Sunday, 17 October 2021 00:00

“ደንጊያና ቅል ተላግቶ፣ ዜጋና ሹም ተሟግቶ” የምንልበት ወቅት አይደለም።

Written by 
Rate this item
(3 votes)

 ከእለታት አንድ ቀን፤
በፈረንሳይ አገር ፓሪስ ውስጥ ዛሬ አምሮ የቆመውን ቱር ኤፌል (ኤፍል ታወር) የተባለውን ሐውልት ዲዛይን ለመስራት ጥንት ብዙ የቅርጽ ባለሙያዎች ተወዳድረው ነበር ይባላል።
ከተወዳደሩት መካከል እጅግ ታዋቂ የሆነ የህነፃ ባለሙያም ይገኝበታል።
ከቀናት በኋላ ውጤቱ ሲመጣ አሸናፊ የሆነው አንድ እስከዚህም በፈረንሳይ የማይታወቅ ወጣት ልጅ ነበር። ሐውልቱ ፓሪስ ውስጥ አምሮ ተሰራ!
 ያ ታዋቂው ቀራፂ በውጤቱ በጣም ስሜቱ ከመነካቱ የተነሳ በጭራሽ ወደ ከተማ ላለመውጣት ወስኖ እቤቱ መቀመጥ ጀመረ። ሆኖም እቤቱ ሆኖ መስኮቱን በከፈተ ጊዜ ሐውልቱ በጉልህ ይታየዋል። ሌላኛውንም መስኮቱን ሲከፍት የቱር ኤፌል ሐውልት ገዝፎ ይታየዋል። ከየትም አቅጣጫ ቢያይ ያ ሐውልት ብቅ ይልበታል።
ስለዚህ ቀራፂው በርና መስኮቶቹን ሁሉ ዘጋግቶ ቤቱ ውስጥ ቆላልፎ ቁጭ አለ።
የቀራፂው ጓደኛ የሆነ አንድ ታዋቂ ፈላስፋ አለ። ብዙ ቀናት ካለፉ በኋላ ይህ ፈላስፋ ወደ እነፃ ባለሙያው ቤት ሄዶ ያንኳኳል። የእነፃ ባለሙያው በሩን ከፍቶ አስገባው። ሰላምታ ከተለዋወጡ በኋላ ፈላስፋው፡
“ወዳጄ፣ ምን ሆነህ ነው የጠፋኸው?” ሲል ጠየቀው። የዕነፃ ባለሙያውም፤
“በፓሪስ ከተማ ውስጥ ያን ሐውልት ፑሬፌልን የማላይበት ምንም ቦታ አጣሁ። ስለዚህ ቡና እንኳን ለመጠጣት ወደ ሻይ ቤት መውጣት ስላቃተኝ ቤቴ ውስጥ ዘግቼ ለመቀመጥ ወሰንኩ።
ፈላስፋውም፤
“ወዳጄ ሆይ! ና እኔ ቡና የት እንደምትጠጣ አሳይሃለሁ” አለና ከቤት ይዞት ወጣ። የወሰደው ከሐውልቱ ሥር ካለች ትንሽ ካፌ ውስጥ ነበር።
ከዚያን ቀን ጀምሮ ያ ቀራፂ ከቤቱ እየወጣ በሰላም ቡናውን ይጠጣ ጀመር።
ፈላስፋውም፣
“አየህ ወዳጄ አንዳንድ ጊዜ ከጠላትህ ለመደበቅ እገዛ ቤቱ ውስጥ፣ እራሱ ጉያ ውስጥ ገብቶ መቀመጥ የሚመረጥ ቦታ ነው” ሲል መከረው፡፡
*   *   *
ጠላትን ከመሸሽ በገዛ ቤቱ፣ በገዛ መንደሩ፣ በአካባቢው ሆኖ መጋፈጥና መጋተር የሚመረጥበት ወቅት አለ። በየትኛውም መልኩ ጠላት ከማይጠረጠርባቸው ቦታዎች ሁሉ የተሻለው በገዛ ጣራው ሥር ያለ ድብቅ ሥፍራ ሆኖ ሊገኝ እንደሚችል እናስተውል። ጓዳ ጎድጓዳውን የምናውቀውን አካባቢ የበለጠ ለማጤን፣ የበለጠ ለማጥቃት፣ የተሻለ ለመበገር አመቺ ይሆንልናልና ነው።
የማጥቃትና የመከላከል ዕውቀት እጅግ የተሳካ እንዲሆን ስልትና ጥበብ ይጠይቃል። ከዕውቀትም በላይ ጥበብ ማናቸውንም ቤተሰብ፣ ድርጅትም ሆነ አገር ለመምራት ቁልፍ መሳሪያ ነው (Wisdom is a bettere weapon than knowledge እንዲል መጽሐፍ) መልካም ምላስ ቁጣን ታበርዳለች የሚባለውም ይሄንኑ የጥበብ አስተውሎት የሚያጠይቅ (Justification)  እና የሚያፀኸይ (Verification) ነው። ከጉልበት ይልቅ ብልሃትንና ስልትን ማወቅም የዚያኑ ያህል ፋይዳ ያለው ስለሆነ ያንን አጥብቆና ይሁነኝ ብሎ መያዝ የሚያዋጣ መንገድ ነው።
እንግዲህ፤
መንገድ ስንመርጥም አንዳንዴ ያልተሄደበትን መምረጥ መልካም ነው-ጸሐፍት The untraveled road (ያልተሄደበት መንገድ እንደሚሉት መሆኑ ነው።)  አዲስ መንገድ ማሰስ፣ ያልተበረበረ ሀብትን ለማሰስና እጅ ለማስገባት፣ ለትውልድ እንዲተርፍ አድርጎም ለማቆየት ያስችላል። ትውልድ የሚለመልመው ኮትኳችም፣ አውራሽም ወላጅ ሲኖረው ነውና ታላቅ ለታናሽ፣ አዋቂው ገና ላላወቀው ማስተማርና ማሳየት ይገባዋል። ወራራሽና ለዋጭ-ተለዋጭ ማህበረሰብ የዕድገት መሰረት ነው። እጅ ለእጅ ተያይዞ፣ ተጋግዞና ተቀናጅቶ መጓዝ፣ የትላንትን ስህተት የዛሬን ድክመት ለማጤንና የነግ-ተነግ ወዲያን ብሩህ ጎዳና ለመጥረግ ያስችለናል። ዛሬም፤ ጥናትም ጽናትም ያድለን የምንለው ከዚህ በመነሳት ነው!
ልጅህን ስታሳድግ ከምድጃ ዳር ያፈሰችህን እናትህን አስብ። እናትህ አገርህ ናት። ታስብልህ የነበረችው እናትህ ለአገርህ አብቅታሃለች፡፡ እንደ ገጣሚው ወዳጃችን ፍትጉ፤ “ከእናቴ ጡት ወደ አንቺ ጡት” የምንላት ለዚህ ነው! ለአገርና ህዝብ ማሰብና አገርና ህዝብን ማስቀደም መሪዎችና ተሿሚዎች ሁሉ ሊያስቡበት የሚገባ መርህ ነው። ዛሬ፤ “ደንጊያና ቅል ተላግቶ፣ ዜጋና ሹም ተሟግቶ” አይሆንም” የምንልበት ወቅት አይደለም! ባስልጣኖችን መጠየቅና መሞገት ይገባል። መተራረም ከዚህ ይመነጫልና!!

Read 11984 times