Monday, 11 October 2021 09:48

የ35 የአለም መሪዎችን ጉድ ያጋለጡት የፓንዶራ ሰነዶች እያነጋገሩ ነው

Written by 
Rate this item
(0 votes)

በስልጣን ላይ ያሉ እና የቀድሞ 35 የአገራት መሪዎችና ከ300 በላይ ከፍተኛ የመንግስት ባለስልጣናት ከህዝብ እጅግ ከፍተኛ መጠን ያለው ሃብት መመዝበራቸውንና በውጭ ኩባንያዎች በድብቅ በቢሊዮኖች የሚቆጠር ዶላር ማፍራታቸውን ባለፈው እሁድ ያጋለጠው የፓንዶራ ሰነዶች የተሰኘ የምርመራ ጋዜጠኝነት ሪፖርት፣ ስማቸው የተጠቀሰ የአለማችን መሪዎችን ሲያንጫጫና ሲያተራምስ ሰንብቷል።
በአለማቀፉ የምርመራ ጋዜጠኞች ጥምረት ፊታውራሪነትና ከ140 በላይ የመገናኛ ብዙሃን በተውጣጡ 650 ያህል ጋዜጠኞች ተሳትፎ አመታትን ፈጅቶ የተሰራውና ከ12 ሚሊዮን በላይ ድብቅ ፋይሎችን በአደባባይ የዘረገፈው ይህ ሪፖርት፣ ከ91 በላይ የአለማችን አገራትና ግዛቶች መሪዎችና ከፍተኛ ባለስልጣናት ድብቅ የሃብት ሚስጥሮችና የንግድ ሰነዶች አጋልጧል።
የፓንዶራ ሰነዶች የኬንያውን ኡሁሩ ኬንያታ፣ የሩስያውን ቭላድሚር ፑቲን፣ የፓኪስታኑን ኢምራን ካሃን፣ የዩክሬኑን ቭላድሚር ዜለንስኪ፣ የአዘርባጃኑን ኢሃም አሊቭ እና የዮርዳኖሱን ንጉስ አብዱላህ ቢን አል ሁሴንን ጨምሮ የ35 የቀድሞና የአሁን የአገራት መሪዎች ስውር የንግድ ስምምነትና የሃብት ምዝበራ ሴራዎች አጋልጧል፡፡
የፓንዶራ ሰነዶች ይፋ መደረጉን ተከትሎ መላው አለም ጉዳዩን መነጋገሪያ ያደረገው ሲሆን፣ ስማቸው በሰነዱ ውስጥ የተጠቀሰ የአገራት መሪዎችም ከያቅጣጫው የየራሳቸውን እየቅል ምላሽ በመስጠትና ጉዳዩን በማስተባበል ተጠምደው ሰንብተዋል፡፡
በውጭ አገራት በሚኖሩ ኩባንያዎች በድብቅ ከ100 ሚሊዮን ዶላር በላይ ሃብት አፍርተዋል ተብለው በሪፖርቱ የተጠቀሱትን የዮርዳኖሱ ንጉስ አብዱላህ በተመለከተ ምላሹን የሰጠው ቤተ መንግስታቸው፣ "ንጉሱ በውጭ አገራት ሃብት ቢኖራቸው ምን ይገርማል፤ ነገሩ ያልተመለደም ነውርም አይደለም" ማለቱን ቢቢሲ ዘግቧል፡፡
የሩስያው ክሪሚሊን ቤተ መንግስት በበኩሉ፤ የሪፖርቱን አስተማማኝነት እንደሚጠራጠር በመግለጽ፣ ፕሬዚዳንት ፑቲን ህዝብ የማያውቀው ድብቅ ሃብት አላቸው ብሎ እንደማያምን አስታውቋል፡፡
በውጭ አገር በሚገኝ ኩባንያ ውስጥ ከፍተኛ የሃብት ድርሻ እንዳላቸውና በኩባንያው አማካይነት በ12 ሚሊዮን ዶላር ፈረንሳይ ውስጥ ሁለት ቤቶችን መግዛታቸው በሰነዱ የተጋለጡት የቼክ ሪፐብሊክ ጠቅላይ ሚኒስትር አንድሬጅ ባቢስ በበኩላቸው በትዊተር በሰጡት ምላሽ፤ ምንም አይነት መሰል ወንጀል አለመስራታቸውን በመግለጽ፣ ውንጀላቸው በዚህ ሳምንት ሊካሄድ የታቀደውን ምርጫ ለማስተጓጎል ተብሎ የተሸረበ ሴራ ነው ማለታቸው ተዘግቧል፡፡
የኬንያው ፕሬዚዳንት ኡሁሩ ኬንያታ ደግሞ ከ6 ሌሎች የቤተሰብ አባላት ጋር በመመሳጠር ከህዝብ የመዘበሩትን ከፍተኛ ሃብት በ13 የውጭ አገራት ኩባንያዎች ኢንቨስት አድርገዋል ሲል ያጋለጣቸውን ይህን ሪፖርት፤ በአዲስ አበባው በዓለ ሲመት ላይ ሆነው እንደሰሙ፣ ወደ አገር ቤት ልመለስና ዝርዝር ምላሽ እሰጥበታለሁ፣ እንዲህ ያለ ቅሌት ውስጥ እንደማልገባ ግን ህዝቤ ይወቅልኝ ማለታቸው ተነግሯል፡፡
በስውር ያቋቋሙት በዲያመንድ ማዕድን ልማት ዘርፍ የተሰማራ ኩባንያ ባለቤት ናቸው የተባሉት የኮንጎ ብራዛቪል ፕሬዚዳንት ዴኒስ ሳሱ ኑጌሶ በበኩላቸው፤ ያለ ስሜ ስም ሰጥተውኛል ባሏቸው መገናኛ ብዙሃን ላይ ከባድ እርምጃ ሊወስዱ መዘጋጀታቸውን የፈረንሳይ ሬዲዮ ጣቢያ ዘግቧል፡፡
በሰነዱ ውስጥ ስማቸው ከተጠቀሰ የድብቅ ሃብት ባለቤት ናቸው የተባሉ የአለማችን ታዋቂ ሰዎች መካከል ታዋቂዋ ኮሎምቢያዊት ድምጻዊት ሻኪራ፣ የቀድሞው የእንግሊዝ ጠቅላይ ሚኒስትር ቶኒ ብሌርና ባለቤታቸው ቼሪ ብሌር እንዲሁም ጀርመናዊቷ ሱፐር ሞዴል ክላውዲያ ሺፈር ይገኙበታል፡፡


Read 1532 times