Monday, 04 October 2021 00:00

በበርሊን ማራቶን ሪከርድ ባይኖርም ከፍተኛው ውጤት የኢትዮጵያ ነው

Written by  ግሩም ሠይፉ
Rate this item
(0 votes)

በተያያዘ ከሳምንት በፊት በተካሄደው የበርሊን ማራቶን የኢትዮጵያ አትሌቶች በሁለቱም ፆታዎች ከፍተኛውን ውጤት አስመዝገበዋል፡፡ በወንዶች ምድብ  ጉዬ አዶላ በ2፡05፡45 ሰዓት ሲያሸንፍ ለዓለም ሪከርድ  የተጠበቀው   ቀነኒሳ በቀለ ሶስተኛ እንዲሁም ታዱ አባተ አራተኛ ደረጃን አግኝተዋል፡፡ በሴቶች ምድብ ከአንደኛ እስከ ሶስተኛ ስፍራ የያዙት ኢትዮጵያውያን ሲሆን ጎተይቶም ገብረስላሴ  በመጀመርያ የማራቶን ውድድሯ 2 ሰዓት ከ20 ደቂቃ ከ09 ሰኮንዶች በማስመዝገብ ስታሸንፍ ሕይወት ገብረ ኪዳንና ሄለን  ቶላ በሁለተኛ እና ሶስተኛነት ደረጃ አግኝተው የሽልማት መድረኩን ተቆጣጥረዋል፡፡  ከኮሮና ቀውስ በኋላ የዓለማችን ትልልቅ ማራቶኖች በተመለሱበት የ2021 የውድድር ዘመን የመጀመርያው የሆነው የበርሊን ማራቶን ከፕሮፌሽናል አትሌቶች ባሻገር ከ25ሺ በላይ ተሳታፊዎችን አግኝቶ ከኮቪድ 19 ስጋት ውጭ የሆነ ውድድር በማካሄዱ ተምሳሌት ሆኖ ተጠቅሷል፡፡ ከውድድሩ በፊት ተሳታፊዎች በሙሉ ክትባት የወሰዱ እንዲሆኑና በቦታው የፒሲአር ቴስት እንዲወስዱ ተሰርቷል። በአጠቃላይ የተገኘው ተመክሮም በቀጣይ ሳምንታት ለሚካሄዱት የለንደን፤ የቦስተን፤ የቺካጎ እና የኒውዮርክ ማራቶኖች የሚጠቅም ይሆናል፡፡
በ43ኛው የበርሊን ማራቶን ላይ የዓለም ማራቶን ሪከርድ ለማሻሻል የተደረገው ሙከራ ሳይሳካ መቅረቱ ብዙ የአትሌቲክስ ሚዲያዎችን ያነጋገረ አጀንዳ ሆኗል፡፡ በተለይ ኢትዮጵያዊው አትሌት ቀነኒሳ በቀለ አግኝቶ የነበረው ትኩረት ከፍተኛ እንደነበር አይዘነጋም፡፡
የበርሊን ማራቶን  ለዓለም ሪከርድ ምቹ መሆኑ ሪከርድ እንዲጠበቅ ዋናው ምክንያት ነበር፡፡ ባለፉት 20 ዓመታት በወንዶች ምድብ 7 የተለያዩ የዓለም ሪከርዶች በስፍራው ተመዝግበዋል። 5 ጊዜ በኬንያውያን ሲሆን ፖል ቴርጋት(2፡04፡55)  በ2003፤ ፓትሪክ ማኩ (2፡03፡38) በ2011፤ ዊልሰን ኪፕሳንግ (2፡03፡23) በ2013፤ ዴኒስ ኪሜቶ (2፡02፡57) በ2014  እና ኤልዊድ ኪፕቾጌ በ2018 እኤአ ላይ፤  ሁለት ጊዜ ደግሞ በኢትዮጵያው  ኃይሌ ገብረስላሴ (2፡04፡26) በ2007 እና   (2፡03፡59) በ2008 እኤአ ላይ ያስመዘገቧቸው ናቸው፡፡
ዘንድሮም በአዲስ ክብረወን ታሪክ ሊሰራበት እንደሚችል ቢጠበቅም በውድድሩ ላይ በአየር ሁኔታው ከፍተኛ ሙቀት መመዝገቡና በአሯሯጮች ላይ የነበረው ድክመት እንዳይሳካ አድርጎታል። በ2018 እኤአ በበርሊን ማራቶን ላይ ኬንያዊው ኤሊውድ ኪፕቾጌ  2፡01፡39 በሆነ ጊዜ የዓለም ሪከርዱን ሲያስመዘግብ በማራቶኑ ርቀት የመጀመርያው ግማሽ በ61፡05 ደቂቃዎች ሁለተኛው ግማሽ ደግሞ በ60፡26 ደቂቃዎች ተሩጦ ነበር፡፡
ዘንድሮ የመጀመርያውን ግማሽ በ60፡ 48 ደቂቃዎች ከዚያም ሁለተኛውን ግማሽ በ64፡ 57 ደቂቃዎች መሸፈኑ ታውቋል። አትሌት ቀነኒሳ በቀለ ሪከርድ ለመስበር ባይችልም የማራቶን ውድድሩን በሶስተኛ ደረጃ በማጠናቀቁ ተደንቋል፡፡
ከአምስት ሳምንት በኋላ በ50ኛው የኒውዮርክ ማራቶን ላይ ሲሳተፍ ጤናማ በመሆኑና በቂ የልምምድ ጊዜ ከኖረው የተሻለ ውጤት ለማስመዝገብ እንደሚችልም ተወስቷል፡፡

Read 2827 times