Tuesday, 12 October 2021 00:00

መነጠል እና መጀመል (crowd and solitude)

Written by  ያዕቆብ ብርሃኑ
Rate this item
(3 votes)

 ... ይልቅ አንድ ታሪክ ልንገርህ፡፡
እ.ኤ.አ በ1750ዎቹ በለንደን ከተማ ጎዳናዎች የሆነ የሚያስገርም ሰው ብቅ አለ። ስሙ ጆናስ ሀንወይ (1712-1786) ይባላል። የሆነ ቀን ከጨርቅና ከቆዳ ቀጣጥሎ የሰራውን ዘባተሎ ግዙፍ ጃንጥላውን ይዞ ብቅ ሲል ‹ምን ጉድ ነው?› በሚል ስሜት ሰዎች ተከተሉት፡፡ ጃንጥላውን ይዞ በወጣ ቁጥር አንድ ገበያ ህዝብ ያጅበው ጀመር፡፡ ምናልባት የሚሸነቁጥ የሚያዋርድ ስድብም ይከተለው ይሆናል፡፡ ለሰላሳ ዓመታት ይሄው ምቾት የሚነሳ አጅብ አልቀረለትም፡፡ እነሆ ዛሬ በአሜሪካ ብቻ በዓመት 33 ሚሊዮን ጃንጥላዎች ይሸጣሉ፡፡ 365 ሚሊዮን ዶላር አካባቢ ለግብይቱ ይውላል፡፡ ከእኛም ሀገር የመከላከያ በጀት ጋር እንደሚወዳደር ልብ በሉልኝ፡፡ በዘመናዊው ዓለም በዓለማቀፍ ደረጃ እስከ 90 በመቶ የሚሆኑት ሴቶች ጃንጥላ ተጠቃሚዎች እንደሆኑ ይገመታል። ዛሬ ጃንጥላዎች ከዝናብና ሀሩር መከላከያነታቸው በተጨማሪ የውበት፣ የፋሽን መሳሪያዎች ሆነው ያገለግላሉ፡፡
ሌላም ነገረ ሀቲታችንን የሚያሰፋ ተረክ እነሆ...
በስብሐትኛ- አቦ ተውና፣ ያኔ ዓመተምህረት አልነበረም፡፡ ብቻ በአስራ ስምንተኛው ክፍለ ዘመን አንድ ቀን፣ የሙዚቃው ጠቢብ ቪትሆቨንናና ወልፍጋንግ ገተ በእግር እየተንሸራሸሩ ሳለ ድንገት አንድ መስፍን በመንገዳቸው ላይ እስከ አጃቢዎቹ መጣ፡፡ ገተ መንገድ ለቆ ሲሽቆጠቆጥ፣ ቪትሆቨን ግን ከመንገዱ ንቅንቅ አላለም፡፡ መስፍኑ ለምን መንገድ እንደማይለቅ ቪትሆቨንን በጠየቀውም ጊዜ አለ...
‹‹ልዑል ሆይ፤ አንተ ልዑልነትን የተቀዳጀኸው በመወለድ ብቻ ነው፡፡ አዕላፍት ልዑላን ነበሩ፡፡ ሌሎች ሺዎች ልዑላን ወደፊት ይኖራሉ፡፡ ነገር ግን አንድ ቪትሆቨን ብቻ...›› ቪትሆቨን፣ ቪትሆቨንን ለመሆን ግን አርባ ዓመታት ፈጅቶበታል። የመስማት ችሎታውን አጥቷል፡፡ ይህ በሞዛርት አንደበት ሳይቀር አድናቆት የዘነበለት የረቂቅ ሙዚቃ (classical music) ጠቢብ ቪትሆቨን፣ በዕድሜ ዘመኑ አጋማሽ ቀስ በቀስ መስማት አቆመ፡፡ ነገሩ እጅግ አስደንጋጭ ሆነበት፡፡ ራሱን እስኪጠላ ድረስ ተረበሸ፡፡ በዝናብ ውስጥ ለረጃጅም ሰዓታት ጠዓረ ሞት መስሎ ተመላለሰ። ተቅበጠበጠ። ራሱን ለማጥፋት ዳዳው። መስማት ያቆመ ሰሞን ራሱን ለማጥፋት አቅዶ ለወንድሞቹ ጽፎት የነበረው የስንብት ደብዳቤ፣ ከሞተ በኋላ በቤቱ ተገኝቷል፡፡ ጥቂት እንቀንጭብ...
‹‹My misfortune is doubly severe from causing me to be misunderstood. No longer can I enjoy recreation in social intercourse, refined conversation, or mutual outpourings of thought. Completely isolated, I only enter society when compelled to do so. I must live like an exile. In company I am assailed by the most painful apprehensions, from the dread of being exposed to the risk of my condition being observed… What humiliation when any one beside me heard a flute in the far distance, while I heard nothing, or when others heard a shepherd singing, and I still heard nothing! Such things brought me to the verge of desperation, and well-nigh caused me to put an end to my life. Art! art alone, deterred me. Ah! how could I possibly quit the world before bringing forth all that I felt it was my vocation to produce?››
… በመጨረሻ አዲሱን ማንነቱን ለመቀበል ተገደደ፡፡ ከዓለም ተገለለ። ተነጠለ፤ የሌለ ያህል ተረሳ፡፡ ራሱን ሙዚቃዊ ፈጠራዎቹ ውስጥ ቀብሮ እሱ የማይሰማውን የረቂቅ ሙዚቃ ጥዑም ውህድ ማርቀቁን ተያያዘው። አስደናቂዎቹን ፈጠራዎቹን የሰራው መስማት ካቆመ በኋላ ነበር፡፡ የተጋፈጠው ፈተና ግን የምንጊዜም ምርጥ የረቂቅ ሙዚቃ (classical music) ሰዎች ተርታ ከመመደብ አላገደውም፡፡ ከገጠመው መራር ዕጣ ጋር ተናንቆ እንዴት የሕይወት መንገዱን እንደቀየረ ሲናገር፤ ‹‹ዕጣ ፋንታዬን ጉሮሮው ላይ ፈጠረቅሁት›› ብሏል። ዛሬ ትውልድ በየዕለቱ በስራዎቹ እየተደነቀ የዓለምን መልክ ከቀየሩ መቶ ሰዎች መሃል ደምሮ ያስታውሰዋል፡፡
ስሙን ለማስታወስ የተቸገርኩት አንድ ሰው ሳነበው የገረመኝ አንድ ሀሳብ አለው፡፡ በአንድ ዐረፍተ ነገር ብቻ ሲቀርብ ‹‹human mind is a gigantic duplicating machine›› ዘመኑን በሚሊዮንም ስፈረው በሺህ የሰው ልጅ ከአደን ዘመን ጀምሮ ያሳየው የኑረት ዘይቤ መሻሻል በጣም ጥቂት ነው፡፡ ብዙው ሰው ኢምንት ሳያበረክት በስህተት እንደተጠራ ተጀምሎ ሲቆጠር ኖሮ ነው የሚያልፈው፡፡ ሱሪያሊቱ (ገሃድ ዘለል ይለዋል ነቢይ መኮንን) ሰዓሊ ሳልቫዶር ዳሊ፤ ‹‹የሴትን ልጅ ውበት ከአበባ ጋር ያመሳሰለው የመጀመሪያው ሰው እሱ ፈላስፋ ነው፡፡ የደገመው ግን ደደብ ነው።›› ይላል። አልበርት ካሙም በካሊጉላ አንደበት፤ ‹‹አያትህን መብለጥ ካልቻልክ አስቀድሞውኑ ሞተህ መቀበር ነበረብህ።›› የሚል ግልምጫ ሰንዝሯል፡፡ ብዙ ሰው በኑረት ለዛው እንደ ተፈጥሮ ስህተት የሚቆጠር ምንም ነው፡፡ የአያቱን ዳዊት የሚደግም የአባቱን ሙታንታ የሚታጠቅ ስርዝ ድልዝ ነገር፡፡ ይሄን ጽሁፍ የማንበብ ተነሳሽነቱ ያለህ አንተ፣ ይሄን ይሄን እንደ ስህተት መቆጠርን የምትጸየፍ ይመስለኛል፡፡
አየህ ዛሬ እኛ የምንኖርበትን ንቅሳታም ዘመናዊ ዓለም የገነቡት ነጠል ብለው መቆም የቻሉ፣ ሌላ ዓይነት የሕይወት ቅኝት የነበራቸው ጥቂት ሰዎች ናቸው። ዛሬ ያለውን ዘመናዊ ስልጡን ዓለም አንድ በአንድ የቀረጹት ሕይወትን በተለየ እንግዳ ዓይን የታዘቡት፣ ከተራ ምልከታ ተነስተው ነባሩን ዘልማዳዊ ዓለም የሚቀይር ሀሳብ ያረቀቁት ነበሩ፡፡ ሲግመን ፍሮይድ፣ አርኪመድስ፣ ኒቼ፣ ማርቲን ሉተር፣ ቻርለስ ዳርዊን፣ ጋሊሊዮ፣ ሶቅራጥስ፣ ቡድሃ፣ ቶማስ ኤዲሰን፣ ቫን ጎ፣ የእኛው ሀገር ፈላስፋ ዘርዓያዕቆብ … ሌሎችም ሌሎችም በየስርቻው በየጉራንጉሩ፣ በእኛም ሀገር ጭምር አሉልህ፡፡ አብዛኞቹ በዘመናቸው የተወገዙ ወይ አድማጭ ያጡ ንጡላን ነበሩ። ዛሬ እግርህን በጀብደኝነት አንፈራጠህ ቆመህ ሰልፊ (ራስ በራስ ፎቶ) የምትነሳበትን ስልጣኔ የመሰረቱት ግን እኒሁ ዘመንን የቀደሙ የትናንት መሰሎችህ ነበሩ፡፡
የቫን ጎ’ማ ይለያል፡፡ እንኳን ሲኖር ሲስል ዛፎቹ ሳይቀር ንጡል ሆነው ለምህላ ቅርጫፎቻቸውን ያንጨፈርራሉ። ያጣ የነጣ ድሃ ነበር፡፡ ኑሮውን የገፋው ወንድሙ በሚልክለት ወርሃዊ 100 ፍራንክ ድጎማ ብቻ... እሱም ብዙ ጊዜ በሰዓቱ አይደርስለትም። ዘመኑን እንደ ስደተኛ ወፍ እየበረገገ ተወጣት፡፡ የመጨረሻዎቹን ስምንት ወራት ባሳለፈባት የፈረንሳይ ገጠራማ መንደር ጥቂት ሳምንታት አብሮት ከተሰለፈው ጋውጊን ሌላ አንድም ጓደኛ አልነበረው፡፡ በህዝቡ ዘንድ የተገለለ እንደ እብድ የሚቆጠር ነበር፡፡ ይህ ብቸኛ ወዳጁ ጋውጊን ለተሻለ ጥበባዊ መደነቅ ወደ ታይቲ ለመሄድ ሲነሳ ወፈፍ አደረገው። አጓጉል ተጫወተ፡፡ ጀሮውን ሸለተ፡፡ ዛሬ ለትውልዶች ሁሉ በአንድ እጅ ጣቶች ከሚቆጠሩ ጥቂት አስደናቂ ጠቢባን ቀዳሚው እሱ ነው፡፡
ሌላ አንድ ታሪክ ልጥቀስልህ... ፈላስፋው ቤኔዲክት ደ ስፒኖዛ ገና በወጣትነት ዕድሜው ከሆላንድ የአይሁድ ማኅበረሰብ የገጠመው ተቃውሞ እጅጉን የሚያስደነግጥ ሆነ፡፡ ስፒኖዛ ‹ኢቲክስ› በተሰኘ መጽሐፉ ላይ እንዳሰፈረው፤ ከአብርሃም ዘመን ጀምሮ የተደነገገው ከአይሁዳዊያኑ አስተሳሰብ ፍጹም ያፈነገጠ ሀይማኖታዊ አረዳድ ነበረው፡፡ ልቀንጭብልህ... ‹‹It is a category mistake to think of God in normative or value terms. What God is Nature itself—the infinite, eternal, and necessarily existing substance of the universe.››
ነገር ግን ገና ሀሳቦቹ እንኳን በቅጡ አድማጭ አግኝተው እንደ ጠያቂ ሳይጎላ በፊት የደች አይሁዳዊያን ማኅበረሰብ ከፍተኛ ውግዘት አዘነቡበት፡፡ በምኩራብ ተሰባስበው በሰው ልጆች ታሪክ እጅግ ከባዱን የመነጠል ውሳኔ አሰሙ፡፡ ተወገዘ፤ ፍጹም ተገለለ፡፡ ‹‹መቼም የትም ሲቆም ሲቀመጥ፣ ሲነሳም ሆነ ሲተኛ፣ ሲሄድም ሆነ ሲመጣ የተረገመ ይሁን፡፡ ማንም ከእርሱ ጋር በአንድ ቤት ጣሪያ ስር ለአፍታ እንኳን እንዳይሆን፡፡ ማንም ከእርሱ ጋር በቃል፣ በጥቅሻም ሆነ በጽሁፍ አይነጋገር፡፡ በቅዱሳቱ መጻሕፍት ላይ የተጻፈው መርገምት ሁሉ ይስፈርበት...››
‹‹If one is different, one is bound to be lonely›› የሚለው የእንግሊዛዊው ፈላስፋ Aldous Leonard Huxley አባባል ለስፒኖዛ በትክክል ይሰራል፡፡ ስፒኖዛ የሚደግፈውም ሆነ ስራ የሚሰጠው ስላጣ በአደገኛው የመስታውት ጥሬ ዕቃ ማድቀቅና ጽዳት ሥራ ላይ ለዓመታት ለመስራት ተገደደ፡፡ በመፍጨት በማድቀቁ ሂደት የሚፈጠረው ብናኝ ተጠራቅሞ ሳንባውን ስለጎዳው ገና በጎልማሳነቱ ለሕልፈት ዳርጎታል፡፡ ቢሆንም ይህን ለመሰለው የሚያብረከርክ ውግዘት ሸብረክ ሳይል ቀጥሎ የተሃድሶውን ዘመን ከመሩ አሳቢያን መካከል ተመድቧል። ከእርሱ በኋላ በተነሱ ጥቂት የማይባሉ ፈላስፎችና ጸሐፍት ላይም ተጽዕኖውን አሳርፏል፡፡
እኔ እንኳን እንደ አቅሚቲ ገና ከጅምሩ የዚህ ገፈት ቀማሽ ሆኜ በሕይወት አጋጣሚ በሕይወት መበርገጌን ብቻ ታቅፌ እንደ አምባሣደር ብርሃኑ ድንቄ ‹‹ብቻዬን ቆሜያለሁ!›› ማለት ከጅሎኛል። አምባሳደር ብርሃኑ፣ የንገሱን አገዛዝ ተቃውመው ራሳቸውን ከማግለላቸው በፊት በአሜሪካ የኢትዮጵያ አምባሳደር ነበሩ፡፡ አጀባቸው እልፍ ነው፡፡ ወዳጆቻው እንኳን ዲፕሎማቶች፣ የሀገራት መሪዎች፣ ታላላቅ ሰባኪያን፣ ጋዜጠኞች ነበሩ፡፡ ራሳቸውን ካገለሉ ጀምሮ ግን ሁሉም ለንጉሱ ቀና አስተሳሰብ በነበረው በአሜሪካ መንግስት መጠቆርን ሽሽት ገለል አደረጓቸው። አምባሣደሩም ከንጉሡ ጋር በፈጠሩት ውርክብ በዙሪያቸው የነበሩ ሁሉም ሰዎች ሲሸሹ፣ ከፍተኛ ብቸኝነትና የመፍራት ድንጋጤ ውስጥ ተዘፈቁ፡፡ I Stand alone በተሰኘች ሚጢጢ መጽሐፋቸው ላይ እንዲህ ይላሉ…
‹‹ለእኔ ጓደኛ ማለት ጓደኛ ነው። ያሉኝን ጓደኞች ማጣት ወይም አዲስ ጓደኛ ማፍራት አልፈልግም፡፡ አንዳንዴ ምነው ለጓደኝነት ደንታ ባልሰጠኝ እላለሁ፡፡ ሆኖም ግን በብቸኝነት ለመኖር እየጣርኩ እንኳን ያለጓደኛ መኖር አልሆነልኝም።  [...] አንድ ጊዜ የዋሽንግተንን መጥፎ ስሜት ለማምለጥ ወደ ኒውዮርክ ከተማ ሄድኩ። እዚያም አንድ ሆቴል ገባሁ፡፡ ብቸኝነት በጣም ስለተሰማኝ ካገኘሁት ሰው ጋር በማንኛውም አርዕስት ላይ መነጋገር ፈለኩ። ግን ከማን ጋር አወራለሁ? ሆቴል ውስጥ ከነበሩት ሰዎች ዞር ብሎ እንኳን ያየኝ ሰው አልነበረም፡፡ ወዲያው ከሆቴል ወጥቼ ወደ ባቡር ጣቢያ አመራሁ፡፡ በዚያ ሠዓት ሰዎች ከስራ ወደ ቤት ለመመለስ ይጣደፉ ነበር። እኔም ከሰው ጋር ተቀላቅዬ ቶሎ ቶሎ መራመድ ጀመርኩ። ወደ የት እንደሚሄድ ሳላውቅ በጣም የተጠቀጠቀ አንድ ባቡር ውስጥ ገባሁ፡፡
ሰው እርስ በእርሱ ይጋፋል፤ ይተያያል፤ ቃል የሚተነፍስ አንድም ሰው ግን አልነበረም። ከሰው ጋር መቀላቀሌ ለጊዜው ደስታ ሰጠኝ። ባቡሩ ውስጥ ያሉት ሰዎች ማየት እንጂ መናገርና መስማት የማይችሉ መስለው ታዩኝ፡፡ ስንተያይ ‹እወድሃለሁ፤ እወድሻለሁ፤ እጠላሻለሁ፤ እጠላሃለሁ ወይም የራስሽ፣ የራስህ ጉዳይ› የሚል ስሜት በገጻቸው የሚነበብ ይመስላል፡፡ ይህም ግንኙነት ነው፡፡ ለጊዜው ብቸኝነቴን አስረስቶኛል፡፡››  
ይህ ዓይነቱ ብቻነት በእርግጥም መነጠል (isolate) መሆን አለበት፡፡ እኔ ከአምባሳደር ብርሃኑ ድንቄ ሳልለይ አልቀርም፡፡ ምንም ነገር፣ ጠብ እንኳን ቢሆን ሚስቲክ የሆነ፣ የተሻገረ፣ ከቶውንም በሌሎች ያልታሰበ ሌላ ጣዕም እንዲኖረው እፈልጋለሁ፡፡ የምንኖረው ግን በጅምላ በሚመለክበት፣ በጅምላ በሚወገዝበት፣ በጅምላ በሚኮነንበት፣ ሽያጩም፣ ዘረፋውም፣ ግድያውም፣ ቀብሩም ጅምላ ሆኖ ተነጥሎ መቆም ወንጀል በሆነበት ማኅበረሰብ ውስጥ ነው። እናስ በዚህ ሂደት ከመንጋው የመነጠል፣ ከዘመን የመጣላት፣ ከትውልድ የመኳረፍ አዝማሚያ የሌለው ጠቢብ፣ የመንጋውን መፈክር በውብ ቃላት ሸላልሞ ከማተም በስተቀር ረብ ያለው ሀቲት ሊወጣው ይችላል? የምንኖረውን የሆነውን ለመፃፍ፣ ለመዝፈን፣ ለማቅለም፣ ለማሰማመር ብዙ መጣር አርቲስት መሆን ያስፈልጋል እንዴ?  በየትኛውም ዘመን ተወለድ (በእኛም ዘመን ይሁን) ብዙዎች ከሚስማሙበት ከተለየህ፣ ብዙዎች የሚያደንቁት ካልመሰጠህ፣ ብዙዎች በጅምላ የሚጠሉትን ካልጠላህ ውግዘት ውርደት፣ ግዞት... ይደርስብሃል። ምክኒያቱም አንተ የሚቀጥለው ትውልድ አባል ነህ፡፡
የእኛን ነገር እንኳን ተውት፣ ተውት፡፡ አዲስ አተያይ ማመንጨቱን፣ የሚቀጥለውን ትውልድ ትልም የማርቀቅ ቅብጠቱን ተውት፣... ተውት፡፡ እኛ ከዘመንና ከትውልድ መኳረፍ ያቃተን፣ ዘልማዳዊ የነተበ ሕይወት የማይሰለቸን፣ አንሰን አንሰን የምናሳንስ፣ በአጥንት እንደሚጣሉ የተራቡ ውሾች እርስ በእርስ የምንናከስ ህዝቦች ነን፡፡  ለብቻ መቆም መቻል ግን ውበት ነው እህቴ፡፡ ፅናት ነው፡፡ ጥንካሬ ነው፡፡ ለብቻ መቆም (solitude) መሟላት እንጂ መነጠል (isolate) አይደለም፡፡ መነጠል ብሎ ነገር የለም፡፡ የምትነጠለው ጉልህ ሰብዕና አጥተህ ተጀምለህ የተቆጠርክ ዕለት ነው፡፡ እንደ ጉሬዛ ከዛፍ ዛፍ እየዘለልክ ብትኖር እንኳን ከሰው እንጂ ከምልዓተ ዓለሙ መነጠል አትችልም፡፡ ማንም ሁን ከየትም ና፣ አንተ የምልዓተ ዓለሙ የልብ ትርታ ነህ። አንተ አንተን መሆን ከቻልክ ያለ አንተ ዓለሙ ይጎድላል፡፡
ተደርቦ ተጀምሎ መቆጠርን ተፀየፍ።  በሰብዕናህ ራስህን ችለህ ስትር ብለህ መቆምን ቻልበት፡፡ ሰዎችን በሙሉ ልብህ ተቀበል። ለመሸኘትም ግን ምንጊዜም ዝግጁ ሁን፡፡ በጊዜ ውስጥ አስቀድሞ ያልሆነ ምንም ነገር የለም፡፡ መወለድህም፣ መሸለም መጋዝም በጊዜ ውስጥ ቀድሞውኑ የታሰበ ነው፡፡ ይሄንን ማሰብ መቀበል ስለማትፈልግ ዘወትር ለእያንዳንዷ የሕይወት እርምጃ እንግዳ ትሆናለህ፡፡ ቀላል እንዳልሆነ አውቃለሁ፡፡ ይሄንን የምነግርህ እኔ እንኳን ዘወትር እንደ ተማሪ ነኝ፡፡ ከሰው ልትደበቅ ትችላለህ፡፡ ማንም ግን ከራሱ መደበቅ አይችልም፡፡ በራስህ ምላስ መቅመስ ካልቻልክ አንተ ጣዕምን አታውቃትም፡፡ ብቻህን መቆም ከቻልክ አንተ ነፃ ወጥተሃል፣ ክንፎችህን ሰርተሃል፡፡ ነፃ በወጣህ ጊዜ ሕይወትን በምልዓት ትኖራታለህ፡፡ ሁልጊዜ ከራሳቸው መታረቅ ተስኗቸው ቀላሉን መንገድ በመሻት እንደሚማስኑ ደካሞች አትሆንም::
ግለሰቦች ሲሳሳቱ ስህተቱ ከራሳቸው ወይም በጣም ከጥቂቶች የተሻገረ ጥፋትን አያስከትልም፡፡ መንጋው ከተሳሳተ ግን አያድርስ ነው፡፡ የመንጋው፣ የጅምላው ስህተት የሚያደርሰውን የጥፋት መጠን ለማወቅ ሩዋንዳን መጥቀሱ ብቻ ይበቃል። መንጋው እንዲያውም ልክ ሆኖ አያውቅም ማለት ይቻላል፡፡ አንተ የዚህ የጅምላ ስህተት አካል መሆንን ተጸየፍ። አስቀድሜ እንዳወጋሁህ ዛሬ ዘመናዊው ዓለም የደረሰበትን የኑረት ቅኝት የቀረጹት ሺህ እንኳን የማይሞሉ በራሳቸው መሻት ወይም በመንጋው ግፊት ተገልለው ማሰብ የቻሉ ጥቂቶች ናቸው፡፡ ሌላው ግብስብሱ ለድምቀት ለጭብጫባ ብቻ የሚፈለግ የቤተ-ሙከራ አይጥ ሆኖ አልፏል፡፡ ያልፍማል፡፡ አንተም በፊናህ ጥቂት ስንኝ ቋጥረህ በብዙ የምታቧትር፣ በርካታ ‹የግል አድናቂዎችን› ቤት ለቤት እየዞርክ ለመፍጠር የምትማስን ሆነህ ባየሁ ጊዜ ግን አዘንኩልህ።
አንተ እኮ አንተ ነህ፡፡ በሠዎች መካከል ስትሆን ደቃቅ አሸዋ ላይ እንደወደቀች አንዲት የጤፍ ዘር ታንሣለህ፡፡ ምርጫህ በሌሎች ምርጫ ይወሰናል፡፡ ድምጽህ በሌሎች ጩኸት ይሸፈናል፡፡ ቁጣህ በሌሎች ግድየለሾች ፌዝ ይከለላል፡፡ ሕማም፣ ሕመምህ በሌሎች ለዛየለሾች ሁካታ ይጨፈለቃል…
ግለሰባዊነት ይለምልም!
ከአዘጋጁ፡- ጸሐፊውን በኢ-ሜይል አድራሻቸው፡- This email address is being protected from spambots. You need JavaScript enabled to view it. ማግኘት ይችላሉ፡፡


Read 10331 times