Print this page
Friday, 01 October 2021 00:00

ብልጽግና ሥልጣን በማጋራት አልተቻለም!

Written by  ኤልያስ
Rate this item
(0 votes)

“በምርጫ ያላሸነፉ ተቃዋሚዎችን መሾም ህገ መንግስቱን መጣስ ነው”


  ወዳጆቼ፤ በአዲሱ ዓመት የመጀመሪያ ወር ላይ እንገኛለን፡፡  በዚያ ላይ አዲስ መንግስት በመመስረት ሂደትም ላይ ነን፡፡ ዓለም ሁሉ ዓይኑን ኢትዮጵያ ላይ አድርጓል። ያለ ምክንያት አይደለም (ተዓምር እየተሰራ ነው!) ከጥቂት ቀናት በፊት  የአዲስ አበባ አስተዳደር አዲስ ካቢኔ አቋቁማል፡፡ የአማራ ክልል፣የኦሮሚያ ክልልና ሌሎችም ክልሎች አዳዲስ መንግስትና  አስተዳደር መስርተዋል የፊታችን ሰኞ ደግሞ አዲሱ የፌደራል መንግስት እንደሚመሰረት ይጠበቃል፡፡ በነገራችን ላይ በአዲሱ የመንግስት ምስረታ ሥነ ስርዓት ላይ ከ40 የማያንሱ የዓለም መሪዎች ይታደማሉ ተብሏል፡፡ የዘንድሮን የአዲስ መንግስት ምስረታ ልዩ የሚያደርገው የተቃዋሚ ፓርቲ አመራሮች በመንግስት አስተዳደር ውስጥ መሾማቸው ነው፡፡ ለአብነትም በአዲሱ  የከተማዋ ካቢኔ ውስጥ  ሁለት የተቃዋሚ አመራሮች መካተታቸውና የከተማዋን ሁለት ቢሮዎች እንዲመሩ መሾማቸው ታውቋል፡፡
 የምዕራብ መንግስታትና አንዳንድ ፅንፈኛ ተቃዋሚዎች፤ አገሪቱን ለቀውስ ይዳርጋታል ሲሉ ያሟረቱባት አገራዊ ምርጫ ያለ ኮሽታ በሰላም ነበር የተጠናቀቀው፡፡ ያኔ ታዲያ   ኢትዮጵያ አሸንፋለች!! ሟርተኞችንና ምዕራብያውያንን ኩም አድርጋቸዋለች። አሁን ደግሞ ተቃዋሚዎች ባላሸነፉበት የአዲስ አበባ ከተማ መስተዳድር ም/ቤት ውስጥ በካቢኔ አባልነት ለመጀመሪያ ጊዜ ተካትተዋል። ይታያችሁ… የኢዜማ አመራር አባል የሆኑት አቶ ግርማ ሰይፉ፣ (ብቸኛው  ተቃዋሚ በሚል ይታወቁ ነበር!) የአዲስ አበባ ኢንቨስትመንት ቢሮ ሃላፊ ተደርገው ተሹመዋል፡፡ የአብን ም/ሊቀመንበር አቶ የሱፍ ኢብራሂም ደግሞ የመንግስት ንብረት አስተዳደር ባለስልጣን ሆነው ተሹመዋል። በኢትዮጵያ የፖለቲካ  መልክአ ምድር አዲስ ክስተት  ይመስለኛል። እንደገና እደግመዋለሁ… በዚህ የስልጣን ማጋራት አዲስ የፖለቲካ ባህል ኢትዮጵያ አሸንፋለች፡፡
የፊታችን ሰኞ በሚመሰረተው አዲስ የመንግስት አስተዳደር ውስጥ ብዙም ባይሆን ጥቂት “ሰርፕራይዝ” ሊኖር እንደሚችል ይጠበቃል፡፡ ባይኖርም ግን እስካሁን የሰማነው ራሱ ከበቂ በላይ ነው፡፡  የተቃዋሚ አባላትን በካቢኔው ያካተተው የከተማው አስተዳደር ብቻ አይደለም፡፡ የአማራ ክልላዊ  መንግስት ሁለት የተቃዋሚ አባላትን በክልሉ የመንግስት ቢሮዎች በሃላፊነት ሾሟቸዋል። ለነገሩ የጠ/ሚኒስትር ዐቢይ አስተዳደር፣ ባለፉት ሶስት የሪፎርም ዓመታት፣ ለተቃዋሚ ፓርቲ አመራሮች ሥልጣን የማጋራት (power sharing) ልምምድ ሲያደርግ ነው የቆየው። ለአብነት ያህል ለ30 ዓመታት ገደማ በተቃዋሚ ፓርቲ መሪነታቸው የሚታወቁት ፕሮፌሰር በየነ ጴጥሮስ ዓምና፣የኢትዮጵያ ፖሊሲ ጥናትና ምርምር ተቋም ዳይሬክተር ሆነው ተሹመዋል (የዛሬን አያድርገውና አቶ በረከት ስምኦን ነበር የሚመሩት)፡፡ የህወኃት መስራች የነበሩትና በአውሮፓ ለሶስት አስርት ዓመታት በስደት ኖረው በለውጡ
ማግስት ወደ አገር ቤት የተመለሱት የትግራይ ዲሞክራሲያዊ ንቅናቄ ፓርቲ ሊቀ መንበር ዶ/ር አረጋዊ በርሄ፤ ደግሞ የታላቁ የህዳሴ ግድብ የገቢ ማሰባሰቢያ ፅ/ቤት ዳይሬክተር ሆነው መሾማቸው ይታወቃል፡፡ (ፅ/ቤቱ በህወኃት አባል ነበር የሚመራው!) ከዚህ በተጨማሪም፣ የተለያዩ የተቃዋሚ ፓርቲ አመራር አባላት በተለያዩ የመንግስት ተቋማት ውስጥ በቦርድ አባልነት መሾማቸው አይዘነጋም። መቃወም የሚታወቁት ፕ/ር መረራ ጉዲናም የኢቢሲ የቦርድ አባል ሆነው ተሹመው ነበር፡፡ (ተሳስተው እንኳን አውርተውት ባያውቁም!) ከዚህ አንጻር ስልጣን የማጋራቱ ባህል ዛሬ ሳይሆን በሪፎርሙ ወቅት ነበር የተጀመረው ማለት ይቻላል፡፡ (ያመሰገነ የለም እንጂ!)
ወዳጆቼ፤ ለተቃዋሚ ፓርቲ (ያውም በምርጫ ሳያሸንፉ) ሥልጣን በማጋራት የፖለቲካ ባህል፣ ኢትዮጵያ በአፍሪካ ፈር ቀዳጅ ሳትሆን አትቀርም፡፡ ምን በአፍሪካ ብቻ… በአሜሪካስ ቢሆን? በስልጣን ላይ ያለው የባይደን ዲሞክራቲክ ፓርቲ፣ ከሪፐብሊካን ፓርቲ አባላት የመንግስት ሃላፊ የሚሾም ይመስላችኋል? (እስካሁን አላደረገውም፤ ወደፊትም አያደርገውም!!) አሁንም አደግመዋለሁ… በዚህ በዚህ አስደናቂ የፖለቲካ ሪፎርም ያሸነፈችው ኢትዮጵያ ናት!!
የፊታችን ሰኞ በሚከናወነው የአዲስ መንግስት ምስረታ ላይ የሚታደሙ የአገራት መሪዎች በመዲናዋ የሚገኙ ድንቅ ፓርኮችን ይጎበኛሉ ተብሎ ይጠበቃል (አንድነት ፓርክን ጨምሮ)  የ“ፖለቲካ በፈገግታ” አምድ ይህን ለአፍሪካም ሆነ ለአገራችን እንግዳ የሆነ ሥልጣን የማጋራት (power sharing) ባህል፤ “የክፍለ ዘመኑ ታላቅ የፖለቲካ ሪፎርም” የሚል ስያሜ ሰጥቶታል- በእውነትና በድፍረት ላይ ተመስርቶ። የስያሜው (ኮፒ ራይቱ የአምዱ ነው!) የሆነስ ሆነና የጦቢያ የፖለቲካ ተንታኞች፤ አክቲቪስቶች፣ ምሁራንም… ባለሃብቶች ይህን ያልተለመደ ሥልጣን የማጋራት ባህል እንዴት አገኙት? ራሳቸው የገዢው ፓርቲ  አባላትና ደጋፊዎችስ? በማዕቀብ የሚያስፈራሩን የምዕራብ አገራት መንግስታትስ? (ሰርፕራይዝ እንደሚሆንባቸው ቅንጣት አልጠራጠርም!) 6ኛው ብሔራዊ ምርጫ ከተካሄደ አገሪቱ ወደ ቀውስና ምስቅልቅል  ውሰጥ ትገባለች በማለት፣ ምርጫው ለሌላ ጊዜ እንዲተላለፍ ሲወተውቱና ተፅዕኖ ለማሳደር ሲሞክሩ የነበሩት ምዕራባውያን፤ በምርጫው ያሸነፈው ብልጽግና (እነሱ በማዕቀብ የሚያስፈራሩት!) ለተቃዋሚዎች ሥልጣን እያጋራ መሆኑን ሰምተው ይሆን? ማን ነግሯቸው! (እነ CNN ይሄን አይዘግቡም!) ለመሆኑ የኢትዮጵያን ገፅታ የሚያጠለሽ የተዛባ መረጃና ፕሮፓጋነዳ ሲያሰራጩ የከረሙ ሌሎች ዓለማቀፍ ሚዲያዎችስ  ይህን ያልተለመደ ስልጣን የማጋራት የፖለቲካ ባህል ዘግበውት ይሆን? (እኔንጃ!)
ይሄ ሥልጣን የማጋራት አዲስ ባህል፣ ከሁሉም በላይ በቀጥታ የሚመለከታቸውና የሚጠቅማቸውም ተቃዋሚ ፓርቲዎችን ይመስለኛል፡፡ (የተሾሙትንም ያልተሸሙትንም!) እናም ሁለቱ የተቃዋሚ ፓርቲ አመራሮች በአዲሱ የአዲስ አበባ አስተዳደር ውስጥ ሹመት ማግኘታቸው በእጅጉ ያስደስታቸዋል ብዬ ተስፋ አደርጋለሁ። የደስታ መግለጫ ያወጣሉ ብዬም እጠብቃለሁ፡፡ (ሆኖ እኮ አያውቅም!) በዚህ ብዙዎች በኢትዮጵያ ፖለቲካ ተስፋቸው ማንሰራራት እንደሚጀምር እምነቴ ነው፡፡ በርግጥ ይሔ ባህር ማዶ ሆነው “ኢትዮጵያ ፈርሳለች” የሚል የሟርት መግለጫ እየሠጡ የሚገኙትን ተወዛጋቢ ፖለቲከኞች አይመለከትም፡፡ (ይሄ ሁሉ ኢትዮጵያዊ የሚዘምተው አገር እንዳትፈርስ መስሎኝ?!) ወዳጆቼ፤ አገር እንዳትፈርስ ተጠንቀቁ ማለት ያባት ነው። የመፍትሄ ሃሳቦችን መሰንዘርም ከጤነኛ ፖለቲከኛ የሚጠበቅ ነው፡፡ በደፈናው “ኢትዮጵያ ፈርሳለች” ማለት ግን  የለየለት ዕብደት ነው። ይሄን በመናገራቸው ለአገራቸው ወይም ለኢትዮጵያውያን ምን ሊፈርዱ አስበው ይሆን?
እውነት ለመናገር በዚህ ወቅት እንደ  እናት  አገር ኢትዮጵያ፣ መከራውን የበላ ማንም የለም፡፡ አንዱ አማጺ ቡድን ተነስቶ  “ኢትዮጵያን ለማፍረስ ሲኦልም መግባት ካለብን እንገባለን” ሲል ይደነፋል፡፡ ሌላው ደግሞ ቁልጭ ብላ ያለችውን አገር ፈርሳለች ብሎ ያረዳናል፡፡ (ቅዠቱን! እኒህ ወገኖች አልገባቸውም እንጂ ኢትዮጵያ ፈርሳለች ማለት እኮ፤ ኢትዮጵያውያን ፈርሰዋል ማለት ነው፡፡ (“ፈርሳችኋል” እያሉን ነው!) እኛ ግን መልሳችን አንድና አንድ ብቻ ነው! “ፈጣሪዋና ጀግኖች ልጆቿ የት ሄደው ነው ኢትዮጵያ የምትፈርሰው!?”  የሚል ነው፡፡
ወደ ጀመርኩት የፖለቲካ አጀንዳችን ልመልሳችሁ፡፡ ተቃዋሚዎች በሰሞኑ አዲስ  የስልጣን ማጋራት ባህል ምን ተሰምቷቸው ይሆን? መቼም ሁሉም ይደግፉታል ብዬ አልጠበቅም፡፡ ሁሉም ይቃወሙታል ብዬም አላስብም ከአንድ የተቃዋሚ ፓርቲ አመራር የሰማሁት አስተያየት ግን ተስፋ የሚያስቆርጥ ሆኖ አግኝቼዋለሁ። “ተቃዋሚዎች በመንግስት አስተዳደር ውስጥ መካተታቸው፣ በመንግስት ሃላፊነት መሾማቸው፣ የስልጣን ማጋራት ባህል መጀመሩ… ለኢትዮጵያም ሆነ ለፖለቲካ ባህላችን ምንም የሚፈይደው ነገር የለም” ብለው አረፉት፡፡ (ተስፋ ቆርጠው ተስፋ ያስቆርጣሉ!) በርግጥ  ከመንግስት የመጣውን ነገር ሁሉ ካልተቃወሙ፣ የተቃዋሚነት ሚናቸው ወይም መክሊታቸውን የተነጠቁ የሚመስላቸው አንዳንድ  ተቃዋሚ ፓርቲዎች  አሉ። እኒህ ዓይነቶችቹ በስህተት የመንግስት ሹመት ቢያገኙ መቃወማቸውን አጧጡፈው የሚቀጥሉበት ይመስለኛል። አገር አስተዳደሩ፤ ህዝብ አገልግሉ ሲባሉ፣ ካልተቃወምን ብለው የሚቀውጡ  ፓርቲዎችን አይጠፉም እኒህ  የተቃዋሚ ፓርቲ አመራር ለመንግስት ሹመት አለመመረጣቸው ቢያበሽቃቸው አይገርመኝም፡፡ ግን አይጠፉም፡፡ መፍትሔውም አይደለም የተቃዋሚ ፓርቲ አመራሮች የተሾሙት በምን መስፈርት እንደሆነ መጠየቅ የአባት ነው፡፡ በደፈናው መቃወምና ማጥላላት ግን ትዝብት ላይ ይጥላል፡፡ (በአበሽኛ “ምቀኝነት ያስመስላል!” ያስብላል)  በሌላ በኩል፤ በገዢው ፓርቲ ብልፅግና መፍረድም አይቻልም፡፡ ወደ 100 ለሚጠጉ ተቃዋሚ ፓርቲዎች በሙሉ ሥልጣን ሊያከፋፍል አይችልም (ከየት አምጥቶ!) ለዚህ ነበር ጠ/ሚኒስትሩ ተሰባሰቡ ያሉት!
እኔ ተቃዋሚ ብሆን ግን በደፈናው ከመቃወም ይልቅ  ቢያንስ “በህዝብ ላልተመረጡ የተቃዋሚ ፓርቲ አባላት ሹመት መስጠት ህገ መንግስቱ አይፈቅድም  ብዬ ብልፅግና ፓርቲን ልከሰው እችላለሁ። (ባያዋጣም!) በነገራችን ላይ ለተቃዋሚ ፓርቲዎች የተሰጠው ሹመት፤ እንድም ተቃዋሚዎችን ከመንግስት ሃላፊነት ጋር የሚያስተዋውቃቸው ሲሆን አንድም ደግሞ ራሳቸውም የሚፈተኑበት ይሆናል። ለምሣሌ የኢዜማው ተወካይ፣ የአዲስ አበባ ኢንቨስትመንት ቢሮን እንዴት ነው የሚመሩት?  (“ከበሮ በሰው እጅ ሲያዩት….” እንዳይሆን!)  የአብን ተወካዩስ የመንግስት ንብረት አስተዳደርን እንዴት ያስተዳድሩታል? በዚህ አጋጣሚ መንግስትን ሲተቹ የኖሩ ተቃዋሚዎች ሰርተው ያሳዩናል ማለት ነው፡፡ (መተቸትና መስራት ለየቅል ነው!) መልካም  የመንግስት ምስረታ!

Read 1389 times