Print this page
Saturday, 09 October 2021 00:00

ከተነገረው ይልቅ ‘የተቀበረውን ጠንቅቆ የማወቅ’ ልዩ ችሎታ!

Written by  ኤፍሬም እንዳለ
Rate this item
(2 votes)

 እንዴት ሰነበታችሁሳ!
የምር ግን ነጋዴዎች... አለ አይደል... በቃ ይሄ የሞኝ የሚመስል ፉክክራችንን እያዩ መሰለኝ የሚጫወቱብን፡፡ የምር ኮሚክ እኮ ነው...አሁን ለምሳሌ ለመስቀል በዓል አንዳንድ ሉካንዳዎች ለክትፎ የሚሆን ንቅል ነው፣ ብቻ የሆነ ስም ያለው ሥጋ ከሳምንት በፊት በሪዘርቭ ወረፋ ተይዞ ማለቁን ከወዳጆቻችን ሰምተናል፡፡ እኔ የምለው ይበልጡኑ ረጋ ብለን ማሰብ ባለብን ዘመን፣ ይበልጡኑ ከመቁረጣችን በፊት ሦስት፣ አራቴ ልንለካ በሚገባን ዘመን እንዲህ አይነት ነገሮች ግራ አይገቧችሁም! ያውም እኮ ኪሎ እስከ ስምንትና ዘጠኝ መቶ ብር በደረሰበት ጊዜ!
እነ እንትና...ጮክ ብላችሁ ባትናገሩትም የምታስቡትን አውቃለሁ፡፡ (አሀ...ዘመኑ ነዋ! ሰው በአንደበቱ የሚናገረውን በትክክል መተርጎም እያቃተን እኮ ያልተናገረውንና ሆድ ውስጥ የቀበረውን ፈልቅቆ የማወቅ ልዩ ተሰጥኦ ያለን መአት ነና! የ‘አዳኝነት’ ማእረግ ለራሳችን የምንሰጥ መብዛታችን ምን ይገርማል!) 
“ስማ ያ እንትና የሚሉት ሰውዬ ያለውን ሰማህ?”
“ስለ ምኑ?”
“ስለ አዲሱ የኮሚቴ ምርጫ...”
“የተለየ ነገር ተናገረ እንዴ!”
“የተለየ ብቻ! ኮሚቴው ብቃት ባላቸው ሰዎች መዋቀር አለበት  ምናምን ሲል አልሰማኸውም?”
“ሰምቸዋለሁ፣ ታዲያ ምን ክፋት አለው?”
“እባክህ ይቺ ይቺን እናውቃታለን፡፡ ብቃት ብቃት የሚሉት እኮ የራሳቸውን ሰዎች አምጥተው ሊሰገስጉበት ነው!#
አያችሁትማ...እንግዲህ ሰውየው ፊት ለፊት ነው የተናገረው፡፡ “ብቃት የሚለው አሁን ያሉት ምን ይጎድላቸዋልና ነው? ከማናችንም የተሻለ ብቃት አላቸው፣” ማለት አንድ ነገር ነው፡፡ ቢያንስ ቢያንስ ሀሳብ ለመስጠት የሚያስችል ሀሳብ ነገር አለበት፡፡
“ስማ ያ እንትና የሚሉት ሰውዬ በቀደም ስብሰባ ላይ አድፍጦ አየኸው አይደል!”
“እኔ ነገሬ አላልኩም፡፡ አድፍጦ ማለት...”
“በቃ ሀሳብ አይሰጥ፣ ምን አይል ዝም ብሎ ሌላው የሚናገረውን ሲቀዳ ነው የዋለው፡፡”
“እና ምን ልትለኝ እየሞከርክ ነው፡፡ የሚናገረው ነገር እስከሌለ ድረስ ዝም ብሎ ቢያዳምጥ እኔ ችግር ያለው አይመስለኝም።”
“እናንተ እኮ እዚህ ላይ ነው ችግራችሁ። ሰውየው ጭጭ ያለው በውስጡ ተንኮል አስቦ ነው እያልኩህ ነው!”
“እንዴት እንደዛ ልትል ቻልክ?”
“ስማ፣ ይቺ፣ ይቺማ አታመልጠንም፡፡”
እኔ የምለው፣ ሰው ሳይናገር፣ ሀሳብ ሳይሰጥ “በሆዱ (‘በኩላሊቱ’ ማለትም እንደ አማራጭ ሊሆን ይችላል...ሆድን ‘ኦቨርሎድ’ ላለማድረግ!) የሚያስበውን በማየት ብቻ የማወቅ ችሎታ ባላቸው ሰዎች ብዛት ዓለምን የምንመራ” ምናምን እያልን ዓለም ላይ የማንነሰነስበትማ!  ቀላል ‘ብቃት’ አይደለማ! ፈረንሳይ እኛን ብታማክር ኖሮ፣ ጉድ ከመሠራቷ በፊት የአውስትራሊያ ሰዎችን ሆድ ነግረናት፣ ያንን ሁሉ ቢሊዮን ዶላር ባላጣች ነበር! ቂ...ቂ...ቂ...
እዚህ ሀገር ይሄ እንደልብ ዋጋ መቆለል ለምን እንደማይቆም ምንም እንቆቅልሽ የለውም፡፡ ከነጋዴዎቹ እኛ ብሰናላ! የምር ግን ከማይረባና ኋላቀር ከሆነ ፉክክር ወጥተን፣ “ኪሎ ሥጋማ በስድስት መቶ ብር ገዝቼ አልበላም! ለምን ጥንቅር አይልም!” አንልም። የምር ግን በብዙ ነገሮች ላይ ጨክነን እንዲህ ቁርጥ ያለ ውሳኔ መወሰን የምንችልበት ዘመን አይናፍቃችሁም! ይልቁንም ሰባት መቶ ብር ሳያስገቡት ብለን በሌሊት ሉካንዳ ቤት በራፍ የምንገኝ እኛ አይደለን! ሁሉም በሚባል ደረጃ ሌሎች ምርቶች ላይ ያለው ይኸው ነው፡፡ እናላችሁ... ነጋዴዎቹም  አውቀውበታል፣ ወይም አውቀውብናል፡፡
መጀመሪያ ጭምጭታው እዚህም እዛም ይለቀቃል፡፡
“ጨው ሀያ ብር ገባ አሉ፡፡”
“አትዪኝም!”
ከዛማ ሰዉ ተሻምቶ ሳይጨርሰው ብለን በማግስቱ ሀያችንን ይዘን ወደ ሱቅ መሮጥ ነው፡፡ ምን ቢሆን ጥሩ ነው... ሀያ አምስት ብር ገብቶ ቁጭ! እየተነጫነጭንም ቢሆን እዚህም አዛም የወሻሸቅናትን አውጥተን እንገዛና እቤት ስንደርስ፣ ስልክ... “ስሚ እኛ ሰፈር እኮ ጨው ሠላሳ ስምንት ብር ገባ!” ያን ጊዜ የሚሰማን ምን መሰላችሁ...ድል አድራጊነት! ልክ ነዋ...እነሱ ሠላሳ ስምንት ብር እየተጠየቁበት ያለውን እኛ በሀያ አምስት ገቢ አደርገናታ! እናላችሁ... ሀያ አምስት ብር ህገወጥ የሆነ ዋጋ መሆኑ ይቀርና...አለ አይደል... “ማን እጅ ይሰጣል. ቶሎ ብዬ በሀያ በአምስት ብር ገዛኋት!” ብለን የምንፎክርበት ሆኖ ቁጭ፡፡ 
እኔ የምለው...አንድ ጉዳይ ጀምረን ወደ ኑሮ መወደድ ዘው አልንና አረፍነው አይደል! ምን ይደረግ! እመኑኝ... አሁን ባለው ሁኔታ የሆነ ወደ ተአምር የሚጠጋ ነገር ካልተፈጠረ በቀር ከዋነኞቹ እና ከአጣዳፊዎች አጀንዳዎቻችን አንዱ ሆኖ ይቀጥላል፡፡
ሀሳብ አለን... ከዚህ በፊት እንደተጫወትነው ሀኪሞች እንድንመገብ የሚያዙንን የምግብ አይነት  “ከተጨባጭ ሁኔታዎች ጋር በማገናዘብ” (ለቦተሊካ ብቻ ሳይሆን ለሁሉም ነገር የምታገለግል ሀረግ!) ያስተካክሉልንማ፡፡
“ዋነኛው ችግርህ በሽታ የመከላከል አቅምህ በጣም ወርዷል፡፡”
(“ዶክተርዬ፣ እሱን መች አጣሁት ብለህ ነው! የያዘ ይዞኝ ነው እንጂ!)
“አሁን በሚገባ አድምጠኝ፡፡ ሰውነትሀ ገንቢ ምግቦችን ማግኘት አለበት፡፡ በተቻለ መጠን በየቀኑ የምትመገበው ምግብ ውስጥ ፕሮቲን ያስፈልጋል፡፡”
(“ዶክተርዬ፣ አትታዘበኝና ፊትህ ያለው ካርድ ላይ ያለውን ስም አጣራልኝ! ድንገት የተምታታ ነገር እንዳይኖር ብዬ ነው!”)
“በተጨማሪ ቪታሚኖች እንደሚያስፈልጉህ ለአንተ መንገር የለብኝም። እየተግባባን ነው?”
“በሚገባ ዶክተር፣ በሚገባ!” (“ዶክተርዬ፣ ችግሩ ፕሮቲን፣ ቪታሚን ምናምን የሚሏቸው ነገሮች እኔ ደጅ ላለመድረስ እንዲህ ጥምድ አድርገው የያዙኝ ለምን እንደሆነ ግራ እየገባኝ ስለሆነ ነው እንጂ!)
“ስለሆነም፣ ስጋና የከብት ተዋጽኦ ሳታበዛ እየመጠነክ፣ በተጨማሪ ደግሞ ፍራፍሬዎችና አረንጓዴ ተክሎችን...”
(“ይቅርታ ዶክተርዬ፣ ግን ስጋ እየመጠነክ ካልካት በኋላ የማዳመጫ ህዋሳቶቼ አድማ መቱብኝ መሰለኝ...ምንም አይሰማኝም፡፡)
ምን መሰላችሁ ሀኪሞቹ፣ እንግዲህ የሙያ ጉዳይም አይደል፤ ሀሳብ የማቅረብ ጉዳይ ሳይሆን ትእዛዝ ነው የሚሰጡን። እናማ... ከአመጋገብ ጋር የተያያዙት ትእዛዞችን በተመለከተ ዋነኛው ትእዛዝ እንዳለ ሆኖ፣ ከላይ ወደታች በየደረጃው ቢያንስ ዘጠኝ፣ አስር የሚሆኑ አማራጮች ይዘጋጁልን ለማለት ነው፡፡ ልክ ነዋ...ማን ያውቃል ዘጠነኛውና አስረኛው ላይ ልንገናኝ እንቻላለና!  የምር ግን ጨዋታን ጨዋታ ያነሳው የለ...እኛማ አኮ መቼም ጫፍ ስለማናጣ ራስን ማባበያ አናጣም፡፡
“ስጋ ምን ያደርጋል፣ ትርፉ ሪህ ነው፡፡”
“ይህን ደግሞ ማነው ነገረህ?”
“ማን ይነግረኛል፣ ሳይንሱ ነዋ!”
“ሳይንሱ መጥኑ ይላል እንጂ ጭራሽ አትመገቡ ይላል እንዴ?”
“አየህ የፈረንጆቹ ተንኮል አልገባህም ማለት ነው፡፡”
“አስረዳኛ...”
“መጥኑ የምትለዋን የጨመሩባት እኮ የስጋ ፋብሪካዎች ናቸው!” ቂ...ቂ...ቂ...
እናማ... ጀምረን ከመስመር ወደወጣንበት ጉዳይ መለስ ለማለት ያህል ....ሰው የተናገረውን በትክክል ለመተርጎም ፈቃደኛ ሳንሆን ሆዱ ውስጥ የቀበረውን ‘ጥንቅቅ አድርገን የምናውቅ’... በአሁኑ ጊዜ ይህ ‘ችሎታችን’ ለብዙ ነገር ሳይጠቅም አይቀርም ለማለት ነው፡፡
ደህና ሰንብቱልኝማ!


Read 967 times