Sunday, 03 October 2021 18:05

ወድቀው የተነሱ የዓለማችን ታላላቆች

Written by 
Rate this item
(0 votes)

የዓለማችንን ቁጥር 1 ስኬታማ ሰዎች ታሪክ ስትመረምሩ፣ ማናቸውም ቢሆኑ በአንድ ጀንበር የስኬት ማማ ላይ እንዳልወጡ ትገነዘባላችሁ። ብዙዎቹ አንድ ጊዜ ወይም ሁለት ጊዜ ብቻ ሳይሆን በተደጋጋሚ ውድቀትና ሽንፈት አጋጥሟቸዋል፡፡ ሥራ ከመቀጠራቸው በፊት ብቁ እንዳልሆኑ እየተነገራቸው ብዙ ጊዜ ተባረዋል፡፡ ዩኒቨርሲቲ ወይም ኮሌጅ ለመግባት ደጋግመው ገና በታዳጊነቱ አመልክተው በመግቢያ ፈተናዎች ላይ ደጋግመው ይወድቃሉ፡፡ የተለያዩ ቢዝነሶች ጀምረው በኪሳራ ዘግተዋል፡፡ የማታ ማታ ግን የስኬት ማግ ላይ ይወጣሉ ወድቀው ወይም ተሸንፈው አይቀሩም፡፡
የአሁኑ ተራማጅ ኩባንያ አፕል፤ በሁለት ሰዎች ትብብር፣ በጋራዥ ውስጥ ነበር የተቆረቆረው፡፡ ከዓመታት በኋላ፤ ከ400 በላይ ሰራተኞችን የሚያስተዳድር፣ የ2.ቢሊዮን  ዶላር ኩባንያ ለመሆን በቅቷል።
ስቲቭ ጆብስ ግን ራሱ ከመሰረተው ኩባንያ ለማመን በሚያዳግት መልኩ ተባረረ፡፡ ይሄን ጊዜ Next እና Pixar የተሰኙ ተጨማሪ የቢዝነስ ዘርፎችን ፈጠረ። የማታ ማታም፣ ወደ ተባረረበት ወደመሰረተው ኩባንያ ተመልሶ ዋና ሥራ አስፈፃሚ ለመሆን በቃ፡፡ በወቅቱ ባይታየኝም፣ ከኩባንያው መባረሬ በእጅጉ ጠቅሞኛል ይላል-ስቲቭ ጆብስ፡፡ ከኩባንያው መባረሩ ተስፋ አላስቆረጠውም። ለተጨማሪ ፈጠራና ትጋት አነቃው እንጂ።
የሃርቫርድ ትምህርቱን አቋርጦ የወጣው ቢል ጌትስ፤ ከሌሎች ጋር በመሆን Traf-o- Data የተሰኘ የበኩር ኩባንያ አቋቁሞ ነበር። ምን ያደርጋል? በአመራር ክህሎት ማነስ በኪሳራ ተዘጋ፡፡ ነገር ግን ለኮምፒዩተር ፕሮግራሚንግ በነበረው ክህሎትና ጥልቅ ፍቅር የተነሳ፤ ፈር ቀዳጁን የሶፍትዌር ኩባንያ፣”ማይክሮ ሶፍት” ለመመስረት በቃ፡፡ ውድቀቱንም ወደ ስኬት ለወጠ፡፡ በ31 ዓመት ዕድሜውም የዓለማችን ወጣቱ ቢሊዬነር ለመሆን ቻለ። ቢል ጌትስ በራሱ አንደበት ሲናገር  “ስኬትን ማጣጣም ሸጋ ነው፤ ግን ከውድቀት መማር የበለጠ ጠቃሚ ነው፡፡” ይላል።
አብርሃም ሊንከን ለሽንፈትና ውድቀት እንግዳ አልነበረም፡፡ እ.ኤ.አ በ1831 በቢዝነስ ሥራው ኪሳራ ገጥሞታል፡፡ በ1836 ዓ.ም በነርቭ ህመም ክፉኛ ተሰቃይቷል፡፡ በ1856 ዓ.ም ለአሜሪካ ፕሬዚዳንትነት ተወዳድሮ ተሸንፏል።
ይሄ ሁሉ ውድቀት ግን ተስፋ አላስቆረጠውም፡፡ ደጋግሞ ከመሞከርም አላቦዘነውም፡፡ በዚህም የተነሳ እ.ኤ.አ በ1861 ዓ.ም በምርጫ ተወዳድሮ የአሜሪካ 16ኛው ፕሬዝዳንት ሆኖ ለመመረጥ በቃ፡፡
የቱንም ያህል ሽንፈት ብትጋፈጥ፣ ስኬት ከመቀዳጀት የሚያግድህ ነገር የለም፡፡
የሚኪ ማውዝ ፈጣሪ የሆነው ዋልት ዲዝኒ፣ የሁለተኛ ደረጃ ትምህርቱን ያቋረጠው የአሜሪካ ጦር ሰራዊቱን ለመቀላቀል ነበር፤ ግና አልተሳካለትም? ከትምህርቱም ከውትድርናውም ሳይሆን ቀረ ከቀደምት ቢዝነሶቹ አንዱ የነበረውን “Lough-0-Gram Studios” የዘጋው በአመራር ችሎታ ማነስ  ከስሮ ነው፡፡ በአንድ ወቅት ደግሞ “ በቂ የፈጠራ ችሎታ የለህም” ተብሎ ከሚሰራበት የሚዙሪ ጋዜጣ መባረሩ ተዘግቧል፡፡
ዛሬ ግን ዲዝኒ፣ የብዙ ትውልድ ህጻናት ትውስታና ህልም ለመሆን በቅቷል። ዲዝኒ ገና ወደ ፊት አያሌ መጪ ትውልዶችን ማዝናናቱን ይቀጥላል። ልብ በሉ! ከስኬታማ ሰው ጀርባ አያሌ ያልተሳኩ ዓመታት አሉ፡፡

Read 1876 times