Saturday, 09 October 2021 00:00

እናት ፓርቲ በአዲሱ መንግስት ቅድሚያ ሊሰጣቸው ይገባል ያላቸውን 6 ጉዳዮች አመለከተ

Written by 
Rate this item
(1 Vote)

እናት ፓርቲ በአዲሱ የዶ/ር ዐቢይ አህመድ መንግስት ቅድሚያ ሊሰጣቸው  ይገባል ያላቸው 6  መሰረታዊ ጉዳዮች ይፋ አደረገ፡፡
ፓርቲው በመግለጫው በቀዳሚነት  የጠቆመው የዜጎች ወጥቶ የመግባት ዋስትና የማረጋገጥ ጉዳይ ሲሆን በዚህ  ረገድ መንግስት የህዝብንና የዜጎችን ደህንነት በማንኛውም መልኩ መጠበቅና የዜጎችን ወጥቶ የመግባት ዋስትና የማረጋገጥ፣ ችግሮች ከመከሰታቸው በፊት አስቀድሞ የመከላከል ተግባር ላይ እንዲያተኩር፣ ከተከሰተ በኋላም በአፋጣኝ ህይወትን የመታደግ ተግባር እንዲያከናውን መክሯል።
በሁለተኛነት ያስቀመጠው የሃገር ሉአላዊነትን የማስከበርና ቀጠናዊ ሁነቶችን የመከታተል ጉዳይ ሲሆን በዚህ ረገድ መንግስት ኢትዮጵያ ካለችበት ቀጠናዊ ሁኔታና የሃይል ሽሚያ አንፃር ተገቢውን ትንተና በማድረግ ጊዜውን የሚመጥን ተለዋዋጭ መፍትሄ ማስቀመጥ ይገባል ብሏል።
ከዚሁ ጋር በተያያዘ  በሰሜኑ የሃገራችን ክፍል ያለው ቶርትም በሉአላዊነታን ላይ ተግዳሮትን የደቀነ እንደመሆኑ በጊዜ የሚቋጭበት መንገድ እንዲፈለግ ጠይቋል።
በሶስተኝነት ትኩረት ይሰጠው ያለው ምጣኔ ሃብታዊ ጉዳይ ሲሆን አሁን  ባለው የኑሮ ውድነት ማህበረሰቡ ወገቡ እየጎበጠ ነው፤ ስለዚህም ተመሳሳይ ክስተት ካስተናገዱ ሃገራት ልምድ ተቀስሞ ከዚህ ችግር መውጫ አፋጣኝ መፍትሄ ካልተበጀለት ሌላ የጦር ግንባር መሆኑ አይቀሬ ነው ብሏል።
በአራተኛነት የተመለከተው ህግና ፍትህ ነክ ጉዳዮች ሲሆን “በሃገራችን  ውስጥ ያሉ ግጭቶች ከአቅም አነስ ሴረኛ አመራሮች የሚነሱ ሆነው ዋናው ምንጫቸው ግን ህገ መንግስቱ ላይ ያሉ አንዳንድ አደገኛ አንቀጾች ናቸው” ያለው ፓርቲው፤ በመሆኑም ህገ መንግስቱ በጥሞና ታይቶ ማስተካከያ ሊደረግበት ይገባል ብሏል። ከዚህ አንጻር እየታየ ያለው የፍትህ እጦት ከወዲሁ አፋጣኝ እርምጃ ተወስዶ ካልተስተካከለ ወዳልተፈለገ አቅጣጫ ሊወስደን ይችላል ብሏል።
ሌላኛውና 5ኛቀው ፓርው ያመላከተው የትኩረት አቅጣጫ  የማህበረሰባዊ መስተጋብር ጉዳይ ሲሆን የኢትዮጵያ ህዝብ ከልዩነቱ አንድነቱ የበረታ ሆኖ ሳለ አሁን እየታዩ ያሉ የልዩነት ግንብ የሚያሳድጉ ክስተቶች ከእለት እየጨመሩ በመሆኑና እነዚህ ጉዳች የኢትዮጵዊነት እሴቶችን ከመሸርሸራቸው በፊት መፍትሄ ሊበጅላቸው ይገባል ብሏል። ለዚህም ሃገራዊ መግባባት ላይ የተያዙ ውጥኖች በአፋጣኝ ወደ መሬት ወርደው እንዲተገበሩ ፓርቲው ጠይቋል።
በመጨረሻም ፓርቲው የትኩረት አቅጣጫ እንዲሆን በሞከረ ሃሳብ ያቀረበው የመልካም አስተዳደር ጉዳይ ሲሆን አዲስ አበባን ጨምሮ በመላ ሃገሪቱ ያው ኢ-ፍትሀዊና አድሏዊ አሰራርን የሚያስወግድ መፍትሄዎች ያሻሉ ብሏል።
እጅ መንሻ የሚጸየፉ፣ ህዝብ የማገልገል ትርጉም የገባቸው አገልጋዮች፣ በየስራ መደቡ የሚቀመጡበት አሰራር እንዲፈጠርም  ፓርቲው አስገንዝቧል።
በአጠቃላይ አሁን ያለው አብዛኛው ችግር የመጣው ከኢትዮጵያና ኢትጵያውያን  ስነልቦና ውጪ ከባዕድ በተኮረጁ ቅንጥብጣቢ እውቀቶችና በእኛ ልክ ባልተሰፋ ርዕዮት አለማዊ ተፋልሶ ነው ለው ፓርቲው፣ በዚህም ርዕዮተ አለሙን በኢትዮጵያዊ መነጸር እንደ አዲስ ማሽትና ማረቅ ተገቢ ነው ብሏል።
ፓርቲው በመግለጫው ማጠቃለያም ለተመሰረተው መንግስትና በየደረጃው በአገልጋይነት ለተሾሙ ሁሉ “እንኳን ደስ አላችሁ መልካም የአገልግሎት ዘመን ይሁንላችሁ” ብሏል።


Read 9698 times