Saturday, 09 October 2021 00:00

ኢሰመጉ በቁጫ ወረዳ ይፈጸማሉ ያላቸውን የሰብአዊ መብት ጥሰቶች እዲታረሙ አሳሰበ

Written by 
Rate this item
(3 votes)

 በደቡብ ክልል በጋሞጎፋ ዞን ቁጫ ወረዳ ዜጎችን በህገ-ወጥ መልኩ ከስራ የማፈናቀልና ህገ-ወጥ እስርን ጨምሮ የተለያዩ ሰብአዊ መብት ጥሰቶች እየተፈጸሙ መሆኑን ኢሰመጉ አስታወቀ።
የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ጉባኤ ከትናንት በስቲያ ይፋ ያደረገው አስቸኳይ ጋዜጣዊ መግለጫ ከቁጫ ወረዳ የደረሰውን ጥቆማ ተከትሎ ባደረገው ምርመራ እና ክትትል ከመስከረም 1 ቀን 2014  ጀምሮ ባሉት ተከታታይ ቀናት በተለያዩ ወረዳዎች ያለምክንያት በጸጥታ አካላት ለእስር እየተዳረጉ ስለመሆኑ፣ ድብደባ እንደሚፈጸምባቸው፣ ፍ/ቤት ሳይቀርቡ ለበርካታ ቀናት እደሚታሰሩ፣ መንግስት ሰራተኞች ከህግ  አግባብ ውጪ ከስራቸው እንደሚባረሩ፣ የሰራተኞች ደመወዝ ያለ አግባብ መያዝና ከህግ ውጪ በሆነ መልኩ ከስራ መደብ ዝቅ ማድረግን የመሳሰሉ ተግባራት እየተፈጸሙ መሆኑን መረጃዎች እንደደረሱት ኢሰመጉ አመልክቷል።
የአካባቢው ባለስልጣናት እየተፈጸመ ያለውን መጠነ ሰፊ የሰብአዊ መብት ጥሰት በቸልታ እንደማመለከቱት የገለጸው ኢሰመጉ በቀጣይ የደረሱትን ጥቆማዎች መነሻ በማድረግ ሰፊ ምርመራ እንደሚያደርግም አመልክቷል።
እነዚህን ጥቆማዎች መሰረት በማድረግ መንግስት አስፈላጊውን የማስተካከያ እርምጃ እንዲወስድ የጠየቀው ኢሰመጉ፣ በተለይ የአካባቢው የፍትህ አካላት ቅሬታ የሚቀርብባቸውን ህገወጥ ድርጊቶች የሚታረሙበትን መንገድ  እንዲያፈላልጉ፤ በህገ ወጥ እስር ላይ የሚገኙ በአስቸኳይ እንዲለቀቁ፣ የሰራተኞች መብቶች  ሳይሸራረፉ  እንዲከበሩና በደል የደረሰባቸው መፍትሄ እንዲሰጣቸውና ኢ-ሰብአዊ ድርጊቶችን በማናቸውም መልኩ የሚፈፀሙ አካላት ለህግ እንዲቀርቡ ኢሰመጉ በመግለጫው ጠይቋል።

Read 10341 times