Sunday, 03 October 2021 18:52

‘ወፍዬ’

Written by  ዘናይን ሐርት
Rate this item
(0 votes)


ክፍል 1    
በአዲስ አበባ ከተማ በሃብት ከናጠጠ ቤተሰብ ነበር የተወለድኩት፡፡ ገና በዘጠኝ ዓመቴ ከግቢዬ ወጥቼ በአራት ኪሎና በቤተ-መንግስቱ ጎዳናዎች እንደ ልብ ስንሸራሸር፣ ተመለሺ ብሎ የሚቆጣኝ የቤተሰቡ አባል አልነበረም፡፡አንድ ቀን ለዘጠነኛ ዓመት የልደት በዓሌ የተገዛልኝን ውብ ቀሚስ ለብሼ በለመድኩት ጎዳና ስጓዝ ከመኪናዉ ወርዶ ወደ ግቢዉ የሚያመራ ሰዉ አየሁና ተከተልኩት፡፡ ዞር ብሎም ሳያየኝ ወደ ግቢዉ ገብቶ በሩን ከረቸመዉ። ከዛን ቀን ጀምሮ ያን ግቢ አዘወተርኩ፡፡ አንድ ቀን ግን ያልታሰበ ነገር ተከሰተ፡፡ የግቢዉ በር ክፍት ነበር፡፡ ወደ ዉስጥ ገባሁ፡፡ በአንደኛዉ ክፍል ሃይለኛ የሆነ የበገና ዜማ ይንቆረቆራል፡፡ የዜማዉን መስመር ተከትዬ ወደ ክፍሉ ሰተት ብዬ ገባሁ፡፡ ለካ ሰዉዬዉ የተዋጣለት የበገና ደርዳሪ ኖሯል፡፡ በሶፋ ላይ ተቀምጦ በገናዉን ሲደረድር ‘ዓይኔን ጨፍኜ በእርካታ ሰባቱን ሰማየ ሰማያት መጠቅሁ፡፡ የበገናዉ ዜማ ሲቋረጥና ከተመስጦዬ ስመለስ፣ የሰዉየዉ ሸካራ እጆች እንገቴን እየጠመዘዟት ነበር፡፡
“ለምን መጣሽ?” አለኝ በቁጣ
ዝም
“እኮ ንገሪኝ.. ምን ፈለግሽ? “
ዝም
በሁለት እጆቹ ወደ ላይ ሲያነሳኝ በመስኮት ወደ ዉጭ የሚወረዉረኝ መስሎኝ ደነገጥኩ፡፡ ትንፋሼ ተቆራረጠ። መልሶ ከሶፋዉ ዘፍ አድርጎኝ ሲጋራዉን ለኮሰ፡፡ አንድ ሲጋራ አጪሶ እስኪጨርስ ምንም አልተነጋገርንም፡፡
“አየሽ..” አለኝ ሹሩባዬን በእጁ እየዳበሰ ከብዙ ዝምታ በኋላ፤ “ብዙ ሰዎች ህልም አላቸዉ፡፡ ልዩነቱ የአንዳንድ ሰዎች ህልም እዉን ሊሆን የሚችል ሲሆን የሌሎቹ ደግሞ ፈፅሞ ሊሳካ የማይችል መሆኑ ነዉ። ሊሳካ የማይችል ህልም ካላቸዉ ሰዎች መካከል አንቺ አንዷ ነሽ፡፡ ለመሆኑ ይህ ሊሳካ የማይችል ህልምሽ ምን እንደሆነ ታዉቂያለሽ?”
ዝም፡፡
“ግዴለም ተይዉ.. እኔ እነግርሻለሁ፡፡” በረጅሙ ተነፈሶ ..”ይሄ የማይሳካ ህልምሽ በዚህ ዕድሜሽ እኔን ማፍቀርሽ ነዉ!”  አስደነገጠኝ፡፡
“ለምን?” ለመጀመሪያ ጊዜ ተናገርኩኝ
“እኔ የሃያ ሰባት ዓመት ወደል፣ አንቺ የዘጠኝ ዓመት ሚጢጢ ህፃን፡፡ እንዴት ፍቅረኛሞች ልንሆን እንችላለን? እኔ አቤሜሌክ ይህንን ፈፅሞ አላደርገዉም፡፡ “
ስሙ አቤሜሌክ መሆኑን ተረዳሁ፡፡
“ጥያቄሽ የተመለሰ ይመስለኛል፡፡”
“ምን" አልኩት አትኩሬ እያየሁት፡፡ በለስላሳ ፀጉር የተሸፈነዉ ደረቱ ላይ አይኔ አረፈ፡፡ በወንዳወንድ ቁመናዉ፣ በብሩህ ፊቱ፣ በሃር ፀጉሩ...ፍጡራንን የመማረክ ችሎታ ያለዉ ነዉ፡፡ ፈፅሞ ሃያ ሰባት ረጃጅም ዓመታትን ምድር ላይ የኖረ አይመስልም፡፡
“ጭራሽ ፍቅረኛሞች ልንሆን አንችልም! እንዳንቺ ትንኝ የሚያክል የዘጠኝ አመት ልጅ ያለኝ ሰዉ ነኝ፡፡ ይልቅ ባለቤቴ ወ/ሮ ሮማን ይህንን ብትሰማ ምን እንደምታደርግሽ ታዉቂያለሽ?”
“ምን?”
“ባልነግርሽ ይሻላል፡፡ አሁን ከዚህ ጥፊ!” ገፍትሮ አስወጣኝ፤  “ሁለተኛ ወደዚህ ግቢ ስትመጪ  እንዳላይሽ!”
* * *
በነጋታዉ ተመልሼ የግቢዉን በር አንኳኳሁ፡፡ ቆንጆ ፀጉር ያላትና በጣም የሚያምር የባህል ቀሚስ የለበሰች ሴት በሩን ከፈተችልኝ፡፡ ወ/ሮ ሮማን መሆን አለባት ስል አሰብኩ፡፡
“ሚጡ ማንን ፈልገሽ ነዉ?” ብሩህ የሆነ ፈገግታ መገበችኝ፡፡ “ወደ ዉስጥ ግቢ”  
ከሰፊዉ ሳሎን ውስጥ ተቀምጬ፣ ሳቁለጨልጭ ወ/ሮ ሮማን ኩሽና ገብታ ሽር ጉድ ማለት ጀመረች፡፡
ከደቂቃዎች በኋላ ቡና በስኒ ይዛ መጣች። “ቡና እንደምትወጂ እገምታለሁ፡፡“ ብላ ሰጠችኝ፡፡
ቡናዉ በጣም ቀዝቃዛና ጎምዛዛ ነበር። እንደምንም አይኔን ጨፍኜ ጨለጥኩት፡፡ ባልጠጣው ይሻለኝ ነበር፡፡ አፌ ባዕድ በሆነ ቆምጣጤ ተሞላ፡፡
“መቼም አቤሜሌክን ፍለጋ እንዳልመጣሽ እርግጠኛ ነኝ፡፡ አሁን አቤሜሌክ እቤት የለም፡፡ እኔ እና ዉዱ ባለቤቴ አቤሜሌክ አንድ ቆንጆ ልጅ አለን፡፡ ላንቺ እንደሚሆን ተስፋ እናደርጋለን፡፡ ብታይዉ በጣም ደስ የሚል ልጅ……”
  ወ/ሮ ሮማን እየለፈለፈች ነበር…እኔ ግን ሁሉም ነገር ዞረብኝ፡፡ ከጥቂት ደቂቃዎች በኋላ ራሴን ሳትኩ፡፡  

Read 377 times

Follow us on twitter

Due to an error, potentially a timed-out connection to Twitter, this user's tweets are unable to be displayed.