል” ይለናል።
ከላይ የተዘረዘሩትን አበክረን ስንገነዘብ ልማድ በእኛ ላይ በሰለጠነ ቁጥር- በተለይ አሉታዊው ፈሊጥ- ሚዛናዊነትን ያሳጣናል። ያ ደግሞ ሁለንተናዊነታችንን ይሰልብብናል። ስለዚህ በጥናት ላይ መመሥረት ዋና ነገር ነው። ያንን በፅናት ማጠናከር ደግሞ ለዘላቂነት ብርቱ መነሻ ነው።
ጉዞህን በእርምጃህ መጠን ለካ፣ አልጋህን በቁመትህ ልክ አድርግ። ከሁሉም በላይ ደግሞ፣ ማረፍ ካለብህ እረፍ (Rest If you Must) ሆኖም አርፈህ መቅረት የለብህም። ቆይተህ መንቀሳቀስ፣ ብሎም መለወጥ ግዴታህ መሆኑን አትርሳ። ሊቃውንት (A change is as good as rest)  ለውጥ የእረፍት መልካም እኩያ ነው፤” የሚሉን ለዚህ ነው።
ወጣም ወረደም ህይወታችን ይለመልም ዘንድ ምንጊዜም ጥናትና ጽናትን ከልቡናችን አለመነጠል ከፍተኛ ፋይዳ እንዳለው ሳናሰልስ እናስብ!
አዲሱ ዓመት የሰላምና የፍቅር እንዲሆን ትምህርታችንን ይግለጥልን!

Read 13801 times