Error
  • JUser: :_load: Unable to load user with ID: 62
Monday, 10 September 2012 14:02

2004 ኢትዮጵያ ታላላቅ ሰዎቿን ያጣችበት ዓመት

Written by 
Rate this item
(3 votes)

ጊዜው በጣም ይነጉዳል፡፡ ትናንት የጀመርነው 2004 ዓ.ም ዛሬ ተጠናቋል፡፡ አንድ ዓመት እንደቀልድ እልም ይላል፡፡ መስከረም አልፎ መስከረም ሲተካ ሁሉም በየእምነቱ ለፈጣሪ እራሱን አደራ ይሰጣል፤ ‹‹ዓመት ከዓመት በሰላም አሸጋግረን›› ሲል፡፡ የተፈቀደላቸው ሲሻገሩ ያልተፈቀደላቸው ደግሞ ዓመቱን ሳይሻገሩ ይቀራሉ፡፡ ይህ የተፈጥሮ ዑደት ነው እና እንዲህ እያለ በያመቱ ይቀጥላል፡፡ ማንም ከሞት የሚቀር የለምና፡፡ ባጠናቀቅነው 2004 ዓ.ም ኢትዮጵያ ታላላቅ ሰዎቿን አጥታለች፡፡

ያሳለፍነው ዓመት ወጣት ጋዜጠኞችንም ወስዶብናል፡፡ በየሁለት ወሩ እና በየሦስት ወሩ አንዳንዴም በአንድ ወር ውስጥ የሁለት ታላቅ ሰዎች ሕይወት አልፏል፡፡ ገና በመስከረም ወር የተጀመረው ሐዘን እስከ ነሐሴ ዘልቋል፡፡ አንጋፋው ተርጓሚ፣ ጋዜጠኛና ደራሲ ማሞ ውድነህ እና አንጋፋው ደራሲ ስብሐት ገብረእግዚአብሔር በአንድ ወር ጊዜ ውስጥ ነበር ከዚህ ዓለም በሞት የተለዩት፡፡ ኢትዮጵያን ለ21 ዓመታት በጠቅላይ ሚኒስትርነት የመሩት መለስ ዜናዊ እና የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያንን ለ20 ዓመታት የመሩት አቡነ ጳውሎስም በአንድ ወር ጊዜ ውስጥ በጥቂት ቀናት ልዩነት ነው ሕይወታቸው ያለፈው፡፡ የእውቅና ታላላቅ ሰዎች ተከታትሎ ማለፍ የተነሳም ከዐይን የራቀ እና የታመመ ሰው ሁሉ ‹‹ሞተ›› እየተባለ ወሬ ሲናፈስበት የዘለቀ ዓመት ነበር- 2004 ዓ.ም፡፡

አርቲስት አስናቀች ወርቁ

(1927-2004)

በተጠናቀቀው የኢትዮጵያውያን 2004 ዓ.ም የመጀመሪያ ሣምንት ከግማሽ ምእት ዓመት በላይ በክራር ቅኝቷ የብዙዎችን ቀልብ ገዝታ የኖረችው አስናቀች ወርቁ ኅልፈተ ሕይወት የተሰማበት ወር ነበር፡፡ በቀድሞው ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ቴአትር (በአሁኑ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቴአትር) በታላላቅ ቴአትሮች ላይ መሪ ተዋናይት የነበረችው ድምጻዊቷና ተዋናይቷ አስናቀች ወርቁ፤ ለ10 ዓመታት ያህል አልጋ ላይ ከዋለች በኋላ በመስከረም ወር ነው ሕይወቷ ያለፈው፡፡ በወቅቱም ዜና እረፍቷ ለወዳጅ ዘመዶቿ እና ለአድናቂዎቿ አስደንጋጭ እና አሳዛኝ ነበር፡፡

ከሕፃንነቷ ጀምሮ የዘፈን ፍቅር እንደነበራት ትናገር የነበረችው አስናቀች ወርቁ፤  ከዘፋኝነቷ በተጨማሪ በዳንሰኝነቷም ትታወቃለች፡፡ በቴአትሩ ዘርፍም በቀድሞው ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ቴአትር (በአሁኑ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቴአትር) ‹‹ዳዊትና ኦሪየን›› እና ‹‹ሥነ ስቅለት›› እንዲሁም በ‹‹እናት ዓለም ጠኑ›› እና ‹‹ኦቴሎ›› በተሰኙት ሁለት የጸሐፌ ተውኔትና ባለቅኔ ሎሬት ጸጋዬ ገብረ መድኅን ሥራዎች ላይ ተውናለች፡፡ ለሦስት ዐሥርት ዓመታት በኢትዮጵያ ብሔራዊ ቴአትር ያገለገለችውና ከዚያም በጡረታ የተገለለችው አርቲስት አስናቀች፤ በአርቲስት ጌታቸው ደባልቄ በ95 ዓ.ም መፅሃፍ ተፅፎላታል ‹‹አስናቀች ወርቁ›› በሚል ርእስ፡፡ ‹‹የክራሯ ንግሥት›› አስናቀች ወርቁ የመጀመሪያ ክራሯን የገዛችው በያኔው ስሌት 25 ሳንቲም እንደነበር ይነገራል፡፡ ‹‹አልበር እንዳሞራ››፣ ‹‹የፍቅር ጮራ››፣ ‹‹እንደየሩሳሌም››፣ በ‹‹ሳብዬ›› እና በሌሎች የክራር ቅኝት ዘፈኖቿ፣ በቴአትር እና በፊልም ትወናዎቿ የምትታወቅ አርቲስት ነበረች፡፡ አርቲስት አስናቀች ወርቁ በተወለደች በ77 ዓመቷ በዓመቱ መጀመርያ ላይ መስከረም 4 ቀን 2004 ዓ.ም ከዚህ ዓለም በሞት ተለይታለች፡፡ ሥርዓተ ቀብሯም መስከረም 5 ቀን 2004 ዓ.ም በመንበረ ጸባዖት ቅድስት ሥላሴ ካቴድራል ተፈጽሟል፡፡

ጋዜጠኛ ጽጌረዳ ኃይሉ

(1970-2004)

ጥቅምት ወደ ኅዳር ሲሻገር ሞትም ከአርቲስት ወደ ጋዜጠኛ ተሻገረና በድንገት ወጣቷን ጋዜጠኛ ጽጌረዳ ኃይሉን ሞት ወሰዳት፡፡ ኅዳር 7 ቀን 2004 ዓ.ም ለጋዜጠኛ ጽጌረዳ ኃይሉ ቤተሰቦች፣ ወዳጅ ዘመዶች እና የሞያ አጋሮች የኅልፈተ ሕይወቷ መጥፎ ዜና የተሰማበት ቀን ነበር፡፡ ጋዜጠኛ ጽጌረዳ ኃይሉ ላለፉት ዓሥር ዓመታት በተለያዩ ጋዜጦች እና መጽሔቶች ላይ የሰራች ሲሆን የ”አዲስ ጉዳይ” መጽሔት ም/አዘጋጅ ነበረች፡፡ ጋዜጠኛ ጽጌረዳ ልጇን በሰላም ለመገላገል ሆስፒታል ገብታ ጤነኛ ሴት ልጅ ከተገላገለች ከአምስት ሰዓት በኋላ ነበር ሕይወቷ ያለፈው፡፡ በወቅቱ ቤተሰቦቿ እንደገለፁት፤ ጽጌረዳ የእርግዝና ክትትል ታደርግ የነበረው ወሎ ሰፈር አካባቢ በሚገኘው ሜሪስቶፕስ ክኒሊክ ሲሆን በሰላም እንዲያዋልዷት የሄደችውም ወደዚሁ ክኒሊክ ነበር፡፡ ጋዜጠኛ ጽጌረዳ በወቅቱ ሴት ልጅ በሰላም ብትገላገልም ሕይወቷ ግን ሊተርፍ አልቻለም፡፡

የካቲት 25 ቀን 1970 ዓ.ም የተወለደችው ጋዜጠኛ ጽጌረዳ ኃይሉ፤ ላለፉት አምስት ዓመታት የአዲስ ጉዳይ መጽሔት መሥራችና ምክትል ዋና አዘጋጅ በመሆን አገልግላለች፡፡ ጽጌረዳ፣ በተለያዩ የፕሬስ ውጤቶች ላይ የሰራት ሲሆን፣ በተለይ በኤፍኤም አዲስ 97.1 ሬዲዮ ጣቢያ ‹‹ብራና›› በተሰኘው ሣምንታዊ ፕሮግራም ላይ የመጻሕፍት ዳሰሳ፣ በኢትዮጵያ ሬዲዮ በሥጋ ደዌ ዙርያ በየ15 ቀኑ የሚተላለፍ ፕሮግራም አዘጋጅ ነበረች፡፡ ጽጌረዳ፤ ‹‹መቶ ደስታ ፍለጋ›› የተሰኘ የአጭር ልብወለድ ደራሲ ከመሆኗም በተጨማሪ፣ ‹‹እኛ›› በተሰኘው የሴት ደራሲያን የግጥም መድበል ውስጥም ግጥሞቿ ተካተዋል፡፡ የሁለት ልጆች እናት የነበረችው ጽጌረዳ፤ ኅዳር 7 ቀን 2004 ዓ.ም ሁለተኛ ልጅዋን ከተገላገለች ከሰዓታት በኋላ ሕይወቷ አልፏል፡፡

ሙዚቀኛው ደረጀ መኮንን

(1957 -2004)

ኅዳር ወር ጋዜጠኛን እና የሙዚቃ ባለሞያን በአንድ ላይ የወሰደበት ወር ነበር፡፡ ከዳሎል ባንድ መሥራቾች አንዱ የነበረው ሙዚቃ ቀማሪው ደረጀ መኮንን፤ ባጠናቀቅነው ኅዳር ወር 2004 ዓ.ም ኅልፈተ ሕይወቱ ሲሰማ ለወዳጅ ዘመዶቹ እና ለሙዚቃ ባለሞያ የሞያ አጋሮቹ አስደንጋጭ ዜና ነበር፡፡ በወቅቱ በርካታ ብዙሃን መገናኛ ዜና እረፍቱን ባይዘግቡትም በሥርዓተ ቀብሩ ላይ ግን በርካታ አርቲስቶች እና ታዋቂ ሰዎች ተገኝተው ነበር፡፡ የታዋቂው የሙዚቃ አቀናባሪ ቴዲ ማክ (ቴዎድሮስ መኮንን) ወንድም የነበረው ደረጀ መኮንን ከታዋቂው የሬጌ አቀንቃኝ የቦብ ማርሌይ ልጅ ዚጊ ማርሌይ ጋር በተለያየ ጊዜ በመላው ዓለም ባቀረበው የሙዚቃ ኮንሰርት ላይ ተሳትፏል፡፡ በተጨማሪም ዚጊ ማርሌይ ዓለም አቀፉን የግራሚ አዋርድ ሽልማት ባሸነፈበት ሁለት አልበሞች ላይም መስራቱ ይታወቃል፡፡ ‹አንድ ኢትዮጵያ›› የተሰኘውን  የአርቲስት እጅጋየሁ ሽባባው (ጂጂን)  የመጀመርያ  አልበም  በ1970ዎቹ  ፕሮዲውስ  ያደረገው  ደረጀ፤ የአይቤክስ  ባንድ  ኪቦርድ  ተጫዋች  ነበር፡፡ አርቲስት መሐሙድ  አሕመድን በሦስት አልበሞቹ ያጀበው ደረጀ መኮንን፤ ከአንጋፋዎቹ ድምፃውያን ጥላሁን ገሠሠ፣  አስቴር አወቀና ኤፍሬም ታምሩን ጨምሮ ከበርካታ ታዋቂ አርቲስቶች ጋር ሠርቷል፡፡ አርቲስቱ ከወጣት ድምፃውያን ጋር አዳዲስ ሙዚቃዎችን በመሥራት ላይ ሳለ ነው በኅዳር ወር በ47 ዓመቱ ሕይወቱ ያለፈው፡፡ የቀብሩ ሥነ ሥርዓትም ኅዳር 14 ቀን 2004 ዓ.ም. በቅድስት ስላሴ ካቴድራል ቤተክርስቲያን ተፈጽሟል፡፡

ስብሐት ለአብ ገብረ እግዚአብሔር

(1928-2004)

የካቲት ሳይጋመስ ኢትዮጵያ አንድ አንጋፋ ደራሲዋን አጣች፡፡ ስብሐት ለአብ ገብረ እግዚአብሔር ነፃ አስተሳሰቦችን የሚያራምድ፣ መድረክ ላይ የሚያደርጋቸው ንግግሮች ሁሌም አስቂኝ እና አነጋጋሪ የነበሩ፤ ከዚያም በላይ ደግሞ የሰዎችን በነፃ የማሰብ፣ በነፃነት የመናገር መብት በይፋ የሚያውጁ ነበሩ፡፡ በትግራይ ጠቅላይ ግዛት፣ ዐድዋ አውራጃ፣ እርባ ገረድ በተባለች መንደር ከአባቱ ከቄስ ገብረ እግዚአብሔር ዮሐንስ እና ከወይዘሮ መአዛ ወልደመድኅን የተወለደው ስብሃት፤ ትምሕርቱን በስዊድን  ሚሲዮን፣ እንዲሁም በአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ ተከታትሎ በትምህርት አስተዳደር የመጀመሪያ ዲግሪውን ተቀብሏል። በአስፋወሰን ትምህርት ቤት በእንግሊዝኛ መምሕርነት ለሁለት ዓመት አገልግሏል። በመቀጠልም ከየተባበሩት መንግሥታት የትምህርት፤ ሳይንስ እና የባህል ድርጅት (ዩኔስኮ) ባገኘው የትምህርት ዕድል አማካይነት ወደ ፈረንሳይ (ኤክስ አን ፕሮቫንስ) በመሄድ ከ1962-1964 ቆይቷል። የሄደበትን ትምህርት አጠናቆ ምስክር ወረቀት ባይቀበልም ቆይታው ከአውሮፓ  ባህል እና ሥነ-ጽሑፍ ጋር እንዲተዋወቅ ረድቶት እንደነበር በሕይወት በነበረበት ጊዜ ተናግሯል። ስብሐት ወደ አዲስ አበባ  ከተመለሰ በኋላ በመነን መጽሔት  የዝግጅት ክፍል ውስጥ ሠርቷል። በ1966 ዓ.ም ወታደራዊው ደርግ ሥልጣን ከያዘ በኋላ  ኩራዝ አሣታሚ ድርጅት  ሲቋቋም በአርታኢነት ተቀጥሮ ሠርቷል። በመንግሥት ትእዛዝም ከሌሎች ሰዎች ጋር በመሆን የካርል ማርክስ ሥራ የሆነውን  ካፒታልን (Das Capital) ከእንግሊዝኛ ወደ አማርኛ  በመመለስ ሥራ ላይ ከሌሎች ፀሃፍት ጋር ተሳትፏል። ስብሐት ገብረእግዚአብሔር ደራሲ፣ አርታኢ፣ ጋዜጠኛ ብቻ አይደለም - የልብወለድ ድርሰት ገጸባህርይም ነበር።‹ ‹ደራሲው›› የተሰኘው የደራሲ በአሉ ግርማ  ልብወለድ፤ በስብሐት ህይወት ላይ ተመስርቶ የተጻፈ ነው። ስብሐት ገብረ እግዚአብሔር የሁለት ወንዶች እና የሦስት ሴቶች አባት የነበረ ሲሆን ባደረበት ሕመም ምክንያት በሕክምና ሲረዳ ቆይቶ የካቲት 12 ቀን 2004 ዓ.ም ሕይወቱ አልፏል፡፡ የቀብር ሥነ ሥርአቱም አራት ኪሎ በሚገኘው የቅድስት ስላሴ ቤተ ክርስቲያን ተፈጽሟል፡፡

አንጋፋው ደራሲ እና ጋዜጠኛ ማሞ ውድነህ

(1923-2004)

የካቲት ወር ስብሐትን ብቻ አልነበረም የወሰደችው፣ ወሩ ሊጠናቀቅ በጣት የሚቆጠሩ ቀናት  ሲቀሩት አንጋፋውን ጋዜጠኛ፣ ደራሲ፣ ገጣሚ፣ ተርጓሚ እና የአገር ሽማግሌውን ማሞ ውድነህ ይዛ እብስ አለች፡፡ የካቲት 23 ቀን 2004 ዓ.ም የአቶ ማሞ ውድነህ ሕይወት አለፈ፡፡ ጥቅምት 12 ቀን 1923 ዓ.ም. በዋግ አውራጃ ዐምደ ወርቅ ከተማ ከአባታቸው አቶ ውድነህ ተፈሪና ከእናታቸው ወይዘሮ አበበች ወልደየስ የተወለዱት ደራሲ እና ጋዜጠኛ ማሞ ውድነህ፤ በሕይወት ዘመናቸው በአምስት ዘርፎች በጋዜጠኛነት፣ ደራሲነት፣ ተርጓሚነት፣ ገጣሚነት እንዲሁም በአገር ሽማግሌነት ከፍተኛ አስተዋፅኦ አበርክተዋል፡፡ አቶ ማሞ በተወለዱ በ81 ዓመታቸው ያረፉት በዚሁ ባጠናቀቅነው ዓመት ነበር፡፡

በማስታወቂያ ሚኒስቴር የጋዜጠኝት ሥራ የጀመሩት አቶ ማሞ ውድነህ፤ የፖሊስ ሠራዊት ህትመት የነበረው ‹‹ፖሊስና እርምጃው›› የተባለው ሳምንታዊ ጋዜጣ ሲቋቋም ከማስታወቂያ ሚኒስቴር ተመርጠው የጋዜጣው ተባባሪ ዋና አዘጋጅ በመሆን ትልቅ ሚና ተጫውተዋል፡፡ በመቀጠልም በኤርትራ የማስታወቂያ ሚኒስቴር ተጠሪ ሆነው በመመደብ ኤርትራ ውስጥ የጣሊያንኛ (ኤልኮቲዲያኖ)፣ የዓረብኛ (ዓልዓለም)፣ የትግርኛ (ኅብረት) እና የአማርኛም ጋዜጦችና የሬዲዮ ፕሮግራሞች ስለነበሩ ለእነኝህ ሁሉ አመራር መስጠትና ሥራቸውን ማስተባበር እንዲሁም ‹‹ኢትዮጵያ›› በተባለው ሳምንታዊ የአማርኛ ጋዜጣ ዘገባዎችና ትንታኔዎች ያቀርቡ ነበር፡፡ አዲስ አበባም ከተመለሱ በኋላ መጀመሪያ በማስታወቂያ ሚኒስቴር የአማርኛ ሥነ ጽሑፍ ክፍል ቀጥሎ በ‹‹የካቲት መጽሔት›› አገልግለዋል፡፡ ደራሲ እና ጋዜጠኛ ማሞ ውድነህ 53 መጻሕፍት ያሳተሙ ሲሆን፣ 54ኛው ‹‹ጣጣኛው›› የተሰኘ ልብወለድ በሕትመት ላይ እያለ ነበር ሕይወታቸው ያለፈው፡፡ ሥራዎቻቸው በስለላ፣ በታሪክ፣ በልብለወድና በተውኔት ላይ ያተኮሩ ናቸው፡፡ አቶ ማሞ ከድሮ እስከ ዘንድሮ ቁጥራቸው በውል የማይታወቁ ግጥሞችንም ገጥመዋል፡፡ አቶ ማሞ ውድነህ ከዘውዳዊውም ሆነ በደርጋዊ ሥርዓት ሕዝብንና መንግሥት ለማቀራረብ ሠናይና ቀና መንገዱን የያዘ ግንኙነት እንዲኖር ለማድረግ በመትጋታቸው በታሪክ ይጠቀሳሉ፡፡ በተለይ የ1983ቱ ለውጥ በተዳረሰበት የግንቦት አጋማሽ አካባቢ አዲስ አበባን ለመታደግ ያቀረቡት ልመና ጉልህ ስፍራ የሚያሰጠው ነው፡፡ የቅንጅት አመራሮች ከእስር እንዲፈቱ ድርድር ያደረገው የሽምግልና ቡድን ውስጥም ነበሩበት፡፡ የኢትዮጵያ ደራስያን ማኅበርን ለ12 ዓመታት በፕሬዝዳንትነት የመሩት አቶ ማሞ፤ ከባለቤታቸው ወይዘሮ አልማዝ ገብሩ ስድስት ልጆችና 10 የልጅ ልጆችን አፍርተዋል፡፡ ባደረባቸው ሕመም ምክንያት በተለያዩ ሆስፒታሎች ሕክምናቸውን ሲከታተሉ የነበሩት አቶ ማሞ፤ ያረፉት ዓርብ የካቲት 23 ቀን 2004 ዓ.ም. ነበር፡፡ ሥርዓተ ቀብራቸውም በመንበረ ጸባዖት ቅድስት ሥላሴ ካቴድራል የካቲት 24 ቀን ተፈጽሟል፡፡

እጅግ የተከበሩ የዓለም ሎሬት

ሜትር አርቲስት አፈወርቅ ተክሌ

(1925-2004)

የሚያዚያ ወር መጀመሪያ አንድ ሌላ አሳዛኝ እና አስደንጋጭ ዜና ይዞ መጣ፡፡ እጅግ የተከበሩ የዓለም ሎሬት ሜትር አርቲስት አፈወርቅ ተክሌ በ80 ዓመታቸው ማክሰኞ ሚያዝያ 2 ቀን 2004 ዓ.ም. ሌሊት አረፉ፡፡ ከሰማንያ ዓመት በፊት በአንኮበር ከተማ ጥቅምት 12 ቀን 1925 ዓ.ም. ከእናታቸው ከእመት ፈለቀች የማታ ወርቅና ከአባታቸው አቶ ተክሌ ማሞ የተወለዱት ሜትር አርቲስት አፈወርቅ፤ የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርታቸውን በአዲስ አበባ ከቀሰሙ በኋላ በወጣትነታቸው በ1940 ዓ.ም ለከፍተኛ ትምህርት ወደ እንግሊዝ አምርተዋል፡፡ የማዕድን ምሕንድስና ለመማር ቢያስቡም ስሜታቸውና ዝንባሌያቸው ወደ ሥነ ጥበቡ በማድላቱ ለንደን ውስጥ በሚገኙት የሥነ ጥበብና የኪነ ጥበብ ማዕከላዊ ትምህርት ቤትና በለንደን ዩኒቨርሲቲ የሥነ ጥበብ ፋኩልቲ ገብተው ኪነ ቅብ፣ ኪነ ቅርጽና  ኪነ ሕንፃ ተምረው አጠናቀዋል፡፡ ወደ ኢትዮጵያ በ1947 ዓ.ም. እንደተመለሱም በ22 ዓመታቸው በአዲስ አበባ ማዘጋጃ ቤት አዳራሽ ለብቻቸው ያዘጋጁት ዓውደ ርዕይ ከፋሺስቱ ጦርነት ወዲህ የመጀመሪያው ዓይነተኛ የሥዕል ትርዒት ሆኖ ተመዝግቦላቸዋል፡፡ ለስልሳ ዓመታት ያህል በሥነ ጥበብ ሥራዎቻቸው ገናና የነበሩት ሎሬት አፈወርቅ፤ ከቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ሽልማት ድርጅት በ1956 ዓ.ም. በሥነ ጥበብ የተሸለሙትን ጨምሮ በርካታ ዓለም አቀፍ ሽልማቶችን አግኝተዋል፡፡ ሎሬት አፈወርቅ ከሠሯቸው በርካታ ሥራዎች ውስጥ ኢትዮጵያን እና አፍሪካን የሚወክሉ አዳዲስ የሥነ ጥበብ ሥራዎች ለወርልድ ፎረም ፌዴሬሽን በዋሽንግተን ዲሲ በ2001 ዓ.ም. ሰኔ መጨረሻ ላይ አቅርበው፣ በ21ኛው ክፍለ ዘመን እጅግ ታላቅ አርቲስት በመባል ከተመረጡት መካከል የምርጦች ምርጥ ‹‹ዘ ግሬተስት ማን›› ክብርን አግኝተውበታል፡፡

የባህል ሚኒስቴር የሥነ ጥበባት ከፍተኛ አማካሪ፣ የኢትዮጵያ ቀይ መስቀል የቦርድ ሥራ አስፈጻሚ የነበሩት አንደበተ ርቱዕ አፈወርቅ፤ ባጠናቀቅነው ዓመት ሚያዚያ 2 ቀን 2004 ዓ.ም ሕይወታቸው አልፏል፡፡ ዓመቱም ኢትዮጵያም ስሟን በዓለም አቀፍ መድረክ ካስጠሩት ልጆቿ አንዱን ያጣችበት ሆኗል፡፡ እጅግ የተከበሩ የዓለም ሎሬት ሜትር አርቲስት አፈወርቅ ተክሌ የቀብር ሥነ ሥርዓት ቅዳሜ ሚያዝያ 6 ቀን 2004 ዓ.ም  በመንበረ ጸባዖት ቅድስት ሥላሴ ካቴድራል ተፈጽሟል፡፡

አንጋፋው ጋዜጠኛ ታደሰ ሙሉነህ

(1938-2004)

ያሳለፍነው ዓመት አንጋፋ እና ወጣት ጋዜጠኞች የታጡበት ዓመት ለመሆኑ በኢትዮጵያ ሬዲዮ፣ ቴሌቪዥን እና በሌሎች ብዙሃን መገናኛ  ከ40 ዓመታት በላይ ያገለገለው ጋዜጠኛ ታደሰ ሙሉነህ ኅልፈተ ሕይወት አንዱ ማረጋገጫ ነበር፡፡ ጋዜጠኛ ታደሰ ሙሉነህ ከአባቱ ከአቶ ሙሉነህ ሽብሬና ከእናቱ ከእመት በለጠች ሰኔ 3 ቀን 1938 ዓ.ም በአዲስ አበባ ከተማ ተወልዶ የአንደኛ ደረጃ ትምህርቱን በተፈሪ መኰንን ትምህርት ቤት፣ የከፍተኛ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርቱን ደግሞ በቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ዩኒቨርሲቲ የልዑል በዕደ ማርያም ትምህርት ቤት ተከታትሏል፡፡ ከ1960 ዓ.ም በኢትዮጵያ ሬዲዮ በዜና አንባቢነት ሥራ ከጀመረ በኋላ  በየጊዜው በተለያዩ አገሮች የወሰዳቸውን የሬዲዮ ፕሮግራም ኮርሶች በተግባር በመተርጎም በመጀመሪያ የቅዳሜ መዝናኛ ፕሮግራም፤ ቀጥሎም እስከዛሬም በበርካታ ኢትዮጵያውያን የሚታወስበትን እጅግ ተወዳጁን የእሑድ ፕሮግራም ከጋዜጠኛ ገዳሙ አብርሃ ጋር መሥርቶ በዋና አዘጋጅነትና ከበርካታ ታዋቂ የሥራ ጓደኞቹ ጋር በአቅራቢነት በመሥራት ከ1973 እስከ 1984 ለዓሥራ አንድ ዓመታት መርቶታል፡፡ በፕሮዳክሽን ኃላፊነት፣ በዋና ክፍል ኃላፊነትና በተጠባባቂ የመምርያ ኃላፊነት የኢትዮጵያ ሬዲዮ ፕሮግራሞች አዘጋጅና አቅራቢ በመሆን በጡረታ እስከወጣበት እስከ ጥቅምት 1986 ዓ.ም. ድረስ ለሃያ ስድስት ዓመታት አገልግሏል፡፡ ከጡረታ በኋላም ለሕይወቱ ማለፍ ምክንያት የሆነው ሕመም እስካደናቀፈው ድረስ ከ1993 እስከ 2000 የአዲስ ቻምበር ድምጽ መሥራችና የፕሮግራም መሪ በመሆን ለሰባት ዓመታት፣ የሞሐ ለስላሳ ሳምንታዊ ፕሮግራሞችን በማዘጋጀት፣ በሸገር ኤፍኤም ‹‹እሑድ እንደገና›› የተባለውን ፕሮግራምንም ከ2000 እስከ 2002 እያዘጋጀ አቅርቧል፡፡ በእነዚህ አገልግሎቶቹ የኢትዮጵያ የሥነ ጥበባትና መገናኛ ብዙኀን ተሸላሚ ለመሆን በቅቷል፡፡ ባለትዳርና የአንዲት ሴት ልጅ አባት የነበረው ጋዜጠኛ ታደሰ ባደረበት ሕመም በአዲስ አበባ፣ በጆሐንስበርግ (ደቡብ አፍሪካ) እና ባንኮክ (ታይላንድ) ሕክምናውን ሲከታተል ቆይቶ በ66 ዓመት ዕድሜው ያረፈው ባሳለፍነው ዓመት ግንቦት 17 ቀን 2004 ዓ.ም.  ነበር፡፡ ሥርዓተ ቀብሩም በገነተ ኢየሱስ ቤተ ክርስቲያን ተፈጽሟል፡፡

ጋዜጠኛ ታደሰ እንግዳው

(1965-2004)

ሞት ከአንጋፋው ጋዜጠኛ ወደ ወጣቱ ጋዜጠኛ ተሻግሮ በሐምሌ ወር 2004 ዓ.ም ላለፉት ስምንት ዓመታት ለጀርመን ሬዲዮ ጣቢያ (ዶቼቬሌ) የአማርኛ ድምጽ ከአዲስ አበባ ይዘግብ የነበረው ጋዜጠኛ ታደሰ እንግዳው  በተወለደ በ39 ዓመቱ በመኪና አደጋ ከዚህ ዓለም በሞት ተለየ፡፡ ጋዜጠኛ ታደሰ መስከረም 14 ቀን 1965 ዓ.ም በጐንደር ክፍለ ሀገር ተወልዶ የአንደኛና ሁለተኛ ደረጃ ትምህርቱን እዚያው ጐንደር ካጠናቀቀ በኋላ፣ በ1991 ዓ.ም አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በመግባት በውጭ ቋንቋና በጋዜጠኝነት ተመርቋል፡፡ ጋዜጠኛ ታደሰ እንግዳው በዶቼቬሌ የሬድዮ ጣቢያ ከመቀጠሩ በፊት በተለያዩ ጋዜጦች ላይ በአምደኝነት፣ በአድማስ ዩኒቨርስቲ ኮሌጅ የሕዝብ ግንኙነት መምሪያ ኃላፊ፣ የፍኖተ አድማስ ወርሃዊ ጋዜጣ ዋና አዘጋጅ፣ በካቶሊክ ካቴድራል የወንዶች ትምህርት ቤት የእንግሊዘኛ ቋንቋ መምሕር በመሆን አገልግሏል። ጋዜጠኛ ታደሰ እንግዳው ባለትዳርና የሦስት ወንድ ልጆች አባት ነበር፡፡ ጋዜጠኛ ታደሰ እንግዳው፤ የቀብር ሥርዓት በተወለደበት በጐንደር ከተማ ሐምሌ 9 ቀን 2004 ዓ.ም ተፈጽሟል፡፡

ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ጳውሎስ

(1928-2004)

ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ጳውሎስ ፓትርያርክ ርእሰ ሊቀነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ ሊቀ ጳጳስ ዘአክሱም ወእጨጌ ዘመንበረ ተክለሃይማኖት፣ የዓለም አብያተ ክርስቲያናት ምክር ቤት ፕሬዚዳንት፣ የዓለም ሃይማኖቶች ምክር ቤት ለሰላም የክብር ፕሬዚዳንት የነበሩት አቡነ ጳውሎስ በኢትዮጵያ እና በመላው ዓለም ዝነኛ እና አነጋጋሪ ፓትርያክ ናቸው፡፡ ሁሌም ከብዙሃን መገናኛ እይታ የማይጠፉት አቡነ ጳውሎስ  በጥቂት ቀናት ሕመም ነበር ዜና እረፍታቸው በድንገት የተሰማው፡፡ ነሐሴ 10 ቀን 2004 ዓ.ም ያረፉት የ76 ዓመቱ ፓትርያርክ የድንገተኛ ሕልፈታቸው መንስዔ የስኳር ሕመምና የደም ግፊት መሆኑን ቅዱስ ሲኖዶስ ይፋ አድርጎ ነበር፡፡ ጥቅምት 25 ቀን 1928 ዓ.ም በዐድዋ ከተማ፣ በመደራ አባ ገሪማ ገዳም አካባቢ ከአባታቸው ከአፈ መምህር ገብረ ዮሐንስ ወልደ ሥላሴና ከእናታቸው ከወ/ሮ አራደች ተድላ የተወለዱት አቡነ ጳውሎስ፤ በጥንታዊው አባ ገሪማ ገዳምና በአዲስ አበባ ቅድስት ሥላሴ መንፈሳዊ ኮሌጅ መንፈሳዊ ትምህርታቸውን ተከታትለዋል፡፡ በወቅቱ ሁለተኛው ፓትርያርክ በነበሩት ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ቴዎፍሎስ አማካይነት ለከፍተኛ ትምህርት ወደ አሜሪካ ተልከው ከሩሲያው የቅዱስ ቭላድሚር ቲኦሎጂካል ሴሚናሪ በኦርየንታልና በምሥራቅ ኦርቶዶክስ አብያተ ክርስቲያናት መካከል ባለው የነገረ መለኮት ይትበሐል (ትምህርት) በ1954 ዓ.ም ዲፕሎማ አግኝተዋል፡፡ ቀጥሎም በየል ዩኒቨርሲቲ በኦሪየንታል፣ በምሥራቅና በምዕራባውያን አብያተ ክርስቲያናት መካከል ስላለው የነገረ መለኮት ትምህርት አመለካከትና ልዩነት ባችለር ኦፍ ዲቪኒቲ ዲግሪን በ1958 ዓ.ም ሲያገኙ፣ ከፕሪንስተን ዩኒቨርሲቲ በክርስቲያናዊ ሥነ ምግባር ማስተርስ ኦፍ ቴኦሎጂ ዲግሪን በ1964 ዓ.ም ተቀብለዋል፡፡ በዚያው ዩኒቨርሲቲ በ1980 ዓ.ም. የዶክትሬት (ፒኤችዲ) ዲግሪያቸውን አግኝተዋል፡፡ የውጭ ትምህርታቸውን አጠናቀው ከአሜሪካ ከተመለሱ በኋላ በቤተ ክርስቲያኒቱ ሁለገብ አገልግሎት ሰጥተዋል፡፡ የጎፋ መካነ ሕያዋን ቅዱስ ገብርኤል ካቴድራል የጥበበ ዕድ የካህናት ማሠልጠኛ በማቋቋም በመምራት፣ የቅዱስ ጳውሎስ መንፈሳዊ ኮሌጅ ዲን፣ የታሪክ፣ የድርሰትና የስብከተ ወንጌል፣ የጋዜጦች፣ የመጽሔቶችና የሬዲዮ መምርያ የበላይ ኃላፊ፣ የሰንበት ትምህርት ቤቶችን ማዕከል በዘመናዊ መልክ በማቋቋም አገልግለዋል፡፡ ቃለ አዋዲ የተሰኘውን የመመርያ ደንብ በማውጣት ምእመናን በሰበካ ጉባዔ፣ ካህናትን በካህናት ማሠልጠኛ ትምህርት ቤቶች በሚያደራጁበት ወቅት ግንባር ቀደም በመሆን ተሳትፈዋል፡፡ እንዲሁም የልማትና ክርስቲያናዊ ተራድኦ ኮሚሽን ዋና ዳይሬክተርና የስደተኞች አገልግሎት ዋና ጸሐፊ፣ የትንሣኤ ዘጉባኤ ማተሚያ ቤት የበላይ ኃላፊ በመሆን ሲሠሩ፣ ከአገር ውጭም ከ1950 ዓ.ም. ጀምሮ ቤተ ክርስቲያኒቱን በመወከል በዓለም አብያተ ክርስቲያናት ማኅበር ቀዋሚ ኮሚቴ አባል ነበሩ፡፡ በ1960 ዓ.ም. ካናዳ ላይ ተደርጎ በነበረው ዓለም አቀፍ ኤክስፖ ኢትዮጵያ ስትሳተፍ፣ የታሪክና የእምነት ክፍል ኃላፊ በመሆን ለስምንት ወራት አገልግሎት ሰጥተዋል፡፡

መስከረም 16 ቀን 1968 ዓ.ም. ብፁዕ ተብለው የተሾሙት አቡነ ጳውሎስ፤ ከሹመት በኋላ ደርግ እርሳቸውንና አብረዋቸው የተሾሙትን አቡነ ባስልዮስና አቡነ ጴጥሮስን ጨምሮ ለሰባት ዓመት አሰራቸው፡፡ በ1974 ዓ.ም. ከእስር ሲለቀቁም በግብጽ በኩል አድርገው  ወደ ባሕር ማዶ በማምራት በእስር ምክንያት ያቋረጡትን የዶክትሬት ትምህርታቸውን አጠናቀዋል፡፡ በአሜሪካ የተለያዩ ግዛቶችም ለኢትዮጵያውያን ዳያስፖራዎች ምዕመናን አገልግሎት የሚሰጡ ሰባት አብያተ ክርስቲያናትን አቋቁመዋል፡፡ የደርግ መንግሥት በ1983 ዓ.ም. መውደቁን ተከትሎ ከስደት የተመለሱት አቡነ ጳውሎስ፤ በዓመቱ በተደረገው ምርጫ አምስተኛው ፓትርያርክ ሆነው በመመረጥ ሕይወታቸው እስካለፈበት እስከ ነሐሴ 10 ቀን 2004 ዓ.ም. ድረስ ለ20 ዓመት የኢትዮጵያን ቤተ ክርስቲያን መርተዋታል፡፡ የብፁዕ ወቅዱስ ዶክተር አቡነ ጳውሎስ ፓትርያርክ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ ስርዓተ ቀብርም ነሐሴ 17/2004 ዓ.ም በመንበረ ፀባዖት ቅድስት ስላሴ ካቴድራል በታላቅ ሥነ ሥርዓት ተፈጽሟል።

ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ

(1947-2004)

አቡነ ጳውሎስ ከሞቱ ከአራት ቀናት በኋላ ኢትዮጵያ ለ21 ዓመታት የመራትን መሪ ስታጣ ዐድዋ ደግሞ በአንድ ዓመት ጊዜ ውስጥ ሦስት ታላላቅ ልጆቿን አጥታለች፡፡ ስብሃት፣ አቡነ ጳውሎስ እና አቶ መለስ፡፡ የኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ዴሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ ሰኞ ነሐሴ 14 ቀን 2004 ዓ.ም በ57 ዓመታቸው ከዚህ ዓለም በሞት መለየታቸው በኢትዮጵያ ቴሌቭዥን ሲነገር የዓመቱ አስደንጋጭ የሞት ዜና ነበር፡፡

በትግራይ ክልል በዐድዋ ከተማ፣ ከአባታቸው ከአቶ ዜናዊ አስረስ እና ከእናታቸው ወይዘሮ አለምነሽ ገብረልዑል ግንቦት 1 ቀን 1947 ዓ.ም የተወለዱት ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ ለቤተሰባቸው ሦስተኛ ልጅ ነበሩ፡፡ የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርታቸውን በዐድዋ ንግስተ ሣባ ትምህርት ቤት የሁለተኛ ደረጃ ትምህርታቸውን ደግሞ ባሳዩት ከፍተኛ የትምህርት ብልጫ ከመላው ሀገሪቱ ከተመረጡ ተማሪዎች መካከል አንዱ በመሆን፣ በአዲስ አበባ ጄነራል ዊንጌት ትምህርት ቤት ተከታትለዋል፡፡ በ1965 የአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲን በመቀላቀል ለሁለት ዓመታት በሕክምና ፋካሊቲ ትምህርታቸውን ሲከታተሉ ቢቆዩም፣ በወቅቱ የነበረውን ብሔራዊ ጭቆናን ለመታገል ሕዝባዊ ወያኔ ሓርነት ትግራይን በመቀላቀል በርሃ ገቡ፡፡ አቶ መለስ በ1967 የተመሰረተው ሕወሓትን ከተቀላቀሉ አንስቶ ከታጋይነት እስከ አመራርነት አገልግለዋል፡፡

በሕወሓት አመራር አባልነት የደርግን መንግሥት ለ17 ዓመታት ከታገሉ በኋላ በድል አድራጊነት አዲስ አበባ በመግባት በሽግግሩ መንግሥት አገሪቱን በፕሬዚዳንት ሲመሩ፣ ከ1988 ዓ.ም. ጀምሮ በጠቅላይ ሚኒስትርነት አገልግለዋል፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ የመጀመሪያ ስማቸው ለገሠ ሲሆን፣ ስማቸውንም የቀየሩት በወቅቱ በነበረው ትግል በደርግ መንግሥት የተገደለውንና የትግል አጋራቸው የነበረውን ወጣት ለመዘከር  ነው፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ላለፉት 21 ዓመታት  መንግሥትንና የኢሕአዴግ ፓርቲን ሲመሩ ቆይተዋል፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ሥልጣን ላይ ከወጡ በኋላ ከእንግሊዙ ኦፕን ዩኒቨርሲቲ በቢዝነስ አድሚኒስትሬሽን ሁለተኛ ዲግሪያቸውን አግኝተዋል፡፡ በተመሳሳይም ኔዘርላንድ ከሚገኘው የኢራስመስ ዩኒቨርሲቲ በኢኮኖሚክስ ሁለተኛ ዲግሪያቸውን አግኝተዋል፡፡ በተጨማሪም ደቡብ ኮሪያ ከሚገኘው ሃናም ዩኒቨርሲቲና ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የክብር ዶክትሬት ዲግሪዎችን ተቀብለዋል፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ከባለቤታቸው ከወይዘሮ አዜብ መስፍን ጋር ለ25 ዓመታት በትዳር ሲቆዩ፣ በትዳር ዘመናቸውም ሁለት ሴት ልጆችንና አንድ ወንድ ልጅ ማፍራት ችለዋል፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ባሳለፉት የሥራ ዘመን በአገር ውስጥም ሆነ በዓለም አቀፍ ደረጃ በርካታ ሥራዎችንን አከናውነዋል፡፡ በአገር ውስጥ ከሠሯቸው ሥራዎች በቀዳሚነት በእርሳቸው ጠንሳሽነት እየተተገበረ ያለው የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ ይጠቀሳል፡፡ በዚህም ፕሮጀክት የተካተተው ታላቁ የህዳሴ ግድብ በቀዳሚነት ይታወቃል፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትሩ በአገር ውስጥ ለዲሞክራሲ ሥርዓት መጐልበት ዳተኛ በመሆን በአንዳንድ በምዕራባዊያን ዘንድ ቢተቹም፣ በበርካታ ምዕራባዊያን መሪዎች ከፍተኛ ቦታ የሚሰጣቸው መሪ ነበሩ፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ በበርካታ ዓለም አቀፍ ስብሰባዎች ላይ የተሳተፉ ሲሆን፣ በኔፓድና በአየር ንብረት ለውጥ አፍሪካን ወክለው በመደራደር የአፍሪካ ድምፅ እየተባሉ ይጠሩ ነበር፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ ከትግል አጋራቸው ወይዘሮ አዜብ መስፍን ጋር በትዳር ከ25 ዓመታት በላይ ተጣምረዋል፡፡

በትዳራቸውም ሦስት ልጆች አፍርተዋል፡፡ በጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ ኅልፈተ ሕይወት ምክንያትም ኢትዮጵያ ለ14 ቀናት በሐዘን ማቅ ውስጥ ሰንብታ ነበር፡፡ የ2004 ዓ.ም መዝጊያ ወር በሐዘን ተደምድሟል፡፡ መስከረም ‹‹2004››ን በአርቲስት አስናቀች ወርቁ ኅልፈተ ሕይወት የተቀበለችው ኢትዮጵያ፤ ነሐሴን በጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ ኅልፈተ ሕይወት ዘግታለች፡፡ ዓመቱም ጋዜጠኞች፣ መሪ፣ የኃይማኖት አባት እና አንጋፋ የኪነጥበብ ባለሞያዎች የታጡበት ዓመት ሆኖ አልፏል፡፡ ወቅቱ ይለያይ እንጂ ከሞት የሚቀር የለም፡፡

ጠ/ሚኒስትር መለስ ዜናዊና ቀ/ኃ/ሥ በሽልማት ዙሪያ

ዶክተር ዩን - ፕዮ ሺን የሐናም ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት (ኮሪያ) የእንኳን ደስ አለዎ ደብዳቤ

የዓለም ሰላምንና ዕርቅን በመላው ዓለም ለማስፋፋት የዓለም የሰላም ጓድ (World peace Corps) ያደረገውን ክቡር ጥረት መሠረት አድረጌ የኢትዮጵያ ጠ/ሚኒስትር መለስ ዜናዊ የዓለም ሰላም የክብር ተሸላሚ ሆነው በመመረጣቸው ከልብ እንኳን ደስ አለዎ እላለሁ፡፡

…ደከመኝ ታከተኝ በማይል የክርስቲያን ጽኑ መንፈስ ህይወታቸውን በ”ሙሉ ለሰላምና ለፍትሕ ላገለገሉት ለአቶ መለስ ዜናዊ ይህ ሽልማት ልዩ ትርጉም እንደሚሰጣቸው እርግጠኛ ነኝ፡፡

የዓለም የሰላም ሽልማት የሚሰጠው የሰላምን ዘር በዓለም ዙሪያ ለመዝራት ከሃይማኖት፣ ከዘር ወይም ከፖለቲካ ነፃ የሆነ መልካም ተግባር ለፈፀሙ ግለሰቦች ነው፡፡

የዓለም ሰላም ሽልማት ድርጅት የተቋቋመው የዓለምን ሰላም ሠረት ለመጣል የጥላቻና የባላንጣነት ግድግዳ ማፍረስና በየአካባቢያችን ሰላምን ማገልገልና ለሰላም መሥራት አለብን፡፡

በዚህ አንፃር የመለስ ዜናዊን የክብር ሽልማት ውሳኔ እንደተገቢና ተፈጥሮአዊ ነገር አድርጌ ነው የምቆጥረው፡፡

እንደገና እንኳን ለ2002 የዓለም ሰላም ሽልማት አበቃዎት ልል እወዳለሁ፡፡

የአምላክ በረከት በርስዎ ላይ ይረፍ፡፡ በዚህ ሽልማት አማካኝነትና በተቀባዩም ክቡር ጥረት የአለም ሰላምና ህብርነት ወደተሻሻለ ደረጃ እንዲያድግ እፀልያለሁ፡፡

በመጨረሻ መለስ ዜናዊ ይህን የክብር የፖለቲካ ሳይንስ ዶክትሬት ዲግሪ በማግኘትዎ እንኳን ደስ አለዎት እላለሁ፡

የጠ/ሚኒስትር መለስ ዜናዊ ሽልማት

(ጠ/ሚኒስትር መለስ በተሸለሙበት ወቅት ካደረጉት ንግግር በከፊል የተቆነፀለ፡፡)

“…ሰላምን ማግኘት በረከት የማይሆንለት አገር ያለ አይመስለኝም፡፡ ሆኖም ከአፍሪካ ህዝቦች የበለጠ ይህን በረከት የሚፈልግ ያለ አይመስለኝም፡፡ ምክንያቱ ግልጽ ነው፡፡ የኢኮኖሚ ሁኔታችንና የምንኖርበት የድህነት ህይወት ሁሉንም ያስረዳልና!

በዚህ ረገድ ለማንኛውም የአፍሪካ አመራር በሰላምና በጦርነት ጉዳይ ላይ መወሰን የጭንቅ የምጥ አጣብቂኝ ይሆንበታል፡፡ ይህ ውሳኔ ጦርነት በሰው ህይወትና በንብረት ላይ ከሚያደርሰው ጥፋትና ውድመት ባሻገር ለአንድ የተራበ ህፃን ቁራሽ ዳቦ በማግኘትና በጥይት መካከል የመምረጥ ጥያቄን ያስከትላሉ፡፡

ከዚህ አንፃር ለህዝባችን የገባንለትን ቃል አለማጠፋችንን በንፁህ ህሊና ስናገር በመንግስት ስም ኩራት ይሰማኛል፡፡

በተቻለንም አቅም ሁሉ ሰላምን ለማስፈን የተገኘውን አጋጣሚ ሁሉ ለመጠቀም ሞክረናል፡፡ እውነቱን ለመናገር ፖለቲካ፣ ዲፕሎማሲና ዓለምአቀፍ ግንኙነቶች ሁሉ እንዳሉ እያሉ ለአንድ ለተራበ ህፃን ቁራሽ ዳቦ በማግኘትና በጥይት መካከል የመምረጥ ጥያቄ ሲባል ርህራሄ አልባነት ይመስላል፡፡ ሆኖም ጉዳዩ ሁሌ ቀላል ሆኖ አይገኝም፡፡ በመጀመሪያ ደረጃ አጋሮቻቸው ትክክለኛውንና ተገቢውን ምርጫ እንዳያደርጉ እንቅፋት የሚሆኑ ወገኖች ይኖራሉ፡፡

ሰላም በፍላጐትና በምኞት ብቻ የሚገለፅ አይደለም፡፡

ሰላም ይሰፍን ዘንድ ተባባሪ አጋር ይፈልጋል፡፡ ሰላም እንዲኖርና እንዲጠበቅ አጋር አለመኖሩ (አለመገኘቱ) አንዱ ችግር ሲሆን…ከዚህም በላይ እጅግ አስጨናቂውን ውሳኔ የሚወስኑ ወገኖች ዲፕሎማሲ በሀሰት የማስመሰያ መድረክ ለከመሆኑንና አለም አቀፍ ህጉም ጠባቂ ዘብ እንደሌለው የሚገነዘቡበት ሁኔታ መከሰቱ ነው፡፡

በዚህ አንፃር የኢትዮጵያ ህዝብ ለአመታት ቅር መሰኘቱ ጥርጥር የለውም፡፡ ያም ሆኖ በማናቸውም የችግርና የመከፋት ጊዜ እንዳደረገው በትዕግሥትና በሀሞተ መራርነት ለሰላም ያለውን ጽናት አረጋግጧል፡፡

…ህዝብ ሰላምን ይፈልጋል ብሎ ማሰብ ምንም አደጋ አያስከትልም፡፡ መንግሥታትም ይፈልጋሉ የሚለው ግን ሁልጊዜ አያዋጣም፡፡

…ምክር ቤቱ በዚህ ሽልማት አማካኝነት የኢትዮጵያ ህዝብ ለሰላም ያለውን ጽናት በማረጋገጡና እውቅና ሰጥቶ አብሮ በመቆሙ አድናቆቴን ለመግለጽ እወዳለሁ፡፡

ስም :- መለስ ዜናዊ

የትውልድ ቀን :- ግንቦት 8,1955 (እኤአ)

የትውልድ ሥፍራ:- አድዋ ትግራይ ሰሜን ኢትዮጵያ

የጋብቻ ሁኔታ:- አግብተዋል ሦስት ልጆች አሏቸው

የትምህርት ሁኔታ

የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርት :- ንግስት ሳባ መለስተኛ ሁለተኛ ደረጃ ት/ቤት፣ አድዋ የሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት:- ጄኔራል ዊንጌት ሁለተኛ ደረጃ ት/ቤት፣ በ1972 በከፍተኛ ማዕረግ አጠናቀቁ፡፡

ዩኒቨርሲቲ:- ህክምና ፋከሊቲ፣ አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ፣ ጥቅምት 1974 የሁለተኛ ዓመት ተማሪ ሳሉ ዩኒቨርሲቲውን ለቀው ከትግራይ ህዝብ ነፃነት ግንባር ጋር ተቀላቀሉ፡፡

ከእንግሊዝ አገር ኦፕን ዩኒቨርሲቲ በተልዕኮ MBA አገኙ፡፡ በአሁኑ ሰዓት ለማስትሬታቸው በኢኮኖሚክስ ማኔጅመንት በተልዕኮ እየተማሩ ይገኛሉ፡፡

ፖለቲካዊና ሙያዊ ተሳትፎ

1974:- ከትግራይ ህዝብ ነፃነት ግንባር ጋር ተቀላቀሉ

1979:- የትግራይ ህዝብ ነፃነት ግንባር ማዕከላዊ ኮሚቴ አባል ሆኑ

1983:- የትግራይ ህዝብ ነፃነት ግንባር ፖሊት ቢሮ አባል ሆኑ

1989:- የኢትዮጵያ ህዝቦች አብዮታዊ ዲሞክራሲ ግንባር ሊቀመንበር ሆኑ

1991-1995 የኢትዮጵያ የሽግግር መንግስት ፕሬዚዳንትና የተወካዮች ምክር ቤት ሊቀመንበር ከላይ በተጠቀሱት ግንባሮች የነበራቸው ኃላፊነት እንደተጠበቀ ሆኖ ከ1995 ጀምሮ - የፌዴራል ዲሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ ኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚኒስቴር በዓለም አቀፍና በአህጉራዊ ደረጃ ያደረጉት እንቅስቃሴ

ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከአፍሪካ አንድነት ድርጅትና ከኢጋድ በተሰጣቸው ማንዴት መሠረት በሶማልያ ብሔራዊ እርቅ ሂደት ላይ የላቀ ተሳትፎ አድርገዋል፡፡ በሱዳን የነበረውን ግጭት ለማቆም በኢጋድ በተደረገው ጥረት ጠቅላይ ሚኒስትሩ ተሳትፎ አድርገዋል፡፡ በግሬት ሌክስ ኤርያ የነበረውን ቀውስ ለመፍታት በተደረገው የአፍሪካውያን ጥረት ውስጥ ተሳትፈዋል፡፡

የአፍሪካ አንድነት ድርጅት ሊቀመንበር በመሆን እ.ኤ.አ ከሰኔ 1995 እስከ 1996 ሰርተዋል፡፡

የግርማዊ ቀዳማዊ ኃ/ሥላሴ የክብር ዶክትሬት

ቀዳማዊ ኃይለሥላሴ የሃያ የዓለም ዩኒቨርሲቲዎችን የክብር ዶክትሬት ተሸላሚ ነበሩ፡፡ እነዚህም የሕግ፣ የፈትሐብሔር ህግ፣ የእርሻ፣ የሥነጽሑፍና የፍልስፍና የክብር ዶክትሬትነት ማዕረጐች ናቸው፡፡

ግርማዊ ንጉሠ ነገሥት ቀዳማዊ አፄ ኃይለሥላሴ ከኬምብሪጅ ዩኒቨርሲቲ ሐምሌ 11 ቀን 1916 ዓ.ም የሕግ ዶክተርነት ሲቀበሉ በኬምብሪጅ ዩኒቨርሲቲ ስለ ልዑል አልጋ ወራሽ ተፈሪ መኮንን የተነገረ፡፡

ልዑል ሆይ

ባለቅኔው ሆሜር የኢትዮጵያ ሰዎች ነውር የሌለባቸው ናቸው ብሏል፡፡ ሄሮዱተስም የኢትዮጵያ ሰዎች ፈጽሞ የወይን ጠጅ አይጠጡምና ዕድሜያቸው ረዥም ነው ብሏል፡፡

የኢትዮጵያ ሰዎች ለካምባይሰሰና ለፋርስ ግብር አንገብርም ማለታቸው ርግጥ ነው፡፡

ከዚያም በኋላ ማንንም ሀገራቸውን ለመውሰድ የመጣውን ሁሉ እንዳይገባ ከለከሉት፡፡ ይህንም ሁሉ ካደረጉ በኋላ አሳባቸው ሁሉ ነጻነታቸው እንዳይነካ ነው፡፡

የሳባ ንግሥት የሰሎሞንን ዝና ሰምታ ሽቶና ቅመም ወርቅና አልማዝ ይዛ ሰሎሞንን በዋና ጥያቄ ለመፈተን በግመል እንደመጣች የማያውቅ ማነው፡፡

የነገሥታትስ ሁሉ እናት ትሆን ዘንድ ወደ ሀገሬ እንደተመለሰች የማያውቅ ማነው፡፡

ምንስ ዘመኑ ቢበዛ ከዳዊት ዘር መሆናቸውን የማያስብ ማን ነበር፡፡ የንግሥት ክንዳሲስ ወገን መሆናቸውን የማያውቅ ማን ነበረ፡፡

ይህም ሁሉ ክርስቲያንነታቸውን በሙሉ ኢትዮጵያ እንደ መሠረቱ የቀድሞ እምነት የብዙ ዘመን ታሪክ እንዳላቸው ያስረዳልና፡፡

የኢትዮጵያውያንን መጻሕፍትና የሕግ መጻሕፍታቸውን ባለፈው ዓመታት በካምብሪጅ ዩኒቨርሲቲ በክርስቶስ ኮሌጅ የተማረ አንድ ሰው ለእንግሊዞች ገለፀው፡፡

አሁንም ዛሬ የኢትዮጵያ መንግሥት አልጋ ወራሽ ተፈሪ መኮንን መካከላችን አሉ፡፡ እርሳቸውም የቀድሞ ያባቶቻችንን መንገድ ይዘው የሚከተሉት ከምሥራቃውያንና ከግብጻውያን ይልቅ ዕውቀት ያላቸው ናቸው፡፡

የቀድሞውንም የዛሬውንም ጥበብና ዕውቀት ይመረምራሉ፡

የቀድሞውን የክርስቲያንን ትምህርት ሁሉ መርምረዋል፡፡ አዲሱንም ዕውቀት ለማግኘት ይጥራሉ፡፡

ከኢትዮጵያ የመንግስት አልጋ ወራሾች በመጀመሪያ ወደ አይሮፕላን ላይ የወጡ ልዑል ተፈሪ መኮንን ናቸው፡፡

ደግሞ የዮሐንስ አፈወርቅን የማር ይስሐቅን መጻሕፍት ከግእዝ ቋንቋ እያስተረጐሙ በገዛ ማተሚያቸው አሳትመዋል፡፡

እነዚህም መጻሕፍት በካምብሪጅ ዩኒቨርሲቲ በመጻሕፍት ቤት ይገኛሉ፡፡

ከዚህም በቀር ለኢትዮጵያ ልጆች መመሪያ እንዲሆን ትምህርት ቤት ሠርተዋል፡፡ ስለዚህ ትልቁን የኢትዮጵያ መንግሥት አልጋ ወራሽና እንደራሴ ከጥንት ዘር የመጡትን የኢትዮጵያን ተስፋ ተፈሪ መኮንንን እናስተዋውቃችኋለን” ብሎ ጨረሰ፡፡ የልዑል አልጋ ወራሽ ተፈሪ መኮንን መልስ

ክቡር ሆይ

ለልዩ ልዩ ሕዝብ የዕውቀትና የጥበብ ምንጭ የሚመነጭበትን የካምብሪጅን ዩኒቨርሲቲ በማየቴ እጅግ ደስ ብሎኛል፡፡

እናንተም በታላቅ ደስታና በልብ ፍቅር አክብራችሁ ስለተቀበላችሁኝ አመሰግናችኋለሁ፡፡

ይልቁንም ደግሞ የኢትዮጵያን ነፃነትና የኢትዮትያን ክርስቲያንነት ከብዙ ዘመን አስቀድሞ መሆኑን አስረድታችሁ ታሪኳን በመናገራችሁ ደስታዬ ከልክ ያለፈ ሆነ፡፡

የኢትዮጵያ መንግሥት በጣም ቀደምትነት እንዳላትና ከተመሠረተች ረዥም ዘመን እንደሆነ የማያውቁ ምናልባት አንዳንድ ሰዎች ይኖራሉ፡ ነገር ግን ታሪኳን በጣም ቢመለከቱ ከግብጻውያንና ከሮማውያንም አስቀድማ ፀንታ የኖረች መሆኗን ለመረዳት ይችሉ ነበር፡፡ በዳዊትና በሰሎሞን ዘመን እንኳ በጣም የታወቀች መንግሥት ነበረች፡፡

ነገር ግን በዘመን ብዛትና በመንገድ ርቀት እስካሁን ከአውሮጳ መንግሥቶች ጋራ በጣም ሳትቃረብ በመቆየቷ እጅግ እናዝናለን፡፡

አሁን ግን በእግዚአብሔር ፈቃድ ጥቂት በጥቂት እያለች ለመቃረብና ለመገናኘት ደረሰች፡፡ ባለፈውም ዓመት ወደ መንግሥታት ማህበር ስለገባች በጣም ለመቃረብ እንደተመቻት ያስረዳል፡፡

ደግሞ የኢትዮጵያን ልጆች በአውሮጳና በሌሎችም ስፍራዎች ለትምህርት ስለ ሰደድናቸው እነርሱም ለትምህርታቸው በጣም ስለተጉ ከጥቂቶች ዘመናት በኋላ የዩኒቨርሲቲ ትምህርት ለመማር ወደ ካምብሪጅ እንዲመጡና ወደ ሀገራቸው ተመልሰው መንግሥታቸውን እንዲያገለግሉ በሙሉ ተስፋ አደርጋለሁ ብለው ጨረሱ፡፡

 

Read 59224 times Last modified on Friday, 05 October 2012 13:43