Print this page
Monday, 11 October 2021 09:06

ፈተና ቁጥር 1- ማንበብና መፃፍ ይሻላል ወይስ “እውነት፣ የምናብ ፈጠራ ነው” የሚል የትምህርት ቅኝት (ቅዠት)።

Written by  ዮሃንስ ሰ
Rate this item
(0 votes)

 ፈተና ቁጥር 2 - ህልውናና ብልጽግና ወይስ የአካባቢ ጥበቃ?
 ፈተና ቁጥር 3 - ጀምስ ቦንድ፣ ወንድ ይሁን ሴት? ወይስ ሌላ?

እውነትና እውቀት፣ ፈተና ላይ ናቸው።
1. የትምህርት ነገር ግራ የሚያጋባ ሆኗል- ከማግባባት ይልቅ።
የማንበብና የመጻፍ ችሎታ ብርቅ እየሆነ ነው።
በእርግጥ፣ ከመንግስት በጀት ሩብ ያህሉ ለትምህርት ይውላል። የመማሪያ ክፍልና የመጽሐፍ ብዛት በጣም ተሻሽሏል። የአስተማሪ ቁጥርና የትምህርት ደረጃ በጣም ጨምሯል።
ከ10 ዓመት በፊት ባለዲፕሎማ አስተማሪ 10% አይሞላም ነበር - (ከ1ኛ-4ኛ ክፍል)። ዛሬ ከ90% በላይ ባለዲፕሎማ ነው።
ነገር ግን፣ በ10 ዓመታት ውስጥ፣ የተማሪዎች የማንበብና የመጻፍ ድክመት አልተሻሻለም።
አብዛኞቹ የ3ኛ ክፍል ተማሪዎች፣ ቀላል ዓረፍተነገሮችን አንብበው መረዳት አይችሉም። 30% ያህሉ ደግሞ፣ ጨርሶ አንድ ቃል የማንበብ አቅም የላቸውም። (በ10 ዓመት ልዩነት የተካሄዱ ጥናቶች ይህን ያረጋግጣሉ)።
ሕፃናት፣ በአብዛኛው በስድስት ወር ውስጥ፣ ፅሁፍ አንብበው የመረዳት ብቃትን መጨበጥ ይችላሉ። ረዘመ ከተባለም፣ በአንድ ዓመት ውስጥ… ለዚያውም ያለ ብዙ ወጪና ያ ብዙ ውጣ ውረድ። በየኔታ ነበርኮ ኢትዮጵያውያን ንባብ የሚማሩት።
እንዲያውም፣ ከ10 ዓመት በፊት የተደረገው ጥናት፣ “የየኔታ ትምህርትን” በጥሩ ምሳሌነት ጠቅሷል። ፊደል ከማስቆጠር የሚጀምር የንባብና የጽሁፍ ትምህርት ስኬታማ ነው። ውጤታማነቱንም በ”የኔታ” ትምህርት ማየት እንደሚቻል ጥናቱ ጠቁሞ ነበር። ጥያቄው እዚህ ላይ ነው።
ብዙ ገንዘብ የሚወጣባቸው፤ ብዙ ቁሳቁስ የሚጎርፍላቸው ትምህርት ቤቶች፣ ለምን “ከየኔታ” በታች ዘቀጡ
“የንባብና የፅሁፍ ትምህርት፣ ከፊደል መጀመር የለበትም” የሚል አስተሳሰብ፣ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተስፋፋ መምጣቱ ነው ዋናው ችግር። “ንባብና ጽሁፍ፣ ከፊደል ሳይሆን ከቃላትና ከዓረፍተነገር መጀመር አለበት” የሚል ፈሊጥ ተንሰራቷል - “Whole language, whole word” በማለት ይጠሩታል።
ፊደል ሳያውቅ፣ እንኳን ዓረፍተነገሮችን ይቅርና አጫጭር ቃላትን እንዴት ማንበብ ይችላል? እያንዳንዱን ቃል፣ እንደ ስዕል ማስታወስ ማለት ነው። ይሄ፣ የትም አያደርስም። ዓመት ሙሉ ተምረው፤ ከዚያም ሁለተኛ ክፍልን አልፈው፤ ሦስተኛም ተጨምሮበት፣ ምን ውጤት ይገኛል? ምንም። የሕፃናትን እድሜና የአገርን ሃብት ማባከን ብቻ። ከመሃይምነት ወደ መሃይምነት ነው - የጥፋት ጉዞ።
እንግዲህ ተመልከቱ።
የተክል ስዕል አለ። ከስዕሉ ጎን፣ ተክል የሚል ጽሁፍ አለ። አንብብ የተባለ የ3ኛ ክፍል ተማሪ፣ “ችግኝ” ብሎ ይመልሳል።
“ቢላዋ” የሚል ቃል፣ ከስለታማ ስዕል ጎን ተጽፏል። የ3ኛ ክፍል ተማሪዋ፣ የስለታማውን ነገር ስም አውቃዋለች። ግን ባለ ሁለት ፊደል ነው ስሙ። ካራ ነው። ጽሁፉ ግን ባለ ሦስት ፊደል ነው። ችግሩ ማንበብ አትችልም። ምን ታድርግ?
ባለ ሶስት ፊደል ቃል… በሃሳቧ ፈለገች። ትክክለኛ ቃል አላገኘችም። ቢጨንቃት፣ “ካራይ” ብላ መለሰች። ለማስማማት ሞከረች።
በስዕል ያልታጀበ ጽሁፍ ግን፣ ለግምት ያስቸግራል። ከሦስተኛ ክፍል ተማሪዎች መካከል 30% ያህሉ፤ አንድም ቃል ማንበብ አይችሉም። አረፍተ ነገር ማንበብና መረዳት ግን፤ ለአብዛኞቹ ፍቺ የሌለው እንቆቅልሽ ነው።
አንደኛ ክፍል ላይ፣ ፊደልን በወጉ ቆጥረው፣ መሰረታዊ የንባብና የጽሁፍ ችሎታን ያላደላደሉ ሕጻናት፣ ለእድሜ ልክ የአእምሮ ጉዳት ይዳረጋሉ። በለጋ እድሜ ያልተማሩና በጉርምስናና በጉልምስና ጊዜ ከመሃይምነት ለመውጣት የሚጥሩ ሰዎች፣ ምንኛ እንደሚቸገሩ አይታችሁ ይሆናል።
በልጅነት መልመድ ቀላል ነው። ፊደላትን ለይቶ ማወቅና አቀናጅቶ ማንበብ፣ በዳዴ ጀምሮ ዘና ብሎ በእግር መራመድን እንደመልመድ ነው።
ከአንድ ዓመት ባልበለጠ ጊዜ፣ በልጅነት፣ ፊደልን ቆጥሮ፣ ንባብን የጀመረ ሕፃን፣ በቀላሉና በፍጥነት የማንበብ ችሎታው ወዲያውኑ ይሻሻላል።
ዓረፍተ ነገሮችን በወጉ አንብቦ ለመረዳት፣ በደቂቃ ቢያንስ ቢያንስ 30 ቃላትን ማንበብ ያስፈልጋል። አለበለዚያ፣ ወደ ኋላ እየተመለሱ ደግመው ደጋግመው የማንበብ ትግል ውስጥ ተጠምደው ይቀራሉ። ሁለተኛና ሦስተኛ ክፍል ላይ፣ በደቂቃ ከ45 እስከ 60 ቃላት የማንበብ ብቃት መድረስ ያስፈልጋል። የአገራችን የ3ኛ ክፍል ተማሪዎች፣ እዚህ መሰረታዊ ችሎታ ላይ አይደርሱም።
ከመቶ ተማሪዎች መካከል፤ 5 ያህሉ ብቻ ቢሳካላቸው ነው። አብዛኞቹ፣ ማንበብ ሳይችሉ፣ ከክፍል ክፍል እየተሸጋገሩ፣ የማወቅ እድላቸው ምንኛ እንደሚሰነካከል አስቡት። ማንበብና መጻፍ፣ ዋና የእውቀት መሳሪያዎች ናቸውና።
አብዛኞቹ ተማሪዎች፣ ቀላል አረፍተነገሮችን አንብበው መረዳት አይችሉም ማለት… ትርጉሙ ያስፈራል። የአእምሮ ተፈጥሮ አቅም ሳይጎድላቸው፤ ትምህርት ቤት የበደላቸው ሆነዋል-ህፃናቱ።
እንግዲህ ታዘቡ። ልጁ፣ የወደቀ ገንዘብ አገኘ። ገንዘብ ለወደቀበት ሰው እንዲመለስለት አሰበ። ገንዘቡን ለፖሊስ ሰጠ።
ይህ ቀላልና አጭር ትረካ በጽሁፍ ይቀርባል። የ3ኛ ክፍል ተማሪዎች ይህን ማንበብ ሊያቅታቸው አይገባም። ከዚያ በኋላ፣ በቃል ጥያቄ ይቀርብላቸዋል። ልጁ፣ ወድቆ ያገኘውን ገንዘብ ለምን ለፖሊስ ሰጠ? ተብለው በቃል ይጠየቃሉ።
ማንበብ የማይችል የ3ኛ ክፍል ተማሪ ምን ብሎ ይመልሳል?
“እ… አባቱና እናቱ፣ ሂድ ለፖሊስ ስጥ ስላሉት ነው” ብሎ የሚመልስ ይኖራል- የአእምሮ አቅም አላጣም። የንባብ ትምህርት ግን ተነፍጎታል።
“ገንዘብ ሰርቀሃል እንዳይሉት፣ ገንዘቡን ለፖሊስ ሰጠ” ብላ መልስ የምትሰጥ፤ ተማሪም አለች። የዘመኑ የትምህርት ውዥንብር ሰለባ ናት።
የሌላ ህፃን መልስ ደግሞ አለላችሁ- በጣም የተራቀቀ መልስ።
“ከህገወጥ የመሳሪያ ሽያጭ የተገኘ ገንዘብ ነው ብለው እንዳያስሩት ፈርቶ፣ ገንዘቡን ለፖሊስ ሰጠ” ብሎ፣ ግሩም ድንቅ ማብራሪያ የሚሰጥ የ3ኛ ክፍል ተማሪ አልጠፋም።
በዘመናችን እየተንሰራፋ የመጣውና መሃይምነትን እያስፋፋ የሚገኘው “አፍራሽ የትምህርት አስተሳሰብ”፤ መርዙና መዘዙ በአይነቱና በመጠኑ ብዙ ነው።
“Constructivist” ፍልስፍና ላይ የተመሰረተና፣ አላማው “Critical thinking” እንደሆነ ይገልጻሉ - አንዳንዶቹ።
“እውነት” እና “እውቀት” የተሰኙትን ፍሬ ሃሳቦች ያጣጥላሉ። እንደየአገሩ፣ እንደየዘመኑ፣ እንደየጾታው፣ እንደየእድሜው፣ እንደ አካል ብቃትና ጉዳቱ፣ እንደየጎሳውና ቋንቋው፣ እንደየሃይማኖቱና ባሕሉ፣ እንደየሃብቱ፣ የኑሮ ደረጃው ወይም የመደብ ጀርባው … “እውነት” ይለያያል ይላሉ። relative ነው ብለው የእውነትን ትርጉም ይጠፋሉ።
“እውነት” በእርግጥ “እውንን” መገንዘብ ማለት ካልሆነ፤ የዘፈቀደና የስሜት ጉዳይ ከሆነ፤ “እውቀት” ምን ትርጉም ይኖረዋል?
እውነተኛ መረጃዎችን እያመሳከሩና እያረጋገጡ፣ እያነጻጸሩና እያገናዘቡ፣ አጣምረውና አዋህደው መረዳት ነው - ማወቅ። ይህንንም በስፋትና በጥልቀት፣ በቅጡና በልኩ የሚገነቡት የሚያዳብሩት ነው- እውቀት።
ይዘቱ እውነታ (reality) ነው።
ዘዴው አእምሮ (reason) ነው።
የሁለቱ ውህደት ነው - እውቀት። ለምሳሌ፤ የምርምር ሙከራ፣ የእውነታና የአእምሮ ጋብቻ ነው። ለግንዛቤ በሚያመች የአእምሮ ዘዴ አማካኝነት፣ እውነታን የማስተዋል ጥበብ ነው- የምርምር ሙከራ።
“እውነት” ማለት፣ ከመነሻው መሰረተ ቢስ ከሆነ ግን፣ በዘር፣ በጾታ፣ በቁመና፣ በአካል ጉዳት፣ በሃብት፣ በድህነት ምክንያት የሚለያይ ከሆነ ግን፣ “እውቀት” ተሰኘው ነገር፣ መሰረት አልባ “ግንባታ” ይሆናል።
ባዶ “ግንባታ” ነው፤ construct ነው ብለው ያጣጥሉታል።
በአብዛኛውም፣ እውቀት ማለት የገዢዎች፣ የጉልበተኞች construct ነው በማለት “እውቀት”ን በጠላትነት ይፈርጁታል።
የትምህርት አላማ፣ “እውቀትን ማንቆርቆር አይደለም። እንዲያውም፤ “እውቀት” የተሰኘውን ነገር መሞገትና ማፍረስ ነው የትምህርት አላማ” ይላሉ። critical thinking (ሞጋች አስተሳሰብ) እና deconstruction እንዲሉ።
ይህን በሰፊው የተንሰራፋ የጥፋት አስተሳሰብ መመከትና መቀየር ከባድ ነው። ነገር ግን፣ ከጥፋት የሚያድን ሌላ መንገድ የለም - የእውነትና የእውቀት መንገድ እንጂ።

------------------------------------------------

      ፈተና ቁጥር 2 - ህልውናና ብልጽግና ወይስ የአካባቢ ጥበቃ?


           በእንግሊዝ፣ 30% ያህል ነዳጅ ማደያዎች ባዷቸውን ሰንብተዋል። በነዳጅ እጦት ያልተነካ የለም። ሰራተኞች ነጋዴዎች ገበሬዎች… በነዳጅ ፈላጊዎች ወረፋ እንግሊዝ ተተራምሳለች። (ዴይሊ ቴሌግራፍ የኦክቶበር 1 እትም)።
በአውሮፓ፣ የጋዝ ዋጋ 6 እጥፍ እንደናረ ይገልጻል - ዘኢኮኖሚስት መጽሔት። የአንድ ቤተሰብ የጋዝ ፍጆታ 140 ዶላር ነበረ - አምና መስከረም። ዘንድሮ መስከረም፣ የጋዝ ወጪ ከብዷል - ወደ 860 ዶላር ንሯል።
በጀርመን፣ የኤሌክትሪክ እጥረት የሚፈጠር አይመስልም ነበር። “የነፋስ ተርባይን፣ የፀሐይ ኃይል” እያሉ በብዙ ድጎማ የኤሌክትሪክ ማመንጫ የተስፋፋው በጀርመን ነው። ግን የኤሌክትክ እጥረቱ ምክንያትም ይሄው ነው። “እንደ ፀሐይና እንደ ነፋስ ሁኔታ” ይሆናል - ኤሌክትሪኩ።
በዚያ ላይ ወጪው ከባድ ነው።
በምድረ አውሮፓ፣ በኤሌክትሪክ ክፍያ ጀርመንን የሚስተካከል የለም - ውድ ነው። ባለፉት ወራት ደግሞ፣ ብሶበታል። አመት ባልሞላ ጊዜ የኤሌክትሪክ ዋጋ ከእጥፍ በላይ ሆኗል።
የነዳጅ ዘር በሙሉ፣ ጋዝና ከሰል ድንጋይ፤ ቤንዚንና ናፍታ፣ ከምድረ ገጽ ይጥፋ፤ ከሰው ኑሮ ይውጣ እያሉ መፎከር ቀላል አይደለም። አዎ፣ እንዲሁ ሲናገሩትና ሲያራግቡት፣ ቀላል ይመስላል፡፡ ግን የዋዛ ጨዋታ አይደለም። አዋቂነት የሚመስላቸው ብዙ ናቸው፡፡ ግን ጭፍንነት እንጂ አዋቂነት አይደለም፡፡
የጃፓንና የጀርመን ፖለቲከኞች፣ የኒውኩለር ሃይል ማመንጫዎችን እየዘጉ ፎክረዋል፡፡ በእንግሊዝ እስከ በስፔን፣የከሰል ድንጋይ ሃይል ማመንጫዎችን፣ በዘመቻ መዝጋት፣ እንደ ፌሽታ ሲቆጠር አይተናል፡፡ 24% የእንግሊዝ የኤሌክትሪክ ፍጆታ፣ “ከታዳሽ ሃይል” “ከነፋስ ተርባይን” የሚመነጭ ነው ተብሎ ተጨብጭቦለታል፡፡
“ግንኮ የነፋስ ነገር ምን ያስተማምናል፤ ይመጣል፤ ይሄዳል” የሚል ሃሳብ ጠፍቶባቸው ነው? የሚናገር አጥተው ነው? አልጠፋአውም፤አላጡም። ግን፤ የማሰብና የመስማት ፈቃደኝነት ያስፈልጋል፡፡ ጭፍንነት ሲበረታ፣ማሰብና መስማማት ያስጠላል፡፡ ግን፣ እውነታን ጠልቶ እስከመቼ? የተጨበጨበላቸው የነፋስ ተርባይኖች፣ ዘንድሮ፣24% አይደለም፣ 2% ያህል የአገሪቱን ኤሌክትሪክ ፍጆታ ማሟላት አልቻሉም፡፡ ምን ተሻለ?
የእንግሊዝ የማዳበሪያ ምርት፣በአንዴ በግማሽ ቀነሰ፡፡ በኤሌክትሪክ እጥረት ሳቢያ፣ ትልቁ የአገሪቱ የማዳበሪያ ኩባንያ፣ፋብሪካዎቹን ዘጋ፡፡ የአለማችን ትልቁ የማዳበሪያ አምራች፣ ያራ ኩባንያም አላመለጠም። በአውሮፓ የሚገኙ ፋብሪካዎቹ፣40 % ምርታቸውን ማቋረጥ ግድ እንደሆነባቸው ገልጿል፡፡ ከሜክሲኮ እስከ ኖርዌይ፣ከስፔን እስከ ቻይና፣የነዳጅና የኤሌክትሪክ እጥረት፣… እጥፍ የሚንረው ዋጋ ተደርቦበት ትርምስ ተፈጥሯል፡፡
በቻይና ሳይቀር፣ኤሌክትሪክ በወረፋ ሆኗል። የብረት ፋብሪካዎች፤ በሳምንት ለ4 ቀን ብቻ፤ እና በግማሽ አቅም ብቻ አንዲሰሩ፣ ገደብ ተጥሎባቸዋል ይላል-ዎል ስትሪት ጆርናል፡፡
የአውሮፓ ፋብሪካዎች፣ ላለፉት 20 ዓመታት እየተዳከሙ ቁጥራቸው መመናመኑ ያነሰ ይመስል፤ አሁንም መከራቸውን እያዩ ነው፡፡
የዚህ ሁሉ መዘዝ መነሻ ሰበብ፣ተራ ተርታው ሰበብ ቢቆጠር ብዙ ሊሆን ይችላል፡፡ ዋናዎቹ የውድቀት መንስኤዎች ግን ጥቂት ናቸው፡፡
ዋና ዋናዎቹ ደግሞ ሁለት ናቸው፡፡
አንደኛ ነገር፤ነባሩ “የሶሻሊዝም ዝንባሌ” አለ፡፡ ብዙሃኑን ሕዝብ፤ድሃውን ሕብረተሰብ ለመደጎም፣ በሚሉ የሶሻሊዝም ሃሳቦች ሳቢያ፣ የመንግስት ወጪ አለልክ ተለጥቷል፡፡ከ100 ዓመት በፊት፣ ከአገሪቱ ዜጎች ጠቅላላ ምኞት ውስጥ፣ መንግስት 10% ያህል አይወስድም ነበር፡፡ ዛሬ ብዙዎች የአውሮፓ መንግስታት፣ ከአገር ምርት ውስጥ ከ40%-50% ያህሉ ይወስዳሉ፡፡ ጉዳቱ እጥፍ ድርብ ነው፡፡ መንግስት በተፈጥሮው፣ሃብት አባካኝ ነው፡፡ በጀቱ ሲጨምር፣ ብክነቱም የከፋ ይሆናል፡፡
ምን ይሄ ብቻ!
መጪውን ለመሸፈን፣የታክስ ጫና በአምራቾች ላይ ይቆልላል፡፡ ይሄም አላንስ ብሎ፣ ስፍር ቁጥር የሌላቸው አላስፈላጊ ቁጥጥሮችን እለት በእለት ይፈለፍላል፡፡
በታክስ ጫና የጎበጡ፣በአስፈላጊ ቁጥጥር መተንፈሻ መፈናፈኛ ያጡ አምራቾች እየከሰሩ ፋብሪካቸው ይዘጋሉ፤ ከቻሉ ኢንቨስትመንታቸውን ወደ ሌላ አገር ይወስዳሉ።
ባለፉት 25 ዓመታት በትልቆቹ የአውሮፓ አገራት ውስጥ፣ የፋብሪካ የስራ እድሎች በሩብ ያህል ቀንሰዋል እየተዘጉ፡፡ ከዚህ ከነባሩ የሶሻሊዝም ዝንባሌ ጎን ለጎን፣ “ፀረ ነዳጅ፣ፀረ ፋብሪካ፣ ፀረ ብልጽግና” ቅኝትን አክርሮ በመላው ዓለም የተንሰራፋ ዘመቻ ታክሎበታል። የአካባቢ ጥበቃ፣ የአየር ንብረት ለውጥ፣ አረንጓዴ ልማት፣ ካርቦን ልቀት፣ የዓለም ሙቀት፣የሰሜን ዋልታ በረዶ መቅለጥ፣ ….. የሚሉ አባባሎች፣ የጥፋት ዘመቻው መፈክሮች ናቸው፡፡
ባለፉት ጥቂት ወራት፣ ከአገር አገር የተዛመተው የነዳጅና ኤለቴክትተሪክ፣የምርትና የዋጋ ቀውስ፣ “greenflation” ተብሎ ቢሰየም ይገርማል? የባለፈው ሳምንት የፋይናንሻል ታይምስ የአረብ እትም፣ እዚህ ላይ አልሳሳተም። ዎልስትሪት ጆርናልና ዘ ኢኮኖሚስት መፅሔትም፣ የዘንድሮው ቀውስ የአካባቢ ጥበቃ ዘመቻዎች መዘዝ እንደሆነ ገልፀዋል፡፡
ይሔ፣ ለአገራችን ለኢትዮጵያ፣ ትልቅ ማስጠንቀቂያ ነው፡፡ “የአካባቢ ጥበቃ”፣ “አረንጓዴ ልማት” የሚሉ የጥፋት ዘመቻዎችን በጭፍን ተቀብሎ ማራገብ፣እንኳን ለድሃ አገር ይቅርና ለሃብታሞችም አላዋጣም፡፡ አደገኛ ነው።
“የካርቦን ልቀትን ዜሮ እናደርጋለን” እያሉ የፋብሪካ እንቨስትመንትን የሚከለክሉ ከተሞች፣ “ከትራፊክ ነፃ መንገዶች” እያሉ ትራንስፖርትን የሚያናጉ ትራንስፖርት ቢሮክራቶች፤ “ድንጋይ ከሰልን እንከለክላለን” እያሉ የሲሚንቶ ምርትንና የአገር ግንባታን የሚያሰናክሉ የኢንድስትሪና የንግድ ሚኒስቴር ኤክስፐርቶች ብዙ ናቸው።….. ይሄ ሁሉ የጥፋት ዘመቻ መቆም አለበት፡፡ መዘዙ በግላጭ በእውን በኑሮ እየታየ ነውና፡፡ ችግሩ ምንድን ነው? የጥፋት ሃሳብ፣ አንዴ ከተንሰራፋ በኋላ፣የጥፋት መዘዙ በኑሮ በእውን ቢታይ እንኳ፣ የተሳሳተ ሃሳብን ማስተካከል እጅግ ከባድ ፈተና ነው፡፡
ከባድ ቢሆንም ግን፣ የጥፋት ሃሳብን መመከትና ሃሳብን ማስተካከል፤ ወደ ተቃና መንገድም ማምራት ይቻላል፡፡
የማዕድን ሚኒስቴር፣ የነዳጅ ፍለጋና ምርት ላይ፣ አላስፈላጊ ገደቦችን አሰናካይ ቁጥጥሮችን ለማቃለል መሞከሩ፣ ተስፋ ሰጪ ምሳሌ ነው።
የከሰል ድንጋይ ምርት ላይ የተከመሩ እንቅፋቶችን ለማቃለልና ለማስወገድ እንደወሰነም ገልጿል፡፡ መልካም ጅምር ነው። ግን፣ በስፋት የተንሰራፉ ፀረ ነዳጅ ጸረ ፋብሪካና ጸረ ብልጽግና ሃሳቦችን ተቋቁሞ ወደ ተቃና መንገድ መግባት፣ ቀላል አይደለም። ዩኒቨርስቲዎች፣ኤንጂኦዎች፣ አለማቀፍ ተቋማት፣ የውጭ አገራት…. በአብዛኛው ጸረ ነዳጅ ዘመቻን የሚያጫጭሁ ሆነዋል፡፡ ፈተናው በሁሉም አቅጣጫ ነው፡፡ ግን፣የአገር ህልውናና ብልጽግና፤ የዜጎች ተስፋና ኑሮ እንዲፈካ እንዲሻሻል ከተፈለገ፣ ከጥፋት ሃሳቦች መውጣትና በፅናት ወደ ተቃና መንገድ መግባት የግድ ነው፡፡


--------------------------------------------------------

    ፈተና ቁጥር 3 - ጀምስ ቦንድ፣ ወንድ ይሁን ሴት? ወይስ ሌላ?

      ነጭ ይሁን ጥቁር፣ ወይስ ሌላ? ሸንቃጣ፣ ወፍራም ወይስ አካል ጉዳተኛ?


               “የግል ማንነትንና ሃላፊነትን” የሚያጣጥል፣ ለዘረኝነት የሚመች ዘመን ላይ ነን። በተለይ ለአገራችን፣ ከድጡ ወደ ማጡ ነው። ዘረኝነት አገርን የሚጠፋ እጅግ ክፉ የህልውና አደጋ ነውና።
አዲሱ የጀምስ ቦንድ ፊልም፣ ለእይታ በበቃበት ሰሞን ላይ ሆነን፣ በርካታ አለማቀፍ ዘገባዎችን ብንሰማ አይገርምም። በመላው ዓለም፣ ሰፊ ተወዳጅነትን ያተረፈ፣ ለበርካታ ዓመታት በአዝናኝነት የዘለቀ፣ ተከታታይ የኪነ-ጥበብ ፍሬ ነው።
“ስታር ዋርስ”፣ በአሜሪካ እንደ አንድ የባህል ገጽታ ለመታየት የመብቃቱ ያህል፤ የ”ጀምስ ቦንድ” ፊልሞችም፣ በእንግሊዝ እንደዚያው ናቸው። ከድርሰቶቹ የጀመረ ነው ነገሩ።
እና፣ የተወዳጅነቱ ያህል፤ አዲሱ ጀምስ ቦንድ ፊልም፣ የሚዲያ መነጋገሪ መሆኑ አይገርምም። የፖለቲካ ፓርቲ፣ በፊልሙ ላይ የአቋም መግለጫ የሚያወጣበት ሲሆን ነው ችግሩ።
በእንግሊዝ፣ የተቃዋሚው የሌበር ፓርቲ  ፖለቲከኛ፣ “ወደፊት፣ የፊልሞቹ ዋና ገፀባሕርይ ሴት መሆን አለባት” ብለዋል።
የገዢው ፓርቲ “የቶሪ” ፖለቲከኛ በበኩላቸው፣ “ሌበር ፓርቲ ሴት መሪ ኖሮት አያውቅም፤ የፊልም ገጸባህሪ ሴት ትሁን ብሎ ለመናገር ግን ይሽቀዳደማል” ሲሉ አፀፋ መልሰዋል።
“ቶሪ” ፓርቲ፣ ከጥቂት ዓመታት በፊት፣ ቴረሳ ሜይን በመሪነት መርጦ ነበር። ከዚያ በፊት፣ ደግሞ፣ “ብረቷ እመቤት” በተሰኙት፣ በዝነኛዋ ማርጋሬት ታቸር የተመራ ፓርቲ ነው።
የሆነ ሆኖ፣ ፖለቲከኞች፣ “የድርሰትና የፊልም ገጸ-ባህርይ ጾታ”፣ ምን መሆን እንዳለበት ለመወሰን ሲነታረኩ የምናይበት ዘመን ላይ ነን።
ለነገሩ፣ ጀምስ ቦንድ፣ በሴት ገጸባህርይ ከተቀየረ በኋላ፣ የተተኪዋ ጀግኒት ስም ምን መሆን እንዳለበት፣ በህዝብ ምርጫ ሊወሰን ይችላል። ወይስ፣ ሴቶች ብቻ በሚሰጡት ድምጽ መሆን አለበት? ጉዳዩ ቀላል አይደለም። “የወንዶችን የምዕተ ዓመታት ጭቆናን የማስወገድ ትግል፤ የሴቶች ጉዳይ ነው” ብለው የሚከራከሩ ሞልተዋል።
ጄሪ ቦንድ፣ ጄን ቦንድ፣… ወይም ትንሽ ወጣ ብሎ፣ ጃስሚን ቦንድ፣.. እነዚህ ስያሜዎች ግን ከአድሏዊነት  የፀዱ አይደሉም። የነጭ ሴቶችን የበላይነት የሚያናፍስ ነው - ቃናቸው። “ጀማ ባንጃው” ይሁን?
“ጄምስ ቦንድ፣ ከመነሻው፣ ከድርሰት ፈጠራው፣ ወንድ ገጸባህርይ ነው። ሴት መሆን የለበትም።” ብለው መከራከሪያ ያቀረቡ አሉ። ግን እንደ ማካካሻ፣ ሌላ አማራጭ ሃሳብ ሰንዝረዋል። “ነጭ ወንድ፣ ጥቁር ወንድ ወይ ሌላ ሊሆን ይችላል” ብለዋል።
ግን፣ ይሄ አያስታርቅም። ሌሎች ብዙ ቅሬታዎች አሉ። “የግድ ሸንቃጣ መሆን የለበትም። ወፍራሞችንና የአካል ጉዳተኞችን ያገለለ ነው” የሚል ውግዘት የተለመደ ሆኗል። የቁንጅና ውድድሮች ላይ፣ እንዲሁም የፋሽንና ሞዴል ኩባንያዎች ላይ ሲካሄድ የከረመውን ዘመቻ ታስታውሱ ይሆናል። አንድ ታዋቂ የፈረንሳይ የፋሽን ኩባንያ፣ አካል ጉዳተኛ ሰራተኛ፣ የአእምሮ ዝግመት ተጠቂ ሞዴል ቀጥሮ፣ እይሉኝ ስሙልኝ ብሏል። አግላይ አይደለሁም፤ አቃፊ ነኝ ማለቱ ነው።
እዚህ ላይ፣ “ሴት ወይስ ወንድ” በሚለው ንትርክ የሚናደዱ አሉ። አግላይ ክርክር ነው ይሉታል።
እና ምን ይሻላል? “ወንድ፣ ሴት ወይስ ሌላ” ተብሎ ይስተካከል ይላሉ። ጾታ፣ በተፈጥሮ ሳይሆን በምርጫ መሆን  አለበት ባይ ናቸው። በማግስቱ የሚጠፋ ጊዜያዊ የስካር ሃሳብ ይመስላል። ነገር ግን ዋና የፖለቲካ ዘመቻ ሆኗል። በቅርቡ የካናዳ ህግ በዚሁ ቅኝት እንደተለወጠም አትርሱ።
ስጋ በል እና ቬጂተሪያን፣ ድሃና ሃብታም፣ የዚህና የዚያ ሃይማኖት፣ የእገሌ ብሔርና የዕገሊት ብሔረሰብ… ምናለፋችሁ። ብዙ ነው ጣጣው።
የጅምላ አስተሳሰብ (Collectivism)፣ በመላው አለም እየነገሰ ነው - ሰርግና ምላሽ ሆኖለታል።
የጅምላ አስተሳሰብ፣ ለየትኛውም አገር አጥፊ ነው።
ለእንደኛ አገር ደግሞ፣ አጣዳፊ የህልውና አደጋ ነው። ነባሩ የዘረኛነት አደጋ ላይ ይህ የዘመናችን ስካር ሲታከልበት፣ ማን ይመልሰዋል - እጅግ ካልተጠነቀቅን በቀር። መፍትሄውስ? የግል ህልውናን፣ የግል ማንነትንና ሃላፊነትን ማክበር ነው መድሃኒቱ።
የእያንዳንዱ ሰው የግል ህልውና መከበር አለበት። እያንዳንዱ ሰው፣ የሕይወቱ የግል ባለቤት ነውና።
እያንዳንዱ ሰው፣ በስራው መመዘን ይኖርበታል - በዘር፣ በጎራ፣ በቡድን ሳይሆን።
እያንዳንዱ ሰው፣ በብቃቱና በባህርይው መዳኘት አለበት - ለአድናቆትም ለፍርድም።
አለበለዚያ ማለቂያ በሌለው የጎራ ክፍልፋይ እየተናቆሩ መተላለቅ ይሆናል - በተለይ በዘረኝነትና በሃይማኖት ጎራ።


Read 10943 times