Tuesday, 05 October 2021 00:00

በለንደን ማራቶን ኢትዮጵያውያኑ ደካማውን የኦሎምፒክ ውጤት ሊያካክሱ ይችላሉ

Written by  ግሩም ሠይፉ
Rate this item
(1 Vote)

በ2020 እኤአ ላይ በኮሮና ቀውስ በርካታ ትልልቅ የማራቶን ውድድሮች ቢሰረዙም ፕሮፌሽናል አትሌቶችን በማሳተፍ የተካሄደው  የለንደን ማራቶን ነበር፡፡ ዘንድሮ በታሪኩ ለ41ኛ ጊዜ ነገ ሲካሄድ ከ40ሺ በላይ ሯጮችን እንደሚያሳትፍና አስደናቂ ፉክክር እንደሚታይበት ተጠብቋል፡፡ በሁለቱም ፆታዎች 11 የኢትዮጵያ አትሌቶች የሚሳተፉ ሲሆን በቶኪዮ 2020 ኦሎምፒክ ላይ የነበራቸውን ደካማ ውጤት የሚያካክሱበት ውጤት ለማግኘት ተስፋ አድርገዋል፡፡ ዘንድሮ የለንደን ማራቶንን ልዩ የሚያደርገው  በፈጣን ሰዓት፤ በቦታው ሪከርድና በዓለም ሪከርድ ዙርያ ለሚመዘገቡ ምርጥ ሰዓቶች ከፍተኛ የሽልማት ገንዘብ በመቅረቡ ነው፡፡ በሁለቱም ፆታዎች ቀዳሚ ሆነው ለሚገቡት አትሌቶች 55ሺ ዶላር በነፍስ ወከፍ እንደሚሸለም ሲታወቅ ፤ ለቦታው ሪከርድ 25ሺ ዶላር እንዲሁም ለዓለም የማራቶን ሪከርድ 125ሺ ዶላር መዘጋጀቱም ተገልጿል፡፡
በወንዶች ምድብ በ2020 እኤአ ላይ ያስመዘገበውን ውጤት ይደግማል በሚል ከፍተኛ ትኩረት ያገኘው ሹራ ኪታታ ሲሆን ብርሃኑ ለገሰ፤ ሞስነት ገረመው እና ሲሳይ ለማ ከፍተኛ ፉክክር እንደሚያሳዩ የተጠበቁ ኢትዮጵያውያን ናቸው፡፡ የውድድሩ አዘጋጆች እንዳስታወቁት በተለይ በወንዶች ምድብ  ለምርጥና ፈጣን ሰዓቶች ከፍተኛ የቦነስ ክፍያዎች ማቅረባቸውን ሲሆን ይህም የዓለም ማራቶን ሪከርድ የሚሻሻልበትን ትንቅንቅ ሊፈጥር ይችላል፡፡ ከ2 ሰዓት 2 ደቂቃዎች በታች 150ሺ ዶላር፤ ከ 2 ሰዓት 3 ደቂቃዎች በታች 100ሺ ዶላር፤ ከ 2 ሰዓት 4 ደቂቃዎች በታች 75ሺ ዶላር እንዲሁም ከ2 ሰዓት 5 ደቂቃዎች በታች 50 ሺ ዶላር እንደሚበረከት ተገልጿል፡፡
ሹራ ኪታ በማራቶን የአሸናፊነት ክብሩን ለማስጠበቅ ከኢትዮጵያ እና ኬንያ አትሌቶች ከፍተኛ ፉክክር ቢጠብቀውም ስለ ውድድሩ በተዘጋጀው መግለጫ ላይ በሰጠው አስተያየት "መቶ በመቶ ከጉዳት ነፃ ነኝ፤ የተሟላ ዝግጅትም አድርጊያለሁ። ባለፈው ዓመት በጠንካራ አቋም ባስመዘገብኩት ውጤት እጅግ ደስተኛ ነበርኩ፤ በመላው ኢትዮጵያ ከፍተኛ ክብር ያገኘሁበትና የኮራሁበት ነበር፡፡›› ብሏል፡፡ በማራቶን 2 ሰዓት ከ2 ደቂቃ ከ48 ሰከንዶች በሆነ ጊዜ ሶስተኘሳውን ፈጣን ሰዓት ያስመዘገበውና በቶኪዮ ማራቶን ለሁለት ጊዜያት ያሸነፈው ብርሃኑ ለገሰ በበኩሉ  "በንግሊዝ ማራቶን ስሮጥ ለመጀመሪያ ጊዜ ነው። በዚህም በጣም ደስተኛ ነኝ እናም ለማሸነፍም ተዘጋጅቻለሁ። ያለፉት 18 ወራት ለሁላችንም በጣም ከባድ ነበር፣ ግን ሁሉም ነገር ወደ መደበኛው በመመለሱ ደስተኛ ነኝ።  ማራቶኑን ከተሳታፊ ህዝብ በማድረጋችን ተደስቻለሁ። በእኛ እና ኬንያውያን ከባድ ፉክክር እጠብቃለሁ" ሲል ተናግሯል፡፡
በሴቶች ምድብ የማራቶኑን ርቀት ከ2 ሰዓት 19  ደቂቃዎች በታች የሚገቡ 5 አትሌቶች እንዲሁም ከ2 ሰዓት ከ20 ደቂቃዎች በታች የሚገቡ ከ9 በላይ አትሌቶች  መሳተፋቸውም የዓለም ሪከርድ የሚሰበርበትን እድል ያሰፋዋል ተብሏል፡፡ በ2 ሰዓት ከ14 ደቂቃ ከ04 ሰከንዶች በሆነ ጊዜ የዓለም ሪከርድን ያስመዘገበችውና በቶኪዮ ኦሎምፒክ የብር ሜዳልያ የተጎናፀፈችው የኬንያዋ  ብርጊድ ኮሴጊ ባለፉት ሶስት ዓመታት በተሳተፈችባቸው የማራቶን ውድድሮች አለመሸነፏ ከፍተኛ ግምት አሰጥቷታል። በቶኪዮ ኦሎምፒክ ጠንካራ ተሳትፎ  የነበራቸው ከ6 በላይ አትሌቶች መወዳደራቸው ፉክክሩን እንደሚያጠነክረውም ተወስቷል፡፡ በለንደን ማራቶን ጊዜ በማሸነፍ ታሪክ ለመስራት ያቀደችው ብርጊድ ኮሴጊ ከኦሎምፒክ ወዲህ በነበሩት ስምንት ሳምንታት ከፍተኛ ዝግጅት ስታደርግ ቆይታለች፡፡ ስለውድድሩ በተዘጋጀው ጋዜጣዊ መግለጫ በሰጠችው አስተያየትም "ለንደንን አፈቅራታለሁ፡፡ በደንብ ዝግጅት በማድረጌ የአሸናፊነት ክብሬን ለማስጠበቅ እፈልጋለሁ" ብላለች፡፡ ለኢትዮጵያውያኑ አትሌቶች ሮዛ ደረጀ፤ ብርሃኔ ዲባባ፤ ደጊቱ አዝመራው፤ ዘይነባ ይመር፤ ትእግስት ግርማ፤ አሸቴ በከሬና መገርቱ አለሙም ከፍተኛ ግምት ተሰጥቷል፡፡ በ2019 እኤአ ላይ የቫሌንሽያ ማራቶንን ያሸነፈችው እና በቶኪዮ ኦሎምፒክ በ4ኛ ደረጃ ዲፕሎማ የወሰደችው ሮዛ ደረጀ እንዲሁም በቶኪዮ ማራቶን ሁለቴ ያሸነፈችው ብርሃኔ ዲባባ ለድል አድራጊነት የተጠበቁ ናቸው፡፡ ከኢትዮጵያ አትሌቶች  ከውድድሩ በፊት በተዘጋጀው መግለጫ ላይ የተሳተፈችው ብርሃኔ ዲባባ "የውድድሩ አዘጋጆች ከአስቸጋሪ ሁኔታዎች ላይ ማራቶኑን ማካሄዳቸውን አደንቃለሁ፡፡ የተሟላ ዝግጅት አድርጌያለሁ፡፡ ልክ እንደ ሁሉም አትሌቶች እዚህ የመጣሁት ውድድሩን ለማሸነፍ ነው።" በማለት አስተያየት ሰጥታለች፡፡
ባለፉት 40 የለንደን ማራቶኖች ላይ ከፍተኛውን ውጤት ያስመዘገበችው ኬንያ  13 ጊዜ በወንዶች እንዲሁም 10 ጊዜ በሴቶች ምድብ በማሸነፍ ሲሆን፤ የኢትዮጵያ አትሌቶች ደግሞ በሁለቱም ፆታዎች 7  ጊዜ አሸንፈዋል፡፡ በወንዶች በ2003 እኤአ ገዛሐኝ አበራ በ2010 እና በ2013 ፀጋዬ ከበደ ፤ በ2020  እኤአ ሹራ ኪታታ እንዲሁም በሴቶች በ2001 ደራርቱ ቱሉ፤ በ2010 አሰለፈች መርጊያ እና በ2015 እአኤአ  ትግስት ቱፋ አሸናፊዎች ነበሩ፡፡

Read 12874 times