Sunday, 03 October 2021 20:38

ሐሙስ ቅዱስ ወይስ እርኩስ?

Written by  ያዕቆብ ብርሃኑ
Rate this item
(0 votes)

‹ባህላዊ የልጅነት ጨዋታዎችን ለድርሰቱ ቅርፅ መጠቀሙን አደንቃለሁ፡፡ ቅርጹ ግን ይሄን የሚያክል ጥልፍልፍ ታሪኮች ተደራርበው የሰሩትን ሙሉ የልብወለድ ታሪክ ለመሸከም የሚያስችል አልነበረም፡፡ አዳም የድርሰቱን እንደ ሚካኤል አንጀሎ ‹Battle of centaurs› የጥበብ ሥራ በጭካኔ የተዛዘለ፣ ዝግ ያለና አማተሪሽ አጀማመር ሕጸጽ ለመሸፋፈን፣ ይህችን የመውጫ ቃል እንደጻፈ ይሰማኛል፡፡.››

ጥቂት ወደ ቀኝ...
ይሄንን መጽሐፍ የሚያነብ ሰው ‹‹አስቀድሞ ምንም አልነበረም፡፡ ከቦዘነ ጭፍግግ አድማስ በታች ሥራ የፈቱ አራት ጎረምሶችና አንዲት ልጃገረድ ብቻ…›› ቢለን ተሳስተሃል ልንለው አቅም ይኖረን ይሆን? ሲጀምር ቅዱሱና እርኩሱ ሐሙስ ተጋምደው የፈጠሩት የሚመስል ጎነ ሦስት ታሪክ አለ፡፡ ነገርየው ሲራኖ በተሰኘውን ተውኔት ላይ የምንመለከተው በትዕንግርታዊ አፈጣጠሩ ተገፍቶ የተቃኘ ስል ደመነፍስ ባዳበረው ሲራኖ፣ እሱ በሚወዳት ሩክሳን እና እሷ በምትወደው ክርስቲያን መካከል የተፈጠረውን ሦስትዮሻዊ (triangular) ቅርጽ የሚመስል ነገር አለው፡፡ ቢሆንም ትረካው አሁንም አሁንም ስለሚዋልል፣ ቅርጹ አንድ ወጥ አይደለም፡፡ ስብስባቸው በአንድ መግነጢስ የሚታዘዙ አራት ቅስቶችን የሚያቅፍበት አጋጣሚ ነበር፡፡ መግነጢሷ ራሷ ጌርሳሞት ነች፡፡
‹‹ይሄ የወጣቶቹ የስብስብ ቅርጽ ብዙ ጊዜ አይለወጥም፡፡ አቅደውት ነው? አንዳንድ ጊዜም ለመሮጥና ወዲያ ወዲህ ለመበታተን ያቀዱ ይመስላሉ፡፡ ምናልባት ወዳጅነታቸው ውስጥ የተገነባው ግን የተደበቀው ጊዜ የሚያወጣው የሕይወት ጉዞ፣ በጨረፍታ እራሱን ሲያሳይ ይሆናል፡፡ ሁሉም ነገር ተለዋጭ ከሆነ በረሃው ካበበ፣ የአበበው ከረገፈ፣ የረገፈው ከጸደቀ እንዲህ የተሰበሰቡት ወጣቶች የማይበታተኑበት [ምን] ምክንያት ይኖራል?›› ገጽ 49
ተረት እስኪመስል ድረስ ሁሉም ነገር የተከናወነው በዚህች ሴት ከንፈር ነበር፡፡ ደጋግሞ አብቦ ደጋግሞ የሚጠወልግ የወጣት ትኩስ ፍላጎት እንደ ቢራቢሮ ይቅበዘበዛል። ስሜቶቻቸው ከምራቅ የቀጠኑ፣ ከጥቅሻ የፈጠኑ ስስና ተለዋዋጭ ናቸው፡፡ በዚህ ላይ እነዚህን ሽልምልም ስሜቶቻቸውን በነጻነት እንዳያስታምሙ፣ ከወዲያም ከወዲህም የሚያካልቡ አደናቃፊዎች ጥቂቶች አይደሉም፡፡
ይህ ሁሉ የሆነው ግን ሐሙስ ተጀምሮ እስከ አርብ ድረስ ነው፡፡ ግዕዛዊያን አባቶች ሐሙስ የሳምንቱ አምስተኛ ዕለት መሆኑን ለማመልከት ‹ኅምስ› ከሚለው የግዕዝ ቃል ተወርሶ የተሰየመ ነው ይላሉ፡፡ አበቃ፡፡ ትንሽ የተለየ ዘርዘር ያለ ብያኔ የምናገኘው ፍለጋችንን ወደ ፀሎተ ሐሙስ ካዞርን ብቻ ነው፡፡ እንግዲህ በውል ካልተገለጹልን ሐሙሲቶች (ይባል ይሆን?) በአንዷ ቅድስናና እርኩሰትን ደርባ በተከናነበችው በዚያች እለት ተራኪያችን ታሪኮቹን ማድራት ጀመረ፡፡ ቢሆንም ይሄኛው ሐሙስ እንዲያው በረቡዕ እና አርብ መካከል የቆመ ዕለት ነበር፣ ብለን ብቻ የምናልፈው አይሆንም፡፡ ነገር ግን ካልጠፋ ቀን ተራኪያችን ስለ ምን ሐሙስን መረጠ? እንጃ!
መሲሁ ‘በሁሉ ነገራችሁ እኔን ምሰሉ’ ብሏልና በሁለመናችን ልንመስለው ግድ ይላል፡፡ በመጽሐፍ ቅዱስ ታሪኮች ላይ እንደምንረዳው፣ ሐሙስ የመታጨት ዕለት ነው፡፡ ‹የአዳም ልጆች ከኃጥያት ቀንበር ነጻ ይወጡ ዘንድ› ‹የሰው ልጅ› ለመከራ፣ ለግፍ ተላልፎ ለመሰጠት የመታጨት ዕለት… ታሪኮቹ ሲተረኩልን ሐሙስ ስቅለተ አርብን ለመርገጥ፣ ብዙ የሰኞና የማክሰኞ ሰልፈኛ ዕለታትን በትዕግስት ማሳለፍ ነበረበት፡፡ ሲያልቅ ግን ሐሙስ እርኩስም ቅዱስም ለሆነባቸው ሁሉ ስቅለተ አርብ ነበር፡፡ አቸነካከራቸው ቢለያይም ቅሉ ሁሉም ገጸባህሪያት የምኞታቸው ሰልፈኛ እያዳፋ ወስዶ የወሸቃቸው ቅርቃር ውስጥ ተጥለዋል፡፡ የአበበው ጠውልጓል፤ ለማየት የሚያስጎመጀው ለማየት አጸይፏል፡፡ ሲያልቅ እርኩሱም ቅዱሱም ሐሙስ ተሸኝቶ አርብ ነበር፡፡ ትንሣዔን የካደ ስቅለተ አርብ...
ሌላ... ደራሲው በኮላሴ ባርያው በኩል የማሰነበት ቅዠትን የሚያስከነዳ፣ ሰው ከዝንጀሮ የሚዳቀልበት ታሪክ አለው፡፡ ኮላሴን አሳዳጊ አባቱ በአንድ አሳቻ ሌሊት እንቅልፍ እምቢ ስላለው ከቤት በወጣበት አፍታ፣ ገደል ስር ከሚራኮቱ ዝንጀሮዎች መካከል አገኘው፡፡ ነገሩን ደብቆ ከዘመድ እንዲያሳድግ እንደተቀበለው ለጎረቤት ለማሳመን አልተቸገረም፡፡ ታሪኩ ሲጀምር ይሄን ያህል ልሙጥና ፍዝ ነበር፡፡ ኮላሴ እያደገ ሲሄድ ግን ፊቱ በጸጉር ተሸፈነ። በተለይ በልጁ ጌርሳሞት ሲመጡበት ከሰዋዊነት በተለየ ቁጡና ምህረትየለሽ ሆነ፡፡ አዳም በቅጠላቅጠል ተመጋቢነቱ በኩል ኮላሴን ከዝንጀሮ እንድናዛምደው ያደረገው መታተር የሰራለት አልመሰለኝም፡፡ ዝንጀሮዎች ከቅጠላቅጠል ይልቅ ፍራፍሬና ሥጋ መመገብ እንደሚወዱ አያውቅም ነበር ይሆን? ደራሲው ይሄን ያህል ሰውን ከዝንጀሮ የሚያዋውል ጭብጥ ለመምዘዝ ሲደፍር ይህችን ትንሽ ዝግጅት ማድረግ ሊከብደው አይችልም፡፡
ሌላው ጥያቄ የሚፈጥረው ጉዳይ ወድቆ የተገኘበት ሁኔታ ነው፡፡ ከዓመታት በፊት በእንግሊዙ Royal society open science journal ላይ ታትሞ ባነበብኩት አንድ ጥናት መሰረት፤ የዝንጀሮ እናቶች እንኳን በሕይወት ያሉ የሞቱ ልጆቻቸውን ከ10 ቀናት እስከ ወራት ተሸክመው ይዞራሉ፡፡ በልጆቻቸው የመጣውን እስከ ሞት ይፋለሙታል እንጂ አይሸሹለትም፡፡ እናስ የኮላሴ ባርያው ነገር እንዴት? በበኩሌ ከቀደመው ታሪክ ይልቅ በመጨረሻ ኮላሴ ወደ ጥንተ ፍጥረቱ ወደ ዝንጀሮዎቹ የተመለሰበትን ሁነት የተረከበት ጉልበት የበለጠ ትንፋሽ ያለውና ‹ድራማቲክ› እንደሆነ ተሰምቶኛል፡፡ ይህ ሁሉ የሆነው ግን ሐሙስ ተጀምሮ እስከ አርብ ድረስ ነበር። ነገር ግን ሐሙስ ቅዱስ ወይስ እርኩስ?
እንጃ!
እልፍ ወደ ግራ...
ይሄን መጽሐፍ እስካጋምሰው ድረስ ንባቡ አሰልቺ ሆኖብኝ ደጋግሜ ለማቋረጥ አመንትቼ ነበር፡፡ በበርካታ ዓመታት ንባቤ እንደዚህ መጽሐፍ ተራኪው፣ ደራሲው እና ገጸባህሪያቱ በአተራረክ ሂደት ቅጥ በሌለው ሁኔታ የተዘበራረቁበት ሌላ ልብወለድ አጋጥሞኝ አያውቅም፡፡ ብዙ ገጾች ላይ በግርጌ ማስታወሻ መልክ የተሰነቀሩ ተቀጥላ ታሪኮች ከዋናው ታሪክ በምን ተለይተው የግርጌ ማስታወሻ ላይ እንደሰፈሩ እንኳን ግልጽ አይደለም፡፡
በዐረፍተ ነገር አሰጋገሩ አዳም፣ ከእኛ ዘመን ይልቅ ለእነ ከበደ ሚካኤል ዘመን የሚቀርብ ይመስላል፡፡ ፍዝዝ ያለ፣ ነፍስን ለመንዘር ተናዳፊነት የሚጎድለው፣ ፈራ ተባ የሚል፣ ጅል መካሪ የሰነዘራቸው የሚመስሉ ትርክቶች መጽሐፉን ከገጽ እስከ ገጽ ሞልተውታል፡፡ ገጸባህሪያቱ እንደ ትንኝ፣ እንደ ብናኝ የቀለሉ፣ የቀጠኑ ሆነው ለመለየት የሚፈታተን ትኩረት ይፈልጋሉ፡፡ ምናልባት ከአንድ ሁለቱ በስተቀር...
እያንዳንዷ ታሪክ በቀጭን መስመር ላይ የተሰመረች ደብዛዛ ሀቲት ነች፡፡ ቀጭኗ ድር ግን ትብታቧ ረጅም ነው፡፡ ከጦስኝ እስከ ዝንጀሮ የሚያዛምድ፣ የሚያጋምድ ሰላላ ሀዲድ አስምራለች፡፡ አዳም እንደ ተራኪ ያገኘውን ቅራቅንቦ ሁሉ እያግበሰበሰ የሚነጉድ ለጋ እብድ ይመስላል፡፡ ምንም ብጣሽ ታሪክ አይንቅም፡፡ ለመጽሐፉ ትርክት ፋይዳ ያለውንም፣ የሌለውንም ሽርፍራፊ ትርክት ሁሉ እየለቃቀመ ይደርታል፡፡ ድርሰት ግን ዘገባ አይደለም (writing isn’t all about narrating the whole story)… የሚያጫውተው የሚያስቆዝመው ጠነን ያለው፣ የተተወው (void) የሆነው ነገር እኮ ነው፡፡
ኦሾ የሐያኛው ክፍለ ዘመን ትልቁ ፈላስፋ ብሎ ባንቆለጳጰሰው ሉድዊን ዊትገንስታይን ሥራዎች ላይ በሰነዘረው አጭር ሀተታ ሀሳቤን የሚያጎላ ግሩም አተያይ አስፍሯል፡፡
‹‹When it is just like a maxim, a bare, naked statement with no decorations around it, it simply hits deeper, although it will be understood by only very few people – people who have the capacity to see in the seed the whole tree, which is not yet existent but is only a potentiality. [...] Ordinarily the philosopher tries to convince you of what he means. He tries to prevent you going astray from his meaning, and he gives you the whole package with all the details. But he leaves nothing for you, no homework for you. He is not helping your intelligence; he is, in fact, destroying you.››
በእርግጥም የሚጽፉ ሰዎች የሚጽፉልን ሕጻናትን እንቅልፍ ለማስተኛት የምንጠቀምባቸውን ዓይነት ታሪኮች (bed time stories) ነግረውን የሚጠይቅ ደመነፍሳችን ዝም ለማሰኘት መሆን የለበትም፡፡ የምናስብበት፣ የምንቆዝምምበት፣ ሌላ አስተውሎት የምንፈለቅቅበት ጥቂት ክፍተት ሊተውልን ይገባል፡፡
ሁሉንም መጻሕፍቱን ለማንበብ ደጋግሜ መሞከሬ ባይቀርም ተሳክቶልኝ ሁለቴ ያነበብኩለት ‹ግራጫ ቃጭሎችን› ብቻ ነው፡፡ በዚህ በመጽሐፉ (አፍ) ውስጥ አዳም ከቁንጽል የህክምና ጽንሰሐሳቦች ጋር የመጣበቅ፣ ብዙ ጭብጦቹንም ከዚያው የመምዘዝ ችክታ አይቼበታለሁ፡፡ አዳም እንደ ደራሲ ከማሳየት ይልቅ መንገር የሚቀናው ተራኪ ይመስላል፡፡
በመጽሐፉ ውስጥ የሚጥም፣ የማይጥም፣ አስማት፣ ምትሃት፣ ድንበር ዘለልነት አበዛዙ ለጉድ ነው፡፡ በስመ ድኅረ ዘመናዊ የፈጠራ ነጻነት፣ እንዴት ድርሰት ፍጹም ገዥ መርኅ ያጣ መረን ይሁን? የአዳም ረታን ልብወለዶች አስቀድሞውኑ ታኝከው በተተፉት የኤግዚስተንሻሊዝምና የአብዘርዲዝም መነጽሮች ለመተንተን የተሽቀዳደሙት ትንታጎች፣ ስለ ሥርዓተ ነጥብ ሲነሳባቸው ግን ሕጉ ምን ይሰራል? ይሉናል፡፡ ህጉ የሚሰራው ለማድነቅ ብቻ ነው እንዴ? የአዳም ረታ ፍጹም ግድየለሽ የስርዓተ ነጥብ አጠቃቀምን ገላልጬ ለማየት በሞከርኳቸው ሁሉም ልብወለዶቹ ውስጥ ፈጦ የሚታይ ነው፡፡
ለምሳሌ በአተራረክ ሂደት የተተወ ወይም የጎደለ ሀሳብ መኖሩን ለማመልከት ሦስት ነጥብ (...) እንጠቀማለን፡፡ ሆነ ብዬ ባደረኩት ትዝብት አዳም በዚህ መጽሐፉ ብቻ ከሁለት እስከ አስራስምንት ነጠብጣቦችን በግዴለሽነት ሲጠቀም አይቻለሁ፡፡ አንድ ደራሲ በአተራረክ ሂደት የተተወውን ወይም ሊዘረዘር የታሰበውን ሀተታ በበቂ አይገልጽልኝም ካለ፣ ከአንድ እስከ ምንም የፈለገውን ያህል ነጠብጣብ መጠቀም ይችላል፡፡ በሌላ አነጋገር የራሱን አዲስ ስርዓተ ነጥብ መፍጠር ይችላል፡፡ ነገር ግን የግድ ወጥነት (uniformity) ያስፈልገዋል። ወጥነትና ሥልት የኪነጥበብ መሰረታዊ አንጓዎች ናቸው፡፡ ወጥነትና ሥልት ያጣ ኪነት መደዴነት አይቀርለትም፡፡ እናም ነጠብጣብ የማዝረክረኩ ልክፍት የአብዛኛው ወጣት ደራሲ ክፉ ውርስ የሆነው ምናልባት በሰውየው ተጽዕኖ ሊሆንም ይችላል፡፡
ይሄን ይሄን ሁሉ ሳስብ አዳም በፊሽካ እየተጠራራ ከሚያዳንቀው ይልቅ፣ ጠጣሩን እውነት እየጋተ የሚያነቃው፣ የሚያተጋው፣ ባስ ሲልም የሚያስደነግጠው ደፋር ሐያሲ ያስፈልገው ነበር ይሆን? እላለሁ፡፡ አዳም በመጽሐፉ የመውጫ ገጽ ላይ ‹የድርሰቱ ቅርጽ› በሚል ርዕስ ሥር፣ ስለ መጽሐፉ ያሰፈረው ሀተታም በእጅጉ አስገርሞኛል። እንዴት በአንድ መጽሐፍ ላይ ራስህን ደራሲም ሀያሲም አድርገህ ትሾማለህ? በበኩሌ ይሄን ሌሎች መጻሕፍቱም ላይ ጭምር የሚከውነውን ድፍረቱን በአንባቢዎቹ በነጻነት የማሰብ መብት ላይ እንደተሰነዘረ መራር ንቀት እቆጥረዋለሁ። ሲፈልግ አንባቢው ለዘለዓለም ሳይረዳው ይቅር እንጂ ደራሲው በድርሰቱ የቅርጽና ይዘት ነጥቦች ላይ ምንም የማለት መብት የለውም፡፡ አንባቢው እንደ ንባቡ ጥልቀት፣ እንደ ሕይወት ልምዱ መጠን ሀሳቡን በመሰለው መልኩ እንዲያንሸራሽር ሊተውለት ይገባል፡፡
የእኛ ሀገር የስነጽሁፍ መድረክ ድብልቅልቁ ስለወጣ አንድ ሰው ደራሲም፣ ሀያሲም፣ አሳታሚም አከፋፋይም ሆኖ ይተውናል፡፡ ከፍሎ ወይ ወዳጅነቱን ተተግኖ ሒስ ቢጤ ያስጽፋል፡፡ በየተጋበዘበት መድረክ በድፍረት የራሱን መጽሐፍ ለመበየን ይሰለፋል፡፡ አዎ ዘመኑ የመተናነስ፣ የመወዳደስ ዘመን ሆኗል፡፡ በፖለቲካችን ብቻ ሳይሆን በኪነት ብያኔያችን፣ አያያዛችን፣ አረዳዳችን ላይ ሳይቀር ስርነቀል አብዮት ግድ ይለናል!
በመጨረሻ...
አዳም ባህላዊ የልጅነት ጨዋታዎችን ለድርሰቱ ቅርፅ መጠቀሙን አደንቃለሁ፡፡ ቅርጹ ግን ይሄን የሚያክል ጥልፍልፍ ታሪኮች ተደራርበው የሰሩትን ሙሉ የልብወለድ ታሪክ ለመሸከም የሚያስችል አልነበረም። አዳም የድርሰቱን እንደ ሚካኤል አንጀሎ ‹Battle of centaurs› የጥበብ ሥራ በጭካኔ የተዛዘለ፣ ዝግ ያለና አማተሪሽ አጀማመር ሕጸጽ ለመሸፋፈን፣ ይህችን የመውጫ ቃል እንደጻፈ ይሰማኛል፡፡
ከአዘጋጁ፡- ጸሐፊውን በኢሜል አድራሻው፡- This email address is being protected from spambots. You need JavaScript enabled to view it. ማግኘት ይቻላል፡፡

Read 704 times