Monday, 04 October 2021 00:00

“በዓሉ ግርማን ጥሎ…”

Written by  አብዲ መሀመድ
Rate this item
(0 votes)

“ጥላሁን ገሰሰን አንጠልጥሎ …”
አብዲ መሀመድ


  ደራሲው ሲደጉስ በነፃነት ነው፡፡ ቃላቶቹ ሳይከብዱን ወረቀት ላይ መራመድ ይችላሉ፡፡ አይጠብቁም፣ አይጠልቁም፡፡ ሀሳቡን መሸከም የሚችል ቃላት ቸግሮት አያውቅም፡፡ በቀላል ቋንቋ ውብ “ስዕል” መሳል ይሆንለታል፡፡ ድርሰቶቹ ከ“ምግብ” ይልቅ ለ“ማር” የቀረቡ ናቸው፡፡  ለ“ጣዕም” እንጂ ለ“ጥጋብ” አይነበቡም፡፡ መጠን በጨመርን ቁጥር እያዋዛና እያባበለ ጥልቅ የፍቅር ባህር ውስጥ አስገብቶ ይለቀናል። መመለሳችንንም እንጃ፡፡  በ“ኑሮ” እና በ“ፍቅር” መሐል ያለ “አስቀያሚ ገጽታ” ቢኖር እንኳን በብልጭልጭ ሣቅ እየጠቀለለ ከርክሞ መልሶ ለኛው ያቀርብልናል፡፡ ይህንን በ“ዛጎል” ፣ በ“ጥቁር ሰማይ ስር”፣ በ“ደርሶ መልስ”… ውስጥ በሚገባ ተግብሮታል፡፡ ሥራዎቹን የዳሰሱ የጥበብ ባለሙያዎችም በቅኝታቸው የሚያስረግጡልን ይህንኑ  እውነት  ነው፡፡
ከጊዜ ወደ ጊዜ ያለመታከት ስነ-ጽሁፍን በማምረት ትጋታቸው ከሚያስደምሙኝ ጥቂት የሀገሬ ደራሲያን መካከል አንዱ ነው፡፡ ከተቀበለው በላይ እየሰጠ ያለም ይመስለኛል፡፡ በርከት ካሉ ሥራዎቹ አንፃር ጠቅለል አድርገን ስንመዝነው ሁሉን አሰናስኖ የያዘና በሥነ-ጽሁፉ “ቆብ የደፋ ቄስ” ነው ለማለት ያስደፍራል፡፡ እንዳለጌታ ከበደ፡፡
እንዳለ የራሱ ፊደል አጣጣልና የራሱ ቀለም ያለው ባለ ልዩ ተሰጥኦ ደራሲ ነው። ምንም እንኳን አሁን-አሁን በአመዛኙ ትኩረቱን ኢ-ልቦለዶች፣ እውነተኛ-ታሪኮች፣ ጥናቶች ላይ ቢያደርግም፣ ለስነ- ጽሑፋችን አዳዲስ “ቅርጽ” እና “አቀራረቦች”ን ሲሞክር የቆየ ደራሲ እንደሆነ እሙን ነው። ለዚህም በአያሌው ደክሟል፡፡ ይህንን ድካም “ማዕቀብ” ውስጥ በራሱ አንደበት እንዲህ ሲል ገልጾት ነበር፡- … “የልቦለድ ደራሲ መሆን አስቸጋሪ ነው፡፡ ገፀ-ባህሪያቱን ጠፍጥፎና በሥርዓት ቀርጾ ማናገርና የሚታዩ ሰዎች ማስመሰል አለበት፡፡ የልቦለድ ደራሲው አንባቢው እንዳይሰለቸው በልብ-ሰቀላ የተሞላ እንዲሆንለት ተአማኒነት ያለው ግጭት መፍጠር አለበት..” ፡፡
ይህንን የራሱን ቃል ይዘን በእርግጥ ደራሲው እንዳለጌታ ተሳክቶለታል ወይ? ብለን መመስከር የምንችለው “ደርሶ መልስ” ልቦለዱን ካነበብን ብቻ ነው፡፡ ለኔ “ደርሶ መልስ” ለዚህ የ “ደራሲነት ድካም” እንደ “ስኬት” ሊታይ የሚችል አይነተኛ ተምሳሌት ሆኖ የሚቆጠር አንጡራ አቅም የፈሰሰበት የጥበብ ሥራ ነው፡፡  እንዳለ በዚህ ሥራው  እንዳሻው  በቋንቋው ተጠቦበታል፡፡ የተዋበ ብዕሩን ያሳየበት የ“ወረቀት አደባባይ” ነበር ማለት ይቻላል፡፡ ደርሶ መልስ የአንድ ወጣት (የሄኖክ) የፍቅር ገድል ብቻ አይደለም፤ የዘመናችን የፊት መስታወትም ጭምር ነው። የልቦለዱ መቼት ዘመነ-አዳል አይደለም፤ ዘመነ-ፊውዳልም እንዲሁ..! ዘመነ-ግሎባል እንጂ….መንፈሱም ሆነ የሕይወት አረዳዱና አተረጓጎሙ የተቀዳው ከኛው ነው፡፡ አሁን ያለውን የተዛባና የተዛነፈ የፍቅር ህይወታችንን በሄኖክ ውስጥ እንድናይ ያነቃናል፡፡ በምልሰት እየፈተሸ ያስዳስሰናል። ድርሰቱ ከቅድመ-ታሪክ እስከ ድሕረ-ታሪክ የተገመደው ጭብጡን ፍቅር ላይ አድርጎ ነውና፣ ወደፊት ዘመናችንን ለማጥናት ለሚነሳ ማንኛውም ተመራማሪ፣ ሁነኛ ፍንጭ መሆን የሚችል (እንደ-ፍቅር እስከ መቃብር) የስነ-ጽሁፍ ሰነድ ነው፡፡
ልቦለዶቹን ፍተሻ ለሌላ ጊዜ እናቆየውና፣ ለዛሬ በኢ-ልቦለድ ሥራዎቹ ላይ እናተኩር፡፡ በተለይም አጽንኦት ሰጥቶ በሚያተኩርባቸው፣ አዋቂም - ታዋቂም ግለሰቦች ላይ ስላነጣጠሩት ተረኮቹ ጥቂት እንቃኝ፡፡
አንዱን ጥሎ ሌላውን …..
የበዓሉ ግርማ ሕይወትና የአሟሟቱ ምስጢራዊ ታሪክን በወጉ ሣይቋጨው “…. ሌላኛው ባለወር-ተራ ዝነኛ ጥላሁን ገሰሰ እንደ ዋዛ  ተረስቶ መቅረቱ ቆጨው፡፡ አንዱን ጥሏል፣ ሌላውን አንጠልጥሏል፡፡  የአንድ ደራሲ ተልዕኮ ማህበረሰቡ ለናቃቸውና ለገፋቸው ነፍሶች መናገርና ዘብ-መቆም  ነው”… ሲል ያደመጥነው ደራሲ፤… ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ ባልተለመደ ሁኔታ የስመ-ጥር ግለሰቦች፣ በታሪክ ምጣድ ላይ በስለው ድስታቸው ያልተከደነ፣ ምስጢራዊ ታሪክ ትኩረቱን ይሰርቁታል። ፋታ አልሰጥ ብለውታል፡፡ እሳታቸውን እፍ ብሎ ከተዳፈኑበት ለማቀጣጠል አይዳዳም። በእርግጥ ምንም ያህል ይርቀቁ፣ የቱንም ያህል ይጥለቁ፤ እንደ-ንስር ቆፍሮ፣ እንደ-ምስጥ ሰርስሮ አንድ የታሪክ አንጓ ላይ መድረስ በቅጡ ተክኖበታል፡፡ በዚያው ልክ እውቅ የጥበብ ከያኒያን ላይ የመንጠልጠል አባዜና መራኮት ግን ለምን እንደፈለገ አልገባኝም፡፡ በአሉ ግርማ ላይ ባጠናው ጥናት የተቀዳጀው ዝና እንዲሁም የጎረፈለት ጭብጨባ ናፍቆት ይሆናል፡፡ ደራሲው በ“ዶሮ ስልት” የማይደርስበትን ታሪክ እየጫረ ማለፍን፣ ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ ተያይዞታል፡፡ አይነኬ የሚስጥር ሰበዞችን መዝዞ እንደ-ነገሩ ነካክቶ ማለፍን በቅጡ የሰለጠነበት ሌላኛው ክህሎቱ ከሆነ ከረምረም ብሏል፡፡
ቀደም ሲል ከደርግ ከፍተኛ ባለስልጣናት (ኮሎኔል መንግስቱ ሃይለ ማርያም፣ ሻምበል ፍቅረ ስላሴ ወግደረስ፣ ፍስሀ ደስታ) እስከ እውቅ ደራሲያን (ሙሉጌታ ሎሌ፣ አስፋው ዳምጤ፣ ደበበ ሰይፉ) በክፉም ይሁን በበጎ፣ ዛሬም በተሸፋፈነ ሁኔታ፣ ግልጽ ባልሆነ መልኩ፣ በሚከሰሱበትና - በሚወቀሱበት፣ በሰማእቱ ደራሲ በዓሉ ግርማ ህይወትና የአሟሟቱን ሚስጥር በፈተሸበት መጽሐፉ፣ “በዓሉ ግርማ ህይወቱና ስራዎቹ”፣ ያልተቋጨ የታሪክ መዳረሻ ላይ ቆሞ ሲያበቃ፣ በተለያዩ መገናኛ ብዙኃን ላይ ቀርቦ ብዙ እንደሚቀረው፣ ያልተጨረሱ ነገር ግን የተጀመሩ የሚስጥር ትርክቶች መጽሐፉ እንደሚበዙበት በመናገር ፍጻሜያቸውን እንደሚያገኝላቸው ቀብድ ይሰጠናል፡፡ ይሁን እንጂ ዱካ እየተወ ማለፍን እንጂ አንድ የታሪከ ፍጻሜ ላይ ሲደርስ አይስተዋልም። ከእንዳለ የምስጢር አርኪዮሎጂካዊ ቁፋሮ በኋላ በበአሉ የ“አሟሟቱ ሚስጥር” ላይ ይፋ የሆኑ አያሌ ጽሁፎች ወጥተዋል፡፡ ለአብነት አንዱን ጠቅሰን እንለፍ፡፡ዓለማየሁ ገ/ህይወት በግንቦት ወር ሁለት ሺ አስራ አንድ በ “ታዛ” መጽሄት ላይ ያስነበበው መጣጥፉ (ደበበ ሰይፉ እና የበዓሉ ግርማ ኦሮማይ) ተጠቃሽ ነው፡፡ አለማየሁ በዚህ ትውስታው ውስጥ.. እጅግ ከሚያከብረው መምህሩ ገጣሚ ደበበ ሰይፉ ጋር በነበረው የአንድ አጋጣሚ ቆይታ!..“እራሴን እንደ-ምንም አደፋፍሬ ሲከነክነኝ የነበረውን ስለ ደራሲ በዓሉ ግርማ መጨረሻ አነሳሁበት..” ሲል እንደሚከተለው አስቀምጦ ነበር፡፡
‘’ጋሽ ደበበ፤ ከበዓሉ ግርማ ጋር ተያይዞ ለምንድን ነው ስምህ በክፉ የሚነሳው ?’’
‘’እንደኔ-እንደኔ ለበዓሉ ግርማ ሞት ተጠያቂ መሆን ያለበት ዳኛቸው ወርቁ ነው”
‘’እንዴት?” (ድንጋጤዬ በግልጽ እየታየ)፡፡
‘’አየህ አንዱ የመጽሐፉ ገምጋሚ እሱ ነበር፡፡ እና በዓሉ ባለበት ስንወያይ እኔ መሻሻል አለባቸው ያልኳቸውን ዋና-ዋና ነጥቦች እያነሳሁ ነበር ፡፡’’
‘’እስቲ የተወሰኑትን ንገረኝ ?’’
‘’ለምሳሌ ኮሎኔል ታሪኩ ወልዳይን ትልቅ ጀግና (hero) አድርገህ ፈጥረህ የሴት ፎቶ  (የፊያሜታ ጊላይን ማለቱ ነው) ታቅፎ እንዲሞት አድርገኸዋል፡ ተምሳሌታዊነት  (symbolism) ነው እንዳይባል ጎልቶ የወጣ ነገር የለም፡፡ እሱና ሌሎች ገጸ-ባህሪያት ላይ ብዙ መስራት አለብህ።’’ እያልኩ ማስታወሻዎቼን አንድ-በአንድ እያነሳሁ ሳቀርብለት በዓሉ የሚቀበል አይነት አልነበረም፡፡
‘’ጓድ ደበበ፣ አልገባህም ማለት ነው፡፡ እኔ የጻፍኩት እንደ-አንድ የታሪክ ሰነድ የሚታይ ስራ ነው፡፡ አንተ እኮ እንደ-ልቦለድ፣ ልክ እንደ “ከአድማስ ባሻገር”፣ እንደ “ደራሲው” አይነት ስራ አድርገህ ነው ያየኸው፡፡ ይህ በፍጹም ትክክል አይደለም ፡፡’’
‘’ኖ ኖ ኖ ኖ ጓድ በዓሉ፣ ለእኔ ደንበኛ ልቦለድ ነው የጻፍከው፡፡ የሚታየውም በዚያው የልቦለድ መለኪያ ነው አልኩት። እናም (ሰፊ የአርትኦት ስራ ያስፈልገዋል) ብዬ ነው የነገርኩት፡፡ ዳኛቸው ወርቁ ደግሞ፣
‘’ጓድ በዓሉ ትክክል አይደለም፣ ይኼ ነገር ፈጽሞ መነካት የለበትም፣ እንዳለ ነው መታተም ያለበት” ይላል፡፡ ተነጋገርን፣ ግን ልንግባባ አልቻልንም፡፡ እኔ አሻሽሎ ያምጣ በሚለው አቋሜ ጸናሁ፡፡ ከዚያ በኋላ ታተመ ሲባል ነው የሰማሁት፡፡ (ቅጽ 02 ቁጥር 21) በማለት ለሞቱ እንደ-ዋነኛ መንስኤ ሆኖ ሊጠየቅ የሚገባው ዳኛቸው እንደሆነ፣ ደበበ ደራሲውን የሞገተበትን ኩርማን ገጠመኝ፣ አለማየሁ ከትዝታው ጨልፎ ያሰፈረው በዚህ መልኩ ነበር፡፡
እንዳለጌታ እንደ በዓሉ ሁሉ የክቡር ዶክተር አርቲስት ጥላሁን ገሰሰንም የተረሳና የተዘነጋ ሚስጥር ነክሶ ይዞታል፡፡ ቅንጣቢ እንዳየ ንስር እየዞረው ይገኛል፡፡ ጥላሁን ላይ ማንዣበብ የጀመረው “ያልተቀበልናቸው” (2009) በተሰኘ መጽሐፉ ነው፡፡.. እነሆ በድጋሚ በጥላሁን ላይ ሌላኛውን የሚስጥር ዶሴ አዋራውን ጠርጎ ከአመት በፊት ለጥራዝ ባበቃው የመጨረሻ መጽሐፉ “መክሊት” ላይ እንደገና ቆስቁሶታል፡፡
በዚህ ረገድ እንዳለ ተመሳሳይ አካሄድ ሲጠቀም ያጋጥመናል። የበአሉን ታሪክ በመጽሐፍ ይዞ ከመምጣቱ በፊት በ“ጽላሎት” ስብስብ ውስጥ የ“ፍጻሜው መጀመርያ” በሚል ፍንጭ ሰጥቶን ነበር። በጥላሁን ላይ እየተጠቀመ ያለው “አካሄዳዊ ስልት” ይህንኑ  ነው:: ከድምጻዊው ነገሬ ብሎ መረቡን የሚጥለው፣ መልህቁን የሚያስተካክለው በልጆቹ ላይ ነው፡፡ ጥላሁን ከተለያዩ ሴቶች የወለዳቸውን ልጆች እያደነ፣ ውበትም-ድምቀትም በመስጠት ያበጃጃቸዋል፡፡ “ያልተቀበልናቸው” ውስጥ (ጥላሁን ገሰሰ በጠና የታመመ ለታ) ያነሳት ሴት ልጁ ትቆይና፣ ለዛሬ ለማየት የመረጥኩት ከ“መክሊት” በመሆኑ፣ የተፈራ ታሪክ ደራሲው ግልጽ ባልሆነ ሁኔታ የተረከበት መንገድ እንግዳ ሆኖብኛል፡፡
ተፈራ የጥላሁን ገሰሰ ልጅ ነው፡፡ አባቱ ማን እንደሆነ ያወቀው፣ በቀብሩ ዕለት ነው፡፡  እስከዚያ እለት ድረስ ጥላሁን አባቱ ስለመሆኑ ከመገመት ውጭ እርግጠኛ አልነበረም፡፡ ጥላሁን በብዙ ሴቶች መወደዱ፣ ከብዙዎችም መውለዱ፣ ብዙ ልጆችን “አባት አልባ” አድርጓቸዋል፡፡ ከፈለቀች የወለዳቸው፣ ከአስራቴ ያፈራቸው፣ ከፌርያል፣ ከብርሀኔ፣ ከሂሩት፣ ከቀለሟ፣ ሮማን … ወዘተ በመጽሐፉ ተዘርዝረዋል። እንዳለም በዚህ-ክፍተት አጮልቆ እውነት የሆኑ ቀደም ሲል ደራሲያን ማህበር ባሳተመለት ግለ-ታሪኩና ዘከርያ አህመድ ባዘጋጀው (ጥላሁን ገሰሰ ህይወቱና የታሪኩ ሚስጥ) በሚል ስለ ጥላሁን እውነተኛ ታሪክ ያነበብናቸውን ለድርሰቱ ማንጸርያነት በማዋል፣ “በእውነተኛ ታሪክ ላይ ያልተመሰረተ” በሚል አይነኬ ሚስጥሮችን ነካክቶ፣ በግርድፉ የምናውቃቸውን በላልቶ፣ ያፈጠጡ እውነቶችን ሊሸነግለን ይዳዳዋል፡፡ ከነዚህ መሃል አንዱ ይሄ ነው፡፡
“ጥላሁን አንገቱ ላይ በስለት ተቆርጦ በህይወት ተርፎ በመጣበት ወቅት የጥላሁን ባለቤትና የተፈራ እናት አፍ-ለአፍ ገጥመው ያወሩትን ተፈራ ሰምቷል፡፡ ሁለቱም ሴቶች ስልጡኖች ናቸው ሲል ተፈራ ያደንቃል፡፡ አንድን ወንድ ለሁለት ተጋርተው ሳይቀናኑ ይኸው ያወራሉ”፡፡
“ማነው አሉ እንዲህ ያደረገው ?” የተፈራ እናት ትጠይቃለች
“ሆድ ይፍጀው ብሏልኮ”
“ምን ሆድ ይፍጀው ይላል? ራሱ ነው በራሱ ላይ እንደዚያ ያለ እርምጃ የሚወስደው፡፡ አታውቂውም? አላውቀውም? አናውቀውም? ሲናደድና ተስፋ ሲቆርጥ ሸሚዙን ገለጥ አድርጎ፣ መዳፉ ስር ያለውን ደም ስር እያሳየን፣ ይህችን ብቆርጣትኮ ተገላግዬ ነበር… ይለን የለ? ጥላሁን ሁሌም ሰው እያለው ሰው እንደሌለው ይሆናል፡፡ ሀብቱን አያውቅም፣ ሀብቱን አይጠብቅም› (ገጽ 48) በማለት ገላልጦ “በፈጠራ ስም” ገመና ከታች ከመሆን ይልቅ ለሚስጥር ገላጭነት ልጆቹን፣ ሚስቶቹን ሲመለምላቸው በብዙ መልኩ፣ እናነባለን፡፡ ይህ በራሱ ተስፋዬ ገብረአብ ሲጠቀም እንደቆየው የሴራ ድርሰቶቹ አይነት፣ እንዳለጌታም በዚህ ፈረንጆች “non fiction novel” በሚሉት ዘርፍ፣ መደጋገሙ፣ ደራሲውንና ስራዎቹን በጥያቄ እንድንመረምራቸውና  እንድንፈትሻቸው ያደርገናል፡፡ ይሄንን (ግራ አጋቢ-አወዛጋቢ) የአጻጻፍ ዘውግ ምሳሌ ጥናታዊ ኢ-ልቦለዱ መግቢያ ላይ እንዲህ ሲል ይተነትነዋል፡፡… ልቦለድ ነው፤ ልቦለድም አይደለም፡፡ ኢ-ልቦለድ ነው፤ ኢ-ልቦለድም አይደለም። ከሁለቱም ዘርፎች ቆንጥሮ የወሰዳቸው መገለጫዎች አሉት፡፡ አብዛኛው ሰው በሚያውቀው ወይም በሚያውቀው በመሰለው በአንድ ሃገር ላይ በተፈጸመ ታሪክና ተራኪ እንዲሁም ሁነት ላይ ተመስርቶ የሚደረስ ነው፡፡ (ገጽ 3)
ጥላሁን ዛሬም ታሪኩ ያልጠራ ፣ ውዝግብ የማያጣው ዜመኛ እንደሆነ እርግጥ ነው፡፡ እንኳን ሌላው-ሌላው የትውልድ መንደሩ ስለሆነችው (ወሊሶ) እንኳን ዛሬም መግባባት ላይ አልተደረሰም ፡፡ ..ጎሮ ፣ አንዳንዴ “ጉሩራ” የሚያደርሱት ሁሉ አሉ፡፡ ከጉሩራ ቀጥሎ የምናገኛት ከተማ ደግሞ ወልቂጤ ናት ፡፡ እንዳለጌታ ወልቂጤ ተወልዶ ያደገ ደራሲ እንደመሆኑ፣ መጪው-ጊዜ በጥላሁን ዙርያ ሰፊ-ጥናት አድርጎ መጽሐፍ ካስደጎሰልን የትውልድ ቦታውን ወልቂጤ ነው?  ሳይለን ይቀራል ብላችሁ ነው? ጥላሁንም ቢሆን እንዲህ ያሉ ውዝግቦች ላይ ገብቶ አስተያየት ሲሰጥ አይደመጥም፡፡ ይሁን እንጂ ጉዳዩን የማጥራት ስራ የባለቤቱ እንጂ የማንም  አልነበረም፡፡ አርቲስቱ ለህልፈት በበቃበት ማግስት በከያኒው ዙርያ ሰፋ-ያለ ዘገባ ያስነበበችው ቁም-ነገር መጽሄት፣ “ጥላሁን ስለ ትውልድ መንደሩ የተናገረው !” በሚል ርዕስ ይህን አስነብባ ነበር፡፡… “እኔ የትም ብወለድ ኢትዮጵያ ውስጥ ነው፡፡ ወሊሶ ግን ለኔ ብርቅ ናት፡፡ የብርቅ ብርቅ ናት፡፡ ክብሬ ናት፡፡ ግርማ ሞገሴ ናት፣ የሌሊት ህልሜ ናት። ለእኔ ወሊሶ ጌጤ ናት፡፡ እኮራባታለሁ!" (2000 ዓ.ም)
መውጫ
ብዙ ጊዜ ወጣትነት ሁለት መልኮች አሉት፡፡ አንድም ብርሃን ሁለትም ጨለማ። ልቦለዶቹ ጽልመትና ተስፋ መቁረጥ ለተጫነው ፣እንደ-ጉድ ለሚፈራረቁበት የወጣትነት ዘመኔ የብርሀን ያህል ፍኖት ነበሩ፡፡ መደዴነቴ ላይ እሰለጥንበት ዘንድ አንቂ ደወሌም ጭምር! ቃለ-ምልልሶቹ አምልጠውኝ አያውቁም፡፡ ከአፉም-ከመጽሃፉም ብዙ ተምሬያለው፡፡ በዚህ ከዘመን-በፊት ጀምሮ በተገመደ የንባብ ዝምድናና ትስስር ምክንያት ከስራዎቹ ጋር እንደ-ሩቅ ወዳጅ እንነፋፈቃለን። ናፍቀውኝ ብቻ አይቀሩም፤ ዛሬም ካሉበት ላጥ አድርጌ እየመዘዝኩ በፍቅር፣ በስስት አጣጥማቸዋለሁ፡፡ ነደው - ያነዱኛል፣ ተቃጥለው - ያጨሱኛል፡፡ ልብ አላቸው፣ ደም አላቸው፡፡ ይቀዘቅዛሉ - ይሞቃሉ፣ ህይወት-ይረጫሉ፡፡ ከመኝታዬ፣ ከትራስ-ጌዬ የራቁበት ጊዜ ትዝ አይለኝም፡፡ ይኖር ይሆን? እንጃ፡፡
እንዳለጌታ በዚህ በጎልማሳነቱ አስራ ሶስት መጽሐፍትን ያበረከተልን ታታሪ ደራሲ ነው፡፡ በእውነቱ በአንድ ሰው ይህን ያህል መጽሐፍ ሲበረከት እልፍ ነው፡፡ ለሰጠን ሁሉ ብናመሰግን እዚህ ቦታ አይበቃም። ከዚህ ወዲያም ብዙ እንደሚሰጠን አልጠራጠርም። ይሁንና እንዲህ ያሉ ስውር-ደባዎች፣ አይነኬ ሚስጥሮችን በመፈልፈል እራሱን ባያባክን፣ የፈጠራ አቅሙን ባያቀጭጭ ይመረጣል ባይ ነኝ፡፡ ምኞቴም ጭምር ነው፡፡ የተድበሰበሱ ታሪኮችን ይበልጥ በማድበስበስ (ከማወሳሰብ በቀር) የሚሞላ ክፍተት፣ የሚታረም ስህተት አለ ብዬ አላምንም፡፡ ሊኖርም አይችልም፡፡  

Read 778 times