Monday, 11 October 2021 08:35

ዶ/ር አረጋ ይርዳው - ስለመንግስት ምስረታ፣ የሚኒስትሮች ሹመት፣ የኑሮ ውድነት፣ ኢንቨስትመንት

Written by 
Rate this item
(2 votes)

(በተለይ ለአዲስ አድማስ)

             ከፍተኛ ትምህርት
የመጀመሪያ ድግሪ- መካኒካል ኢንጂነሪንግ
ሁለተኛ ድግሪ- በኤር ትራንስፖርት ኢንጂነሪንግ
ሦስተኛ ድግሪ- በትምህርትና አመራር
የሥራ ልምድ
ለ10 ዓመት በኤሮፔስና ከአቬሽን ጋር የተገናኙ ሥራዎች- በኢትዮጵያ አየር መንገድ
ለ20 ዓመት በኢንጂነሪንግ ማኔጅመንት ማኔጀር ሊደር- በካሊፎርኒያ ኤሮስፔስ ኩባንያዎች
ለ20 ዓመት የሚድሮክ ቴክኖሎጂ ግሩፕ ዋና ሥራ አስፈፃሚ
አሁን የዩኒቲ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት
 
          የቃለመጠይቃችን መነሻ አዲሱ የኢትዮጵያ መንግስት ምሥረታና  የጠ/ሚኒስትር ዐቢይ  የአዳዲስ ካቢኔ አባላት ሹመት ይሁን እንጂ የማያነሱት ጉዳይ የለም። በተለይ ለመንግስት፣ ለተሿሚዎች፣ ለተፎካካሪ ፓርቲዎች፣ ለኢንቨስተሮች፣ ለህግ አውጪዎች… ለኢትዮጵያውያን የሚያስተላልፉት መልዕክት አላቸው። ከአዲስ አድማስ ጋዜጠኛ ናፍቆት ዮሴፍ ጋር ባደረጉት ቃለ ምልልስ ትችቶችም  አድናቆቶችም፤ ገንቢ አስተያየቶችም ተንፀባርቀዋል፡ እነሆ ያንብቡት- ይወዱታል።
             

                አዲስ መንግስት በተመሰረተ ማግስት ነውና የተገናኘነው…በአጠቃላይ የአዲሱን መንግስት ምስረታና የካቢኔ ሹመቱን እንዴት አገኙት? ከሌላው ጊዜ በምን ይለያል?
በእርግጥ አዲስ መንግስት ምስረታው ለእኔ አዲስ አይደለም፡፡ ነገር ግን እንደ ማንኛውም ሰው ደስ ብሎኛል፤ ለዚህ ሽግግር በመድረሳችን፡፡ በተለይ በኮቪድም ሆነ በሰላም እጦት ውስጥ ሆነን ይህን ምርጫ ማካሄድም ሆነ አዲስ መንግስት መመስረት የሚደነቅ ነው፡፡ በአጠቃላይ ደስ ብሎኛል፡፡
እርስዎ ከኃይለ ስላሴ ዘመን  ጀምሮ በደርግም ጊዜ ነበሩ። በዘመነ  ኢህአዴግም አምስት ጊዜ የተካሄዱ ምርጫዎችንና የመንግስት ምስረታዎችን የማየት እድል ነበረዎትና የዘንድሮው  በምን  ይለያል?
የዘንድሮውን ምርጫ ካለፉት ምርጫዎች ለየት የሚያደርገው ተሻሽሏል፤ መሻሻልም ነበረበት፡፡ ዴሞክራሲ ሂደት ስለሆነም ብዙ በጎ ጎኖች አሉት። ሰው እንደሚለው፤ መቶ በመቶ ፍፁም ነው ማለት አይቻልም፡፡ ምክንያቱም እንኳን እዚህ ያለው፣ አሜሪካ ያለውም ምርጫ ፍጹም አይደለም። በመሆኑም አሁን ድረስ እያነዛነዛቸው ነው ያለው፡፡ የሆነ ሆኖ የዘንድሮው ዕመርታ ያለው ሆኖ ነው የተሰማኝ፡፡ ይበልጥ የሚደነቀው ደግሞ በኮቪድ ዘመን፣ አለመረጋጋት ባለበት ወቅት ብዙ ተፅዕኖዎች ባሉበት ወቅት ይሄን ማድረግ መቻሉ ነው ብዬ አስባለሁ፡፡
በአዲሱ መንግስት የካቢኔ ሹመት ውስጥ አብን፣ ኢዜማና ኦነግን የመሳሰሉ ተቃዋሚ (ተፎካካሪ) ፓርቲዎችን ማካተቱ በኢትዮጵያ ፖለቲካ ውስጥ ያለው ፋይዳ ምንድን ነው ይላሉ?
በዚህ ጉዳይ በዛ ያለ ነገር ነው የምንነጋገረው፤ ነገር ግን አዲስ አይደለም። አሜሪካን ብትወስጂ የሪፐብሊካን ፓርቲ ፕሮፌሽናል ነው፤ ይጠቅማል የሚሉትን ከሌላ ፓርቲ ይወስዳሉ፤  እኛ አገር እንደ አዲስ ታይቶ ይሆናል እንጂ በሌላው ዓለም የተለመደ ነው፡፡ መርሳት የሌለብን የዚህም ፓርቲ አባል ሁኚ የዛኛው ለሀገር አገልግሎት ነውና የምትሰሪው፣ የሚጠቅም ነገር አለሽ ከተባለ መመረጥ መካተት አለብሽ፡፡ ከባህል አኳያ መለመዱ ቆንጆ ነው፤ አስፈላጊም ነው፡፡ ፓርቲዎች ቅድም እንዳልሽው ቀድሞውንም ተቃዋሚ መባላቸው የተሳሳተ ቃል ነው፤ ተፎካካሪ ማለቱ የተሻለ ይሆናል። ለምን ከተባለ የኔ ሀሳብ ይሻላል፣ የኔ የበለጠ ጠቃሚ ነው እንጂ የሚሉት መቃወም  አይደለም፤ እሱንም እያጠራን ነው መሄድ ያለብን፡፡ እንዲያውም ማይኖሪቲ ፓርቲ፣ ማጆሪቲ ፓርቲ እየተባለ ነው መጠራት ያለበት እንጂ ተፎካካሪ ተቃዋሚ እየተባሉ መቀጠሉም በራሱ አስፈላጊ አይመስለኝም። ከዚህ አንጻር ሁሉም አላማና ችሎታ ያላቸው፣ በቂ ልምድ ያካበቱ ፓርቲዎች አሁን ስልጣን ከያዘው ፓርቲ ጋር ገብተው በጋራ መስራታቸው ቆንጆ ነው፡፡ ይህም ሲባል ጥንቃቄ ማድረግ ያስፈልጋቸዋል። ከዚያኛው ፓርቲ ሄደው ስለገቡ ብቻ ያልተመረጠውን ፓርቲ ፖሊሲ ሊያራምድ አይችልም፡፡ የተመረጠው ብልጽግና ከሆነ፣ ሰውየው ከየትም ይምጣ ከየትም  የሚያራምደው የብልጽግናን ፖሊሲ ብቻ እንጂ የራሳቸውን አይደለም። የራሱን  ሊያራምድ አይችልም። ይህን ጥንቃቄ እስካደረጉ ድረስ ሌላ ችግር ይገጥማቸዋል ብዬ አላስብም፡፡
የካቢኔ ምርጫውን በተመለከተ ላነሳሽው ጥያቄ በመጀመሪያ ምርጫ ቦርድ እራሱ አነሰም በዛም ስራውን በተገቢው መንገድ ማከናወኑ አንድ ነገር ነው። የካቢኔ ምርጫን በተመለከተም ቅድም ያልሽው ከሌሎች ፓርቲዎች ሚኒስትሮችን መሾሙ ብቻ አይደለም፤ ሌሎችም ጥሩ ጥሩ ነገሮች አሉት፡፡ ለምሳሌ ባለፈው ጊዜ በነበረው ካቢኔ 50 በመቶ ሴቶች መሆናቸው እንዳስደነቀን ማለቴ ነው፡፡ በአዲሱ የካቢኔ ሹመትም ፆታን ሳይሆን ችሎታን መሰረት ያደረገ መሆኑ፣ ከተፎካካሪ ፓርቲዎች መሾሙ፣ አንዳንድ የተዛቡ የሚኒስቴር መስሪያ ቤት መጠሪያዎች መስተካከላቸው ተጠቃሽ ናቸው፡፡
ከተስተካከሉት ውስጥ የሚጠቅሱልኝ ይኖራል?
ጥሩ! ምሳሌ ትምህርት ሚኒስቴርን ብንወስድ ሁለት መጠሪያ ነው የነበረው፡፡ እኔ በዚህ ጉዳይ ላይ ብዙ ስብሰባዎች ላይ ተናግሬያለሁ። እንደሚታወቀው ትምህርት ሚኒስቴር እያለ “ሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስቴር” የሚል ሌላ ነበር። እኔ አስፈላጊ አይደለም  እያልኩ ነበር አሁን ወደ “ትምህርት ሚኒስቴር” መመለሱ አንዱ መልካም ነገር ነው፡፡ “ሰላም ሚኒስቴር” የሚለው እንዲሁ ሌላው ግራ የሚያጋባ ስያሜ ስለሆነ ሊታሰብበት የሚገባ ጉዳይ ነው። ለምን የተባለ እንደሆነ… ሰላም ሚኒስቴር ብለሽ ከጠራሽ፤ ሰላም የለም፣ ሰላም ላይ ትኩረት ያደረገ ነው ማለት ነው። ስለዚህ ሌላ ስያሜ ቢሰጠው ይመረጣል ብዬ አምናለሁ። በሌላው ዓለም የተለመደ አይደለም። የትራንስፖርትና ሎጅስቲክ ሚኒስቴር የሚል ሰምቻለሁ፡፡ ነገር ግን “የትራንስፖርት ሚኒስቴር” የሚለው በቂ ነው፡፡ ምንድን ነው ሎጀስቲክስ? እንደዚህ ዓይነቶቹ በሂደት ይሻሻላሉ ብዬ አስባለሁ፡፡ ለምሳሌ የሀገር የትምህርት ጉዳይ አንድ ነው ብለው ወደ ትምህርት ሚኒስቴር መምጣታቸው መልካም ነው፡፡ በሌላ በኩል፤ ጠቅላይ ሚኒስትሩ የካቢኔ አባላቶቻቸውን ሹመት ባስጸደቁበት ወቅት በፓርላማ የተናገሯቸውን ጥሩ ጥሩ ነገሮች ማስታወስ መልካም ይመስለኛል። ሚኒስትሮች የሚያገለግሉት ኢትዮጵያን እንደሆነ፣ የተለየ የክልል ኢንተረስት ማስተጋባት እንደሌለባቸው ገልፀዋል፡፡ ይሄ እስከ ዛሬ ድረስ ቋሚ ችግር ስለነበረ መነሳቱ ተገቢ ነው፡፡ እኔ ባለፉት 20 ዓመታት እስከማውቀው ድረስ፣ ሚኒስትር ሆኖ የተሾመ ሁሉ የሚያንጸባርቀው የክልሉን የአካባቢውን ፍላጎት ነበር፡፡ ይሄ እንደ ሀገር ትልቅ ፈተና ሆኖ ቆይቷል፡፡ ይህን ለመቅረፍ አስተዳደሩ አወቃቀሩ ታስቦበት እንደተሰራና መዋቅር እንዳለው መግለፃቸው ጥሩ ነው ብዬ አምናለሁ፡፡
ዞሮ ዘሮ ሰዎቹ ላይ ብቻ ማተኮሩ በቂ አይመስለኝም ገቨርናንሱ ከዚህ በኋላ ምን ይመስላል የሚለውም  ትኩረት ይፈልጋል። የሚኒስቴር መ/ቤቱ ሥራው አገልግሎት መስጠት ከሆነ ይሄ ገብቶታል ወይ? ጊዜን በአግባቡ ከመጠቀም፣ ማህበረሰቡን ከማገልግል አኳያ ምን ያህል ተለውጧል? ሚኒስትሩ አለቃን ማገልግል ነው ወይስ ፓርቲን ማገልግል ወይስ ህዝብን የሚለው ተለይቶ ከታወቀና ሚኒስትሩም ሚናውን ካወቀ ጥሩ ይሆናል፡፡
ሌላውና መደረግ ያለበት ዶ/ር ዐቢይም ያደርጋሉ ብዬ የምጠብቀው፣ ቢሮክራሲውን የሚመራው (ፕሮፌሽናል) የግድ የፓርቲ አባል መሆን የለበትም፡፡ የፓርቲውን ፖሊሲ መተግበር ግን ይኖርበታል። ከዚህ ቀደም  የፓርቲ አባል ካልሆንክ የሚባለው ነገር፣  ቀስ እያለ መጥፋት አለበት፡፡ ፓርቲ ይቀየር፣ ሌላም ይምጣ ሙያተኛ የሆነ ሰው ከሙያው ጋር ነው መቀጠል ያለበት። አንድ ፕሮፌሽናል መሃንዲስ የፓርቲ አባል ሲሆንና ሳይሆን እይታው የተለየ ነው። ስለዚህ የቢሮክራሲ ማሽነሪውን ማሻሻል ተገቢ ይመስለኛል።  እስከ ዛሬ የለመድናቸው አንዳንድ ነገሮች መጥፋት አለባቸው ብዬም አምናለሁ፡፡ ለምሳሌ ግምገማ፣የስብሰባ ብዛትና መሰል ነገሮች መጥፋት አለባቸው፡፡  “ግምገማ” የሚለው ቃል ራሱ አስቀያሚ ነው። ሰው “appriase” ነው እንጂ የሚደረገው አይገመገምም፡፡
እስኪ በደንብ ያብራሩልኝ?
ይሄ ማለት አንድ ሰው በመጀመሪያ የሰራው ጥሩ ጥሩ ስራ ተነግሮት ከዚያ በኋላ ወደ ጎደለው ይኬዳል እንጂ መጀመሪያ ወደ ግምገማ አይደለም የሚገባው። አንድ ሰራተኛ ወደግምገማ ልሄድ ነው ብሎ ሲያስብ፣ እየተሸማቀቀ ነው የሚሄደው፣ ምክንያቱም ቃሉ እራሱ አሉታዊ ነው። ስለዚህ ይሄ ነገር መሻሻል አለበት ብዬ አምናለሁ፡፡
ሌላው ማንሳት ያለብን ነገር ጠቅላይ ሚኒስትሩ በስራ ያሳዩት ጉዳይ አለ፡፡ አንድን ነገር ጀምሮ መጨረስ። ስራው ምንም ይሁን ምንም  ከጀመሩ በኋላ መጨረስ። ይሄ ትልቅ ነገር ነው፡፡ መጨረስ የማይችል ከሆነ ሚኒስቴሩ ቀድሞውንም መጀመር የለበትም። ስለዚህ “መጨረስ” የሚለው… ፈረንጆቹ “ሴንስ ኦፍ ክሎዠር” የሚሉትን አይነት አሰራር ከፈጠርን፣ የፓርቲ አፍሌሽኑ ግልጽ እየሆነና ጥገኝነት እየጠፋ ከሄደ መልካም ይሆናል፡፡ ጥገኝት ማለት አንዳንዱ ከግል ሴክተሩ ጋር ይጠጋል አንዳንዱ ከመንግስት ይጠጋል፡፡ ይሔ አደገኛ ነው። አንድ ሰው ከጥገኝነት ነፃ ሆኖ ራሱን ችሎ መቆምና መስራት ነው ያለበት፡፡
ሌላው ደግሞ አንዳንድ ሚኒስትሮች ባሉበት ሃላፊነት መቀጠላቸው ደስ ብሎኛል።
ለምሳሌ የትኞቹ?
ለምሳሌ የግብርና ሚኒስትሩን በደንብ አውቀዋለሁ። ጥሩ  ስራ ሲሰራ የቆየ ነው። ስራው ቀጣይነት እንዲኖረው፣ በዚያው መቀጠሉ መልካም ,ነው ባይ ነኝ። ያለው ብቃት ላይ ጨምሮ፣ ጉድለቶችን አስተካክሎ መሄድ እንጂ እንዲህ ብቃት ያላቸውን አንስቶ እንደገና አዲሱን ከዜሮ ማስጀመር ውጤታማ አያደርግም ይበል የሚያሰኝ ነው። ይሔ ባህል መለመድና መቀጠል አለበት አሁንም ወደዚያ እያመራን ስለሚመስለኝ የሚበረታታ ነው ባይ ነኝ፡፡
እርስዎም እንደገለፁት ሁሉ መንግስት ምስረታው ተስፋ ሰጪ መሆኑን ብዙዎች ይስማሙበታል። ነገር ግን ከፊት ለፊት ብዙ ፈተናዎች ተጋርጠውበታል፡፡ ለምሳሌ የሰሜኑ ጦርነት፣የህዳሴው ግድብ ውዝግብ፣ የኑሮ ውድነት፣ የዋጋ ግሽበት፣ስራ አጥነት ዓለም አቀፍ ውትረትና ጫና… የሚጠቀሱ ናቸው። እነዚህን ፈተናዎች እንዴት ነው የምንወጣቸው ይላሉ?
በነገራችን ላይ የማንወጣው ችግር፣ የማናልፈው ፈተና የለም፡፡ ነገር ግን ችግሩን የምንወጣው፣ ችግሮችን ቅደም ተከተል በማስያዝ ነው፡፡ በእኔ አስተሳሰብ አሁን የተመሰረተው መንግስት ከሁለት የተከፈለ ፈተና አለበት ብዬ አምናለሁ። አንዱ በቅርብ ጊዜ መስራትና መፈታት ያለባቸው ጉዳዮች አሉ። ሌላው በሂደት የሚከናወን ነው፡፡
እስኪ ቀዳሚና ተከታይ የሚሏቸውን ጉዳዮች እንያቸው?
በአንድኛ ደረጃ ሰላም ማስፈን ላይ መሰራት አለበት። ይሄ በቀዳሚነት ሊሰራ የሚገባው ነው፡፡ ሁለተኛው ጉዳይ የኮቪድ ወረርሽኝን መታገል ነው፡፡ ኮቪድን የረሳነው ይመስለኛል፡፡ እሱ ግን እኛን አልረሳንም። በሶስተኛ ደረጃ አንድነትን ማጠናከር ነው ያለብን፡፡ ብዙ ጊዜ የሀገር የችግር ምንጭ ስለሆነ አንድነትን ማጠናከር የግድ ያስፈልጋል፡፡ በቀጣይ የምናነሳው እንደምታውቂው የተፈናቀሉ ወገኖች አሉ። እኔ ከወልዲያ አካባቢ ነኝ እስከ አሁን ወልዲያ እንዳልተረጋጋች አውቃለሁ፡፡ ስለዚህ ይህን ችግር ባስቸኳይ መፍታት አለባቸው ብዬ አምናለሁ፡፡ ከዚህ ቀጥሎም ቅድም ያነሳሽው የኑሮ ውድነት ችግር በከፍተኛ ሁኔታ አለ  የወጣቱ ስራ አጥነት ቅድሚያ ከሚሰጣቸው ጉዳዮች የሚመደብ ነው። እስካሁን የገለፅናቸው ወደ ስድስት ያህል ችግሮች አንገብጋቢና ቅድሚያ አግኝተው ሊሰሩ የሚገባቸው ጉዳዮች ናቸው- በእኔ እምነት፡፡ እነዚህን ችግሮች እየፈታን ቅድም ያነሳሻቸው ዓለም አቀፍ ተፅዕኖዎችንና ሌሎቹንም እንሰራለን፡፡ ችግሩን ቅደም ተከተል ካላስያዝነውና እነዚህን መሰረቶች ካልጣልን ችግሩን መቅረፍ ያስቸግራል እነዚህ ችግሮች ሰው ሰራሽ ናቸው እኛው የሰራናቸው ችግሮች ናቸው ማስተካከል አለብን፡፡
ከእነዚህ ቀጥሎ መሰራት ያለበት ነገር መከላከያን አንድ ዓይነት መስመር  ማስያዝ ያስፈልጋል፡፡ በብዛት ሰዎች እየተቀጠሩ ነው፤ ወጣቶች እየተመለመሉ ነው የተለያየ የፀጥታ ቡድንም እየተቋቋመ ነው፡፡ ለጊዜው አስፈላጊ ነው፤ ጥሩም ነው፡፡ መጨረሻ ላይ ተቀናጅቶ፣ አንድ አይነት አመራር ውስጥ ካልገባች ግር ሊፈጥር ይችላል፡፡
“ልዩ ሀይል”  የሚባሉትን ማለት ነው?
አዎ እርግጥ ነው አሁን ላለብን ችግር ያስፈልጉናል። ነገር ግን ማሰብ የሚያስፈልገው ይሄ ቁጥር ይሄ ብዛት ደሞዝ ያስፈልገዋል። አንድ ላይ መቀናጀትና መዋቀር ይኖርበታል። አለበትም፡፡ ይሄ ጉዳይ በአጽንኦት ሊታሰብብት ይገባል ብዬ አምናለሁ፡፡ በቀጣይም የኢኮኖሚውን ጉዳይ በዝርዝርና በጥልቀት መመልከት ያስፈልጋል፡፡ ከዚህ ሁሉ በኋላ ቅድም ወደ ጠቀስሻቸው ፕሮጀክቶች ማለትም ወደ ህዳሴው ግድብ ፕሮጀክታችን፣ የግሉን ዘርፍ ወደ ማጠናከርና ሌሎች ጉዳዮቻችን እንሄዳለን። በእኔ እምነት ችግሮቹን እንዲህ ቅደም ተከተል በማስያዝ ነው የምንፈታቸው። እርግጠኛ ነኝ እነሱም የ10 ዓመት ቆንጆ እቅድ አላቸው አውቃለሁ እነ ዶ/ር ፍጹም የሰሩትን በዛ መልኩ መፍትሔ ማግኘት አለበት፡፡ አንቺ በተደጋጋሚ ያነሳሽው የሰሜኑ ጦርነት ለመንግስት አንድ ጉዳይ ነች፡፡ ነገር ግን ለፖለቲካ ጥሩ ስለሆነችና ለማውራት ስለምትመች ሁሉም እሷ ላይ ያተኩራል። መሆን ያለበት መንግስት ቁጭ ብሎ ቅደም ተከተል ማስያዝ ነው። ሰላም ዋነኛ ነገር ነው ሰላም ከሌለ መነቃነቅ አይቻልም፡፡ አሁንም አገሪቱን እንቅ አድርጎ  የያዛት ጉዳይ በአፅንኦት መታየትና መፈታት አለበት። ሰላም መፈጠር ይኖርበታል። ሰላም እንዲኖር ማድረግ ሲባል ደግሞ በጥበብ፣ በሆደ ሰፊነትና በማስተዋል መሆን አለበት፡፡ ምክንያቱም ይሔ የአገር ውስጥ የወንድማማቾች ችግር ስለሆነ፣ አፈታቱ ጥበብ የሚያስፈልገው ይመስለኛል። ያንን መንግስት ይሰራል ብዬ አምናለሁ፡፡ በአዲስ መንግስት አዲስ ሀሳብ ይመጣል፤ ይንሸራሸራል።  እልባት ይሰጣል ብዬ አምናለሁ፡፡ በተለይ  ፍጥጫ የበዛባቸው እንደ ወልዲያ ያሉ አካባቢዎች በጣም ያስጨንቁኛል፡፡ እኔ ለ”ሪፖርተር” ጋዜጣ አቤቱታና ግልጽ ደብዳቤ ፅፌያለሁ፡፡ ይሔ ነገር ያልፋል፤ እህትና ወንድማማቾች ደግሞ ይገናኛሉ፡፡ የማያልፍ ጠባሳና ስም ጥሎ እንዳያልፍ መጠንቀቅ ግን ያስፈልጋል፡፡
ቀደም ሲል በውይይታችን ኢኮኖሚውን ማስተካከል ብለው ብዙም ሳያብራሩ ነው ያለፉት። በአኛ አገር የኢኮኖሚው አካሄድና የንግድ ስርዓቱም  ሆነ በነጋዴውና በመንግስት መካከል ያው ግንኙነት ጤናማ ባለመሆኑ፣ ኢኮኖሚው መጎዳቱ በስፋት ይነገራል፡፡ ኢኮኖሚው የአንድ አገር የጀርባ አጥንት እንደመሆኑ ጤናማ አካሄድና እድገት እንዲያመጣ ምን መደረግ አለበት ይላሉ?
ቅድም ግምገማ የሚለው ቃል አሉታዊ ነው መቅረት አለበት ብያለሁ አይደለም? አገራችንን ስንገመግምም እየተሳሳትን ነው፤ ጤነኛ የሆነ ኢኮኖሚ የትኛውም አገር የለም፡፡ ሁሉም አገር ችግር አለበት፡ ዛሬ እዚህ ቁጭ ብዬ አሜሪካ በሶስት ቀን በጀቱ ስለሚጠፋ ይከራከራሉ፡፡ እንደ ሌላው አገር ሁሉ አኛም እንደ አቅማችን ችግር አለን፡፡ የሌላው አገር ወርቅ ነው አንበል፡፡ የሌላውም አገር ወርቅ አይደለም፤ እናውቀዋለን። እኔ ኢኮኖሚስት ባልሆንም የራሴን ሃሳብ መስጠት እችላለሁ። አሁን ላይ አገራችን ውስጥ የኑሮ ውድነት አለ፣ የዋጋ ንረት አለ፣ የዋጋ ንረትን የምንተነትንበት የራሱ ሳይንስ አለው፡፡ የዚህ ባለሙያዎችም አሉ። በቀላል ቋንቋ ለመነጋገር ግን የዋጋ ንረት የሚመጣው አንቺ ብዙ ብር ኖሮሽ  አንድ ልትገዢ የምትፈልጊው ነገር ትንሽ ከሆነ ግሽበት አለ ማለት ነው፡፡ ይሄ የሚስተካከልበት የራሱ ጥበብ አለው፡፡ አንዳንድ ቦታ ላይ የኑሮ ውድነት  ስንል አሁን በተጨባጭ ስንመለከተው የህዝቡ ችግር የቤት ኪራይ  ነው፡፡  በሁለተኛ ደረጃ ትራንስፖርት ነው። እነዚህ ነገሮች የሰውን ህይወት ፈታኝ ያደርጉታል፡፡ ሌላው ሥራ አጥነት ነው። ስራ አጥነት በስፋት አለ፡፡
በዚህ ችግር ውስጥ እያለን  ደግሞ ዓለም አቀፍ ተፅዕኖውም ይመጣና ችግሩን ያባብሰዋል፡፡ እነዚህ አይነት ፈታኝ ችግሮች በተጨባጭ አሉብን ቅድም ካነሳነው የሰላም እጦት ችግር በተጨማሪ። ስለዚህ እኔ ነገ ሄጄ ለሰራተኞቼ ደሞዝ ጨምሬ እጠጥፍ ባደርግላቸው የኑሮ ውድነቱን አያጠፋላቸውም ጭራሽ ያባብሳል እንጂ፡፡ ስለዚህ መፍትሔው ማምረት ነው። የሰውን ጉልበት የወጣቱን ሃይል ወደማምረት አዙሮ ምርትን ማሳደግ ይኖርብናል። ቁልፍ መፍትሔ እሱ ነው፡፡ አገራችን ደግሞ የምርት አገር ናት፡፡ የገበሬ አገር ናት፡፡ የሰው ልጅ መጀመሪያ የሚፈልገው በተፈጥሮም የሚገደደው ልብስ መልበስ አይደለም፤ ሆዱን መሙላት ነው። ሆድን ለመሙላት ደግሞ ከመሬት ጋር፣ ከዝናብ ጋር ፈጣሪ ከሰጠን ጸጋ ጋር መያያዝ ነው፡፡ እነዚህ ጉዳዮች ላይ ያለው ትኩረት በጣም ብዙና ከፍተኛ መሆን አለበት ብዬ አምናለሁ፡፡ በአጠቃላይ ግን ሰው ስራ ከሌለው፣ ስራ ወደሚሰራበት ቦታ ሲሄድ፣ ትራንስፖርት ካላገኘ፣ በተለይ አዲስ አበባን ብንወስድ ህዝቡ፣ ከመሃል ወደ ዳር እየወጣ በሄደ ቁጥር አቅሙ እያነሰ ከመጣ ትራንስፖርት ስለሚያስቸግረው ይጨነቃል፡፡ ስለዚህ ሰዎች ማገዝ ይችላሉ። እኔ አሁን ዩኒቲ ዩኒቨርስቲን ነው የምመራው። ለሰራተኞቻችን አውቶቡስ አለን፡፡ ትልልቅ ድርጅቶች ካላቸው በጀት ቀንሰው ለሰራተኞቻቸው ተከራይተውም ሆነ በራሳቸው አውቶቡስ ቢያዘጋጁ ሰዎቹን ይረዳቸዋል፡፡ ለመስሪያ ቤቱም ውጤታማ አምራች ይሆናሉ፡፡ በትራንስፖርትና መንገድ ላይ የሚያጠፉትን ጊዜና ጉልበት ስራቸው ላይ ያውሉታል፡፡
ሌላው የቤት ኪራይ ማህበረሰቡን አስጨንቆ  ይዞታል ብዬ አስባለሁ፡፡ አሜሪካ ውስጥ አንድ ምሳሌ ልንገርሽ። ችግር እኛ አገር ብቻ አይደለም ብዬሽ ነበር፡፡ ኮቪድ መጣና አስቸገራቸው ቤት መዋል ጀመሩና ስራ አጡ። መንግስት ምን አደረገ? የተከራዩ ሰዎች ከተከራዩበት መውጣት  አይችሉም፤ እንዳታስወጧቸው አለ። ቤት በብድር ሰርተው እዳ ያለባቸው ባንኮች ለጊዜው ብድር እንዳይጠይቁ በማድረግ ችግሩን አለፉት። አሁንም እንደዛ እያደረጉ ነው። እንዲህ ዓይነት ችግር ሲከሰት እንደ ኮሶ መረር ያለች እርምጃ ወስዶ ማስተካከል ያስፈልጋል፡፡
ቤት አከራይ በየጊዜው ቁጭ ብሎ ኪራይ እየጨመረ፣ ህዝብ ሲያሰቃይ፤ ለኢንፍሌሽን አስተዋጽኦ ሲያደርግ አፋጣኝ እርምጃ መውሰድ ያለበት መንግስት ነው። አንዳንዴ መንግስትም ትንሽ ዘይት ትንሽ ዱቄት ያመጣና ሳይቆይ ይጠፋል አንድ ጊዜ “አለ በጅምላ” የሚል ተከፍቶ ሳይቆይ ጠፍቷል፡፡ ለችግሩ ዘላቂ መፍትሔ እንጂ በማስታገሻ የሚታለፍ አይደለም፡፡
 የሰሜኑ ጉዳይ ጥበብ ከታከለበት ይፈታል፡፡ ሁሉም ነገር ጨለማ አይደለም። ለዚህ ሁሉ ምስቅልቅል የሰሜኑ ጉዳይም ድርሻ  ይኖረዋልና፡፡ ይህቺ አገር ብዙ ሺህ ዓመት ችግር ሲገጥማት ስትፈታ ኖራለች፡፡ በደጃዝማቾች፣ መካከል በሳፍንቶች መካከል ጦርነት ሲነሳ ሲበርድ ነበር፡፡ በአሁኑ ወቅት በተነሳው ችግር ቁም ነገሩ እየተዋጉ ያሉት ወንድማማቾች ናቸው አንድ እናት አለች፣ ሁለት ልጆቿ ችግር ገጥሟቸዋል፤ ሁለቱንም ማጣት አትፈልግም ሁለቱ ችግሮቻቸውን  ፈትተው በጤና እንዲኖሩላት ትፈልጋለች። መፍትሔው ላይ ጥበበኛ መሆን እንጂ አፍራሽ የሆነ የሚያስተዛዝብ፣ ለታሪክ የማይመቹ ነገሮች መፈጸም የለባቸውም እላለሁ። እንደሌላው ችግራችን ሁሉ እሱም ይፈታል፤ ጨለማ አይደለም፡፡Read 3132 times