Saturday, 09 October 2021 00:00

በኢትዮጵያ ጉዳይ እንቅልፍ ያጡት የመንግስታቱ ጽ/ቤትና የአውሮፓ ህብረት

Written by  መታሰቢያ ካሣዬ
Rate this item
(13 votes)

• የተባበሩት መንግስታት ድርጅት በኢትዮጵያ ጉዳይ ለ10ኛ ጊዜ ያካሄደው ስብሰባ ያለ ውጤት ተበትኗል
 • የአውሮፓ ፓርላማ በኢትዮጵያ ላይ ማዕቀብ ለመጣል እየተዘጋጀ ነው

• በጀርመን የሚኖሩ ኢትዮጵያውያንየአውሮፓ ፓርላማ ያቀረበውን ረቂቅ ሃሳብ ተቃወሙ
  በኢትዮጵያ የውስጥ ጉዳይ ጣልቃ በመግባት በአገሪቱ ላይ ጫና ለማሳደር ሌት ተቀን እየሰሩ ያሉት የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የጸጥታው ጥበቃ ምክር ቤትና የአውሮፓ ህብረት ፓርላማ፤ በኢትዮጵያ ጉዳይ ላይ እያሳዩ ያሉትን ግልጽ አድልዎ እንዲያቆሙና እውነታውን እንዲያገናዝቡ ተጠየቀ።
በጀርመን የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን ተቋማቱ በኢትዮጵያ የውስጥ ጉዳይ ላይ እያካሄዱ ያሉትን ጣልቃ ገብነትና ግልጽ አድልዎ እንዲያቆሙና እውነታውን እንዲያገናዝቡ ጠይቀዋል።
የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የጸጥታ ጥበቃ ምክር ቤት ከትናንት በስቲያ ለ10ኛ ጊዜ በኢትዮጵያ በትግራይ  ጉዳይ ላይ ያደረገው ውይይት ያለ ውጤት ተበትኗል። ይህ የምክር ቤቱ ስብሰባ የኢትዮጵያ መንግስት፣  በተባበሩት መንግስታት ድርጅት  ውስጥ የሚሰሩት ከፍተኛ ሃላፊዎችን በአገሪቱ የውስጥ ጉዳይ ጣልቃ ገብተዋል በሚል ከግዛቷ እንዲወጡ ካዘዘች በኋላ የተደረገ ሁለተኛ ስብሰባ ነው።
የጸጥታው ምክር ቤት አባል አገራት የሆኑት አሜሪካ፣ አየርላንድ፣ ኖርዌይ፣ ዩክሬን፣ ሂስቶኒያና ፈረንሳይ፤ ምክር ቤቱ በጉዳዩ ላይ ተወያይቶ ውሳኔ እንዲያሳልፍ በጠየቁት መሰረት የተከናወነ ቢሆንም ስብሰባው ያለውጤት መበተኑ ታውቋል።
ምክር ቤቱ ከትናንት በስቲያ ያካሄደው ስብሰባ  ዋንኛ አጀንዳ በኢትዮጵያ በትግራይ ክልል ስላለው ሁኔታ ተወያይቶ ውሳኔ እንደሚያሳልፍ ተነግሮ የነበረ ቢሆንም ሰፊውን ጊዜ የወሰደው ግን የኢትዮጵያ መንግስት ከአገር እንዲወጡ ያደረጋቸውን 7 ሰራተኞች የተመለከተ ነበር። በዚህ ስብሰባ ላይ የተሳተፉት በተባበሩት መንግስታት ድርጅት የኢትዮጵያ አምባሳደር ታዬ አጽቀስላሴ ፣ ለፀጥታ ምክር ቤቱ ጉዳዩን  በተመለከተ ማብራሪያ ሰጥተዋል።
አንድ አገር በግዛቷ ውስጥ ማን እንደሚገባ እደሚወጣና እንደሚቆይ የመወሰን መብቷ በተፈጥሮም ሆነ በአለም አቀፍ ህጎች የተጠበቀ ነው ያሉት አምባሳደር ታዬ፤  የኢትዮጵያ መንግስትም ይህንን ውሳኔውን ለማንም ማሳወቅ አይጠበቅበትም ብለዋል። ስብሰባው የአንዲት ሉአላዊት አገርን ውሳኔ የሚጋፋና ራስን በራስ የማስተዳደር ህጋዊ መብትን የሚጻረር እንደሆነ የተናገሩት አምባሳደሩ በዚህ ጉዳይ ላይ የመወያያ አጀንዳ መፍጠሩም ተቀባይነት ሊኖረው አይገባም ሲሉ ተናግረዋል።
በተለያዩ አገራት በተለያየ ጊዜ የተመድ ሰራተኞችና ዲፕሎማቶች ከተሰጣቸው ተልዕኮ ውጪ ተንቀሳቅሰዋል ተብለው ያለ ምንም ማብራሪያ ከአገር እንዲወጡ መደረጋቸውን ጠቅሰው፤ በእነዚህ አገራት ላይ ድርጅቱ አንዳችም ጥያቄ አንስቶ አያውቅም። የኢትዮጵያ መንግስትም ይህንን ውሳኔውን ለማንም ማሳወቅ አይጠበቅበትም።
ስብሰባው የአንዲት ሉአላዊት አገርን ውሳኔ የሚጋፋና ራስን በራስ የማስተዳደር ህጋዊ መብትን የሚጻረር እንደሆነ የገለጹት አምባሳደሩ፣ በዚህ ጉዳይ ላይ መወያያ አጀንዳ መፈጠሩም ተቀባይነት ሊኖረው አይገባም ሲሉ ተናግረዋል። በተለያዩ አገራት በተለያየ ጊዜ የተመድ ሰራተኞችና ዲፕሎማቶች ከተሰጣቸው ተልዕኮ ውጪ ተንቀሳቅሰዋል ተብለው ያለምንም ማብራሪያ ከአገር እንዲወጡ መደረጋቸውን ጠቅሰው፤ በእነዚህ አገራት ላይ ድርጅቱ አንዳችም ጥያቄ አንስቶ አያውቅም የኢትዮጵያ መንግስትም ይህንን ውሳኔውን ለማንም የማሳወቅ ግዴታ የለበትም ብለዋል።
ከአገር እንዲወጡ የተደረጉት የድርጅቱ ሰራተኞች የአገሪቱን ቀይ መስመር ያለፉ ናቸው ያሉት አምባሳደሩ፤ ሰራተኞቹ የፈጸሟቸውን ህገ-ወጥ ተግባራት ለምክርቤቱ በዝርዝር አስረድተዋል።
ሰራተኞቹ የሰብአዊ ድጋፍ ከሚጠይቀው የስራ ስነ-ምግባርና እንቅስቃሴ ውጪ ለአሸባሪው የህውሃት ቡድን በተለያዩ መንገዶች ድጋፍ ሲደርጉ መገኘታቸውን ተናግረዋል።
በሰብአዊ ድጋፍ መስጫ ስፍራዎች የአሸባሪውን ቡድን አባላት በማስገባትና ለሽብር ቡድኑ የመገናኛና የህክምና መሳሪያ ድጋፍ በማድረግ “ዜጎች በረሃብ ሞተዋል” የሚል ሃሰተኛ መረጃ በማሰራጨት፣ ወንጀል ውስጥ ሲሳተፉ በመገኘታቸው፣ ከአገር እንዲወጡ መደረጉን ተናግረዋል።
መንግስት  እዚህ ውሳኔ ላይ ከመድረሱ በፊት በተለያዩ ጊዜያት ለድርጅቱ ደብዳቤ በመጻፍ
ሁኔታውን እንዲከታተልና የማስተካከያ እርምጃ እንዲወስድ ጥያቄ ቢያቀርብም ምላሽ እንዳላገኘና ለዚህ ውሳኔ እንደተገደደ ገልጸዋል። በቀጣይ ድርጅቱ ለተልዕኮአቸው ብቁ የሆኑትና በአንድ አገር የውስጥ ጉዳይ ጣልቃ የማይጋቡ የሰብአዊ ድጋፍ ሰራተኞችን በመላክ ድጋፉን እንዲቀጥልም አምባሳደሩ ጠይቀዋል።
የአውሮፓ ፓርላማ በኢትዮጵያ ጉዳይ ላይ ትናንት ያካሄደውን ውይይት ሲያጠናቅቅ ባወጣው መግለጫ፤ በኢትዮጵያ ያለው ሁኔታ በቀጣዮቹ ሶስት ሳምንታት ውስጥ መሻሻል የማያሳይ ከሆነ በጦርነቱ ተሳታፊዎች ላይ ማዕቀብ እንዲጣል ጠይቋል።
የኢትዮጵያና የኤርትራ መንግስታትና ህውሃት እንዲሁም ግጭቱ እንዲራዘምና እንዲባባስ አስተዋጽኦ አድርገዋል፤ የተባሉ ወገኖች ሁሉ ማዕቀቡ እንዲጣልባቸው ጥያቄ አቅርበዋል። በ58 አባላት ድምጸ ተአቅቦና በአራት አባላት ተቃውሞ የ618 አባላትን ድጋፍ አግኝቶ በፓርላማው ለኮሚሽኑ የቀረበው ጥያቄ፤ ከኮሚሽኑ ምላሽ አላገኘም።
ይህንኑ የአውሮፓ ፓርላማ ያቀረበውን የውሳኔ ሀሳብ ተከትሎ፣ በጀርመን አገር የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን የውሳኔ ሃሳቡን  የሚቃወምና ፓርላማው እውነታውን እንዲያገናዝብ የሚጠይቅ ደብዳቤ ጽፈዋል።
የቀረበው የውሳኔ ሃሳብ በአንድ ክልል ላይ ብቻ ያተኮረና በአሸባሪው ህወሃት በአማራና በአፋር ክልሎች የተፈጸመውን ጥቃትና ውድመት ፈጽሞ የዘነጋ ነው ያሉት ኢትዮጵያውያኑ፤ የውሳኔ ሃሳቡ ሙሉ በሙሉ ለአሸባሪው የህውሃት ቡድን በግልፅ ያደላ ነው ሲሉ ኮንነዋል።
አሸባሪ ቡድኑ ተኩስ አቁም ስምምነቱን በመጣስ በንፁሃን ላይ እያደረሰ ያለው ኢ-ሰብአዊ ድርጊትና ስለፈጸማቸው ዘግናኝ ጥቃቶች አንዳችም ነገር አለመግለጹ የተቋሙን ወገንተኝነት የሚያሳይ ነው ያሉት  ኢትዮጵያውያኑ ለግጭቱ መነሻ የሆነውንና አሸባሪውን ቡድን በሰሜን ዕዝ ላይ የፈጸመው ጥቃትና በአሸባሪው ቡድን ታግተው በክልሉ የጦር ማመላለሻ ስለሆኑት ከ400 በላይ የእርዳታ መጫኛ መኪኖች ምንም አለመገለጹ በእጅጉ አሳዝኖናል ብለዋል።
 የኢትዮጵያ መንግስት በቅርቡ ያካሄደውን ዲሞክራሲያዊ ምርጫ ተከትሎ፣ በኢትዮጵያ አዲስ መንግስት መቋቋሙን የጠቆሙት በጀርመን የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን በውሳኔ ሃሳቡ ግን ይሄ አልተካተተም ብለዋል። መንግስት ሁሉን አቀፍ ውይይት ለማድረግ ዝግጁ መሆኑንም መግለጹን አስታውሰዋል- ኢትዮጵያውያኑ በጻፉት ደብዳቤ። የአውሮፓ ፓርላማ ኢትዮጵያ በተደጋጋሚ ለምታቀርባቸው መረጃዎች እውነታውን ለማሳወቅ ለምታደርገው ጥረት ጀርባውን ሳይሰጥ የቀረበውን የውሳኔ ሃሳብ በድጋሜ እንዲያጤነውና ውድቅ እንዲያደርገው አሳስበዋል።Read 10926 times Last modified on Monday, 11 October 2021 08:33