Print this page
Tuesday, 05 October 2021 00:00

“የፕሬዚዳንት ባይደን ማዕቀብ አገር ያፈርሳል”

Written by 
Rate this item
(0 votes)

የአፍሪካ ፖለቲካዊ-ኢኮኖሚ ተንታኙ ሎውረንስ ፍሪማን፣ ፕሬዚዳንት ባይደን በኢትዮጵያ ላይ ለመጣል ያቀዱት ተጨማሪ ማዕቀብ የሚያስከትለውን መዘዝ ከኦሮሚያ ብሮድካስቲንግ ኔትዎርክ (OBN) ጋር ባደረጉት የ36 ደቂቃ ቃለ ምልልስ  በስፋት ያስረዳሉ፡፡ በኢትዮጵያ ላይ ተጨማሪ ማዕቀብ በመጣል፣ የጠ/ሚኒስትር ዐቢይ አህመድን መንግስት ማዳከም፣ የአዲስ አበባውን መንግስት ለመጣል የሚታትሩ ተጨማሪ አማፂ ገንጣይ ቡድኖችን የመፍጠር አደጋ እንዳለው ስጋታቸውን ይገልጻሉ፡፡ ማዕቀቡን ተከትሎ ኢትዮጵያ እንደ አገር ከፈረሰች ዳፋው ለአፍሪካውያንም ይተርፋል የሚሉት ፍሪማን፤ በአፍሪካ ቀንድ በመቶ ሚሊዮኖች የሚቆጠሩ አፍሪካውያ ህይወት ለአደጋ ይጋለጣል ሲሉ ያስጠነቅቃሉ፡፡
ፕሬዚዳንቱ ህወሓትን የሚደግፉና የአገዛዝ ለውጥን የሚያቀነቅኑ አማካሪዎቻቸውን ከመስማት መታቀብ  እንዳለባቸው የሚመክሩት አሜሪካዊው ፍሪማን፤ ህወኃትና የሎቢስት ቡድኑ በአሜሪካ የተሳካለት  የአሜሪካ ኮንግረስ ስለ ኢትዮጵያ ምንም ነገር የማያውቅ በመሆኑ ነው ይላሉ፡፡ የኢትዮጵያ ወዳጅ የሆኑት አሜሪካዊው ሎውረንስ ፍሪማን ከኦሮሚያ ብሮድካስቲንግ ኔትዎርክ (OBN) ጋር ሴፕቴምበር 24 ቀን 2021 ዓ.ም ካደረጉት ቃለ-ምልልስ ጥቂቱን እንደሚከተለው ተርጉመን አቅርበነዋል።
የፕሬዚዳንት ባይደን ፖሊሲ አንደምታ
…ወደ ዓመት ገደማ ያስቆጠረው የትግራይ ጦርነት አስከፊ ነው። ሰዎች እየሞቱ ነው። ሰዎች እየተሰቃዩ ነው። ሰዎች እየተራቡ ነው። በመቶ ሺዎች… ምናልባትም ከዚያም በላይ፡፡ ይሄ ደግሞ እንዳለመታደል ሆኖ የጦርነት ውጤት ነው። ጦርነት በራሱ የሰብአዊ መብት ጥሰት ነው። አሁን በትግራይ እየተሰቃዩ ያሉት በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ ሊሆኑ ይችላሉ። ኢትዮጵያ ከፈረሰች ግን በአፍሪካ በሚገኙ በመቶ ሺዎች የሚገመቱ ህዝቦች ላይ ምስቅልቅል ይፈጠራል። --- በትግራይ ስላለው ስቃይ ተገቢ የሆነ ስጋት ያላቸው ወገኖች ቢኖሩም፣ የባይደን ፖሊሲ፣ በአፍሪካ ቀንድ፣ በመቶ ሚሊዮን ህዝቦች ላይ ሊያስከትል የሚችለውን አስከፊ፣ አደገኛና አጥፊ ውጤት ማንም አልተረዳውም፡፡
… በመሰረቱ ሁለት ትላልቅ ችግሮች አሉ። አንደኛው፣ እኔ እስከማውቀው ድረስ ፕሬዚዳንት ባይደን ስለ አፍሪካ ምንም የሚያውቀው ነገር የለም። አብዛኞቹ የኮንግረስ አባላትና ሴናተሮችም ስለ አፍሪካ አያውቁም፡፡ ኢትዮጵያን ላለፉት አንድ ምዕተ ዓመት ከግማሽ፣ ከአድዋ ድል በኋላ፣ በአንድነት አስተሳስሮ ያቆያት ምስጢር ምን እንደሆነ አያውቁም፡፡ ነገር ግን ሁለተኛ ችግርም አለ። ኢትዮጵያ ላይ በአሜሪካ ወይም በሌላ አገር ወታደራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ማዕቀብ በመጣል ተጽዕኖ መፍጠር ትክክለኛ አካሄድ ነው ብለው የሚያምኑ ሰዎች አሉ። ይሄ ደግሞ የዚህችን አገር ጥፋት ያስከትላል።… ቻይናን ከአፍሪካ ማስወጣትም ይፈልጋሉ። አፍሪካን እንዲሁም በራሳቸው መንገድ በነጻነት የሚጓዙ ማናቸውንም አገራት መቆጣጠር የሚፈልጉ የፖለቲካና ኢኮኖሚ ከበርቴዎች አሉ። እነዚህ አገራትን ያወድማሉ፤ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ህዝቦችን ይገድላሉ። ሊቢያ ከ10 ዓመት በኋላ እንደምናያት ነው --- ኢራቅን ተመልከታት … ከ20 ዓመት በኋላ (አንድ ትውልድ ማለት ነው)  አሜሪካ ያልነበረ ጅምላ ጨራሽ መሳሪያ  አለ በማለት በአገሪቱ ላይ በወሰደችው የጣልቃ ገብነት እርምጃ የተነሳ፣ አሁንም ደካማ አገር ሆና ቀርታለች። ሶሪያን ተመልከት…… በነገራችን ላይ ፕሬዚዳንት ባይደን … ወታደሮቻችንን ከአፍጋኒስታን በማስወጣቱ---እንኳን ደስ ያለህ ልለው እፈልጋለሁ። በ20 ዓመታት  ቆይታችን ምንም ያሳካነው ነገር የለም፡፡
አሁን ደግሞ ወታደራዊ ሃይላችንን በሌላ አቅጣጫ እያሰማሩ ነው። የባይደን አስተዳደር፣  ቻይና  ቁጥር 1 የአሜሪካ ጠላት ናት ብሎ ያስባል። በውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ቶኒ ብሊንከንና በሌሎች የሚመራው የባይደን አስተዳደር፣ የሊብራል ዲሞክራሲ አምባገነናዊ እሳቤውን ሌላው አገር ላይ የመጫን መብት እንዳለው ያምናሉ። ጠ/ሚኒስትር ዐቢይ አስደናቂ የአመራር አቅሙን አሳይቷል።
በኢትዮጵያ ደፋር ባለራዕይ  የኢኮኖሚ ዕድገት ፖሊሲ ቀርጿል። ኢትዮጵያ 37 ሺ ተጨማሪ ሜጋዋት የኤሌክትሪክ ሃይል ለማመንጨት ማቀዷን አንብቤአለሁ። ይህ ነው ዕድገት ማለት! አሜሪካና ፕሬዚዳንት ባይደን ዕድገትን በመቃወም ነው አቋም የያዙት፤ በብልፅግና ፓርቲ ከሚመራው የኢትዮጵያ መንግስት ጥቅም፣ ፍላጎት፣ አቅጣጫና ዓላማ በተቃራኒው በመቆም።
የህወሓት ብልጣብልጥነት
ህወኃትና የሎቢስት ቡድኑ ውጤታማ የሆኑበት ብቸኛው ምክንያት፣ የአሜሪካ ኮንግረስ ስለ አፍሪካና ኢትዮጵያ ምንም ነገር የማያውቅ በመሆኑ ነው። በዚህም የተነሳ እንደፈለጉ ይጠመዝዟቸዋል፤ እንዳለመታደልም ሆኖ ራሱ ፕሬዚዳንት ባይደንን ጨምሮ።
እያንዳንዱ የኢትዮጵያ  ክልላዊ መንግስት በ1995 (እ.ኤአ) የወጣውን ህገ መንግስት ከተቀበለ በኋላ፣ የኢትዮጵያ መንግስት ላይ ጥቃት መፈጸም የህገመንግስቱን ጥሰት ነው። ህውሐቶች በጥቅምት ወር መጨረሻ  በመቀሌ በመከላከያ ሰራዊቱ ላይ ጥቃት ሲፈጽሙ፣ የኢትዮጵያን ህገ መንግስት የጣሱ ከዚያን ጊዜ አንስቶ ከኢትዮጵያ ሌሎች አሸባሪ ቡድኖች ጋር በመቀላቀል፣ የኢትዮጵያ መንግስት ከሥልጣን መውረድ እንዳለበት… ነፃ አገር እንደሚመሰርቱ በግልፅ ይናገሩ  ጀመር። ይሄ የህገ መንግስት ጥሰት ነው።ራሳቸውን ያፀደቁትን ህገ መንግስት ነው የጣሱት። ከዚያም በሰኔ ወር 6ኛው አገራዊ ምርጫ ተካሂዶ፣ 40 ሚሊዮን ገደማ ህዝብ ድምፁን ለብልፅግና ፓርቲ… ለኢትዮጵያ መንግስት፤ ለኢትዮጵያ ህገመንግስት ሰጥቷል። ይህ በአሜሪካ መንግስት  ትኩረት ተነፍጎታል፡፡ ተዘንግቷል፤ ችላ ተብሏል። በጥቅምት መጨረሻ የኢትዮጵያ መንግስት በገንጣዩ አማፂ ቡድን፣ በተጠቃ ጊዜ፣ አሜሪካ ኢትዮጵያን በመደገፍ ምላሽ አለመስጠቷን ስመለከት ወዴት እያመራን እንደሆነ አውቄው ነበር። ለነገሩ አሜሪካ በሰኔ የተካሄደውንና ጠ/ሚኒስትር ዐቢይና ብልፅግና ፓርቲ ያሸነፈበትን ምርጫ አልደገፈችም፤ አላወደሰችም። ያን ጊዜ ነው አሜሪካ  ነገር ማሰቧ የገባኝ። አሜሪካ እስከ ዛሬም ድረስ የኤሌክትሪክ ሃይል ለማመንጨት ኢትዮጵያ የምትገነባውን፣ በምስራቅ አፍሪካ የሚሊዮኖች ህይወት የሚያሻሽለውን የታላቁን ህዳሴ ግድብ አትደግፍም። የኤሌክትሪክ ሃይል ለልማት ያለውን ፋይዳ ዕውቅና ያልሰጠው የባይደን አስተዳደር፤ ለኢትዮጵያም ሆነ ለአፍሪካ መጪ ዘመን እንደማይጨነቅ አሳይተዋል።
አዲስ ስለሚመሰረተረው የኢትዮጵያ መንግስት
…ጠ/ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ ጥሩ ያደረገው ነገር፣ የብልፅግና ፓርቲን ሲመሰረት ብሔር ተኮር አለመሆኑ ነው። ይሄ በጎ ነገር ነው። ህዝቡ ኢትዮጵያ በሚለው እሳቤ ዙሪያ  መሰባሰብ አለበት።  ክልሌ… አካባቢዬ… ትውልዴ ወዘተ የሚሉ ውዝግቦች መቆም አለባቸው፤ አደገኛ ናቸው። …ዲሞክራሲ በራሱ መፍትሄ አይደለም። ያለ ኢኮኖሚ ዕድገት ዲሞክራሲን እውን ማድረግ አይቻልም። የኢኮኖሚ ዕድገት፣ ኢነርጂ፣ ኢንዱስትሪ፣ ማምረቻዎች፣ የባቡር ትራንስፖርት፣ ንፁህ የመጠጥ ውሃ… መሰረተ ልማቶች ወዘተ እነዚህ መሰረታዊ የሰብአዊ መብቶች ናቸው። የዲሞክራሲ አቀንቃኞች እኒህን ጉዳዮች አያነሷቸውም፤ አሳስቧቸውም እንኳ አያውቅም። በቀን ምን ያህል ኢትዮጵያውያንና፤ ምን ያህል አፍሪካውያን …በንፁህ ውሃ እጦት፣ በውሃ ወለድ በሽታዎች፣ በኤሌክትሪክ ሃይል… በመሰረተ ልማት ችግር ለሞት ይዳርጋሉ። እነዚህ ጉዳዮች ለምንድነው የማያነሳቸው? ለምንድነው ፕሬዚዳንት ባይደን የማያሳስቧቸው?  የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ብሊንከንና የአሜሪካ ሴኔት እኒህ ጉዳዮች ለምን አያሳስባቸውም? ዲሞክራሲ በራሱ መፍትሄ አይሆንም ከዚያ በፊት መሟላት ያለባቸው ነገሮች አሉ። የእያንዳንዱን ግለሰብ አቅም ማሳደግ ይጠይቃል።
የመኖሪያ ቤት ይፈልጋል። የኤሌክትሪክ ሃይል ይጠይቃል፤ በቂ የአኗኗር ደረጃ ይጠይቃል። ቁጭ ብሎ ስለ ኢትዮጵያ ፖሊሲ ለመወያየት ትርፍ ጊዜ ይጠይቃል። ምግብ፣ ሥራ፣ ውሃ ወዘተ ፍለጋ እየኳተኑ የሚሆን አይደለም። እንዳለመታደል ሆኖ ባለፉት 15 ዓመታት ዲሞክራሲ በምዕራቡ ዓለም በተሳሳተ መንገድ ጥቅም ላይ ውሏል። የእኔ መለኪያ ከዚህ ላቅ ያለ። ኢትዮጵያ ወደፊት በዚህ መልኩ ብሄራዊ ውይይት ታደርጋለች ብዬ ተስፋ አደርጋለሁ…።


Read 11620 times
Administrator

Latest from Administrator