Sunday, 10 October 2021 00:00

"አንድ ብር"

Written by  ደሳለኝ ሥዩም
Rate this item
(4 votes)

 ከመድከሙ የተነሣ ፊቱ ተጨማድዷል፤ ፊቱም ከመጨማደዱ የተነሣ የግንባሩ ሰምበሮች የተፈተለ ጅራፍ አስመስለውታል። ታክቷል፤ የተጓዘው መንገድ ተጫውቶበት፣ ሰውነቱ ሁሉ ዝሏል፡፡ መኝታ ፍለጋ የሚያንቀዋልላቸው ዐይኖቹ አንድ ግቢ ላይ አረፉ፡፡ በግቢው ውስጥ አንድ አሮጌ የጭቃ ፎቅ ይታያል፡፡ ከሥረኛው ወለል በላይ ሁለት ወለሎች አሉት፡፡ ሥረኛው ወለል ምግብ ቤት ነው፤ የአልኮል መጠጫ ስፍራም አለው፡፡ ሥጋ ቤትም ይታያል፡፡  
የድሮ ሙዚቃ ይጮሃል፤ ሙዚቃው የተከፈተበት ቴፕ ጥርስ ምላሱ ያለቀ ስለነበር ከቴፑ የሚወጣው ዜማ በኮረኮንች ላይ እንደሚሄድ ጋሪ የሚደነቃቀፍ ነው። ጩኸቱ ብቻ ሰላም ይነሣል፡፡ እሱ ደግሞ ማረፍን ፈልጓል፡፡ አልጋ ላይ ዘፍ ማለት፣ የደከመ ሰውነቱ እስኪቀልለው ድረስ፡፡
ምግብ ቤቱ በር ላይ አንዲት አሮጊት ተቀምጠዋል፡፡ የብርጭቆ ቂጥ የመሰለ መነጽራቸውን አፍንጫቸው ላይ ደግነው ወደ እሳቸው እየመጣ ያለውን ሰው አስተዋሉት፡፡ ቀለላቸው፡፡ ዛሬ አልጋቸው ባዶ እንደማያድር ጠርጥረዋል፡፡ ወዲያውም የሚያስፈልጋቸውን ነገር ከእሱ እንደሚያገኙ በብዙ ተስፋ ተሞሉ፡፡ ፈገግ ለማለት አሰቡና ጥርስ የከዳው ፍም የመሰለ ድዳቸው እንዳይታይባቸው ሐሳባቸውን ቀየሩ፡፡
‹‹እንዴት ዋሉ እሜቴ!›› ሰውየው ነው፤ ድካም ባዛለው አንደበቱ፡፡
‹‹ይመስገን ደኅና! ምን እንታዘዝህ››
‹‹ሌሎች ወጣቶች የሉም እሜቴ?››
‹‹የለም እንዲያ አይነት ነገር እኛ ሆቴል የለም፣ ሳይመሽብህ ሌላ ቦታ አፈላለግ›› በስጨት አሉ፡፡ ህልማቸው የከሰመ መሰላቸውና ውስጣቸው መብከንከን ጀመረ፡፡
‹‹የለ የለ እሜቴ! እርስዎን እናቴን የግልብጥ ማዘዝ እንዳይሆንብኝ ብዬ … የትህትና ነው እሜቴ … አልጋ ፈልጌ ነው››
‹‹አዲያ ምን ችግር አለ፤ ሥራዬ አይደለ! እዚህ ቁጭ ብዬ ደንበኞችን ነው የምጠብቀው፡፡ አይዞህ ጥሩ ማረፊያ አለን፣ ሰውነትህም የዛለ ይመስላል፣ ውሃ እናሞቅልሃልን፡፡ ከላይ የምታየው ሁለቱ ፎቅ ሙሉ መኝታ ነው››
ሰውየው ፈገግ አለ፡፡ ማረፍ ፈልጓል፡፡ ቀና ብሎ ሁለቱን ፎቆች ተመለከታቸው፡፡ አሁን አጠገቡ ስለነበር ቤቱ በጣም ያረጀ መሆኑን አስተዋለ፡፡ አንዳንዱ የግድግዳው ክፍል አይጥ የናዳቸው ጉድጓዶችም የሚታዩበት ነው፡፡ ተባይም እንደማይጠፋው ያስታውቅ ነበር፡፡
‹‹ገብቼ ማየት እችል ይሆን እሜቴ?››
‹‹ምን ችግር! ባይሆን ሒሳቡ ቅድሚያ ነውና  ከፍለኸኝ ወደ ፎቁ መውጣት ትችላለህ፡፡ ቁልፎቹ ያው በሮቹ ላይ ናቸው። ሁሉንም ክፍል አይተህ ያሰኘህ ላይ ማረፍ ትችላለህ››
ተጠራጠረ፡፡ ክፍሎቹ ንጹህ ላይሆኑ ይችላሉ፤ ፍራሹ የበሰበሰ፣ አንሶላው የበከተ፣ ትኋን የሚርመሰመስበት፣ አይጦች የሚዘሉበት ቢሆንስ? እንዴት ሊያርፍ ይችላል?
 ‹‹እሜቴ ክፍሎቹ ባይሆኑኝስ?››
‹‹ታዲያ ምን ችግር ብርህን እመልስልሃለኋ!››
ተስማማ፡፡ የአንድ አልጋ ዋጋ አንድ ብር ነበር፡፡ አንድ ብሩን ቅድሚያ ለሴትየዋ ሰጥቶ ክፍሎቹን ሊያይ በሚንቋቋው የእንጨት ደረጃ ወደ ፎቁ አዘገመ፡፡
ሴትየዋ አንድ ብሩ እጃቸው እንደገባ ወዲያውኑ የብርጭቆ ቂጥ ፊት ለፊት የተደገነባቸውን ዐይኖቻቸውን አንቀዋለሉ። ጥግ ላይ የማገዶ እንጨት የሚፈልጥ ረድ ታያቸው፡፡ በእጃቸው ምልክት ሰጥተው ጠሩት፡፡ ሲንከወከው መጣ፡፡
‹‹ቶሎ በልማ! ያ የሥጋ ቤቱ ሰው አለ ዛሬ ገብቷል?››
ረዱ እጅ እንደመንሳት እየቃጣው ትዕዛዛቸውን ይጠብቅ ስለነበር ፈጣን ምላሽ ነበር የሰጣቸው፡ ‹አዎን እትዬ፣ ገብቷል ሊታጠብ ዞር ብሎ ነው ወደ ጓሮ››
‹‹እንግዲያው ይኸውልህ ይህንን ብር ያዝና ከትናንት በፊት ኪሎ ሥጋ በዱቤ ወስጄ ነበርና ሒሳብህ ነው ብለህ ስጠው ቶሎ በል!››
ረድ ሆዬ ሲንከወከው እንደመጣ ሲንከወከው የታዘዘውን ሊፈጽም ወደ ጓሮ ሄደ፡፡ አይኑን እዚህና እዚያ ሲያሽከረክርም ቦርጫሙ ስጋ ሻጭ፣ የሽንት ጨው የቀረጣጠሰውን የመጸዳጃ በር ከፍቶ ሲወጣ አየው፡፡ ቦርጩን እያሻሸ (አለመጉደሉ አሳስቦት ይመስል) ወደ እሱ እየመጣ ያለውን የእሜቴ ረዳት ተመለከተ፡፡
‹‹ጋሽዬ እትዬ እንዳሉት የዱቤ ስጋ ወስጄ ነበርና፣ ሒሳቡ እነሆ አንድ ብር ብለዋል›› አለ ረዱ፡፡
ቦርጮ ፊቱ ፈካ፡፡ እንደ መሳቅ እየቃጣው ‹‹ውይ ገዳይ ሲደርስ አዳኝ ይደርስ የሚባለው ለካ እውነት ነበረ፡፡ እትዬን አመስግንልኝ፡፡ ብሩም ደርሶኛል በልልኝ፡፡ ግን ሮጥ ብለህ ይሄንን ብር ለሰው ታደርስልኛህ››
‹‹ለማን ጋሼ?››
‹‹ይኸውልህ ከትናንት በፊት በሬውን ስገዛ አንድ ብር ጎድሎኝ ከሰሞኑ እሰጥሃለሁ ብዬ ነው በሬውን ከገበሬው ያመጣሁት፤ እና እንዲህ በለው .. እግዚሐር ይስጥልኝ፤ ብድር መላሽ ያድርገኝ፣ ይኸውና ከትናንት በፊት የጎደለኝ አንድ ብር በለው››
ረድ እንደለመደው እየሮጠ ወጣ፡፡ ወደ ገበሬው ቤት በፍጥነት ሮጠ፡፡ ብዙ አልፈጀበትም፡፡ ብዙም አይርቅምና፡፡ የገበሬው ግቢ በብዙ በሬዎች የተሞላ ነው፡፡ ገበሬው ሥራ ላይ ነበር፡፡ ጭድ ከክምር ላይ እያወረደ ለበሬዎቹ እየመገበ ነው፡፡ ድንገት ቀና ሲል ወደ እሱ እየሮጠ የሚመጣውን የእትዬ ረዳት አስተዋለ፡፡ ምን ችግር ተፈጥሮ ይሆን ብሎ ስጋት ብጤ ልቡን ጓጎጠው፡፡ ትንፋሹ ቁርጥ ቁርጥ የሚለው የእሜቴ ረድ አጠገቡ እንደደረሰ፣ ከቁርጥራጭ ትንፋሹ ጋር እየታገለ፤
‹‹ጋሼ ባለስጋ ቤቱ እንዳሉት፣ ከትናንት በፊት ከእርስዎ በሬ ስገዛ የጎደለብኝንና ከሰሞኑ እከፍላለሁ ያልኩትን አንድ ብር እነሆ … እግዚሐር ይስጥልኝ፣ ብድር መላሽ ያድርገኝ ብለዋል››
ገበሬው ፈገግ አለ፡፡ እጁን እያረጋገፈ ወደ ረዳቱ ተጠጋ፡፡
‹‹አንተንም እግዚሐር ያክብርልኝ፡፡ ብሩም ደርሶኛልና አመሰግናለሁ በልልኝ፤ ይሄንን ብር ግን ለሰው ታደርስልኛለህ››
‹‹ወደየት  ጋሼ!››
‹‹ይኸውልህ ልጄ፤ ከሶስት ቀን በፊት ይሄንን ክምር ጭድ ስገዛ፣ አንድ ብር ጎድሎኝ ከሰሞኑ እከፍልሃለሁ ብዬ በዱቤ ነው የገዛሁት፡፡ የሰውየው ቤት እዚህ ቅርብ ነው፤ እንዲህ ብለህ ስጠው …. ከሶስት ቀን በፊት የነበረብኝን እዳ እነሆ፤ እግዚሐር ያክብርልኝ››
ረድ እንደለመደው እየሮጠ ወጣ። የባለጭዱም ቤት ሩቅ አልነበረም፡፡ ባርኔጣውን እንዳደረገ እዛፍ ስር ቁጭ ብሎ አገኘው፤ ባለጭዱን፡፡
‹‹አንተ የእትዬ ረዳት አይደለህምን! ምነው በሰላም እትዬ ደህና አይደሉም?››
 ሰውየው በጥርጣሬ ቀና ብሎ ረዱን አየ፡፡ ረዱ ግን ፈገግ ብሎ ቀረበውና ‹‹የለም ጌታዬ ከገበሬው ዘንዳ ተልኬ ነው፡፡ ከሶስት ቀን በፊት ጭድ ስገዛ አንድ ብር ጎድሎኝ ከሰሞኑ እከፍላለሁ ብዬ ነበርና ይኸው አንድ ብሩ፤ እግዚሐር ይስጥልኝ ብለዋል››
‹‹ነው እንዴ ኧረ ተባረክ በለው፡፡ ብሩ ደርሶኛል በጣም አመሰግናለሁ በልልኝ… ይሄንን ብር ግን ለሌላ ሰው ታደርስልኛለህ››
‹‹ለማን ጋሼ!››
‹‹ለእትዬ ነው የምትሰጥልኝ፡፡ ሣምንት ለታ ተሆቴላቸው ምሳ በልቼ አንድ ብር ጎድሎኝ ሳልከፍል ከሰሞኑ እከፍላለሁ ብያቸው ነበርና ለእሳቸው ስጥልኝ፡፡ እግዚሐር ይስጥልኝ ብለህም ምስጋናዬን አድርሳቸው››
ረድ እንደለመደው ሲሮጥ ሄደ፡፡ እሜቴ ከተቀመጡበት አልተንቀሳቀሱም፡፡ ብሩን ከእነ መልዕክቱ አደረሳቸው፡፡  ሴትየዋ ብሩን በእጃቸው እንደያዙ ቀና አሉ፤ ወደ ፎቁ፡፡ ሰውየው በተስፋ መቁረጥ ወደ ምድር ሲወርድ አዩት፡፡
‹‹ምነው አልሆነህም ልጄ?!››
‹‹ክፍሎቹ ለማረፊያ አይሆኑም፤ ይቅርብኝ››
‹‹ታዲያ ምን ችግር .. ይኸው አንድ ብርህ … ደኅና ዋል››   




Read 1787 times