Print this page
Saturday, 09 October 2021 00:00

"የመንገድ ጠራጊነት" ሚና ከሁሉም ይጠበቃል

Written by  አያሌው አስረስ
Rate this item
(0 votes)

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ ሃያ ሁለት ሚኒስትሮችን በመሾምና ካቢኒያቸውን በማቋቋም አዲሱን የአምስት ዓመት የስልጣን ዘመናቸውን ጀምረዋል፡፡ ባለፉት ሶስት ዓመታት የስልጣን ዘመናቸው የተሰሩ ስህተቶች የማይደገሙበት፣ እንደ ተመኙትም በሃገራችን ኢትዮጵያ አዲስ የታሪክ ምዕራፍ የሚከፈትበትና የሚቀጥልበት እንዲሆንላቸው ከልብ እመኛለሁ፡፡
ተሿሚ ሚኒስትሮች ሌብነትንና ልመናን የሚጠየፉ፣ የተሰጣቸው ሥልጣን የተቀመጡበት ወንበር የመላው የኢትዮጵያ ሕዝብ መሆኑን የሚረዱ፣ ቦታው በሕዝብና በአገር ውክልና  የሚገኝ እንጂ በኮታ አለመሆኑን እንዲገነዘቡ አሳስበዋል። ከተፎካካሪ ፓርቲዎች መካከል በካቢኔ አባልነት የተካተቱ አመራሮችም፣ ተቋም መምራትና መቃወም ለየቅል እንደሆኑ ተገንዝበው፣ በተቋም መሪነት የተሰጣቸውን ኃላፊነት በተገቢው መንገድ በመወጣት፣ የመንገድ ጠራጊነት ሚና  እንዲወጡ ጠ/ሚኒስትሩ አሳስበዋል፡፡
“መንገድ ጠራጊዎች” የሚለው ንግግራቸው፣ መንገዱ ላይ ምን አለ? ምኑ ነው የሚጠረገው? እንዴትስ ነው የሚጠረገው? የሚሉ ተከታታይ ጥያቄዎችን የሚቀሰቅስ ሆኖ አግኝቼዋለሁ፡፡ በፌደራል በሚኒስትርነት፣ በክልል ደግሞ በቢሮ ኃላፊነት ስልጣን የተሰጣቸው የተፎካካሪ ፓርቲ አባላት፣ ወደ ሥራው የሚገቡት አንድ ነፍሳቸው፣ እውቀታቸውንና የስራ ልምዳቸውን  ይዘው ነው፡፡
ተሿሚዎች ራሳቸውን ለስራ አዘጋጅተው መግባት ላይከብዳቸው ወይም ላያስቸግራቸው ይችላል፡፡ የሚጠብቃቸው የስራ አካባቢ ግን በጥብቅ ሊታሰብበት ይገባል፡፡ የእነሱንም የጠቅላይ ሚኒስትሩንም ድካም ከንቱ ላለማድረግ፡፡
ነገር ከስሩ ውኃ ከጥሩ ይላሉ አበው፡፡ በንጉስ ዘመን የነበረው ቢሮ፣ አንዳንዱ ዘሩን ቆጥሮ የሚሾምበት ቢሆንም፣ የሚበዛው በስራውና በአገልግሎቱ ለሹመትና ለሽልማት የሚበቃበት ነበር፡፡ ከሲቪል፣ ፀሐፊ ትእዛዝ ወልደ ጊዮርጊስ ወልደ ዮሐንስን፣ ከወታደር ደግሞ ጄኔራል መንግስቱ ነዋይን መጥቀስ ይቻላል፡፡
ደርግ የንጉሱን መንግስት ከስልጣን አውርዶ መንግስት በሆነ ጊዜ፣ በየቦታው የለውጥ ሐዋርያና ቋሚ ተጠሪ እያለ የመደባቸው ሰዎች ለእሱ የታመኑ፣ በየቢሮው ላይ የበላይነት ያላቸው ነበሩ። ሁሉም ነገር በእነሱ ሥር እንዲያልፍ ማድረግ የግድ ነበር፡፡ ኢሠፓን ለመመስረት መንገድና ድልድይ የሆነው ኢሠፓኮ ደግሞ በየመሥሪያ ቤቱ ያሉ የመንግስት ሠራተኞች፣ ወደውም ይሁን ተገደው የአዲሱ ፓርቲ አባል እንዲሆኑ ማድረግን ሥራዬ ብሎ ተያያዘው። የመንግስት የአስተዳደር መዋቅር ሙሉ በሙሉ በኢሠፓ እጅ ወደቀ፡፡ መንግስትና ፓርቲ ቢያቃኑም ቢዘቀዘቁም አንድ ሆኑ፡፡
ይህ አሰራር በዘመነ ወያኔ ኢሕአዴግም ቀጠለ፡፡ በደርግ መስፈርት የነበረው የማርክሲስት ሌኒኒስት ርዕዮተ ዓለም ቀርቶ ዘርና ቋንቋ መስፈርት ሆነ፡፡ በየደረጃው ለሃላፊነት የሚበቁ ሰዎች ወደ ቦታው የሚሳቡት  በኮታ ብሔረሰባቸው እየተመዘዘ ሆኖ አረፈው፡፡ እንዲያም ሆኖ የአንድ ብሔር ወይም ፓርቲ ማለትም ህወኃት የበላይነት ጎልቶ እንዲታይ ተደረገ፡፡ የመምሪያው ሃላፊነት ቢያመልጣቸው ምክትልነቱ፣ እሱም ካልሆነ ፀሐፊነቱ ትሕነጎች በእጃቸው እንዲገባ ሲያደርጉ ኖሩ፡፡ አሁን ያለው የስልጣን ድልድይ ከዚህ አይነቱ አሠራር የተለየ ነው ብሎ ለመናገር የሚያስችል ሁኔታ ላይ አይደለንም፡፡ የተከበሩ አቶ ክርስቲያን ታደለ፤ “መቼ ነው በሞያ ሥነ ምግባር የሚመራ ቢሮ አስተዳደር የምናቆመው ወይም የምንመሰርተው?” ሲሉ ለጠ/ሚኒስትሩ ያቀረቡት ጥያቄ፣ ጆሮአችን ላይ ደጋግሞ የሚያቃጭለው ለዚህ ይመስለኛል፡፡ ስለዚህ የመንግስትና የተቀናቃኝ ፓርቲዎች አብሮ መስራት ለአገር የሚጠቅም ፍሬ ያፈራ ዘንድ መንገድ የመጥረጉ ሥራ ለተቀናቃኝ ፓርቲዎች ብቻ የሚተው ሳይሆን የገዢው ፓርቲም ኃላፊነት መሆኑ ሊሰመርበት ይገባል፡፡ በየመሥሪያ ቤቱ ያሉ የበታች ተሿሚዎች፣ ከአዲሶቹ ተሿሚዎች ጋር በትብብርና በቅንነት  በመስራት ትጋታቸውንና ዝግጅታቸውን ማሳየት አለባቸው፡፡ በጀርባ ውይይት ተደርጎ ያለቀላቸውን አጀንዳዎች አቅርቦ ከማስወሰን ይልቅ፣ በጥሬ አጀንዳዎች ላይ ለመወያየት ለመከራከርና ለመወሰን የተዘጋጀ የስራ ባልደረባ ሊኖረው ይገባል። ይሄኔ መንገዱ በአንድ ክንድ ሳይሆን በሁለት ክንድ ይጠረጋል፡፡ ሠራተኛው ለድርጅት ታማኝነት ሳይሆን ለሙያ ብቃት ልብ ይሰጣል፡፡ ከድርጅት በላይ ለሙያው ታማኝነት ይኖረዋል፡፡
በነገራችን ላይ #ሌብነትንና ልመናን መጠየፍ፤ ከብሔር ይልቅ መላው የኢትዮጵያ ህዝብን በእኩል ማገልገል; የሚለው የጠ/ሚኒስትሩ ማሳሰቢያ፣ ለተወካዮች ምክር ቤት አባላትም ይደርሳቸዋል ብዬ አምናለሁ።


Read 1223 times