Saturday, 16 October 2021 00:00

በምዕራብ ጎንደር በሰዎች ላይ እገታ እየተፈጸመ ነው ተባለ

Written by 
Rate this item
(2 votes)

 “መንግስት የህብረተሰቡን ነፃነትና ደህንነት ማረጋገጥ ይገባዋል”
                   
            በአማራ ክልል በምዕራብ ጎንደርና አካባቢው ተደጋጋሚ የንጹሃን ዜጎች እገታ እየተፈጸመ መሆኑን  የጠቆመው የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ጉባኤ (ኢሰመጉ) ለማምለጥ የሚሞክሩም ግድያ እየተፈጸመባቸው መሆኑን አመልክቷል።
ኢሰመጉ ከአካባቢው አሰባስቤያለሁ ባለው መረጃ፤ህፃናትና ሴቶችን ጨምሮ አቅመ ደካሞችን በማገት ከፍተኛ መጠን ያለው ገንዘብ እንደሚጠየቅና በዚህም ሳቢያ ከህብረተሰቡ ለታገቱ ወገኖች ማስለቀቂያ በሚል የመዋጮ ገንዘብ መሰብሰብ እየተለመደ መምጣቱን ጠቁሟል።
ቤተሰቦቻቸው የተጠየቀውን ገንዘቡን መክፈል የማይችሉና ለማምለጥ የሚሞክሩ ታጋቾችም ግድያ እንደሚፈጸምባቸው በመግለጫው ያመለከተው ኢሰመጉ፤ በዚህም የአካባቢው ህብረተሰብ በነጻነት የመንቀሳቀስ መብቱ ተገድቦ በስጋት ውስጥ እንዳለ መገንዘቡን አስታውቋል።
ለአብነትም በጎንደር ከተማ ቀበሌ 18 አካባቢ አጋቾች የ13 ዓመት ህጻን ልጅ አግተው በመውሰድ ገንዘብ እንዲከፈላቸው ጠይቀው በኋላ ገንዘቡ ከተከፈለ በኋላ መስከረም 13 ቀን 2014 ዓ.ም ህጻኑ ተገድሎ አስክሬኑ እንደተገኘ፣ በጎንደር ከተማ መስከረም 10 ቀን 2014  በቀበሌ 17 ልዩ ስሙ ፋሲለደስ ት/ቤት አካባቢ የሁለት ዓመት ህጻን እናት በአጋቾች እንደተወሰደችና ለመልቀቅ ገንዘብ መጠየቁን እንዲሁም መስከረም 17 ቀን 2014 ከጎንደር ከተማ ወደ ገንደ ውሃ ሲጓዝ የነበረ መኪና በአጋቾች በተከፈተበት ተኩስ ሹፌሩና አንድ ተሳፋሪ ሲገደሉ፣ ሌሎች ሁለት ተሳፋሪዎች ደግሞ በአጋቾቹ እንደተወሰዱ ኢሰመጉ ያሰባሰበው መረጃ ይጠቁማል።
በዚህ የእገታ ተግባር በተለይ ሴቶችና ህጸናት ሰለባ መሆናቸው  በእጅጉ አሳሳቢ መሆኑን መንግስት ለጉዳዩ ትኩረት  እንዲሰጥ ያመለከተው ኢሰመጉ ጥሪ አቅርቧል።
የድርጊቱን ፈጻሚዎችን በፍጥነት ተከታትሎ በመያዝ ለህግ ማቅረብና የህብረተሰቡን ነጻነት ማረጋገጥ ከመንግስት እንደሚጠበቅም ኢሰመጉ አሳስቧል።

Read 7040 times