Monday, 04 October 2021 00:00

ከአዲሱ የኢትዮጵያ መንግስት ምን እንጠብቃለን?

Written by  ጉ ጆርጊ ታ
Rate this item
(0 votes)

ሰሞኑን ጀርመናውያን ባደረጉት ምርጫ፣ ከ15 ዓመታት በላይ ሀገሪቱን ሲመሩ የነበሩትንና የጀርመን ብቻ ሳይሆን የአውሮፓም መሪ ተደርገው ሲቆጠሩ የቆዩት፣  በዓለም እጅግ ኃያሏ ሴት፣ የአንጌላ ሜርክል ፓርቲ መሸነፍን ከመገናኛ ብዙኃን  ሰምተናል፡፡ ሴትየዋ የስልጣን ጊዜያቸው ስላበቃ ለውድድር ባይቀርቡም፣ እንዴት የሳቸው ፓርቲ ሳያሸንፍ እንደቀረ  ለመረዳት፣ የጀርመንን ህዝብ ፖለቲካዊ፣ ባህላዊና ታሪካዊ ሁኔታ በቅርበት ማወቅ ወይም መመርመርን ይጠይቃል፡፡
በእኛም ሀገር በዐጼ ምኒሊክ ዘመን ተነገረ የተባለና ዛሬም ድረስ ቢያንስ በእኔ አስተያየት እውነት የሆነ አንድ ባህል አለን፡፡ ታሪኩ ንጉሠ ነገስቱ የግብር ክፍያ ላይ ጭማሪ ለማድረግ ከማሰባቸው ጋር የተያያዘ ነው፡፡ እናም የግብር ጭማሪ አዋጅ ያስነግሩና ተግባራዊ ከመሆኑ በፊት እስቲ ሰው ምን እንደሚል አዳምጡ ብለው አገልጋዮቻቸውን ያዛሉ። የተሰበሰበው ወይም የተሰለለው የህዝብ ድምጽ “እንዲህማ ተሆነ ንጉስ ቢቸግራቸው ነው” የሚል መሆኑን በሰሙ ጊዜ፣ በሉ እንግዲህ በአዋጁ መሰረት ይፈጸም አሉ ተባለ፡፡ ይኸው ታሪክ ከጥቂት ዓመታት በኋላ ሲደገም እንደተለመደው ሕዝቡ ምን ይላል ተብሎ ጥናት ሲደረግ--ብትፈልጉ መረጃ ሲሰበሰብ ልትሉት ትችላላችሁ--የተገኘው ምላሽ “ዝም አለ ወይም ምንም አላለም” ሆኖ ሲገኝ፣ ንጉሡ “እህህ! ነገር አለ ማለት ነው፣ በሉ ተውት“ የሚል ትዕዛዝ ይሰጣሉ፡፡  ይህን ታሪክ ምን ላይ እንዳነበብኩት ወይም የት እንደሰማሁት አሁን ትዝ አይለኝም፣ እኔ የፈበረኩት ግን አይደለም፡፡ ባለፈው ሰኔ ወር ኢትዮጵያውያን ወደ ምርጫ ጣቢያ የሄዱት፣ የሆዳቸውን በሆዳቸው ይዘው ይመስለኛል፡፡
ከፖለቲካው ንፍቀ ክበብ  ብዙ የራቅሁ ስለሆነ፣ ከወዳጆቼና ከቤተሰብ ጋር ከማደርገው ውይይት ባሻገር የዘንድሮን ምርጫ ማን ያሸንፋል የሚለውን ለመተንበይ የሚያስችል መረጃ አልነበረኝም። እንዳብዛኛው የኔ ቢጤ አንደኛው ፓርቲ እዚህና እዚያ አካባቢ፣ ሌላኛው ደግሞ እንዲሁ በተወሰኑ አካባቢዎች፣ ሌሎችም እንዲሁ ያሸንፉና የሚመሰረተው መንግስት ጥምር ሊሆን ይችላል ብዬ ነበር የገመትኩት። የኔ በዕውቀት ላይ ያልተመሰረተ የፖለቲካ ግምቴ ሚዛን የሚደፋ እንደማይሆን ቢገባኝም፣ ብልጽግና በዚህ የሰፋ ልዩነት ያሸንፋል ብሎ የጠበቀ ብዙ ሰው አለ ብዬ አላስብም--ፖለቲከኞቹ የነበራቸውን ትንበያ ሳናካትት፡፡ ታዲያ ለብዙዎቻችን--በተባራሪ ወሬ እንደሰማሁት፣ የምርጫ ቦርድ ሰዎች ሳይቀሩ--ይህ የሰፋ የድምጽ ልዩነት ያልተጠበቀ ነበር፡፡ ጥያቄው እኛ በተለይም ቀለም ቆጥረናል፣ የሀገራችንን የፖለቲካ ትኩሳት በደንብ ተረድተናል ብለን የምናስብ ሰዎች፣ እንዴት የህዝቡን ስሜት ሳናነበው ሳንረዳው ቀረን? በሚል ሊቀርብ ይችላል፡፡ ግን ከዚያም የጠለቀው ጥያቄ፣ ከሞላ ጎደል በሁሉም የፖለቲካ ፓርቲዎች--ከምርጫው ውድድር ራሳቸውን ያገለሉ ሳይቀሩ--ዘርፈ-ብዙ መከራከሪያ እያቀረቡ የረገሙትና ለዚህች ሃገር አይመጥንም ወይም ለዚህ ብሔር አይበጅም ብለው ያወገዙት ፓርቲ፤ እንዴት በዚህ ዓይነት የሰፋ ልዩነት የህዝቡን ድምጽ ሊያገኝ ቻለ? የሚለው ይመስለኛል። የምኒልክ ዘመንን ታሪክ ያስታወሰኝም ይህ አስገራሚ ኩነት ነው፡፡ በባህላችን አለመስማማታችንን ከምንገልፅባቸው ብልሀቶች አንደኛው ዝምታ ነው--ብትፈልጉት በጓደኛሞች መሀከል ወይም በቤተሰብ ውስጥ አሊያም በስራ ባልደረቦችና በጎረቤታሞች መሀከል ታገኙታላችሁ፤ ሙያ በልብ ነው፡፡ ከምርጫው ጋር ለምን ይህንን ፓርቲ ከሌሎች አብልጠህ/ሽ መረጥሽ/ክ የሚል መጠይቅ በሌለበት ይህን ሚስጥር በምን ማወቅ ይቻላል? መካድ የማይቻለው ግን እያንዳንዱ መራጭ ብልጽግናን ይሁን ሌላ ፓርቲ አለምክንያት አለመምረጡን ነው፡፡ የዘርፉ ባለሙያዎች የተጠኚዎችን ማንነት የማይለይ ወይም በሚስጥር የሚይዝ (anonymous) መለስተኛ ጥናት አድርጋችሁ፣ ውጤቱን ጀባ ብትሉን፣ ለተመረጡትም፣ ላልተመረጡትም፣ ለኛም አወቅን ባዮች ጭምር ብዙ ትምህርት ይሰጠናል፡፡
ህዝቡ የመረጠውን ፓርቲ ተጠያቂ ከማድረግ ባለፈ የሚመሰረተው መንግስት በስልጣን ዘመኑ እንዲያከናውን ህዝቡ የሚጠብቀውን ለውጥ ከ“ወትሯዊ" ምርጫዎች የተለየ  የሚያደርጉት ወቅት ላይ መሆናችንን መገንዘብና ይህንንም የህዝብ ስሜት በከፍተኛ ጥንቃቄ ማዳመጥና ተገቢውን የአጭርና የረዥም ጊዜ ዕቅድ ነድፎ ምላሽ መስጠትና፣ ይህም ሲደረግ ህዝቡን በየደረጃው ማሳተፍ እጅግ አስፈላጊ ይመስለኛል፡፡ የዚህ ውጤትም ህዝብ በመንግስት ላይ አመኔታ እንዲሳድርና “ ሀገሬ ነው“  የሚለው ስሜቱ እንዲጎለብት ማስቻል ነው፡፡ በኔ አስተያየት፣ በህዝብ ዘንድ “ይህ መንግስት የቆመው ለኔ ነው፤ ሀገሪቷም የኔ ናት!“ የሚል ስሜት ማስፈን ተቻለ ማለት፣ ከድኅነት ማጥ ለመውጣትና ሰላማዊ ሀገር ለመመስረት መሰረቱ ተቀመጠ፤ የማይናወጥ መሰረት ተጣለ ማለት ነው፡፡
ከአዲሱ መንግስት ሕዝቡ ብዙ እንዲጠብቅና ይህም ባይሟላለት እንዲቆጣና ላመጽ እንዲነሳሳ የሚያደርጉት አንዳንድ ቁልፍ ጉዳዮች የምላቸውን ላንሳ፡-
ሀ) መንግስት በሰሜኑ የሀገራችን ክፍል የገባበትን ጦርነት እንደ ራሱ ጦርነት በመውሰድ ገደብ የለሽ ተሳትፎ አድርጓል። ተዋግቷል፤ ልጆቹን ወደ ግንባር መርቆ ልኳል፤ ደም ሰጥቷል፤ ገንዘብ፣ ምግብና ቁሳቁስ አቅርቧል፡፡ ከባለሀብቱ፣ ከክልል መንግስታት፣ ከመንግስት ሠራተኞችና ከሌሎች ተራ ዜጎች ባሻገር አንዲት ገጽታቸው የተጎሳቆለ እናት፤ አንድ ሺህ እንጀራ ጋግረው፣ ለሠራዊቱ ማቅረባቸውና በአማራ ክልል ባለ አንድ የጦር ግንባር የሆነ ከተማ ነዋሪ የሆኑ ወጣቶች፣ የመስቀልን በዓል የወታደሮችን ጫማ በመወልወል፣ ለሠራዊቱ ያላቸውን ክብር የገለጹበት መንገድ ብቻ እንኳን የሚናገሩት ታሪክና ጮክ ብሎ የሚጣራ  የዕዳ ቁልል ነው፡፡
ለ) በብዙ ሀገራት እንደታየው፣ ህዝብን ለቁጣና ለአመጻ አነሳስቶ፣ መንግስት በነውጥ አንዲነሣ የሚያደርገው የኑሮ ውድነት ነው፡፡ መራጩ ህዝብ ግን ዝም ያለው ያለምክንያት አይደለም--የገባውን ያህል ተረድቶ ደግሞም ይህንኑ ችግርና ሰቆቃ ችሎ ነው ብልጽግና ያስተዳድረኝ ብሎ የወሰነው፡፡ ምናልባትም እስቲ መጀመሪያ የገባበትን የሕልውና ጦርነት ይወጣ ብሎ ይሆናል፤ ፋታ እንስጠው ያለው። በመንግስት በኩል “ዋጋ ለማረጋጋት" የሚደረገውን ጥረት እንሰማለን፤ የሺህ ማይል ጉዞ ባንድ እርምጃ ነው የሚጀመረው እንዲሉ፣ ድርጊቱ ጥሩ ጅማሮ ቢሆንም፣ ከኑሮ ውድነቱና የዋጋ ግሽበቱ አንፃር አባይን በጭልፋ ነው-- መንግስት ረዥም ሥራና ብዙ ፈተና ይጠብቀዋል፡፡ በሌላ በኩል፤ ሕዝብ ከመንግስት ያልዘገየ ምላሽ ይጠብቃል፡፡
ሐ) በያካባቢው ሕዝብ በሰላም እንዳይኖር ጸጥታ በማደፍረስ፣ ዜጎችን በመግደልና አካለ ጎደሎ በማድረግ በዛቻና ማስፈራሪያ የመኖሪያ ቀያቸውን ትተው እንዲፈናቀሉና እንዲሰደዱ፣ ቤትና ንብረታቸው እንዲፈርስ …..ወዘተ የተደረጉ ሕብረተሰቦችንና ዜጎችን ብዛት በተመለከተ መንግስት በቂ መረጃ እንዳለው የሚያጠራጥር አይደለም። ከመንግስት ባለሥልጣናት ጭምር እንደምንሰማውም፣ ይህ ውስብስብ የአፈናና የወንጀል መረብ እራሳቸው የመንግስት ባለስልጣናትን ያካተተ ነው፡፡ ወንጀለኞቹ ለሕግ እንዲቀርቡ፣ ተፈናቃዮች ወደ መንደራቸው ተመልሰው፣ የቀደመ ኑሯቸውን በሰላም አንዲቀጥሉ፣  መንግስትን አሁኑኑ መፍትሄ ካልሰጠኸን ብለው ያልጠየቁት፣ አሁንም በምከንያት ነው፡፡ ግን ጥበቃው ገደብ አለው፡፡ ገደቡን ሲያልፍ…?
መ) ሙስናና የጎደፈ አስተዳደር፡- ይህ ጉዳይ መልከ-ብዙ ነው፡፡ የቀበሌና የወረዳ መስተዳድሮች፣ አብዛኛው ህዝብ፣ ለትንሹም ለትልቁም ጉዳይ በየዕለቱ ደጅ የሚጠናቸው ናቸው፡፡ የነዋሪነት መታወቂያ ለማውጣት፣ ያገባ/ያላገባ ማስረጃ፣ ለጥቃቅን የቤት ወይም የአጥር ዕድሳት ወይም ጥገና ፈቃድ ፍለጋ፣ እዚህ ግባ ለማይባሉ ጥቃቅን ግጭቶች ፍትህ ፈላጊዎች፣ ላነስተኛና ጥቃቅን ንግድ ፍቃድ፣ ግብር ለመክፈል፣ ፍቃድ ለማሳደስ፣ የሁከት ይወገድልኝ አቤቱታዎች……ወዘተ ህዝቡ ተስፋ የቆረጠባቸው ግን ደግሞ ምርጫ ስለሌለው “ቀን እስኪያልፍ……." እንዲሉ፣ “ድንጋዩን በኪሱ…….." ቀን እየጠበቀላቸው መሆኑን የተመራጩ  መንግስት አካላት የማያውቁት ሚስጥር አይደለም፡፡ የመንግስትና የግል ጤና ተቋማት፣ የውሃ፣ የስልክና የመብራት አገልግሎት፣ የመሬት ይዞታ አስተዳደር፣ ግብር ተቀባይ መስሪያ ቤቶች፣ ፍርድ ቤቶችን ጨምሮ ከሞላ ጎደል በሁሉም አገልግሎት ሰጪ ተቋማት፣ ዛሬም ተገልጋዩ ሕዝብ፣ እንደ ደጅ ጠኚ ተለማምጦ፣ አንገቱን ደፍቶ፣ እጅ መንሻ ሰጥቶ፣ ለዚያውም ጥራቱ የተጓደለ ግልጋሎት የሚሰጥን መንግስት የሚታገሰው ለዝንታለም አይመስለኝም። በነገራችን ላይ ሰው ታሞብኛል ብላችሁ አምቡላንስ ብትደውሉ፣ አለ ላኪና ተቀባይ ሀኪምና ተቋም ስምና ስልክ ለታመመባችሁ ሰው የአምቡላንስ አገልግሎት እንደማታገኙ ስንቶቻችሁ ናችሁ የምታውቁት? የግል የህክምና ተቋማት የሚጠይቁት የአገልግሎት ክፍያም በህዝቡ ዘንድ መነጋገሪያ ከሆነ ውሎ አደረ፡፡ ከፋም ለማም እንደ ብዙዎች አስተያየት፣ እነዚህ ግልጋሎቶች ካዲሳባ እየራቃችሁ ስትሄዱ “ከዝንጀሮ ቆንጆ……" እንዲሉ፣ የባሰ ብልሹ ሆነው ነው የምታገኟቸው። ከአስተዳደር፤ ከአገልግሎትና ከፍትሕ እጦት ጋር በተያያዘ ህዝብ ብዙ ያልተመለሱ ጥያቄዎች አሉት-- እነዚህም ጥያቄዎች ህዝብ ያልዘገየ ምላሽ የሚጠይቅባቸው ናቸው፡፡
ምን ይደረግ?
ሀ) አገልግሎቶች ይቀላጠፉ፡- ሃኪም ሁሉንም በሽተኛ ሊያድን አይችልም። በድህነታችን ምክንያት ደግሞ የህክምና ጥበብ የደረሰባቸውን ቴክኖሎጂዎች በሁሉም ቦታ ማዳረስ ለጊዜው አንችልም። በከፍተኛ ደረጃ የሰለጠኑ ባለሙያዎችን በሁሉም ቦታ ላናገኝ እንችላለን፡፡ ግን ቢያንስ አንድ ታማሚ ሰብዓዊ ክብሩ ሳይዋረድ ወይም ዘመድና ጓደኛ ሳያሻው፣ ምንህን ነው ያመመህ? ምን ልርዳህ? ልርዳሽ ተብሎ/ላ የምትስተናገድበት የጤና አጠባበቅ ስርዓት ብርቅ ሊሆንብን አይገባም። አዎን ሁሉም የጤና ባለሙያዎች፣ በቂ የክህሎትና የባህርይ ወይም የሥነ-ምግባር ስልጠና ሳይገኙ ቀርተው ይሆናል። የጤና ባለሙያዎች ከስራቸው ክብደትና ኃላፊነትአኳያ የሚያገኙት ደሞዝና ጥቅማ ጥቅም በቂ ላይሆን ይችላል፡፡ ይህ ግን ከአገሪቱ የኢኮኖሚ አቅም ዕድገት ጋር አብሮ እንደሚያድግ ይታወቃል፡፡  የህክምና አገልግሎት እንደ ምሳሌ ይቅረብ እንጂ የአገልግሎት ማሻሻያዎች ሁሉንም ዘርፎች ይመለከታል፡፡ በኔ አስተያየት ከሁሉ የሚቀድመው፣ የፖለቲካ አመራሩ ቁርጠኝነት ነው፡-ሌላ ሌላው ሁሉ ከዚያ ይከተላል፡፡
ለ) ህዝባዊ ተሳትፎ፡- ህዝብ በሀገሬ ጉዳይ ያገባኛል ሊል የሚችለው መንግስት የህዝብን ድምጽ የሚሰማባቸው መድረኮች ሲፈጠሩለትና የሰጠው ሃሳብና አስተያየት በመንግስት ውሳኔዎች ዓይነተኛ ግምት እንደሚሰጣቸው ሲገነዘብ ነው፡፡ እንደሚመስለኝ በብዙ የገጠር አካባቢዎች፣ የተዳከሙ ግን ያልፈረሱ የኅብረተሰብ ስርዓቶችና መዋቅሮች አሉ፡፡ እነዚህን እንደየሁኔታው ማጥበቅ፣ ማጠናከርና ማሻሻል ጠቀሜታው እጅግ የላቀ ነው። ሰሞኑን የኢትዮጵያ ቴሌቪዥን ያቀረበው የሶዶ ጉራጌዎች የዳኝነትና የእርቅ ጉባኤ አንድ ጥሩ ምሳሌ ነው፡፡ የጋሞ አባቶችና እናቶች ያን ሰሞን የተፈጸመው የቡራዩ ሰቆቃና ግፍ ባጭሩ እንዲቀጭ የወሰዱት አርአያነት ያለው ተግባር፣ በየአካባቢው ያለንን ባህላዊ እውቀትና ጥበብ አንዴት ለሀገር ጥቅም ማዋል እንደሚቻል አስተምሮን ያለፈ የታሪካችን አንድ አካል ሆኗል፡፡ እነዚህ በምሳሌነት ተጠቀሱ እንጂ በሁሉም ብሔሮች ዘንድ ያሉ ዕድሜ ጠገብ የትየለሌ የማህበረሰብ አስተዳደር ስርዓቶች እንዳሉን የታወቀ ነው፡፡ ከተሞች የተለየ አሰራር ያስፈልጋቸው ይሆናል፡፡ ነገር ግን ከመኖሪያ ሰፈሮችና ጎረቤቶች  ጀምሮ በያካባቢው በሰላምና ጸጥታ ጉዳዮች፣ በአካባቢ ጥበቃና ጽዳት፣ በግጭት አፈታት፣ በደስታና በኃዘን ጊዜ ስለሚኖሩ ትብብሮች….. ወዘተ ብዙ ስራ ይቀረናል፡፡ አዲሳባና ምናልባትም አንዳንድ ትላልቅ ከተሞች፣ የመኖሪያና የንግድ ወይም የስራ ቦታዎች መቀላቀልና በስርዓት አለመደራጀት፣ በነዋሪዎች ላይ ከሚያስከትለው የጤና ጉዳትና በልጆች አስተዳደግ ላይ ሊፈጠር ከሚችለው በጎ ያልሆነ ተጽዕኖ ማላቀቅ ታላቅ ትኩረት የሚያሻው ጉዳይ ነው፡፡ የከተማ እቅድ አውጪዎችና የጤና ተመራማሪዎች በዚህ ጉዳይ ላይ አንድ የናሙና ጥናት አድርገው፣ ከውሳኔ ሃሳብ ጋር ለመንግስት ቢያቀርቡ፣ በመረጃ ላይ የተመሰረተ የፖሊሲና የተግባር አቅጣጫ ለመንደፍ ያስችላሉ፡፡
ሐ) ሰላም እርቅ፡- ልዩነቶቻችንን በአጉሊ መነጽር እየፈለግን ተቋስለናል። ይህን ቁስል ለመሻር መትጋት አለብን። በያካባቢው የተጀመሩ የእርቅና የሰላም ጥረቶች ተጠናክረው ይቀጥሉ፣ በእውቀት ልምድና ሀገራዊ ጥበብ ላይ ተመረኩዘው ይበልጽጉ፡፡ በየከተማውና የገጠር መንደሮች ሰላም ይሰበክ፤ እርቅ ይውረድ፡፡ በትግራይ ሕዝብና በተቀሩት ኢትዮጵያዊያን መሀከል የተፈጠረው ልዩነትና መከፋፈል ከሁሉም ወገን የላቀ ትኩረት የሚሻ ይመስለኛል፡፡ የትግራይ ልጆች  በማንኛውም የኢትዮጵያ ክፍል እንዳሻቸው ተዘዋውረው ይማሩ፤ ይነግዱ፣ ይስሩ፡፡ ሌላውም ኢትዮጵያዊ በየትኛውም የኢትዮጵያ ክፍል፣ ያለገደብ እየተዘዋወረ ሀገሩን ይወቅ፤ ይማር፡ ይነግድ፤ ይስራ፡፡ ምናልባትም በ“demographic engineering“ ነት እንዳልከሰስ እንጂ ወጣቶች የትዳር ጓደኞቻቸውን ከራሳቸው ብሔር ወይም ጎሳ ውጪ እንዲሹ ቢበረታቱስ? ይህ ሃሳብ ተቀባይነት የሚያገኝ ከሆነ፣ የየብሔሩን ባህልና ቋንቋ ከመጠበቅና ከማበልጸግ ተግባር ጋር ተባባሪ እንጂ ተጻራሪ መሆን እንደሌለበት ልብ ይሏል፡፡ እንዲያውም ከተለያዩ ብሔሮች የሚወለዱ ልጆች የሁለቱንም ወላጆቻቸውን ባህልና ቋንቋ እንዲያጠኑ፣ የወላጆቻቸው ወይም የአያቶቻቸውን የትውልድ መንደር እንዲያውቁ ዕድል መፍጠር፣ ሀገራቸውን የበለጠ  እንዲያውቁ ይጠቅማቸዋል ብዬ አስባለሁ፡፡
ከላይ የተሰነዘሩት አስተያየቶች እጅግ የገዘፉ የሀገር አስተዳደር ብልሀቶችን ወይም ፖሊሲዎችን (የኢኮኖሚ፣ የፖለቲካ፣ የማሕበራዊ ሕይወትና አገልግሎቶችን፣ የሀገር ደሕንነትና ጸጥታን ወይም የውጪ ፖሊሲን…ወዘተ) የሚተኩ ወይም እነዚህ ፖሊሲዎች ላይ አስተያየትና ትችት ማቀረብ ላይ ያተኮሩ አይደሉም፡፡ በያንዳንዱ ትላልቅ ሀገራዊ ፖሊሲ ላይ መተቸት ምናልባትም የዘርፉ ባለሙያዎችንና የሚመለከታቸውን  አካላት ያካተተ ውይይትና ምክክር የሚጠይቅ ሰፊ ስራ ይመስለኛል፡፡ ይልቁንም የጸሃፊው መልዕክት ህዝቡ መንግስትን እንዲያምንና ሀገሬ ነው የሚል የባለቤትነት ስሜቱ በበለጠ እንዲዳብር  ዛሬ ነገ ሳይባል በቅድሚያ ሊሰራ የሚገባው መሰረታዊ የአገልግሎትና የአስተዳደር ማሻሻያ ላይ የግሉን አስተያየት ለማጋራት ከሚል መነሳሳት ያቀረበው፡፡ ለነዚህ ጉዳዮች እልባት መስጠት ከተቻለ በጋራ ወገባችንን አስረን ከድህነት ለመውጣት የሚያስችል ስርዓት ገነባን ማለት ነው፡፡ ይህ አጭር ጽሑፍ በሌሎች ዘንድ ውይይት ከቀሰቀሰና  ትችት ካስከተለ  ግቡን መቷል ማለት ነው፡፡ ባለስልጣናቱ በሚዲያ ፍተሻቸው ዓይናቸው ካረፈበት ደግሞ ተጨማሪ ስኬት ነው-ካላሰቡበት እንዲያስቡበት፣ ካሰቡበት እንደ ተጨማሪ ግብአት ይሆናቸዋል ብዬ አስባለሁ፡፡
መልካም የአዲስ መንግስት ምሥረታ

Read 3372 times