Monday, 11 October 2021 08:49

ኢትዮጵያ ትፈርሳለች ሲባል ተመሰረተች

Written by  ኤልያስ
Rate this item
(1 Vote)

“ኢትዮጵያ እናታችን ናት፤ እናት ከሌለች ቤተሰብ ይበተናል”
                           
     ወዳጆቼ፤ ለካ የሳምንትም “ታሪካዊ” አለው። በርግጥም ሳምንቱ ታሪካዊ ነበር። በኢትዮጵያ ታሪክ ለመጀመሪያ ጊዜ በአደባባይና በአደይ አበባ፣  የአዲስ መንግስት ምስረታ  ተከናውኗል። በመንግስት ምስረታው ላይ  ምን ደስ አለህ አትሉኝም? የአፍሪካ መሪዎች ስለ ኢትዮጵያ በአደባባይ የልባቸውን መናገራቸው፣ በተለይ የኬኒያው  ፕሬዝዳንት የተናገሩት በእጅጉ ልብ ያሞቃል፡፡  
“…. ኢትዮጵያ እናታችን ናት፤ እናት ከሌለች ቤተሰብ ይበተናል፡፡ ኢትዮጵያ የአፍሪካ ነፃነት እናት ናት፡፡ ኢትዮጵያ የፓን አፍሪካኒዝም መሰረት የጣለች፣ በቅኝ ግዛት ሥር ያልወደቀች ሃገር ናት….” ሲሉ አሞካሽተዋታል- የኬኒያው መሪ ኡኹሩ ኬንያታ። ከጃንሆይ ጀምሮ እስከ አሁኑ መንግስት ድረስ ለደቡብ ሱዳናውያን ድጋፍና እገዛ እንደተደረገላቸው የተናገሩት የደቡብ ሱዳኑ ፕሬዝዳንት ሳልቫኬር በበኩላቸው፤ ምንጊዜም  ከኢትዮጵያ ጎን እንደሚቆሙ ተናግረዋል። “ያለ ኢትዮጵያ ድጋፍ ደቡብ ሱዳን አገር አትሆንም ነበር” ብለዋል። ኢትዮጵያ መሄድ ወደ ምትፈልግበት ሁሉ አብረን እንሄዳለን ሲሉም ፕሬዚዳንቱ ድጋፋቸውን ገልፀዋል፡፡
ወዳጆቼ፡- ጎረቤት አፍሪካውያን “እናታችን” ብለው የሚያከብሯትን አገር፣ ከማህፀኗ ወጥተው፣ በሃብትም በሹመትም የተንበሸበሹባት የገዛ ልጆቿ  “እናፈርሳታለን” ብለው  እንቅልፍ ማጣታቸው የታሪክ ምፀት ነው፡፡ በነገራችን ላይ የምዕራብ አገራት መንግስታትም ሆኑ ዓለማቀፉ ማህበረሰብ የመንግስት ምስረታቸውን ሲመለከቱ ምን ብለው ይሆን? ይደሰታሉ ብዬ እኮ አይደለም፡፡
እግዲህ ጠሉም ኢትዮጵያ ይህቺ ናት-እውነትም ውበትም። አንድ ጥያቄ አለኝ። እነ አሜሪካም ሆኑ ሌሎች በእርዳታና በማእቀብ የሚያስፈራሩን ለጋሾች፤ ከኢትዮጵያ ከምር የሚፈልጉት ምንድን ነው? ሰላም….?  ዲሞክራሲ? …መቻቻል?... የሰለጠነ ፖለቲካ? …ዲሞክራሲ? በህዝብም የተመረጠ መንግስት? ወይስ መንበርከክ? ወይስ የድሮው ዓይነት በቅኝ መገዛት?  እውነቱን በግልጽ ከአፋቸው ብንሰማው ሸጋ ነበር። (ለመቁረጥ ይመቻቸናል!) ለነገሩ በዚህ ሳምንት በኢትዮጵያ ፖለቲካ ራሳቸው ሰልጠንን የሚሉት ምዕራባውያን ያለሙት ያሰቡትም አይመስለኝም አዲስ መንግስት በመመስረት ሂደት ላይ የሚገኘው የጠ/ሚኒስትር አስተዳደር፤ ባለፈው ረቡዕ 3 የተቃዋሚ ፓርቲ መሪዎችን በሚኒስትርነት መሾሙ አናዷቸው ይሆን? (እናዝናለን!) ወዳጆቼ፤ በአዲስ አበባ አስተዳደር ካቢኔ ውስጥ ሁለት የተቃዋሚ ፓርቲ አመራሮች መካተታቸውስ? በክልላዊ መንግስታት አስተዳደር ውስጥ ተቃዋሚዎች በሃላፊነት መሾማቸውንስ ሰምተው ይሆን?(ቢሰሙ ባይሰሙ ለውጥ የለውም!) ኢትዮጵያ ያዝልቅላት እንጂ ለአፍሪካም ጭምር ፈር ቀዳጅ የሆነ ተግባር እያከናወነች ነው፡፡ (እናታችን መባል ሲያንሳት ነው?)
ከሁሉም ግን ምን እንዳስደሰተኝ ታውቃላችሁ? የሰኔው ምርጫ ያለ ኮሽታ እንደተጠናቀቀ ሁሉ የመንግስት ምስረታውም፣ በአስተማማኝ ሰላምና ፀጥታ መጠናቀቁ ያኮራል፡፡ (ለወዳጅም ለጠላትም!) ባለፈው ረቡዕ በፓርላማ የተከናወነውን የሚኒስትሮች ሹመትም አስደሳች ተስፋ ሰጪ ድባብ ነበረው (ክብር ለኢትዮጵያ ዓምላክ!)
የኢትዮጵያ ተፎካካሪ ፓርቲዎች በምርጫው ቅሬታ እያላቸውም ጭምር ለአገር ቅድሚያ በመስጠት ግርግርና ሁካታ ከመፍጠር መቆጠባቸው የሚያስመሰግናቸውና የሚያስደንቃቸው ነው፡፡ (ሥልጣንም ሆነ ምርጫ አገር ስትኖር ነው!) መንግስት በበኩሉ፤ ቃሉን ጠብቆ ተቃዋሚዎችን በመንግስት ሁነኛ የሥልጣን ቦታዎች ላይ መሾሙ ያስመሰግነዋል፤ ያስደነቀዋል፡፡ (ሁለቱም ልብ ገዝተውልናል!)
እንግዲህ ገዢው ፓርቲና ተቃዋሚዎች በህብረት የሚመሯትን አገር አብረን  እናያታለን፡፡ መቼም ምንም ቢሆን ከእስከዛሬው ቢሻል እንጂ አይከፋም፡፡ የረቡዕ ዕለቱ የፓርላማውን ድባብ ለማስታወስ ያህል ጠ/ሚኒስተሩ በፓርላማ ለተሿሚዎች የሰጡትን በምክር የተጠቀለለ ትሁት መመሪያ  እንቆንጥር።
“የሚቀጥለው መንግስት የካቢኔ አባላት የሆናችሁ ሚኒስትሮች ዋና ተልዕኳችሁ አድርጋችሁ እንድትወስዱት ብዬ የማነሳው ሌብነትና ልመናን ማጥፋት ነው፡፡ ሁለተኛ፤ የካቢኔ አባላት የኢትዮጵያ ሚኒስትሮች ናችሁ፡፡ የብሔር ተወካይ ለመሆን መሞከር በፌደሬሽን ም/ቤት ትክክል ነው፤ በካቢኔ ትክክል አይደለም፡፡ አንድ ሰው የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ከሆነ፣ ለመላው ኢትዮጵያውያን የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሆኖ ነው የሚሰራው፡፡ ለአንድ አካባቢ ተወክሎ በዚያ መንፈስ የሚሰራ ከሆነ፣ የምናስባትን ኢትዮጵያ እንዳንፈጥር ስለሚገዳደር፣ እያንዳንዱ የካቢኔ አባል፣ ይህን ጉዳይ ከወዲሁ ታሳቢ እንዲያደርግ….” ሲሉ አሳስበዋል ጠ/ሚኒስትሩ፡፡
 በነገራችን ላይ ከአዲሱ ፓርላማ ብዙ ይጠበቃል፡፡ በቅርጽም በይዘትም መለወጥ አለበት፡፡   የመንግስት ባለስልጣናትን በፓርላማ እየጠራ በኢትዮጵያ ህዝብ ፊት  በወሳኝነት የአገር ጉዳዮች ላይ የሚያፋጥጥና የሚያጋልጥ- እንዲሁም ተጠያቂነትን የሚያሰፍን መሆን አለባት (ሥራው እኮ ነው!)፡፡  ከአዲሱ የፓርላማ አባላት መካከል አንዱ በግብርና ሚኒስቴር አወቃቀር ላይ ባለፈው ረቡዕ የሰነዘሩትን ውሃ የሚያነሳ አስተያየት ቆንጥረን እንመልከት-፡፡
የፓርላማውን ድባብ ለማስታወስ፡፡ ወዳጆቼ፡- ለጠ/ሚኒስትሩ የሚያቀርቡት ጥያቄ  ተፅፎ የሚሰጣቸው የፓርላማ አባላት ከእንግዲህ ወዲህ  እንደማይኖሩን እርግጠኛ ነኝ፡፡ (ተሳስቼ ይሆን አንዴ?)
የፓርላማ አባሉ ወደ ሰጡት አስተያየት ልውሰዳችሁ፡፡
“…ግብርና በጥልቀት መታየት፣በጥልቀት መመርመር፣በጥልቀት መዋቀር ያለበት ነው። አሁን ግን ሳየው ግብርና overstretched (ከሚገባው  በላይ ተለጥጧል) ሆኗል፡፡ የተፈጥሮ ሃብት ልማት፣የእንስሳት ልማት፣የዓሳ ሃብት ልማት፣ቡና…  ሁሉ እዚህ ውስጥ ነው ያለው፡፡ ይሄ ትኩረትን ይቀንሳል…” ብለዋል- የተከበሩ የም/ቤት አባል  የኢትዮጵያ ግብርና፤ በግብርና ሚኒስቴር እየተመራ እንዴት እስካሁን በምግብ ራሳችንን አልቻልንም? እንዴት እስካሁን ከእርዳታ ስንዴ እለወጣንም? እንዴት  ለውጭ ገበያ የሚቀርብ ምርት ማምረት አልቻልንም?” ወዘተ  ሲሉም ጠይቀዋል- የም/ቤት አባል፡፡(ከእርዳታ ስንዴ ብንወጣም ኖሮ ዛሬ የማዕቀብ ማስፈራሪያ አይኖርም ነበር)
በነገራችን ላይ ጠ/ሚኒስትሩ በፓርላማ እንደገለፁት፤32 በአዋጅ የተቋቋሙ ተቋማት የታጠፉ ሲሆን በዚህም የብዙ ቢሊዮን ብሮች ወጪ ማዳን ተችሏል፡፡ (ሰራተኞቹስ የት ገቡ?) በሌላ በኩል 30 ያህል በውጭ ያሉ ኤምባሲዎቻችንም እንደሚታጠፉ አሊያም እንደሚሸጋሸጉ ጠ/ሚኒስትሩ በቅርቡ ተናግረው ነበር፡፡ (ጡረታ የወጡ ባለስልጣናትን አምባሳደር አድርጎ መሾም ታሪክ ይሆናል!) ዲጂታል ዲፕሎማሲ ላይ ማተኮር አንድ አማራጭ መወሰድ አለበት፡፡)
ወደ ሰሞኑ ሹም ሽር ልመልሳችሁ፤ ከሚኒስትሮች ሹመት ጋር በተያያዘ የኢዜማው መስራችና መሪው ፕ/ር ብርሃኑ ነጋ፣ የትምህርት ሚኒስቴር ሆነው መሾማቸውን ተከትሎ  ሁለት የም/ቤቱ አባላት ተቃውሞ አሰምተዋል፡፡ አንደኛዋ  አስተያየት የሰጡት በኦሮምኛ በመሆኑ የተነሳ በትክክል ያሉትን አልሰማሁም፡፡ ጠ/ሚኒስትሩ በከፊል እንደገለፁት፤ ተቃውሞው በምርጫ ቅስቀሳ ወቅት ፕ/ር ብርሃኑ ከተናገሩት ጋር የተያያዘ ነው (ቂም ይዘዋል ማለት ነው?) ከእንዲህ አይነቱ ተቃውሞ ራስን ማቀብ እንደሚገባ የመከሩት ጠ/ሚኒስትሩ፤ ብልፅግናም በምርጫ ቅስቀሳ ወቅት ያልተናገረው ነገር የለም ብለዋል፡፡ (ብርቅ አይሁንባችሁ ለማለት!)
ሌላኛዋ የፕ/ር ብርሃኑ ሹመት ተቃዋሚ ደግሞ ልጅ እግር የም/ቤቱ አባል ስትሆን፤ ዘና የሚያደርግ አስተያየት ሰጥታለች በዋናነት   የተቃውሞዋ መነሻ በምርጫ ቅስቀሳ ወቅት ፕሮፌሰሩ ወይም ፓርቲያቸው ያቀነቀነው  ሃሳብ ይመስለኛል፡፡ ግን ጎልቶ የወጣው የፕሮፌሰሩ የትምህርት ዝግጅት ትምህርት ሚኒስቴሩን በሚኒስተርነት ለመምራት ብቁ አያደርጋቸውም የሚለው  ሃሳባቸው ሀሳባቸው ነው፡፡
(ከመቼ ወዲህ ነው ሚኒስትር የትምህርት ዝግጅቱ እየታየ የሚሾመው?)
“ፕሮፌሰሩ ውጭ ጉዳይ ላይ የተሻለ ስለተከራከሩ እዛ ቢመደቡ…ወይ ኢኮኖሚክስ ስለተማሩ  የገንዘብ ሚኒስትርነት ቢሰጣቸው…ካልሆነ የምርጫ ምልክታቸው ሚዛን ስለሆነ ፍትህ ሚኒስቴር ቢደረጉ….” የሚል አስተያየት ሰንዝረዋል-የም/ቤት አባሏ፡፡ እሳቸው ግን የሰለጠኑትና የተመረቁት በፔዳጎጂና ኢጁኬሽን መሆኑን አስረግጠው ተናግረዋል፡፡(“ለሹመት ትክክለኛው እጩ እዚህ ነው ያለው” እንደማለት ነው!)
በትምህርት ሚኒስቴር ጉዳይ ጠ/ሚኒስትሩን በግል ለማማከርም ፈቃደኛ መሆናቸውን  የም/ቤቷ ተናግረዋል፡፡ (ማመልከቻ ሳይመስልባቸው አልቀረም)
ዶ/ር ዮሴፍ ወርቅነህ በፌስ ቡክ ገፃቸው  “የዛሬው የፓርላማ ትዝብቶች” በሚል ርዕስ ባሰፈሩት ፅሁፍ እንዲህ ብለዋል፡፡ “…እውነት ለመናገር የሴቲቷ ሃሳብ ምንም ባይገባኝም፣የተፃፈላቸውን ሃተታ የሚያነበንቡ የገደል ማሚቱ ተወካዮችን ለለመደ ፓርላማ፣እንዲህ የተሰማውን በሙሉ በልበ ሙሉነት የሚናገር፣የሚከራከር ስብስብ ማየት ትልቅ ተስፋን ይሰጣል፡፡”
እንግዲህ እያወራን ያለነው ስለ ፓርላማም አይደል፡፡ የም/ቤቱ አባላት ደግሞ የሹመኞችን ተጠያቂነት ማረጋገጥ ይኖርባቸዋል፤ ይጠበቅባቸዋል (በአንድ ወቅት “ፓርላማው ጥርስ አወጣ” ተብሎ ነበር!) እናም ከፓርላማ አባላት ህዝብ ምን እንደሚጠበቅ… ሌላ ጊዜ በዝርዝር እናነሳለን፡፡ የዛሬ  የፖለቲካ ወጋችንን ግን በአንዲት የሰሞኑ ክስተት ልቋጨው፡፡ ባለፈው ሰኞ ለተከናወነው በዓይነቱ የመጀመሪያ የአደባባይ የመንግስት ምስረታበመስቀል አደባባይ የተገነባው ግሩም መድረክ እስከ ሳምንቱ መጨረሻ የሚያፈርሰው አጥቶ ተሽከርካሪዎች በመንገድ መዘጋት ሲያማርሩ ሰንብተዋል፡፡ ለመድረኩ አለመፍረስ ማነው ተጠያቂው?


Read 1268 times