Sunday, 03 October 2021 20:50

‹‹ፌሚኒስቱ›› ጸጋዬ ገ/መድኅን

Written by  ደሳለኝ ሥዩም
Rate this item
(2 votes)

ክፍል ሁለት
ባለፈው ሣምንት ጽሑፌ የጸጋዬን ‹ማነው ምንትስ?› የተሰኘ ግጥም ፌሚኒዝም የንባብ ዕይታ አንጻር ለመተንተን በማሰብ መፈለግ፣ አስቀድሜ ደግሞ ስለ ፌሚኒዝም ምንነት ፈር ለመያዝ  በጥቂቱ  ሞክሬአለሁ። ዛሬ ደግሞ ከግጥሙ ጥቂት መስመሮችን እየመዘዝን በፌሚኒዝም እይታ ጸጋዬ ምን ሊል ፈለገ? የሚለውን እንቃኛለን፡፡
ያው መቼም እኔም እንደሰው
አንዳንዴ አንዳንዴ ብቻ ሕሊናዬን እውነት ሲያምረው
ሰብሰብ ብዬ እማስበው
ቀድሞስ ቢሆን ለኔ ብጤ ለኔ ብጤ የሄዋን ዘር
አዳሜ በኔ ላይ በቀር ለኔ መስክሮ አይናገር
ፌሚኒስቶች ደጋግመው ከሚያነሱት ጉዳይ አንዱ እዚህ ውስጥ ተጠቅሷል፡፡ የሲሞን ዲቦቮር ‹‹ሌሎች›› ሐሳብም በዚህ የግጥሙ አንጓ ውስጥ ይገኛል፡፡  አክራሪ ፌሚኒስቶቹ በመጽሐፍ ቅዱስ የተጠቀሰው ‹ስጋዋ ከስጋዬ አጥንቷ ከአጥንቴ ናትና ሴት ብያታለሁ›› የሚለውን የአዳም ንግግር አይቀበሉም፡፡ መከራከሪያቸውም ‹ስምን ያወጣ የባለቤትነት መብት አለው›፤ ስለዚህ አዳም ስም ሲያወጣ ሄዋን የእኔ ተገዥ ናት ለማለት ነው› የሚል ነው፡፡ ይህ መከራከሪያ በሲሞን ዲቦቮርም የሚደገፍ ነው፡፡ እሷ እንደምትለው፤ ወንዶች ራሳቸውን ሰው አድርገው ሲቆጥሩ፣ ሴቶቹን ግን እንደ መጠቀሚያ ቁሶች ያያሉ፤ ስለዚህም ‹‹ሌሎች›› ያደርጓቸዋል፡፡
በዚህ የግጥም አንጓ ውስጥ ‹‹አንዳንዴ አንዳንዴ ብቻ ህሊናዬን እውነት ሲያምረው›› የሚለው ሀረግ፤ ይህች ሴት ማህበረሰቡ የፈጠራት መሆኗን ያሳያል፡፡ እሷም ማህበረሰቡ ያሳደረባትን ተጽዕኖ እንደ ጠቅላላ እውነት መቀበሏን የሚያሳይ ነው፡፡ ‹‹አንዳንዴ›› ብቻ ነው እንዲህ የምታስበው፤ እንጂማ ብዙ ጊዜ ማኅበረሰቡ የሰጣትን ማንነት ብቻ ተቀብላ ቁጭ ብላለች ማለት ነው፡፡ ይቀጥልና  ‹‹አዳሜ በኔላይ በቀር›› የሚል ሐረግ አለ፡፡ ‹‹አዳሜ›› ሁለት ትርጉም ያለው ይመስላል፣ አንደኛው-ማህበረሰቡን ሁለተኛው የእሷን አዳም። የሄዋን አዳም በሄዋን ላይ ፈረደ፤ ከዚያም ወዲህ የመጡ ነብያትና መምህራን ሁሉ ስለ ሄዋን ኃጢአትና ሥህተት ሲናገሩ ኖሩ፤ አዳም በሄዋን ላይ ይፈርድ ይሆናል እንጅ ለሄዋን ወግኖ ሲፈርድ አላስተዋለችም፡፡
ሁለተኛው ደግሞ ‹አዳሜ› ዘረ አዳምን የሚወክል ይመስላል፡፡ ወንዶች ሴቶችን እንደቁስ ያያሉ፤ ‹ምን ሴት ብታውቅ በወንድ ያልቅ› እያሉ ያቃልሏታልና፣ ሴት ሆና የንብረት ባለቤት መሆን የማይፈቀድላት በብዙ ዘመናትና በብዙ ማኅበረሰብ ውስጥ ነው፡፡ ሴት ሆና በአደባባይ ልትሟገት ቀርቶ ጉዳይዋን ወደ አደባባይ ያወጣች እንደሆነ ‹ኧረ ይች!›› ተብላ የሚፈረድባት በእሷ ነው፡፡ ወንድ ቢያጠፋ የምትቀጣው ሴቷ ሆና ቆይታለች፡፡ ጸጋዬ የሳላት ሴት ስለዚህ ነው የምትነግረን፡፡ ወንዶቹ ቢያጠፉ ቅሉ ተወቃሽና  ኃጢአተኛ ሴቷ ተደርጋ ትታያለች።
… መንፈሴ ውስጥ የሚያቃጫል
እውነትስ ማነው ምንትስ? እስቲ
እንጠያየቅ የሚል
ህመም አለኝ .. ይኸም ሆኖ እግዜር
ያሳያችሁ ላልል
ለይታችሁ አጥራችሁኝ ከዳኝነታችሁ
ባህል
ከፍርድ አደባባይ ክልል
በዚህኛው የግጥሙ አንጓ ውስጥ የምናየው ከላይ ያነሳነውን ሀተታ ነው፡፡ ‹‹ከፍርድ አደባባይ ክልል›› ነው የሚለው ግጥሙ፡፡ ክልል የተከለከለን፣ ያለፈቃድ የማይገባበትን፣ የተወሰኑ ግለሰቦች ወይም ቡድን ብቻ የባለቤትነት ወይም የሥልጣን መብት ያለበት ቦታ ነው፡፡ የዳኝት አደባባይ ለሴቶች እንዲህ ነው፤ አንዴ ከዚህ ክልል አስወጥታችሁኛልና የትኛው የፍርድ አደባባይ ላይ ተገኝቼ አቤት ማለት ይቻለኛል? እያለች ነው፤ ይህች የጸጋዬ ሴት ስሞታዋን የምታሰሙተው፡፡
እንዲህ የተደነባን ደምብ አልፋ ወደ አደባባይ መውጣት አትችልም፡፡ ምክንያቱም የዳኝቱ ባህል አንዴ ታጥሯልና። ነገር ግን ይህች ሴት ‹‹አንዳንዴ - አንዳንዴ ብቻ›› ብቻዋን ቁጭ ስትል ህሊናዋን ወጥሮ የሚይዛት ጥያቄ አለ፡፡ ‹‹ሸርሙጣ›› እያለ የሚያወግዟት- እውነት ሸርሙጣው ማን ሆኖ ነው የሚል፡፡ እሷ አንድ ብቻ ናት፣ ጓደኞችም እንኳ መጥተው ይዳሯታል፤ ባለትዳር መሆናቸውን የምታውቃቸው እንኳ መጥተው ይዳሯታል፤ እሷ ዛሬ ለእንጅራ፣ ነገም ለእንጀራ በምታመሽበት መሸታ፣ ትዳር ያላቸው እንኳ ሳይቀሩ በየጊዜው እየመጡ ይዳሯታል፡፡ እና ማነው ምንትስ?
ኧረ ስንቱ ሞልቶ ስንቱ ብኩን የመንፈስ
ምንትስ
ለስጋውም አብሮን ወድቆ ዳግም
በአእምሮው ሲረክስ
በልቦናው ሲሴስን በህሊናው ህግ ሲድስ
‹ፍሪ-ደሜ›› ነው እያለ የኔኑ ደም
ሲያልከሰክስ
በቃሉና በመንፈሱ ወድቆ ደቅቆ ሲበሰብስ
ተይህ ወዲያ ማነው ምንትስ?  
እዚህ ላይ ያለው መከራከሪያ ዊልስቶን ክራፍት ከምትለው ጋር የሚሄድ ነው። ማኅበረሰቡ የተቀረጸበት መንገድ ሁሉን ኃጢአት ለሴቶች ማስታቀፍ ነው፡፡ ይህንን ለማድረግ የማኅበራዊ ተቋማት እገዛ ከፍ ያለ ነው፡፡ ሃይማኖት፣ ኢኮኖሚና ትምህርትን በመሰሉ ማኅበራዊ ተቋማት ውስጥ ሴቶች በበቂ ደረጃ መወሰን የማይችሉ በመሆናቸው፤ ወንዶቹ ደግሞ የበዛ ነጻነትን በመቀዳጀታቸው ወንዶች ሲያደርጉት ልክ የሆነ ነገር፣ ሴቶች ሲያደርጉት ስህተት ይሆናል፡፡
ወንዶቹ ከብዙ ሴቶች ጋር ቢተኙ እንደ ጀግንነት ይቆጠራል፡ ከብዙ ወንዶች ጋር የታየች ሴት ግን እንደነውራም ተቆጥራ በድንጋይ ትወገራለች፡፡ በአንዳንድ ሃይማኖቶች ውስጥ ሴቶች ከትዳር ውጭ እንዳይተኙ ይገደዳሉ፤ ወንዶቹ ግን ከትዳር ውጭ እንዲተኙ ይበረታታሉ (አንዳንድ ማኅበረሰብና ሃይማኖት ወንዶች ከትዳር በፊት ከማንም ጋር ቢሆን ወሲብ እንዲለማመዱ ያዝዛሉ)፤ አንዲት ሴት ከሌላ ወንድ ጋር ተኝታ ብትገኝ፣ እሷ በድንጋይ ትወገራለች፤ እሱ ደግሞ አበጀህ ተብሎ ይሞገሳል፡፡ በዚህ የግጥም ዘለላዎች ውስጥ የምናየው መከራከሪያ ይህ ጥኑ የሚያጠናክር ነው፡፡
ስንት በመንፈሱ የባከነ፣ ልቡ የሸፈተበት፣ እዚህም እዚያም የሚረግጠው፣ በአእምሮው ሁሉ የረከሰ ባለበት ዓለም ላይ እንጀራ ፍለጋ የወጣችን ሴት ‹ምንትስ› (ሸርሙጣ) ብሎ መጥራቱ ልክ አይደለም፡፡ በዚህ ቃል መጠራት ያለበት ካለ በመንፈሱ የመነተሰው፣ የረከሰው እሱ ራሱ ነው የሚል መከራከሪያ ነው እዚህ ግጥም ውስጥ የምናገኘው፡፡
በሌላ በኩል፤ በዊልስቶን ክራፍት እና በዲቦቮር ከተቀነቀኑ ፌሚኒስታዊ ዕይታዎች ውስጥ በተለይ ትምህርት ሴቶች በተዛባ መንገድ እንዲሳሉ አድርጓል የሚል ነው። ሴቶች ዝቅተኞች፣ ሌሎች፣ የወንዶች መጠቀሚያ ቁሶች ወዘተ. ተደርገው እንዲሳሉ በትምህርት ሥርዓቶች ውስጥ ያለው ሥርዓተ ትምህርት አሉታዊ አስተዋጽኦ እንደሚያደርግ ከላይ ሁለቱ እንስት ጸሐፊዎች መከራከሪያ አስተውለናል፡፡ የጸጋዬዋ ባለታሪክም ስለትምህርት ሥርዓት እንዲህ እያለች ነው የምታሰሙተው፡፡
ይኸም ሆኖ እኔ ልጄን እግዚአብሔር
ያሳይህ አልል
ቢከብደው ይሆናል ማለፍ ከትምህርቱ
ክልል
ከሥልጣኔው ኬላ ደፍ እሱ ከእሱ ዘመን
ባህል
በዚህም ሀረግ ውስጥ የምንመለከተው ወጣቶቹን የእናቶችን ልጆች እንኳ ትምህርትና የስልጣኔ ባህል ጠፍጥፎ እንደሚሠራቸው ነው፡፡ ይህ ልጅ እናቱ በምን ሁኔታ እንዳሳደገችው ያውቃል፡፡ እቤቱ ሲገባ የሚቀርብለትን እንጀራ ምንጩን ያውቀዋል። እናቱ ምን ሠርታ አምጥታ እንደምታበላው፤ እንደምታለብሰውና… እንደምታስተምረው ያውቃል፡፡ ነገር ግን በምርቃቱ ቀን ‹‹እናቴ›› ብሎ ሊያቅፋት ቀርቶ ሊጠጋት አልፈቀደም። ይህን ‹‹ምንትስ›› የተባለች እናቱን ለመሸሽ ድፍረት ያጎናጸፈው አመለካከት ያገኘው ደግሞ ትምህርቱ ነው፡፡
ትምህርቱ ሥልጣኔውና የዘመኑ መንፈስ እንዲህ እንዲወስን እንዳደረገው የምታውቀው እናት ብዙ አልተጫነችውም። ‹‹ልጄ እንኳን ከዳኝ›› ብላ ለእግዚአብሔር ስሞታ አልተናገረችም፡፡ ምክንያቱም ልጇ ከነባራዊው የትምህርት ሥርዓትና ከማኀበረሰብ ደምብ ውጭ ሊሆን እንደማይችል ታውቃለች፡፡ ስለዚህም ጸቡ ከማኅበረሰቡ ደምብ እንጅ ከሰው አይደለም ነው፡፡
ለማጠቃለል፤ ቀደም ሲል ባየነው የጸጋዬ ገብረ መድኅን ግጥም ውስጥ በተለያዩ ዘመናት በፌኒሚኒስቶች የተነሡ ሐሳቦች ተንጸባርቀው ተመልክተናል፡፡ እነዚህ ሐሳቦች ለዘብተኞች ናቸው፡፡ እንደ አክራሪዎቹ ወንድ የተባለ እንዳናይ ከሚል መነሻ የመጡ ሳይሆኑ ተቋማዊ ማስተካከያዎች ከተደረጉ በሴት ልጅ ላይ የሚደርሱ በደሎች ይቆማሉ ከሚል እሳቤ የመነጩ መከራከሪያዎች ይመስላሉ፡፡ ይሄን ይመስላል ‹‹ፌሚኒስቱ›› ጸጋዬ ለእኔ፡፡  
ቸር ሰንበት!


Read 558 times