Sunday, 03 October 2021 21:22

“ዲጂታል ስቶቭ የለንም እንዳትሉኝ!”

Written by  ኤፍሬም እንዳለ
Rate this item
(2 votes)

እንዴት ሰነበታችሁሳ!
ሻይ ከአንድ ወይ ከጠባሹ፣ ወይ ከመጥበሻው ከፍተኛ መጎሳቆል ከደረሰባት ቦምቦሊኖ ጋር በልቶ ለከፈለው መቶ ብር፣ ሀምሳ አምስቷ ስትመለስለት፣ “የሌላ ሰው ሂሳብ አሳስታቸሁ መሆን አለበት፡፡ እኔ እኮ አንድ ሻይና ቦምቦሊኖ ብቻ ነው የወሰድኩት፣” የሚል ምስኪን አያሳዝናችሁም!
ሂሳቡ እንደዛ ነው፡፡
”ምን! ለቦምቦሊኖና ለሻይ አርባ አምስት ብር!” በዚህ ላይ እኮ ደግሞ አሳላፊዋ ቲፕ ፍለጋ ትቁለጨለጫለች። ያሰባችሁትን ተጠቅማችሁ ያላሰባችሁት ሂሳብ ከመምጣት ይሰውራችሁ! አሀ...ክው ነው የሚያደርገዋ! እኔ የምለው የብር በዚህ ፍጥነትና በዚህ መጠን ከከባድ ሚዛን ወደ ላባ ሚዛን የመንሸራተቷ ነገር እንደኮረኮረን ይኖራል፡፡ መቶ ብር ፌስታል ሞልታ ያልወጣጠረችውን ያህል አሁን የፌስታሏ ክብደት ከእቃው ክብደት ጋር፣ በቃ...ጎረቤት ናቸው፡፡
“አባዬ...”
“ምን ነበር ልጄ...”
“ዛሬ ቆንጆ ጨዋታ አለ፡፡ ስታዲየም መግቢያ ትሰጠኛለህ?”
“ስንት ነው የምትፈልገው?”
“አምስት ብር”
“አምስት ብር! አምስት ብር ለቅሪላ መመልከቻ ሰጥቼ ዛሬ ጦማችንን እንደር!”
ልጅ ሆዬ ድምጽ አልባ ተቃውሞውን ይገልጻል... ለምቦጩን በመጣል፡፡ (እንደዛ የሚባል ነገር ስለነበር ነው፡፡)
እናት ደግሞ ጣልቃ ገብታ “ምን አለ ብትሰጠው፡፡ ጓደኞቹ ሁሉ ሄደው እሱ ብቻውን ሰፈር ሲጠብቅ ይዋል!”
“ስጠው አልሽ አይደል! እሺ አሰጠዋለሁ፣ ግን በኋላ የሹሮው እቃ ባዶ ሆነ፣ የበርበሬው ከረጢት ተራገፈ እያልሽ እንደ በርበሬ እንዳትለበልቢኝ፡፡”
እና አምስት ብር የእውነት ብር የሆነችበት ዘመን ይህን ያህል ‘አንሺየንት ‘ስቶሪ’ ምናምን አይደለም፡፡ እንዴ... ሌላ አምስት ስትጨመርባት እኮ ለቅዳሜ ‘ዴት’ ትበቃ ነበር፡፡
ዘንድሮ ልጄ ‘ስታዲየም ልገባ ነው..” “ከልጆች ጋር አንበሳ ግቢ ልሄድ ነው፣” ምናምን ከቤተሰብ ‘ፈንድ’ ጥየቃ የለም። ልጄ...ጨዋታውም የጨዋታ ህጉም ተለውጠዋል፡፡
“ዳድ ዘጠኝ፣ ወይ አስር ሺህ ብር ይኖርሀል?” (ስሙኝማ...ጨዋታን ጨዋታ ያነሳው የለ... ገንዘብ ይኖርሀል ወይ ብሎ ጥየቃ ከመቼ ወዲህ ነው የመጣው! ሂድና ኪሱ ገንዘብ እንዳለው አጣራ...” “እስቲ ቦርሳዋ ውስጥ የሆነ ገንዘብ ይዛ እንደሆን ሰልያት...” የተባልን ነው እኮ የሚመስለው! ብድር ምናምን ለመጠቅ ይሄ ሁሉ ‘ኢንተሮጌሽን’ ምንድነው! የምር...ወደፊት እኮ “አዎን ይዣለሁ...” ካልን “ስንት ነው የያዝከው?” የሚል የኦዲተር ምርመራ የሚመስል ጥያቄ ሊመጣብን ይችላላ!
“ኋት ፎር?” ይላል ‘ዳድ’ በፈረንጅ አፍ፡፡ እኔ የምለው...“ዳድ” ማለት “አባዬ” ከማለት በስንት ክፍለ ዘመን ነው የሚርቀው? ቂ...ቂ...ቂ...
 “ለስማርትፎን ፈልጌ ነው፡፡” ሰዎች “ወይ ዘመን! ሶፋው ለሀያ አምስት ዓመት ሳይለወጥ ስማርት ፎን በየሁለት ወሩ የሚለወጥበት ዘመን!” የሚሉት ግራ ቢገባቸው ነው፡፡
“በዛ ሰሞን የገዛኸው አለ አይደለም እንዴ! እሱ ምን ሆነብህ?”
“እሱን ልቀይር ፈልጌ ነው፣ ዳድ፡፡”
“ምነ ሆነና ነው የምትቀይረው?”
“ዳድ አንደኛ ነገር ባክዋርድ ነው፣ ደግሞም ላስት ዊክ ከዩቲዩብ የሆነ ፊልም እያወረድኩ እያለ ቫይረስ ገባበት መሰለኝ፣  ኮረፕት አደረገ፡፡”
“ኦኬ ለወደፊቱ ቴክ ኬር…” ቴን ታውዘንዷን ጠብ ነው፡፡
በቃ…አለ አይደል...እዛ ሰፈር ስለ ሹሮው እቃ ባዶ መሆን፣ ስለ በርበሬው ከረጢት መራገፍ ዲስኩር ምናምን የለም፡፡ ለነገሩ... መጀመሪያ ነገር ‘ከባለ ስማርትፎኖቹ’ ሲሶዎቹ ከረጢት ምን ማለት እንደሆነና አገልግሎቱ ቢነገራቸው...  “ሁዋት! ዩ ሚን ሁዋት ዊ ኢት እዛ ውስጥ ነው የሚቀመጠው?” ባይሉ ነው! እመኑኝማ ጠንከር አድርጋችሁ ያያችሁት የሚያስገርም፣ ለስለስ አድርጋችሁ ካያችሁት በሳቅ ጦሽ ሊያደርግ የሚችል ነው። የሆነ የሼክሰፒር ደቀ መዝሙር ምናምን ነገር ቢኖር እኮ ዓለም የስታንድአፕ ኮሜዲ መድረክ ነች ሊል ሁሉ ይችላል፡፡ 
ደግሞላችሁ...አለ አይደል...“ሰው እንደ ቤቱ ነው የሚኖረው፣” ብላችሁ ስትቀመጡ በዚህም፣ በዛም ‘ጠቅ፣ ጠቅ’ የሚያደርግ አይጠፋም፡፡
“ስሚ፣ ቅዳሜ ጠዋት እንገናኝና ዘና እንበል እባክሽ፡፡”
“ጠዋት አልችልም፡፡ ዘጠኝ ሰዓት አካባቢ መገናኘት እንችላለን፡፡”
“አንቺ ደግሞ ጀመረሽ... ጠዋት የማንን ጎፈሬ ታበጥሪያለሽና ነው?”
“ብታዪ፣ የቆሸሸ ልብስ እንደ ጋራ ነው የተከመረው፡፡”
“እናስ..”
“እናማ... ልብስ ማጠብ አለብኛ!”
“ምንድነው ያልሽው አንቺ!”
“ደንቁረሻል እንዴ! ልብስ ማጠብ አለብኝ።”
“እማዬ ድረሽ! አንቺ እስካሁን ልብስ በእጅ ነው የምታጥቡት?”
“አይ የለም፣ በእግር ነው፡፡ ምን አይነት ጥያቄ ነው!”
“ብቻ ወሺንግ ማሽን የለንም እንዳትዪኝና እሪታዬን እንዳላቀልጠው፡፡”
አቅልጪው፡፡
እኔ የምለው..እንዲህ የሚሉ ሰዎች የሚናገሯቸውን የሰዎች ሞራለ ሊነኩ እንደሚችሉ እንዴት ነው የማይገባቸው። ማንም ሰው እኮ ወሺንግ ማሽን ምናምን ቢኖረው ደስተኛ ነው፡፡ ማንም ሰው ሙቅ ሻወር ቢኖረው ደስተኛ ነው፡፡ ሰው ኩም ለማድረግ መሞከር ምን የሚሉት ‘ስልጣኔ’ ነው!
“ብቻ ቴሊቪዥናችሁ አርባ ሦስት ኢንች ብቻ ነው እንዳትዪኝ!” የስንቱ ግድግዳ ከአርባ ሦስት ኢንች እጥፍ ብዙም በማይሰፋበት ሀገር ምን የሚሉት ‘ዘመናይነት ነው!’
“ብቻ ጫማ ለመግዛት አሁንም እሁድ፣ እሁድ ኮልፌ እሄዳለሁ እንዳትለኝ!”  የሚል ‘ዘመናይን’ በአዲስ አባበ ኮብልስቶን ላይ መንፈቅ ያህል በባዶ እግሩ ማስኬድ ነበር!
“ዊክኤንድ ላይ አሁን፣ አሁን ከሰው ጋር መቀላቀል ትትሃል፡፡”
“ምን ታደርገዋለህ...”
“ግን፣ ቅዳሜና እሁድ የት ነው ያምታሳልፈው?”
“አብዛኛውን ጊዜ ቤቴ ነኝ፡፡”
“ዩ ሚን እዚሁ አዲስ አባበ ውስጥ?”
“እና... የት ልሂድ?”
“ኩሪፍቱ ምናምን እንኳን አትሄድም!”
እመኑኝ... ‘ኩሪፍቱ’ ምናምን የሚላችሁ ሰው ስፍራውን አንድ ጊዜ ብቻ ግፋ ቢል ለሀያ ደቂቃ ያየ ሊሆን ይችላል፡፡ ግን በቃ...ይሄ ጉሮሮውን አንቀን የግል ንብረታችን ልናደርገው የምንሞክረው ‘ዘመናዊነት’ የሚሉት ነገር እያስለፈለፈን፣ የሰው ስሜት እጎዳለሁ ብሎ ነገር የለም!
ስሙኝማ...ጨዋታን ጨዋታ ያነሳው የለ...የቴሌቪዥንና የዲኮደር ሪሞት የሚሉት ነገር ከቁጭ ብድግ መገላገሉ አሪፍ ነው...ሁሉ ቦታ አንደዛ ላይሆን ይችላል እንጂ!  ከዓመት ምናምን ገደማ በፊት በሪሞት ምክንያት በተነሳ ጭቅጭቅ የሚኖሩበትን የኮንዶሚኒየም ህንጻ በጥፍሩ ሊያቆሙት ምንም ስላልቀራቸው ባልና ሚስት ሰምተን ነበር፡፡ አባወራ ሆዬ መሸት አድርጎ ይገባና ‘ቲቪ’ ለመክፈት የዲኮደሩን ሪሞት ያጣዋል፡፡
ይህን ጊዜ “ሪሞት ኮንትሮሉን የት ወሰዳችሁት?” ብሎ ሲጮህ፣ ሚስት ሆዬ አገር ሰላም ብላ “እኔ’ጃ፣ እስቲ ሶፋው ስር ተወሽቆ እንደሆነ ፈልገው፣” ትላለች። እናላችሁ...አባወራ ሆዬ ‘ባሊስቲክ’ ሆኖ አረፈዋ! መጀመሪያ ነገር ለምን ከነበረበት ይነሳል ምናምን ብሎ...ምን አለፋችሁ ላይ ፎቆቹም፣ ታች ፎቆቹም ብቅ፣ በቅ እስኪሉ ድረስ ሲጮህ ነበር አሉ...ሪሞት ለሚሏት ነገር!
“ብቻ ዲጂታል ስቶቭ የለንም እንዳትሉኝ!” አሀ...ማን ከማን ያንሳል! እኔ የምለው... ዲጂታል ስቶቭ የተባለው...እንደ ሞባይል ካርድ እየተሞላ የሚሠራ ነው? ቂ...ቂ...ቂ...
ደህና ሰንብቱልኝማ!

Read 1771 times