Error
  • JUser: :_load: Unable to load user with ID: 62
Monday, 10 September 2012 14:30

“ደሀ ሞኝ ነው ሞቱን ይመኛል እልፍ ሲሉ እልፍ ይገኛል!”

Written by 
Rate this item
(4 votes)

ነብሷን ይማርና፤ ዶሮ እንደዛሬው አልቀመስ ሳትል በፊት፤ በብርም በብር ተሃምሣም ትሸጥ በነበረ ጊዜ፤ የሚከተለውን ተረት ከዓመታት በፊት ተርተነዋል  ለአንድ በዓል ብለን፡፡ ያኔ ያልነውን ላልሰማና ሰምቶ ዝም ላለ ዛሬም መተረቱ አስፈላጊ ሆኖ ነው እንጂ፤ አሁን ቅንጦት ሊመስልብን ይችላል፡፡ እነሆ፡- የዕንቁጣጣሽ ዕለት ነው፡፡ አባትና እናት አንድ ቋሚ ልማድ አላቸው፡፡ በተለይ እንግዳ ከመጣ ልጃቸውን እቆጥ ላይ አውጥተው ያስሩታል፡፡ ልጁምለቅሶውን ይቀጥላል፡፡ ምግቡ ተበልቶ ሲያበቃ ይፈቱና ያወርዱታል፡፡ ይህ እንግዲህ በዓመት በዓል፣ በዓመት በዓል የሚሆን ነገር ነው፡፡ ከዓመት በዓላቱ በአንደኛው ዕንቁጣጣሽ ቀን አንድ እንግዳ ይመጣል፡፡

“ቤቶች?” ይላል፡፡

“ደጆች” ይሉታል፡፡

“ጥቁር እንግዳ ታስገባላችሁ?”

“እንኳን የዕንቁጣጣሽ ዕለት፣ በአዘቦቱም ቀን ቤታችን የእግዚብሔር ቤት ነው፡፡ ቤት ለእንግዳ!” ይሉታል፡፡

እንግዳውም፤

“እግዜር ዕድሜ ከእንጀራ ይስጣችሁ!”

ይልና ገብቶ ይቀመጣል፡፡

ሚስት የእግር ውሃ አሙቃ፣ የእንግዳውን እግር አጥባ ስታበቃ፤ ምግብ ታቀራርባለች፡፡

ባል ያንን የፈረደበት ልጅ ቆጡ ላይ ያወጣና እግር - እጁን አሥሮ ጠፍሮ ያስቀምጠዋል፡፡

እንግዳው እጁን ታሥሮ ገበታው ዘንድ እንዲቀርብ ይጋበዛል፡፡ ዶሮ ወጥ ከነድስቱ ይቀርባል፡፡ ሚስቲቱ ወጡን ጨልፋ እንግዳው ፊት ዕንቁላልም

ብልትም ታወጣለች፡፡

ባል፤ “እንግዲህ ቤትህ ነው፡፡ ቀኑም ዕንቁጣጣሽ ነው - ዘና ብለህ ብላ!” ይልና ይጋብዘዋል፡፡

እንግዳ፤

“እንደናንተ ያሉ ደግ ሰዎች አጋጥመውኝ አያውቁም፡፡ አምላክ ውለታችሁን ይክፈላችሁ!” ብሎ መብላት ሲጀምር አንድ ድምፅ ከወደ ጣራው ይሰማል፡፡

“እ..እ…እ…እ!” ይላል፡፡

እንጀራ በተቆረሰ፣ ሥጋ በተጐረሰ ቁጥር፣ ያ ለቅሶ ልክ እንደተሞላ ቴፕ ይቀጥላል፡፡

“እእ!...እ..እ!” ይላል፡፡

እንግዳው ነገሩ ግራ ይገባውና ሙሉ በሙሉ ዞሮ ወደ ቆጡ ሲመለከት ያ የታሠረ ልጅ፤ ከላይ ወደ ታች ገበታው ላይ አፍጦ፣ ዕንባው እየተዝረበረበ

ያለቅሳል፡፡

እንግዳ፤ “ምን ሆኖ ነው ይሄ ልጅ?” ሲል ይጠይቃል፡፡

አባት፤ “ተወው በዓመሉ ምክንያት አሥረነው ነው!”

እንግዳ፤ “ዓመሉ ምንድን ነው?”

አባት፤ “ከእንግዳ ጋር ገበታ ከቀረበ፤ የራሱን ትቶ ከእንግዳ ፊት ሥጋም፤ ዕንቁላልም እያነሳ ሰው እያስቀየመ ስላስቸገረ ነው!”

እንግዳ፤

“ኧረ አይገባም! ምነው ጐበዝ! ልጅ አደለም እንዴ? ኧረ በዝጊሃር ፍቱት!“

አባት፤

“ተው አይሆንም የኔ ጌታ ዓመሉን አታውቀውም!”

እንግዳ፤

“በእኔ ይሁንባችሁ! ግፍ ነው ልጅን እንዲህ የበይ ተመልካች ማድረግ! ኧረ እግዚሃር አይወደውም ጐበዝ!”

አባት፤ ውትወታው ሲበዛበት ይነሳና ልጁን ፈትቶ ያወርደዋል፡፡ ልጅ ዕንባውን ያዘራበትን ፊቱን ይታጠብና ገበታ ይቀርባል፡፡ እናት ዕንቁላልም ሥጋም

ታወጣለታለች!

ከጥቂት ጊዜ በኋላ ለእንግዳው ብልት ይወጣለታል፡፡ ልጁ አፍታም ሳይቆይ ያንን ብልት ከእንግዳው ፊት አፈፍ ያደርጋል፡፡ እናት ደንግጣ፤

“አንተ የፍትሕን አትበላም? ባለጌ!” ትላለች፡፡

እንግዳ፤ “ተዉት ግዴለም፤ ልጅ አይደለም እንዴ?” ይላል፡፡

ሌላ ብልት ለእንግዳው ወጣ፡፡ ልጅ አሁንም አፈፍ ያደርጋል፡፡ አባት ይቆጣል!

እንግዳው፤ “ተዉት እንጂ! ልጅ አይደለም እንዴ?” ይላል፤ ትንሽ ሐፍረት እየታየበት፡፡

ለሶስተኛ ጊዜ ብልት ለእንግዳው ወጣ፡፡ ልጅ አፍታም ሳይቆይ፤ አፈፍ!

ይሄኔ እንግዳው ተስፋ ቆርጦ፤

“እንግዲህ ሸብ!” አለ፡፡

የተፈረደበት ልጅ እቆጡ ላይ ታሠረ!

***

ገና ከልጅነት አርመን ኮትኩተን ያላስተካከልነው ዓመል፤ ካደገ በኋላ እናስተካክልህ ብንለው እጅግ ከባድ ነው የሚሆነው! የበይ ተመልካች፣ የበይ ተመልካች እንደሆነ ይቀራል! በዓሉም መምጣቱን አይተው፡፡ እንግዳውም መከሰቱ አይቀር፡፡ ልጁም ዓመሉን አይተውምና መታሠሩ አይቀር! “እንግዲህ ሸብ” መባሉም አይቀር! “ከእንግዲህ ሸብ” ዘዴ ሌላ፣ ቅጣት ማረሚያ፣ ማስተማሪያም ሆነ መምከሪያ ጊዜ አልነበረም ወይ? ልጁስ ለምን እንደዚያ እንደሚያደርግ ተጠይቋል ወይ? በምን ምክንያትና ሁኔታ ከሰው ፊት መመንተፍ ጀመረ? እስከ መቼስ መታሠሩ ይቀጥላል? ለእንግዳ ሲባል እስከ መቼ የራስ ልጅ ይጐዳል? የሚሉትና ሌሎች ጥያቄዎች አይቀሬ መወያያዎች ናቸው! አባትና እናት “ማሠራችን ልክ ነው ወይ?” ብለው አንድም ቀን ራሳቸውን አይጠይቁም፡፡ ልማድ አድርገውታልና! ልጅም አቅም የለውምና ማልቀሱን ይቀጥላል፡፡ ልማድ አድርጐታልና!

“…ዛሬ ለወግ ያደረግሽው፤ ወይ ለነገ ይለምድብሻል

ልማድ ፊት እንዳሳዩት ነው፣ ወይ ይጠፋል ወይ ያጠፋል!

ከርሞም የሠለጠነ እንዲሁ፣ ተፈጥሮ ይሆናል ይባላል”

ይለናል ሼክስፒር፡፡ ይህ አዲስ ዓመት ከብዙ አጓጉል ልማዶች ይገላግለን!

ይህኛው ዘመን አፍረንም ሆነ ፈርተን፣ ባለማወቅም ሆነ ይሉታ ይዞን፤ መብታችንን የአለመጠየቅን ልማድ ይገላግለን!

ይህኛው ዘመን ከሰብዓዊ መብት ረገጣ፣ ከኢፍትሐዊነት በደል፣ ከሙስናዊ ወንጀል ሰለባነት፣ ከኢኮኖሚያዊ ዝቅጠት፣ ከፖለቲካዊ ዛቻና ሽኩቻ፣ ከፕሬሳዊ ዕገዳ፣ ከህዝብ ግንኙነታዊ ሽወዳ፣ ከሱሪ በአንገት ናዳ፤ ከድንቁርና ዱቤ - ዕዳ፤ ከቡድን ስሜት የቤት - ጣጣ… ከነዚህ ሁሉ አጓጉል ልማዶች ይሰውረን!

ይህ ዘመን ለመጀመሪያ ጊዜ ያለ ጠቅላይ ሚኒስትር የምናከብረው ዐውደ ዓመት መጀመሪያ  ነው፡፡

ለመንግሥትም ለህዝብም እንግዳ ዐውደ - ዓመት ነው! በእርግጥም ለሀገራችን አዲስ ነው፡፡ ሀዘን፣ ሥጋት፣ ድፍረት፣ ፍርሃት፣ ንቀት፣ ፌዝ - ቡክ፣ የኢንተርኔት ንትርክ ፣ የህዝብ አይገመቴነት፣ የኑሮ ምሬት፣ የነገ ጥርጣሬና የአቦ - ሰጡኝ መላ - ምት፣ ዝግጁነትን ማጣት፣ የሥነ ልቡና መሸርሸር… ምኑ ቅጡ፡፡ ግሱና ግሳንግሱ የበዛ ዓመት ነው፡፡ ካለፈው ዓመት ወደ አዲሱ ዓመት የዞረ - ድምር ይዞ የመጣ ዘመን ነው፡፡ የተሻለ ጊዜ እንዲመጣ እንመኝ! የጠነከረ ራዕይ ይኑረን በአንድ  ጥናቱን ይስጠን “እንግዲህ ሸብ” ከመባልም፤ እንደታሳሪው ከማልቀስም ወጥተን፣ የተሻለ ዓመት፣ የተሻለ አገር ለማየት ያብቃን! መቼም ቢሆን መቼ፤ “ደሀ ሞኝ ነው፣ ሞቱን ይመኛል

እልፍ ሲሉ፣ እልፍ ይገኛል!!”

የሚለውን በተስፋና በአዎንታዊነት (Optimistic) ሀገርኛ ግጥም አንርሳ! ከድህነት እንወጣ ዘንድ ወገባችንን ጠበቅ እናድርግ!

መልካም አዲስ ዓመት!!

 

 

 

Read 5894 times Last modified on Monday, 10 September 2012 14:36