Tuesday, 05 October 2021 00:00

811 ሚ. ህዝብ በተራበባት አለም በየአመቱ 1.3 ቢ. ቶን ምግብ ይባክናል

Written by 
Rate this item
(0 votes)

የአለማችን እጅግ ደሃ አገራት ወደባሰ ድህነት መግባታቸው ተነገረ

በየአመቱ በመላው አለም እየተመረተ ለተጠቃሚዎች ከሚቀርበው ምግብ ውስጥ 17 በመቶ ያህሉ ወይም 1.3 ቢሊዮን ቶን ምግብ ጥቅም ላይ ሳይውል ወደ ቆሻሻ ማጠራቀሚያ እንደሚገባ፣ የአለም የምግብና የእርሻ ድርጅት፣ ከሰሞኑ ባወጣው መረጃ አስታውቋል፡፡
811 ሚሊዮን ህዝብ የረሃብ ተጠቂ በሆነባት አለም በየአመቱ 1 ትሪሊዮን ዶላር የሚያወጣ ምግብ መባከኑ እጅግ አሳዛኝ ነው፤ መንግስታት ለጉዳዩ ትኩረት ሊሰጡት ይገባል ብሏል፡፡
የምግብ ብክነት ያደጉ አገራት ብቻ ሳይሆን የድሃ አገራትም ችግር ነው ያለው ድርጅቱ፤ 2 ቢሊዮን ያህል ሰዎች የተመጣጠነ የምግብ እጥረት ተጠቂዎች በሆኑባት አለም የሚባክነው ምግብ ጉዳቱ የከፋ ነው ብሏል፡፡
በሌላ ዜና ደግሞ፤  የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የንግድና የልማት ጉባኤ ሰሞኑን ባወጣው የ2021 የፈረንጆች አመት ሪፖርቱ፣ ከአለማችን አጠቃላይ ህዝብ 15 በመቶ ያህሉ የሚኖርባቸው 46 የአለማችን እጅግ ደሃ አገራት በአመቱ ወደባሰ ድህነት መግባታቸውን አስታወቀ፡፡
አገራቱ በተለይ ከኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ ጋር በተያያዘ ኢኮኖሚያቸው ከፍተኛ ጉዳት እንደደረሰበት የጠቆመው ሪፖርቱ፣ የአጠቃላይ የአገር ውስጥ ምርት የነፍስ ወከፍ ገቢ ድርሻቸውን አብዛኞቹ አገራት ከወረርሽኙ በፊት ወደነበረው ለመመለስ አምስት አመትና ከዚያ በላይ ጊዜ ሊፈጅባቸው እንደሚችልም አሳስቧል፡፡
አገራቱ በ2020 የፈረንጆች አመት ያስመዘገቡት የኢኮኖሚ ዕድገት በሦስት አስርት አመታት ታሪካቸው እጅግ ዝቅተኛው እንደሆነ የጠቆመው ሪፖርቱ፣ አገራቱ ምርታቸውን ማሳደግና መዋቅራዊ የኢኮኖሚ ትራንስፎርሜሽን በአለማቀፍ ንግድ ተወዳዳሪ መሆን እንዲችሉ ከፍተኛ የፋይናንስ ድጋፍ እንደሚያስፈልጋቸውም አመልክቷል፡፡ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት፣ እጅግ ድሃ አገራት ብሎ ከሚጠራቸው የአለማችን 46 አገራት ውስጥ  33ቱ በአፍሪካ፣ 9ኙ በእስያ፣ 3ቱ በፓሲፊክ አይስላንድ አገራት፣  አንዷ ደግሞ በደቡብ አሜሪካ እንደምትገኝም መረጃው ያሳያል፡፡

Read 10526 times