Print this page
Sunday, 03 October 2021 20:59

ግልፅ ደብዳቤ ለአቶ ሺመልስ አብዲሳ (የኦሮሚያ ክልል ርዕሰ መስተዳደር)

Written by  አያሌው አስረስ
Rate this item
(3 votes)

በ2013 ዓ.ም በተካሔደው አገር አቀፍና ክልላዊ ምርጫ፣ በሕዝብ ድምጽ ወደ ስልጣን የመጣው ስድስተኛው የኦሮሚያ ክልላዊ መንግሥት ምክር ቤት ጨፊው፣ አርስዎን ርዕሰ መስተዳድር፣ ወይዘሮ ሳዕዳ አብዱራህማንን  ዋና አፈጉባኤ አድርጎ መርጧል። እርስዎ ያቀረቧቸውን የክልላዊ መንግስቱ የካቢኒ አባላት ሹመትም ተቀብሎ አጽድቋል። አሁን የኦሮሚያ ክልላዊ መንግሥት ስልጣንና ኃላፊነት ከነሙሉ ተጠያቂነቱ በእርስዎና በስራ ባልደረባዎችዎ እጅ ገብቷል።
ከሁሉ አስቀድሜ ለእርስዎና ለስራ ባልደረባዎችዎ መልካም የሥራ ዘመን እንዲሆን ከልብ እመኛለሁ።
ጣሊያኖች ኢትዮጵያን ለመውረርና ለማስገበር በተዘጋጁበት በሃይማኖት ሰባኪነትና በእጅ ባለሙያነት ወደ ኢትዮጵያ የላኳቸው ዜጎቻቸው ዋና ሥራ አድርገውት የነበረው አንደኛውን መስፍን ወይም ባላባት በሌላኛው ላይ እንዲዘምት ማነሳሳት መሳሪያ መስጠትና ሃይል ማዳከም ብቻ ሳይሆን፣ እጅግ ከፍተኛ ገንዘብ በማፍሰስ በሰሩት የፕሮፓጋዳ ሥራ፣ የተወሰነው የኢትዮጵያ ሕዝብ በመንግስቱ ላይ ፊቱን እንዲያዞር ማድረግ ችለዋል። ይህ “ጣሊያን ኢትዮጵያን ሊያሰለጥን የመጣ ነው” ከሚለው ቅስቀሳቸው ጋር ተዳምሮ፣ ከሶስት መቶ ሺህ በላይ ባንዳ ኢትዮጵያውያንን ለማፍራት አስችሎታል።
እነ ደጃዝማች በላይ ዘለቀ፣  ደጃዝማች ገረሱ ዱኪ… ነቅተው የውጊያ ስልት ለውጠው ከኋላ እየገቡ ነጩን ጣሊያን  እየመረጡ መውጋት እስከጀመሩበት ድረስም ባንዳ አበሾች የአርበኛ ጥይት ማብረጃ ሆነው እንዲረግፉ አድርጓል።
የአማራ ብሔርን ቀዳሚ ጠላት አድርጎ በ1968 ዓ.ም ፕሮግራሙን የቀረፀው የትግራይ ሕዝብ ነፃነት ግንባር (ትሕነግ)፤ ግንቦት 1983 ዓ.ም የኢትዮጵያን የመንግስት ስልጣን ከተቆጣጠረ በኋላ የተከተለው የጣሊያንን መንገድ ነው። እንደ ጣሊያኖች የእስልምናን እምነት በክርስትና እምነት ላይ ባያነሳሳም፣ የአማራን ህዝብ “ነፍጠኛ” የሚል ተቀጥላ ስም በመስጠት አንዱ አማርኛ  ተናጋሪው የአማራ ሕዝብ፣ በአንድ ጊዜ ሰማኒያ ከሚሆነው ልዩ ልዩ ቋንቋ ተናጋሪ ከሆነው የኢትዮጵያ ሕዝብ አንፃር በጠላትነት እንዲታይ አደረገ። አማራ፣ የትግሬ፣ የኦሮሞ፣ የወላይታ የሃድያ፣ የከምባታ ወዘተ ሕዝብ ጠላት ተደረገ። በመንግሥት ባለስልጣናት አንደበት፣ በመንግስት መገናኛ ብዙሃን የአማራ ጨቋኝነት ለሁሉም ሕዝብ ተሰበከ። ተቀሰቀሰ። አማራ ላይ ጉዳት ማድረስ አንድን ጠላት እንደ ማጥቃት ተቆጠረ፤ ተተገበረ።
አሁን በግልፅ እየተነገረ እንዳለው አማራን በዘር ለይቶ ማጥቃት ተጀመረው ሐምሌ 1983 ዓ.ም የኦሮሞ ነፃነት ግንባር (ኦነግ) ሐረርጌ ጀሌቻ በተባለ ቀበሌ 18 አማራዎችን በዘራቸው መርጦ በገደለ ጊዜ ነው። የኦነግና ኢህአዴግ መካሰስ እንደተጠበቀ ሆኖ፣ ወተር ላይ 390፣ እንቅፋቱ 79 አማሮች የተገደሉ ሲሆን ድጓ መድኃኔዓለም፣ ፈዲስና ቡርቃ በተባሉ አካባቢዎች ደግሞ 14 ሴቶችን ከተገደሉ በኋላ ጡታቸው ተቆርጠዋል።
አቶ ታምራት ላይኔ ድሬደዋ ላይ የኢሳና የአፋር ሰዎችን ሰብስበው “ግመል ጎታች፤ ሽርጣም” ሲልህ የነበረውን ነፍጠኛ ለምን ዝም ትላለህ” ሲሉ መናገራቸውን ተከትሎ፣ አማራን በዘሩ ለይቶ ማጥቃትና መግደል በመንግሥት ፊት የተፈቀደ ተግባር ሆነ። ገለምሶ አውራጃ ቢታንያ 30፣ ሀርዲም 2000 እና ደኮቻ ከ50 በላይ እንዲሁም ወይ ቀሎ ከ300 በላይ አማሮች ተገድለዋል። በዚህ አካባቢ ከሞት የተረፉ አማሮች ሃይማኖታቸውን እንደለወጡም ይነገራል።
የአሩሲው የአርባ ጉጉ አውራጃ ጃጁ፣ መርቲ፣ ጉና፣ አስኮ እና ጎለልቻ የተባሉ ወረዳዎች አሉት። አውራጃው ብዙ አማራዎች የሚኖሩበት አካባቢ ነው። በመስከረም ወር ውስጥ (1984) 11 አማራዎች በኦነግ ኃይሎች ተገድለዋል። ጥቅምት 21 ቀን 1984 ዓ.ም በአማራዎችና በኦሮሞዎች መካከል ጦርነት ተጀመረ። እስከ መጋቢት ድረስም ግጭቱና ሞቱ ቀጠለ። ከምንጀር የተነሳ የባላገር ጦር ሽፋን ሰጥቶ ከሞት የተረፉትን አወጣቸው። የሐረርጌውና የአሩሲው ፀረ “አማራ እቅስቃሴ”፣ ለመላ አማራ ሕዝብ ድርጅት (መኢሕድ) መመስረት፣ ከምንጃር ተነስቶ ወደ አሩሲ የገባው የገበሬ ጦር ለፕሮፌሰር አስራት መታሰር ምክንያት እንደሆነ ሳይጠቀስ አይታለፍም።
በዘር ላይ አተኩረው አማራውን ከኦሮሚያ ክልል ለማፅዳት የተነሱ ኃይሎች እንደ ነበሩሁሉ፣ “እኛ ከአማራው ጋር እድሜ ልካችንን ኖረናል። እርስ በእርስ መጨራረስ አንፈልግም” በማለት ከአማራው  ጎን ቆመው አማራውን ከሞት በመታደጋቸው ልዩ ልዩ ጉዳት የደረሰባቸው ኦሮሞዎች አሉ።  የምስራቅ ሀረርጌ የጋራ ውለታ ኗሪው አቶ ሙሜ አበዱላሂ ለአብነት ይጠቀሳሉ።
አሁንም ግን በኦሮሚያ ክልል አማራው ለመፈናቀል፣ ለስደትና ለሞት የሚዳረግበት አካባቢ አለ።
ባለፉት ሶስት ዓመታት በምስራቅ ሀረርጌ፣ በአርሲና በባሌ፣ እንዲሁም በምስራቅ ወለጋ በሚገኙ ወረዳዎች በአማራው ላይ የተፈጸሙ ማንነት ተኮር ጥቃቶች እንዲሁም የሃብት ንብረት ውድመት አሰቃቂነት ለመናገር የሚከብድ ነው።
ክቡር ፕሬዚዳንት!
እስከ አሁን የጠቀስኳቸው ጉዳዮች የችግሩን ክብደት ለማሳየት ወይም ለማመልከት እንጂ ጉዳዩን በበቂ መጠን አቅርቤዋለሁ ማለት አልችልም። ላሰምርበት የምፈልገው ጉዳይ ግን፣ የኦሮሚያ
ክልላዊ መንግስት ከተቋቋመበት ጊዜ አንስቶ እርስዎ  ወደ ስልጣን እስከመጡበት ጊዜ ድረስ፣  ስምንት የክልል ፕሬዚዳንቶች ተሸመዋል። በሁሉም የስልጣን ዘመን በኦሮሚያ ክልል ውስጥ የሚኖሩ አማሮች ላይ ያልተቋረጠ ዘር ተኮር ጥቃት ሲፈጸም ቆይቷል። ከተሳሳትኩ ልታረም እችላለሁ  እርስዎን ጨምሮ አንድም የክልሉ ፕሬዝዳንት ወደ አደባባይ ወጥቶ “በኦሮሚያ ክልል ውስጥ በሚኖሩ አማሮች ላይ የሚፈጸመውን ማንኛውንም አይነት ጥቃት አወግዛለሁ” ሲል ሰምቼ አላውቅም።
ሌላው፤ ዘር ተኮር ጥቃት በአማራው ላይ የፈጸሙ ሰዎች ወይም ቡድኖች ሕግ ፊት ቀርበው ከጥፋታቸው ጋር ተመጣጣኝ የሆነ ቅጣት መቀበላቸውንም ሰምቼ አለማወቄ ነው።  ይህ ማለት ደግሞ በኦሮሚያ ከልል አማራ ላይ ዘር ተኮር ጥቃት መፈጸም የማያስከስስና የማያስወቅስ የወንጅል ድርጊት ሆኗል ማለት ነው።
ክቡር ፕሬዚዳንት፡
30 ዓመት ሙሉ በአማራው ላይ ሲወርድ የኖረው መከራ ከእንግዲህ እንዲቀጥል አልፈልግም። እርስዎም ይቀጥል እንደማይሉ እተማመናለሁ። አሁን ስልጣን በያዙበት ጊዜ ደግሞ ጥቃቱ እንዳይቀጥል ለመከላከል ምቹ ሁኔታ ይፈጥርልዎታል።
“ኢትዮጵያን ለማፈራረስ ሲኦል ቢሆን እንወርዳለን” የሚለው የጌታቸው ረዳ ንግግር እንዲሁም ኢትዮጵያን ለማፈራረስ ትሕነግ ቆርጦ የተነሳ መሆኑ የኢትዮጵያን መኖር ለሚፈልገው የኦሮሞ ህዝብና ለሌላውም አማራው አጋሩና ከንዱ መሆኑን ለመገንዘብ ያስችሉታል።
አማራውን መጠበቅ ኦሮሞውን መጠበቅ፣ ሌላውንም ሕዝብ መጠበቅ መሆኑን ምቹ ጊዜ ተፈጥሯል።
ስለዚህ እያንዳንዱ ኦሮሞ በአጠገቡ የሚገኘውን ጎረቤቱን አማራውን በመጠበቅ እንዲተጋ፣ እንደ ምስራቅ ወለጋ እንደ አንገር ጉትን አቢደንጎሮ ወዘተ ባሉ ቀበሌዎች ቋሚ ልዩ ሃይል ወይም ሚሊሽያ  በመመደብ አማራውን ከጥቃት ይከላከሉ ዘንድ በአክብሮት እጠይቃለሁ።
በዚህ አጋጣሚ ከሁሉም ክልሎች ወደ አማራና አፋር ክልል በመግባት አሸባሪውን የትህነግን ወራሪ ጦር እየተፋለ ለሚገኙ ሁሉም ሚሊሺያና ልዩ ሃይል አባላት አክብሮቴን በላቀ ትህትና ለማቅረብ እወዳለሁ። ክቡር ፕሬዚዳንት፤ ስኬታማ የአመራር ዘመን እመኝልዎታለሁ።
ፈጣሪ ኢትዮጵያንና ሕዝቧን ይጠብቅልን!

Read 2459 times