Saturday, 16 October 2021 00:00

ልከኛ ቦታቸውን ያገኙት ሚኒስትር

Written by  መታሰቢያ ካሳዬ
Rate this item
(0 votes)

 ጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር ዐቢይ አህመድ ባለፈው ሳምንት የካቢኒያቸውን እጩ አባላት ለህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ባቀረቡበት ወቅት፣ የውሃ መስኖና ኢነርጂ ሚኒስትሩና የህዳሴ ግድቡ ጠበቃ ዶ/ር ኢንጂነር ስለሺ በቀለ በካቢኔያቸው ውስጥ አለመካተታቸው በብዙዎች ዘንድ ቅሬታን ፈጥሮ ነበር፡፡  ይሁን እንጂ  ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ ዶ/ር ኢንጂነር ስለሺ በቀለ በሚኒስትር ማእረግ  የድንበር ተሻጋሪ ወንዞችና የህዳሴ ግድብ ዋና ተደራዳሪና አማካሪ በማድረግ አዲሱን  ተቋም እንዲመሩ ሾመዋቸዋል፡፡ ይህን ሹመት ብዙዎች “በልካቸው የተሰራ” ብለውታል፡፡
ዶ/ር ኢንጂር ስለሺ በቀለ፣ የመጀመሪያ ድግሪያቸውን ከአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ በሲቪል ኢንጂነሪንግ ያገኙ ሲሆን ሁለተኛ ድግሪያቸውን ደግሞ ዩናይትድ ኪንግደም ከሚገኘው ዩኒቨርስቲ ኦፍ ኒውካስል በሃይድሮሊክ እንጂነሪንግና ሃይድሮሎጂ አግኝተዋል። የዶክትሬት ድግሪያቸውን ደግሞ ከድሬሰደን ዩኒቨርስቲ ኦፍ ቴክኒሎጂ፣ በውሃ ሃብትና ሃይድሮሊክ ኢንጂነሪንግ ነው ያገኙት፡፡
የቀድሞው  ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ ሃይለማርያም ደሳለኝ ከዶ/ር ኢንጂነር ስለሺ በቀለ ጋር የተዋወቁት እርባ ምንጭ ዩኒቨርስቲ ይሰሩ በነበረበት ወቅት ነበር፡፡ ከዓመታት በኋላ አቶ ሃይለ ማሪያም ለስራ ወደ አሜሪካ ባቀኑበት ወቅት ከዶ/ር ኢንጂነር ስለሺ በቀለ ጋር በአጋጣሚ ይገናኛሉ። አቶ ሃይለማርያም እኚህ ታላቅ ምሁር ወደ አገራቸው በመግባት በሚኒስትርነት እንዲያገለግሉ ጥሪ አቀረቡላቸው ፡፡ዶ/ሩ ይህን ጥሪ  የተቀበሉት በከፍተኛ ደስታ ነበር፡፡ “አገሬ ሙያዬንና ዕውቀቴን ስትፈልግ እድሉን ተቀብሎ ማገልግል ለእኔ ታላቅ ክብር” ነው በማለት በአሜሪካ በተባበሩት መንግስታት ድርጅት ውስጥ የነበራቸውን ትልቅ ኃላፊነትና ዳጎስ ያለ ደሞዝ ለቀው ወደ አገራቸው መጡ - ከእነ ሙሉ ቤተሰባቸውን በመያዝ፡፡
በዘርፉ ከ30 ዓመታት በላይ በጥናትና ምርምር እንዲሁም በመምህርነት የዳበረ ልምድ ያላቸው ዶ/ሩ፤ የኢትዮጵያ የውሃ መስኖና ኢነርጂ ሚኒስትር በመሆን ለ3 ዓመታት አገራቸውን አገልግለዋል። እኚህ ታላቅ ምሁር ወደ አገራቸው በመመለስ ሚኒስትር ከመሆናቸው በፊት ኒውዮርክ በሚገኘው የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ዋና መ/ቤት ውስጥ የማህበራዊ ጉዳዮች ክፍል የኢኮኖሚና ዘላቂ ልማት ክልላዊ አማካሪ ሆነው ሰርተዋል፡፡ በተባበሩት መንግስታት በነበራቸው ቆይታ ዘላቂ ልማት ከብሔራዊ የዕድገት ዕቅዶች ጋር መጣመር የሚችሉባቸው መንገዶች ላይ ከፍተኛ አስተዋጽኦ እንዳበረከቱ ይነገርላቸዋል፡፡ በዚህም የአፍሪካ ኢኮኖሚ ኮሚሽን አባል በሆኑ የአፍሪካ አገራት እንዲሁም በእስያ በላቲን አሜሪካና በካረቢያን  አካባቢ በዘርፉ ከፍተኛ አስተዋጽኦ ማበርከት የቻሉ ባለሙያ  ናቸው። ከዚህ ቀደም ሲል ለሰባት ዓመታት የዓለም አቀፉ ውሃ አስተዳደር ተቋም የናይል ተፋሰስና የምስራቅ አፍሪካ ክልላዊ ቢሮ ሃላፊ ሆነው አገልግለዋል። ዶ/ር ስለሺ ይህንን ቢሮ ከትንሽ ቡድን ተነስቶ ዓለም አቀፍ ተቋም እንዲሆን ያስቻሉ ታላቅ ባለሙያ ናቸው፡፡
በ2025 በመላው ኢትዮጵያ  የኤሌክትሪክ ሀይል ለማዳረስ የተያዘውን ዕቅድ ለማሳካት ከፍተኛ  ተግባራት ሲያከናውኑ ቆይተዋል። ለዚህ ዓላማ መሳካት ትልቅ አስተዋጽኦ ያለው የህዳሴ ግድብ ሳይስተጓጎል እንዲቀጥል በማድረጉ ረገድ ያበረከቱት አስተዋጽኦ ከፍተኛ ግምት የሚሰጠው ነው፡፡
ከዚህ በተጨማሪም ከአፍሪካና ሌሎች አገራት የተውጣጡ ከ45 በላይ ተመራማሪዎች የተሳተፉበት የናይል ወንዝ ተፋሰስ መጽሐፍ መሪ አርታኢ  እንዲሁም አስተባባሪ ሆነው ሰርተዋል፡፡
ዶ/ር ኢንጂነር ስለሺ በቀለ ላለፉት 3 ዓመታት አገራቸውን በውሃ መስኖና ኢነርጂ ሚኒስትርነት ሲያገለግሉና በህዳሴው ግድብ ዙሪያ እጅግ ስኬታማ የተባሉ ድርድሮችን ሲያካሂዱ፣ በየትኛውም የፖለቲካ ድርጅት ውስጥ አባል ሳይሆኑ ነበር፡፡
በ6ኛው አገር አቀፍ ምርጫ የብልጽግና ፓርቲን በመወከል በአዲስ አበባ ምርጫ ክልል 17 ለህዝብ  ተወካዮች ምከር ቤት አባልነት በመወዳደር አሸንፈው ምክር ቤት ገብተዋል።
አዲስ በተዋቀረው መንግስት ደግሞ አዲስ በተመሰረተው ተቋም በሚኒስትር ማዕረግ የድንበር ተሻጋሪ ወንዞችና የህዳሴ ግድብ ዋና ተደራዳሪና አማካሪ በመሆን ተሹመዋል፡፡

Read 1002 times