Saturday, 09 October 2021 00:00

አዳም ረታ፤ ጎምቱ ብዕረኛ

Written by  መኮንን ደፍሮ
Rate this item
(5 votes)


              ክፍል አንድ
የዚህ ጽሑፍ ውልደት ሰበብ ባለፈው ሳምንት ቅዳሜ፣ በዚሁ ጋዜጣ ላይ ያነበብኩት አፍ በተሰኘው የታዋቂው ደራሲ አዳም ረታ የረዥም ልብወለድ ሥራ ላይ የቀረበ ሥነ-ጽሑፋዊ ምልከታ ነው፡፡ የጽሑፉ ባለቤት አቶ ያዕቆብ ብርሃኑ የተባሉ ጸሐፊ ናቸው። አቶ ያዕቆብ እዚሁ ጋዜጣ ላይ በየሳምንቱ በርካታ ቁምነገሮችን እያስነበቡን ያሉ ትጉህ ጸሐፊ ናቸው፡፡ ጸሐፊው የደራሲ አዳም ረታን ሥራ የመዘኑበት መንገድ በከፊል የተዛባ ሆኖ ስላገኘሁት ይህ አጭር ጽሑፍ ሊፃፍ በቃ፡፡ በመሆኑም፣ የዚህ ጽሑፍ ዐቢይ አላማ ይህን የአቶ ያዕቆብ በከፊል የተዛቡ ትችቶች እየነቀሱ መሞገት ነው፡፡ የአቶ ያዕቆብን ተግባር ግን በእጅጉ አደንቃለሁ፤ ምክንያቱም ይኸ ነዉ የሚባል ጠንካራ የሥነ-ጽሑፍ ሃያሲ በጠፋበት በዚህ ዘመን፣ እኝህ ጸሐፊ ይህን ጽሑፍ ማቅረባቸው ይበል የሚያሰኝ ነውና፡፡ የዚህ አገራዊ ተግዳሮት ዋናው ምክንያት ገና ከድንቁርና እግር ብረት ነፃ ያልወጣን ህዝቦች በመሆናችን የሀቲት ባህልን (intellectual discourse) ለመገንባታ አቅመ-ቢስ መሆናችን ይመስለኛል፡፡
አቶ ያዕቆብ በብዙዎቹ የአዳም ረታ የልብወለድ ሥራዎች ውስጥ በገሀድ የሚስተዋለውን ፈር የሌለው የሥርአተ-ነጥብ ግልጋሎት አስመልክተው የሰነዘሩትን ሂስ ሙሉ በሙሉ የምጋራው ነዉ፡፡ ሥርአተ-ነጥብ በሥነ-ጽሑፍ ውስጥ ያለውን የላቀ ፋይዳ አስመልክቶ እኔም ቀደም ባለ ጽሑፌ ውስጥ የአቶ ያዕቆብን ሙግት የሚደግፍ አቋሜን ገልጫለሁ፡፡ ይኸው ጽሑፌ እንዲህ ይላል፦
የአማርኛ ሰዋሰዉ ድንጋጌን ተከትሎ በአግባቡ ሥራ ላይ የተተገበረ የሥርአተ-ነጥብ ግልጋሎት በአንባቢና በደራሲዉ የድርሰት ሥራ መካከል ያለው ተግባቦት የተሳለጠ እንዲሆን እጅጉን ያግዛል፡፡ ይህም ተግባር ፈፅሞ መሻር የለበትም፡፡ ሥርአተ-ነጥብ በራሱ ቋንቋ በመሆኑ በተገቢው መልኩ መቀመጡም ሆነ መገደፉ በአንባቢና በድርሰት ሥራው መካከል የሚኖረውን ተግባቦት ሊያሳልጥ አልያም ሊያደናቅፍ መቻሉ እሙን ነው፡፡ በወጉ የተተገበረ ሥርአተ-ነጥብ የድርሰት ሥራ ውበትም ነው፡፡  
አቶ ያዕቆብ አዳምን የገለፁበት መንገድ ከሂስ መሠረታዊ ሚና እና ግብ እጅግ የራቀ ተራ አስተያየት የተንፀባረቀበት ሆኖ አግኝቼዋለሁ፡፡ የጸሐፊው ምልከታ አዳም ረታ የአገራችን ሥነ-ጽሑፍ የማዕዘን ድንጋይ እንደመሆኑ መጠን ሊቸረዉ የሚገባውን ተገቢ እውቅና እና ሥፍራ የነፈገ፣ ፍርደ-ገምድል ምልከታ ነው፡፡
የሃያሲ ዐቢይ ሚና የቀረበለትን የሥነ-ጽሑፍ ሥራ በጥልቀት ከብዙ አቅጣጫ በመመዘን፣ የሥራው ባለቤት በሥራው ውስጥ ማቅረብ የፈለገውን ዐቢይ ጉዳይ አንደምታና ሀቲት (ይህ ተግባር አንዳንዴም የደራሲዉን የምናብ አድማስ ተሻግሮ በመሄድ (transcending or surpassing beyond the authoer’s paradigm) ሊሆን ይችላል) የአመክንዮ መርህን ተንተርሶ መተንተን ነው፡፡ በዚህ አግባብ፣ አዳምንም ሆነ የኤግዚስቴንሻሊዝም ፍልስፍናን አስመልክቶ አቶ ያዕቆብ የሰነዘረው ግላዊ ብያኔ እውነትን መሰረት ያላደረገ ነው፡፡ ለምሳሌ እኔ ከአመታት በፊት አዳም ረታ ደንበኛ ኤግዚስቴንሻሊስት ጸሐፊ መሆኑን ያወጅኩት የድርሰት ስራዎቹ በጥልቀት የሚዳስሳቸውን ዐቢይ ኤግዚስቴንሻል ርእሰ ጉዳዮች፣ የፍልስፍናውን ዐቢይ ደቀመዛሙርት ትንታኔ ዋቢ አድርጌ በማስነብብ ነዉ፡፡              
አዳም ቀዳሚዎቹ ደራሲያን ስብሐት፣ ሐዲስ፣ በአሉ እና ዳኛቸው ያልጻፉልንን ዘርፈ ብዙ ፍልስፍናዊ ጭብጦች (philosophical themes) በጥልቀት ከዚያ በፊት በኢትዮጵያ ሥነ-ጽሑፍ ባልተተገበሩ የሥነ-ጽሑፍ የአጻጻፍ ይትባህሎች ማለትም ኢምፕረሺኒዝም፣ ኤግዚስቴንሻሊዝም፣ ሳይኮአናላሲስ፣ ትሩማ፣ ፖስትሞደርኒዝም እና ሱሪያሊዝም የጻፈ ታላቅ ጸሐፊ ነው፡፡ ይህን በገሀድ አለመመስከር ፍርደ-ገምድልነት ነዉ፡፡
አዳም በሥራዎቹ ላይ ተግባራዊ የሚያደርጋቸውን ልዩ ልዩ የሥነ-ጽሑፍ አፃፃፍ ዘውጎች የጀርባ አጥንት የሆኑትን መሠረታዊ መርህ በወጉ ካላጠኑ በስተቀር አዳምን በጥልቀት መረዳት አዳጋች ነው። አቶ ያዕቆብም ይህን ጉዳይ በጥልቀት የተረዱት አልመሰለኝም፡፡ በመሆኑም በዚህኛው ጽሑፌ አዳምን በጥልቀት ለመረዳት የሚያግዙንን ጥቂት የንባብ አቀራረቦችን አስተዋውቃለሁ፡፡   
አዳም ረታ ፍልስፍናን ሥነ-ጽሑፋዊ  በሆነ መንገድ የሚጽፍ ደራሲ ነው፡፡ የአዳም ጽሑፍ ፍልስፍናዊ ሀተታ (philosophical treatise) በመሆኑ ምክንያት የሚዳስሰው ቁምነገር ተጨባጭ እውነት ላይ የፀና አመክንዮአዊ (logical) እንዲሆን አያሌ ማስረገጫ ጉዳዮችን እየጠቀሰ (እዚህም እዚያም እየረገጠ) በጥልቀት የሚያትት ነው፡፡ ይህም በመሆኑ ነው የደራሲው ሀቲት (argument) ሁላችንም ቀድመን የካብነውን ርእዮተ-ዓለም የሚንድ ሞጋችና አመራማሪ ሆኖ የተገኘው፡፡
እንደ እኔ እሳቤ፣ የልብወለድ ጸሐፊ ዐቢይ ተግባር የሰውን ልጅ ዘወትራዊ የህልውና ስንክሳር (existential condtion) እንደወረደ መዘገብ አይደለም፤ ከዚህ የህላዌ ቀመር ጀርባ ያለውን ስውር እውነት የተገነዘበበትን የፍልስፍና ዱቄት በገሀድ ማረጋገጥ በሚቻል ቋት ላይ ከስቶ የማሳየት ተግባር እንጂ፡፡ ልብወለድ የሰውን ልጅ ዘወትራዊ የሕይወት ስንክሳር ከነግብስብሱ የመክተብ ተግባር (reporting) ሳይሆን ላቅ ያለ ፍልስፍናዊ ርእሰ ጉዳይን በተዋበ ቋንቋ ሰንዶ የማቅረብ ተግባር ነው፡፡ በሌላ አነጋገር፣ የሰው ልጅ የኑሮ ስንክሳር ስለተገለጠበት ብቻ አንድን የድርሰት ሥር ታላቅ ሥራ አያደርገውም። አንድ የድርሰት ሥራ ታላቅ ሥራ የሚሆነው የሕይወት ዐቢይ ጉዳዮችን (ዐቢይ ፍልስፍናዊ ርእሰ ጉዳዮችን) ውበቱ በሰመረ አቀራረብ የሚዳስስ ሆኖ ሲገኝ ነዉ፡፡ ለምሳሌ፣ እጅግ መሠረታዊ ከሆኑ የሰዉ ልጅ ዘወትራዊ ጥያቄዎች አንዱ የሕይወት ፋይዳ ነዉ፡፡ ይህ መሠረታዊ ጥያቄ ለዘመናት የዘለቀ የፍልስፍናም ብርቱ ጥያቄ ነዉ፡፡ አዳም ይህን ዐቢይ ፍልስፍናዊ ጥያቄ በተመለከተ #ከሰማይ የወረደ ፍርፍር; በተሰኘው የአጫጭር ልብወለዶች መድብል ውስጥ ከረሜሎች በሚለው የአጭር ልብወለድ ሥራው  ጥልቅ ዳሰሳ አቅርቧል፡፡
አንድን የሥነ-ጽሑፍ ሥራ የላቀ ሥራ እንዲሆን ከሚያበቁት ዐቢይ መስፈርቶች በግንባር ቀደምትነት የሚጠቀሰው መስፈርት የፈጠራ ሥራዉ ተጽፎ የቀረበበት ቋንቋ ደረጃ ነው፡፡ በዚህ ረገድ የአዳም የቋንቋ ሊቅነት የሚያስደምም ነው፡፡ ሌላው፣ አንድን የሥነ-ጽሐፍ ሥራ ታላቅ የሚያስብለው በእያንዳንዳችን አእምሮ ውስጥ እየተንከላወሰ የሚዘልቅ ብርቱ ጥያቄን ሲፈጥር ነው፡፡ የስንብት ቀለማት በተሰኘው የረዥም ልብወለድ መጽሐፉ አዳም እንዲህ ጽፏል፦
እስኪ አሳዩኝ ለአገራችሁና ለመዲናችሁ የነደፋችሁትንና የተዋጣላችሁን ሰናይ እቅድ? እሱንም ያስቀመጣችሁበት ስፍራ? ትናንት ካንደባለላችሁ ዠላጣ ወደ አማረው ኮረብታ መንገድ ቀይራችሁዋል? ይህቺ ቀበሌያችሁ ንፁህ ውሃ ቢያጥራት ወደ መልካም አዲስ ነገር ተጠምቃችሁ ማለፍ ስላልቻላችሁ ነዉ፡፡ የጎዳናዎቻችሁ ትራፊክ መብራት ነጋ ጠባ ባይበራ፣ የምትሄዱት ወደየት እንደሆነ የማታውቁ ራዕየ-ቢስ ስለሆናችሁ ነዉ፡፡ ትምህርት ቤቶቻችሁ ቢቆረቁዙና ቢፈርሱ፣ ዘር ማንዘራችሁ መደንቆር ቢወድ ነው፡፡ ከተማችሁ ብትሸት እንደዛ መሆኗን ስለሻታችሁ ነዉ፡፡ በየቤታችሁ መብራት ባይኖራችሁ ነፍሳችሁ ስለጨለመ ነው … ታዲያ ስለምን ቀደም ቀደም ብላችሁ ፀሐይ ገና ከማዘቅዘቋ ትተኛላችሁ? ራእይ ባይኖራችሁና በየዐልጋችሁ ላይ ተንጋላችሁ ኑሮን በፅላሎት ለመገላገል አቅዳችሁ ካልሆነ?
(አዳም፣ 2008፣ ገጽ 7)
አዳም ለመጀመሪያ ጊዜ የትራውማን (trauma) የሥነ-ጽሑፍ ይትባህል ለአገራችን ሥነ-ጽሑፍ ያስተዋወቀበት ሥራው ማሕሌት በተሰኘው የአጫጭር ልብወለዶች መድበል ውስጥ የቀረበው ማሕሌት የሚለው አጭር ልብወለድ ነው፡፡
የትራውማ ይትባህል የሚያተኩረው በልብወለድ ሥራው ውስጥ የተወከለው ገጸ-ባሕርይ በቀደመ ህልውናው የደረሰበትን አሉታዊ ገጠመኝ እና ይኸው አሉታዊ ትዝታ በግለሰቡ ዘላቂ ርዕዮት ላይ ሲፈጥር የሚስተዋለውን ዉስብስብ ሥነ-ልቦናዊ የሰብዕና ቀውስ የሚያስቃኝ የሥነ-ጽሑፍ ዘውግ ነዉ (ባሌቭ፣2018፣ ገጽ 360)፡፡
የሥነ-ልቦና ሳይንስ እንደሚነግረን በኑሮአችን የምናስተናግደዉ እያንዳንዱ ኩነት አሉታዊ አልያም አዎንታዊ ጥላዉን አጥልቶብን ያልፋል፡፡ ይህን ሁኔታ የምናስተዉለዉ አዳም በሳለልን ገጸ-ባሕርይ ማሕሌት አማካኝነት ነዉ፡፡ አዳም ከላይ በጠቀስኩት የልብወለድ ሥራዉ ዉስጥ እስጢፋኖስ ለተባለ ሠዓሊ ርቃኗን በመሆን በሞዴልነት እንድታገለግል አድርጎ የሳላት ዋናዋ ገጸ-ባሕርይ ከንፈረ ዉቧ ማሕሌት፣ በኮረዳነት እድሜዋ በሦስት ወንዶች ያለፈቃዷ የመደፈር ወሲባዊ ጥቃት ሰለባ የሆነችና ይኸዉ አሰቃቂ ገጠመኟ በዘላቂ ሕይወቷ ጥቃት ያደረሱባት ወንዶች አይነት መልክና ቁመና ያለዉን ሌላ ወንድ ሁሉ የመጥላት ሥነ-ልቦናዊ ህመም አድሮባት በመንፈስ ስቃይ ዉስጥ ተዘፍቃ እናገኛታለን። የመጀመሪያ ደፋሪዋ ፈርጣማ ክንድ ያለው ሸጋዉ የተባለዉ ባሏ ነዉ። ለሁለተኛ ጊዜ አስገድዶ የደፈራት ወንድ ሲደፍራት ነጭ የቆሸሸ ካናቴራ ለብሶ ነበር። ሦስተኛው ደፋሪዋ ወንድ (ጌታዋ) ዐይነ-ልም ነበር፡፡
“አንድ መቶ ብር እሰጥሻለሁ፡፡ ሥዕል ልሣልሽ?” አላት፣ ጌታዋ ሳይኖር እቤት መጥቶ… እስጢፋኖስ፡፡
“እንዴት?”
“ራቁትሽን ትሆኝና እሥልሻለሁ፣፡፡ ሞዴል ትሆኛለሽ ማለት ነዉ፡፡”
እንደ ጌታዋ ሊደፍራት በማታዉቀዉ ነገር የሚያታልላት መሰላት … እስጢፋኖስ። በሲጋራ ይሁን ወይም ሲፈጠር የጠቆረ ወፍራም ከንፈር አለዉ፡፡ ዐይኖቹ ትናንሽ ናቸዉ፣ ሲስቅ ህፃን ልጅ ይመስላል፡፡
ብዙ ጊዜ ለጓደኛዉ ለጌታዋ፣ ስለ ፈላስፋ ሠዓሊዎች ያወራለታል፡፡ ሥዕሎች ያሳየዋል።
“የሥዕል አስተማሪ ነኝ፡፡” አላት አንድ ቀን ሳትጠይቀዉ፡፡
“ሞዴል” ሆነችለት፡፡
“እስጢፋኖስ ቢስም … እንደ መጀመሪያ ባሌ ይናከሳል … ወይስ … እንደ አጎቴ ጓደኛ እንደ ጌታዬ ትዝም አይለዉ? ከንፈሩ ግን ያስጠላል” … በሐሳቧ፡፡
ቀርቦ አንዳንድ ቀን ሲያወራት ወደ አፏ … ይዘገንናታል … ጥርሶቹ ላይ የተደረተዉ ጥቀርሻ፡፡ ለመቶ ብሩ እንጂ፣ በብርድ ድንክ ወንበር ላይ ለአንድ ሰዓት መጎለት ያስቀይማታል፡፡
አሰሪዋ ዘመነ ደግሞ እየሣቀ “ሞዴል” እንድትሆንለት ፈቅዶለታል፡፡ ምናልባት ሳታይ ከጀርባዋ እስጢፋኖስን ደስ ለማይል ዓላማ እንዲዘጋጅ ጠቅሶትም ይሆናል፡፡  
ከወንበር ላይ ፈንግሎ ሲያያት ለማወቅ ብትጠብቅ ቀረ፡፡ ሦስት ቀን አለፈ፡፡ እስጢፋኖስ ትንሽ እንኳን አልዳዳዉም፡፡
ወደአለበት አቅጣጫ ተመለከተች፡፡ መላጣዉን የሸፈነበት ባርኔጣ ወደ ኋላዉ ተንሸራቷል፡፡ ግንባሩን አልቦታል፣ ከመነፅሩ ጀርባ ያሉት ትናንሽ ዐይኖቹ ፈዘዋል፡፡
“ምን አይነት ወንድ ነው የምትሥልልኝ? የምስመው ወንድ?”
“ነገርኩሽ’ኮ!”
“ዐይኑ ምን ይመስላል?”
“ዐይኑን ስለሚጨፍነው አይታወቅም፡፡”
“ሠውነቱ ጡንቻማ ነዉ?”
“አዎ!”
“ለምሳሌ ክንዱ ላይ ልዩ ምልክት ይኖረዋል?”
“ምን አሳሰበሽ?”
“እንዲሁ፡፡”
“የክትባት ጠባሳ አለው፡፡”
በጥፍሮቿ ጭኗን ቧጠጠች፡፡ አላያትም፡፡
“ፀጉሩስ?”
“ረዥም፡፡” እጁን ከፍ አድርጎ አሳያት፡፡
“አልወደድኩትም፡፡”
“ለአንቺ እኮ አይደለም ለአድናቂ ነዉ፡፡”
“ሌላ ወንድ ጠፋ እንዴ?”
ተደናገጠ፡፡ ግሩምቡድ ላይ ተቀምጦ ወደ እሷ እያየ፡
“ንገሪኝ አንቺ፡፡”
“ስለማላውቀው ነዉ የጠየቅሁህ፡፡”
“ለምሳሌ … ልብስ ቢለብስ?”
“ምን?”
“ካናቴራ፡፡”
“ምን አይነት?” … በፍጥነት፡፡
“ነጭ የቆሸሸ!”
“አይቻልም!”
ተነስቶ ቆመ፡፡ ከጥቂት ጊዜ በኋላ ወደ ሸራው ጀርባ ጠፋ፡፡
“ሌላ ወንድ ሐሳብህ ዉስጥ የለም?” አለችዉ፡፡
“ምንም፡፡” ጸጥ አለች፡፡ አፏን አሞጥሙጣ እንዳንጋጠጠች እንባ በጉንጮቿ ወረደ፡፡
“ማሕሌት! … ማሕሌት!”
ዞር ብላ አየችው፡፡
“ምን ሆንሽ?”
“ምንም፡፡”
“ማልቀስ? እባክሽን እንዳትጠርጊዉ … ግን ምን ሆነሽ ነዉ?”
“ዕንባዬ ምን ያረግልሃል?”
“ያላሰብኩትን በአጋጣሚ አመጣሽዉ ታንኪዩ!”
“የሚስመኝ ወንድ ያለቅሳል?”
“ለምን?”
“ለምን እኔ አለቅሳለሁ?”
“ፍቅር ሴት ላይ ይጠናል ይባላል … ማረጋገጫ ባይኖረውም … ሴት ስታለቅስ ደግሞ ታሳዝናለች፡፡”
“ሁለታችንም እናልቅስ?”
“ይቅር አታልቅሱ፡፡”
“አይ የለም ላልቅስ፡፡ ሥዕሉ ላይ እንኳን ላልቅስ፡፡”
“አታለቅሽም”
የሚሣለው ሥዕል በሐሳቧ ዉስጥ እየዋኘ መጣባት፡፡ ነጭ ካናቴራ የለበሰ ወንድ በወፍራም ክንዶቹ አቅፏት፣ እጆቿን ይዞ፣ ራቁቷን ተቀምጣ፣ ጭኖቿን አቆላልፋ ሸጉጣ … በሌላ እጁ ፀጉሯን እየጎተተ … ከንፈሮቿን ለመሳም … ጥርሷን … ጉንጯን … አንገቷን …
ሸራው ፊት ለፊት ሄዳ ቆመች፡፡ እንዳለች ሥሏታል፡፡ ሰዉዬዉ እንደ ባሏ ጡንቻማ … እንደ ደፈራት ወንድ ነጭ ካኔቴራ … እንደ ጌታዋ ትናንሽ ዐይኖች አሉት፡፡ ሥዕሉን ከተደገፈችበት ጣለችው፡፡
“ምን ነካሽ!?” አላት እስጢፋኖስ፡፡
ሊይዛት እየሮጠ መጣ፡፡ ብርድ ልብስ እላዩ ላይ ወረወረችበት፡፡ ወዲያው የሥዕሉን ሸራ በምስማር ከተያያዘበት የጣውላ ጠርዝ እስከ መኻሉ ድረስ በአንድ ስንዘራ ሸረከተችው፡፡ ሌላም ቀዳዳ … ሌላም ቀዳዳ …ሌላም፡፡ ብርድ ልብሱን ከላዩ ላይ ጥሎ ወገቡን ይዞ አያት፡፡
አንድም ቃል ሳይነጋገሩ ለባብሳ ወጣች፡፡
(አዳም፣ 2002፡ ገፅ 99-102)
ከአዘጋጁ፡- ጸሐፊውን በኢሜይል አድራሻው፡- This email address is being protected from spambots. You need JavaScript enabled to view it. ማግኘት ይቻላል፡፡

Read 1510 times