Print this page
Monday, 11 October 2021 09:00

ተፎካካሪ ፓርቲዎች - ስለ ጠ/ሚኒስትሩ የካቢኔ ሹመት

Written by 
Rate this item
(0 votes)

 “ተቃዋሚዎች በካቢኔው መካተታቸው ጥቅም የለውም”
        (አቶ ሙላቱ ገመቹ፤ የኦፌኮ ም/ሊቀመንበር)


“አዲሱ የመንግስት አካሄ የሚበረታታ ነው
   (ዶ/ር ሰይፈስላሴ አያሌው፤ የእናት ፓርቲ ም/ሊቀመንበር)

 መስከረም 24 ቀን 2014 ዓ.ም የተቋቋመው የፌደራል መንግስት፤ ዶ/ር ዐቢይ አህመድን በጠቅላይ ሚኒስትርነት የሰየመ ሲሆን አቶ ታገሰ ጫፎ አፈጉባኤ፣ ወ/ሮ ሎሚ ቢዶ፣ ምክትል አፈ ጉባኤ ወ/ሮ ሎሚ ባዶ ምክትል አፈጉባኤ ሆነው ተመርጠዋል። የመንግስት ምስረታውን ተከትሎም፣ በጠ/ሚኒስትርነት የተሰየሙት ዶ/ር ዐቢይ አህመድ፣ አብረውኝ ቢሰሩ የተሻለ ያግዙኛል፣ ሃገራቸውንም ይጠቅማሉ ብለው ያመኑባቸውን 22 ሚኒስትሮች፣ ባለፈው ረቡዕ መስከረም 26 ቀን 2014 ዓ.ም ለህዝብ ተወካዮች ም/ቤት አቅርበው ሹመታቸውን አጽድቀዋል። ከእነዚህ የካቢኔ አባላት መካከልም ሦስት የተቃዋሚ ፓርቲ መሪዎች የተካተቱ ሲሆን የኢዜማ መሥራችና መሪ ፕ/ር ብርሃኑ ነጋ የትምህርት ሚኒስቴር፣ በሰኔው የአማራ ክልል ምርጫ ከብልጽግና ቀጥሎ ከፍተኛ ድምጽ ያገኘው የአብን ሊቀ መንበር አቶ በለጠ ሞላ፣ የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ  ሚኒስትር እንዲሁም በራሱ የአመራር ውዝግብ በምርጫው ሳይሳተፍ የቀረው ኦነግ ም/ሊቀመንበር አቶ ቀጀላ መርዳሳ፣ የባህልና ስፖርት ሚኒስትር ሆነው ተሹመዋል።
ጠ/ሚኒስትሩ በካቢኔያቸው ውስጥ ዋና ዋና የተቃዋሚ ፓርቲዎች አመራሮችን ማካተታቸው፣ በአዲስ አበባ መስተዳደርና በክልል መንግስታትም ተቃዋሚዎች ሹመት ማግኘታቸውን እንዲሁም አጠቃላይ የመንግስት ምስረታውን አስመልክቶ በምርጫው የተወዳደረው የእናት ፓርቲ ም/ሊቀመንበር ዶ/ር ሰይፈስላሴ አያሌውንና በመንግስት ተገፍቼአለሁ በሚል ራሱን ከምርጫው ያገለለው የኦፌኮ ም/ሊቀ መንበር አቶ ሙላቱ ገመቹን የአዲስ አድማስ ጋዜጠኛ አለማየሁ አንበሴ እንደሚከተለው አነጋግሯቸዋል፡፡ እነሆ፡-
   

      “ተቃዋሚዎች በካቢኔው መካተታቸው ጥቅም የለውም”
        (አቶ ሙላቱ ገመቹ፤ የኦፌኮ ም/ሊቀመንበር)

       የተቃዋሚ ፓርቲ አመራሮች በመንግስት ሥራ አስፈጻሚ ውስጥ መካተታቸው ፋይዳው ምንድን ነው?
ብልፅግና ተመርጫለሁ ብሎ ሲያውጅ፣ ፖሊሲውንና ዓላማውን ለማስፈጸም ወስኖ ነው የሚነሳው።  የራሱን አላማም ማስፈጸም ያለበት ዓላማውን አምነው በተቀበሉ  ሰዎች ነው፡፡ በሌላ በኩል፤ ሹመት አግኝተው የተመደቡ የተቃዋሚ አመራሮችም ሲወዳደሩ የነበሩት፣ ከገዥው ፓርቲ የተለየ አላማ አለን ብለው ነው። ከዚህ አንጻር ለአላማቸው መቆም ይገባቸዋል። በሌላ የፓርቲ አስተሳሰብ ውስጥ ገብተው ያላመኑትን አላማና ራዕይ ማስፈጸም እንዴት እንደሚቻል አይገባኝም። ለምሳሌ የፌደራል አወቃቀሩ እንደዚህ መሆን የለበትም ብሎ ሲሟገት የነበረ ፓርቲ፤ ከክልሎች ጋር እንዴት ነው መስራት የሚችለው?
የሃገሪቱን ፖለቲካ በመግባባትና መተማመን ላይ የተመሰረተ ከማድረግ አንፃር፣ መንግስት አካታች መሆኑ በራሱ ትልቅ ፋይዳ አለው ብለው የሚያምኑ ፖለቲከኞች  አሉ፡፡ እርስዎ ምን ይላሉ?
ብዙም ትርጉም  የለውም። አውራ ፓርቲ ነኝ የሚል ፓርቲን አላማ ከማስፈጸም ውጪ እርባና የለውም። ከዚህ ጥቅም እስካገኘሁ ድረስ አብሬ እሰራለሁ በሚል ዘው ብሎ መግባት ዘላቂ ውጤት አያመጣም። በሰለጠኑ ሃገሮች ለምሳሌ በአሜሪካ፣ ሪፐብሊካን ፓርቲ ሲያሸንፍ፣ ዲሞክራቶቹ ተቃውሞ እያቀረቡ ይቀጥላሉ እንጂ የጎራ መደበላለቅ ብዙም አይታይባቸውም። ምናልባት ጥምር መንግስት ካልሆነ በስተቀር እንደዚህ አይነቱ  አካሄድ ጥቅሙ ብዙም አይታየኝም።
የተቃዋሚዎቹ ሹመት የአካታችነት አሰራርን እንዲሁም አብሮ የመስራት ባህልን ለመለማመድ ጉልህ አስተዋጽኦ እንደሚያበረክት የሚናገሩ ወገኖች አሉ ---
አካታች መንግስት ማለት የሚቻለው ፓርላማው ውስጥ በርከት ያሉ ተቃዋሚዎች ቢኖሩ ነበር፡፡ አሁን እኮ 410 ወንበር ያሸነፈው አንድ ፓርቲ ነው። ስለዚህ መንግስቱ አካታች ነው ማለት አይቻልም።
በሥራ አስፈጻሚ ደረጃ ከተለያዩ የተፎካካሪ ፓርቲዎች የተወከሉ ድርሻ እንዲኖራቸው መደረጉ በራሱ የተመሰረተውን መንግስት አካታች አያደርገውም?
እንዳልኩት አካታች ሊሆን የሚችለው 40 በ60፣ 70 በ30 አይነት የመንግስት አወቃቀር ቢኖር ነበር፡፡ እንዲህ ሲሆን ቢያንስ በጉዳዮች ላይ ተመጣጣኝ ክርክሮች ይካሄዳል ተብሎ ይታሰባል። አሁን ሶስትና አራት ተቃዋሚ አካትቶ፣ ምን ጥቅም እንደሚኖረው ለኔ አይገባኝም። የእነዚህ ሰዎች ተጽዕኖ የትም አይደርስም፡፡ እኔን ከኛ ጋር ስራ ቢሉኝ በጣም እጨነቃለሁ። መስራት አልችልም። ለምሳሌ አንድ ፓርቲ አሁን ያለውን የትምህርት ፖሊሲ መቀየር ይፈልጋል። ዓላማው የራሱን የትምህርት ፖሊሲ በመተግበር ለውጥ ማምጣት ነው። ብልጽግና ደግሞ የራሱ ፖሊሲ አለው። አሁን የትምህርት ሚኒስትር የሆኑት የኢዜማ ተወካይ፣ ፓርቲያቸው፣ የራሱ የትምህርት ፖሊሲ ያለው ነው፡፡ ታዲያ ፕሮፌሰሩ የትኛውን ፖሊሲ ነው የሚተገብሩት? ሌላው አቶ ቀጀላን የባህልና ስፖርት ሚኒስትር አድርገው ሾመዋቸዋል።
እሳቸው አሁን የማንን ፖሊሲ ነው የሚተገብሩት። ለኔ ዋናው አስፈጻሚው ሳይሆን ፓርላማው ነው አካታች መሆን ያለበት። ለምሳሌ የ97ን ምርጫ ተከትሎ የተመሰረተው ፓርላማ፤ በርካታ ተቃዋሚዎችን ያካተተ ነበር። ብዙ የተቃውሞ ድምጾችና ክርክሮች የሚስተጋቡበትም ነበር፡፡ በኢኮኖሚ፣ ማህበራዊና ፖለቲካዊ ጉዳዮች ላይ ጠንካራ ክርክሮች ይካሄዱበታል፡፡ አሁንም ያን አይነት ፓርላማ መፍጠር ነበር የሚሻለው። አስፈጻሚው በጠቅላይ ሚኒስትሩ በጎ ፈቃድ የሚቋቋም ነው። ካልፈለጉ ይሽሩታል። ፓርላማው ግን ህግ አውጪ አካል ነው። በህዝብ ተመርጠው የሚገቡበት በመሆኑ በየትኛውም መንገድ ለመረጣቸው ህዝብ ለህዝብ ናቸው የፓርላማ አባላቱ በህዝብ የተመረጡ በመሆናቸው ጠ/ሚኒስትሩንም ካቢኔያቸውንም በሚገባ ይሞግታል። አሁን ግን ስልጣን ያገኙ አካላት በሾማቸው መንግስት ቁጥጥር ስር ናቸው። በሱ በጎ ፈቃድ ስር ናቸው። የተለየ ሙግት አቀርባለሁ ቢሉ ሊሻሩ ይችላሉ። ስለዚህ ለኔ የተቃዋሚዎች በአስፈጻሚ አካል ውስጥ መካተት ያን ያህል ትርጉም የሚሰጥ አይደለም።

______________________

          “አዲሱ የመንግስት አካሄ የሚበረታታ ነው

   (ዶ/ር ሰይፈስላሴ አያሌው፤ የእናት ፓርቲ ም/ሊቀመንበር)


            አዲስ የተቋቋመው መንግስት ተቃዋሚዎችን በስራ አስፈጻሚ ውስጥ ማካተቱን እንዴት ይመለከቱታል?
በመጀመሪያ አንድ ነገር ግልጽ አድርገን መነሳት አለብን። በአገራችን ህገ መንግስት፣ አብላጫውን ወንበር ያገኘ ፓርቲ፣ መንግስት ይመሰርታል ነው የሚለው። በዚህ መሰረት በተደረገው ምርጫ አሸናፊው የፖለቲካ ፓርቲ ተለይቷል። የኛ እናት ፓርቲም፣ አሸናፊውን ብልጽግና ፓርቲ፣ ባልተለመደ መልኩ እንኳን ደስ አለህ በማለት የደስታ ስሜቱን ገልጿል። በዚሀ መሰረት አሸናፊው ፓርቲ መንግስት መስርቷል። ይሄ መንግስት ደግሞ የአሸናፊው የብልፅግና መንግስት ነው። በዚህ መሃል ግን ከዚህ ቀደም ያልነበረ ለየት ያለ አሰራር ታይቷል፡፡ አሸናፊው ፓርቲ ብቻዬን ከምሆን ሌሎችንም ባካትት ብሎ ተቃዋሚዎችንም በራሱ መስፈርት እያካተተ መሆኑን እየተመለከትን ነው፡፡ ከዚህ በፊት በነበረው አሰራር ወይም ፓርቲ እንዲህ አይነቱ ነገር እምብዛም የተለመደ አይደለም። ከዚህ አንጻር አሁን እየተደረገ ያለው ነገር፣ የአገሪቱን የፖለቲካ ባህል የሰበረ ነው ብለን እናምናለን። ይሄ ባህል መሰበሩን ደግሞ እጅግ የምናደንቀው ነው።
ተቃዋሚዎች በስራ አስፈጻሚው ውስጥ መካተታቸው ብዙም ፋይዳ የለውም፤ በፓርላማው በቁጥር በርከት ብለው ቢገቡ የበለጠ ጠቃሚ ነበር የሚሉ ወገኖች አሉ፡፡ እርስዎ  ምን ይላሉ?
እርግጥ አንድ ነገር ቢሆን ጥሩ ነበር። የምርጫ መደላደሉ ተስተካክሎ፣ የተወካዮች ም/ቤት ስብጥሩ ተመጣጣኝ ቢሆን፣ ማለትም በዛ ያሉ ተፎካካሪዎች የሚሳተፉበት ቢሆን፣ እጅግ በጣም ተመራጭ ይሆን ነበር። አሁን ወደ ኋላ ተመልሰን ይሄ ቢሆን፣ ያ ቢሆን ማለቱ ብዙም አይጠቅምም። ባለው ሁኔታ  ለሃገር የሚበጀውን ማሰብ ነው የሚሻለው። አሁን ያለው ነገር ለኔ ጥሩ ነው። ቢያንስ ተፎካካሪ ፓርቲዎች በምርጫ አሸንፈው ስልጣን መያዝ ባልቻሉበት ሁኔታ፣ ከእኔ የፖለቲካ አመለካከት ውጪ ሌሎችም የፖለቲካ ፓርቲዎች፣ በሃገራቸው ጉዳይ ያገባቸዋል በሚል ተፎካካሪ ፓርቲዎችን በመንግስት ሥልጣን ውስጥ ማካተት ለኔ አንድ እርምጃ ወደፊት ነው፡፡ በጎ ጅምር የሚባል ነው።
ተቃዋሚዎች በስራ አስፈጻሚ ውስጥ መካተታቸው ምን ያህል የሃሳብ ፍጭት ማስተናገድ የሚያስችል ይሆናል?
የሃሳብ ፍጭት ያለበት መንግስት ለመፍጠር አሁን ከተሾሙት ካቢኔ ውስጥ ቢያንስ ሶስት የተቃዋሚ ፓርቲ ሰዎች አሉ። ቁጥሩ አነስተኛ ቢሆንም፣ ካቢኔው ውስጥ የሃሳብ ፍጭት ሊፈጥር ይችላል ብለን መገመት እንችላለን። ከዚህ አኳያ ለሃገርም ለመንግስት ስርአታችንም የተሻለ ነገር ይፈጥራል ብለን እናስባለን። በሌላ በኩል ግን አሸናፊው ፓርቲ የራሱን የፖለቲካ ፕሮግራም ነው ማስፈጸም የሚፈልገው። ስለዚህ በዚህ ካቢኔ ውስጥ የተካተቱ ተፎካካሪዎች ከራሳቸው የፖለቲካ ፕሮግራም ጋር ሊጋጭባቸው እንደሚችል ምንም ጥርጥር የለውም።
ዋናው ነገር፣ ይሄን ልዩነት አስታርቆ ለሃገር በሚበጅ መንገድ ወደፊት መራመድ የሚቻልበትን መላ መፈለግ ላይ መትጋት ነው፡፡ ይሄ በመንግስት አስተዳደር ውስጥ ለተካተቱ የተፎካካሪ አመራሮች፣ የመጀመሪያ የቤት ስራ ይሆናል ማለት ነው። እንደ ፖለቲካ ፓርቲ አመራር የራሳቸውን ማንነት ሳያጡ፣ እንደገና ደግሞ የመንግስትን ፕሮግራም የማስፈጸምን ጥበብ ሊካኑበት ይገባል። በአጠቃላይ ግን በጎ ጅምር ነው ብለን መውሰድ እንችላለን።


Read 1415 times Last modified on Monday, 11 October 2021 09:31
Administrator

Latest from Administrator